ወጪ ንግድንና ጤናን እየፈተነ ያለው ሻጋታ/አፍላቶክሲን/

ወደ ህብረተሰቡ ሊሰራጭ የነበረ የሻገተና በአፍላቶክሲን የተበከለ በርበሬ ህብረተሰቡ ባደረገው ጥቆማ ተይዞ በግብረ ኃይል መወገዱን የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ እንደኔ ላለ የሸማች መብት ተቆርቋሪና ጋዜጠኛ አስደንጋጭ ነው። ለዛሬ መጣጥፌ መነሻ የሆነኝም ይህን ድንጋጤ የፈጠረው ዜና ነው። ዜናው እንዲህ ይቀጥላል። የባለሥልጣኑ ኮልፌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በማህበረሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል 227 ኩንታል ወይም 22 ሺህ 700 ኪ.ግ በርበሬ ነው ያስወገደው። ይህም በትክክለኛ በርበሬ ዋጋ ቢሸጥ ኖሮ 4.5 ሚሊዮን ብር ያወጣ እንደነበር ነው የተገለጸው።

ችግሩ በሸማቹ ጤና ላይ ሊያደርሰው የነበረው ጉዳት በምንም ዋጋ ሊተመን የማይችልና ከባድ ነው። በወጪ ንግዳችን ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ከኢኮኖሚያዊ ዳፋው አልፎ የሀገርን ገጽታም እያጠለሸ የሚገኝ ችግር ስለሆነ ከምርት መሰብሰብ፣ ማከማቸትና ማጓጓዝ ድረስ ያለው ሂደት መፈተሽና መፍትሔ ማስቀመጥ ይሻላል። በእንስሳት ተዋጽኦ በተለይ ወተት ላይ የሚታየውን አፍላቶክሲን ለመቀነስ ደግሞ የመኖ ዝግጅት ሂደቱን፣ ማከማቻቸውንና ማጓጓዣውን እንዲሁ መፈተሽ ግድ ይላል።

የተበላሸው ምርት የተገኘው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኝ መጋዘን ውስጥ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት የናሙና ምርመራ ተደርጎ ምርቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ አፍላቶክሲን የተገኘበት ሲሆን፤ ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስ እና ከንግድ ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት እንዲወገድ መደረጉን የባለሥልጣኑ መረጃ ያመላክታል። የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ሙኒራ ነጋሽ፣ ተቋሙ በርበሬ እያዘጋጀ ለህብረተሰቡ እንዲያከፋፍል ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ፍቃድ እንዳልተሰጠውና የጥራት ማረጋገጫ ሰነድም እንደሌለው ገልጸው፤ የተወገደው በርበሬ ወደ ህብረተሰቡ ቢሰራጭ ኖሮ ከፍተኛ የጤና ጉዳት እንደሚያስከትል፤ ማህበረሰቡ ማንኛውንም ምርት ሲገዛ ጥራቱና ደኅንነቱን የጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገዛና ጤናውን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

ከፍ ብሎ ለመጠቆም እንደተሞከረው አፍላቶክሲንና የጥራት ችግሮች ተጃምለው ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ገበያ እያሳጣ ነው። አፍላቶክሲንን (ሻጋታ) ጨምሮ የጥራት ደረጃቸው በላቦራቶሪ ሳይፈተሽ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች የገበያ ተቀባይነት እያጡ ሲሆን፤ እስከ ጥራት መንደር ግንባታ ድረስ የምርቶችን የጥራት ደረጃ የሚፈትሹ ማሽኖች አገልግሎት እየሰጡ ስላልነበር በእንቅርት ላይ ቆረቆር እንዲሉ ሆኗል።

አፍላቶክሲን ወይም ሻጋታ አስፓሪጊለስ ፍላቨስና አስፓሪጊለስ ፓራክቲከስ በተባሉ የፈንገስ ዓይነቶች የሚመጣና ምግብን የሚመርዝ የተህዋሲያን ውጤት ነው። የአፍላቶክሲን ዓይነቶች ቢ1፣ ቢ2፣ ጂ1ና ጂ2 ሲሆኑ በተለይ ቢ1 የተባለው አደገኛ፣ መርዛማና ቶሎ ሊገድል የሚችል መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። በዓለም ላይ 30 በመቶ የሚሆነው የጉበት ካንሠር በአፍላቶክሲን መርዝ የሚከሰት ሲሆን የኩላሊት ካንሠር፣ የእድገት መቀነስና የደም መፍሰስ ችግሮችንም ያስከትላል።

በተለይ በቆሎ፣ ኦቾሎኒ፣ የዛፍ ፍሬና የእንስሳት ውጤቶች በከፍተኛ ሁኔታ የፈንገሱ ተጠቂ ሲሆኑ ሌሎች ምርቶች ላይም በየደረጃው ይከሰታል። አፍላቶክሲን ወይም ሻጋታ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እንዲያጡ ማድረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የድህረ ምርት ባለሙያ አቶ አውራሪስ አስፋው በአንድ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ˝ትልቁ ጉዳት ደግሞ አሁን ኤክስፖርት የምናደርጋቸው ሰብሎች ላይ በተለይ አውሮፓ ገበያ ላይ እኛ ማቅረብ አንችልም። ምክንያቱም ከፍተኛ ኮንታሚኔትድ የሆነ ነው፤ ስለዚህ በኤክስፖርት ሰብሎች ላይም ሆነ በጤና ላይ ችግር አለው፣ በአፍላቶክሲን የተጠቁ ሰብሎችን ወደ ገበያ በሚቀርቡበት ጊዜ ጥራታቸው የወረደ ስለሚሆን፡፡

በሚኒስቴሩ የእጽዋት ኳረንታይል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ በለጠ ሞገስ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ጥራጥሬ በብዛት ይገዙ የነበሩት የአውሮፓ ሀገሮች፣ ህንድና ፓኪስታን በነፍሳት ተባይና በሽታ እንዲሁም ከአደገኛ የአረም ዝርያዎች ነፃ መሆኑን ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው መግዛት ማቆማቸውን ተናግረዋል። ከፍተኛ እርጥበት፣ በማሳና በጎተራ የነፍሳትና ተባዮች መከሰት፣ ምቹ ያልሆነ ማከማቻና ማጓጓዣ ለፈንገሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል።

የአፍሪካ ህብረት አፍላቶክሲንን ከአፍሪካ ለማጥፋት እኤአ ከ2015 እስከ 2018 በማላዊ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ጋምቢያና ኡጋንዳ ባዮ ኮንትሮል (አፍላሴፍ) የተባለ ፕሮጀክት ነድፎ ወደ ሥራ ገብቷል። ይህ ፕሮጀክት በየሀገሮቹ የአፍላቶክሲን ዓይነቱን በመለየት ራሱ ፈንገሱን በመርጨት ከ80 እስከ 90 በመቶ መከላከል ተችሏል። ይህን ፕሮጀክት ከ2018 ጀምሮ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና ቤኒን ወደ ትግበራ ለማስገባት ቅድመ ዝግጅቶች መጀመራቸውን አቶ አውራሪስ ይናገራሉ። ይህ ፕሮጀክት ገና ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ እየተባባሰ ለመጣው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ የማይታሰብ በመሆኑ ለአምራቹና ለተጠቃሚው ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የእጽዋት ኳረንታይል ከፍተኛ ባለሙያው አቶ በለጠ ሞገስ፤ አብዛኞቹ የግብርና ምርቶችን የሚገዙ ሀገሮች ምርቶቹ ከተባይ ነፃ መሆናቸውን በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ማስረጃ ይፈልጋሉ። ይህ የላቦራቶሪ ማረጋገጫ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አለመኖር ደግሞ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ እንደመሆኑ በየዓመቱ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ካለማስገኘቱ ባለፈ ምርቶች ላይ እያጋጠመ ያለው የጥራት ችግር ሌላ ፈተና ከሆነ ሰነባብቷል።

አፍላቶክሲን ወደ ውጭ ከሚልኩት የቅመማ ቅመም ምርት የሚያገኙትን ጥቅምና ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታስገባውን ገቢ እየቀነሰው መሆኑን የዘርፉ ባለሀብቶች ይናገራሉ። በአፍላቶክሲን /ሻጋታ/ በከፍተኛ መጠን እየተጎዳ ያለውን የቅመማ ቅመም ዘርፍ ለመደገፍ ዘመናዊ የምርት አሰባሰብ ሥርዓት መዘርጋትና ሕግ የማስከበር ተግባራት እንዲከናወን፤ ሀገሪቱ ለቅመማ ቅመም ምርት ምቹ የአየር ንብረት ቢኖራትም የምግብ ደህንነትና ጥራት ችግሮች ተጠቃሚነቷን እያሳጧት ነው።

አፍላቶክሲን አስፈርጊለስ ፍላገስና አስፈርጊለስ ፓራሲቲከስ በሚባሉ ሁለት ዓይነት የፈንገስ ዓይነቶች የሚመረት ጎጂ ንጥረ ነገር ነው። የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም አምራቾች፣ አቀነባባሪዎችና ላኪዎች ማህበር ሥራ አስኪያጅና የኢትዮ-ሆላንድ የንግድ ትብብር ለግብርና ልማት የቅመማ ቅመም ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲሱ ዓለማየሁ “ዘርፉ በአፍላቶክሲን በከፍተኛ መጠን እየተጎዳ ነው” ይላሉ። ወደ ውጭ ከሚላከው የቅመማ ቅመም ምርት የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

ማህበሩ ከኢትዮ-ሆላንድ የንግድ ትብብር ለግብርና ልማት የቅመማ ቅመም ፕሮጀክት ጋር በመሆን ችግሩን የተመለከተ ጥናት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስጠንቶ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክና ፎረሞችን በማካሄድ ማወያየቱን ገልጸዋል። ችግሮቹን በልምድ ልውውጥ ለመፍታት ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ በዘርፉ የተሠማሩ ሰዎችን የሚያሳትፉ መድረኮችም አካሂዷል። የአፍላቶክሲን መጠን ናሙናዎችን በላቦራቶሪ በማሠራት በተገኘ ውጤት ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ላኪዎች ጋር እስኪደርስ እየጨመረ መምጣቱን መለየቱንም አቶ አዲሱ አስረድተዋል። አፍላቶክሲን በምርት አሰባሰብና አያያዝ ችግር የሚከሰት መሆኑን ጠቁመው መፍትሔ ያሏቸውን ዘረዝረዋል።

የሻጋታ ተጋላጭነት የሚጨምሩ እርጥበትና ሙቀትን ለመከላከል የምርት አሰባሰብና ክምችት ሥራ በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበትም ብለዋል። ትርፍ ለማግኘት ሲባል ምርትን ከባዕድ ነገር ጋር የሚቀላቅሉ በመኖራቸው እነዚህንም በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። የማህበሩ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ሚሊዮን ቦጋለ በበኩላቸው ተመሳሳይ ጥራት ያለውን የኢትዮጵያና የህንድ እርድ ለአብነት አንስተው የኢትዮጵያው በምርት አሰባሰብ ሂደት ጥራቱን እንደሚያጣ ተናግረዋል። ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ በመጠቆም።

“በቅመማ ቅመም ዘርፍ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የጥራት ችግር መኖሩን ለይተናል” ያሉት ደግሞ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን የልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውግቸው ተሾመ ናቸው። በርበሬ ኪሎ እንዲጨምር ውሃ ማርከፍከፍ፣ እርድንም አስመስሎ የመሥራት ተግባር እየተስተዋለ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ሥልጠናና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት እየተከናወኑ ነው። የአርሶ አደሩ የምርት አሰባሰብና አያያዝ ለማሻሻልም ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

አንድ ቆየት ያለ መረጃ በአፍላቶክሲን ምክንያት ወደ እንግሊዝና ጀርመን የተላከ በርበሬ መመለሱና ሀገሪቱም ከዘርፉ ታገኝ የነበረውን ገቢ ማጣቷ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ያገኘች ሲሆን በ2010 ዓ.ም ያገኘችው ገቢ ወደ 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር መውረዱን ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ይሁንና መንግሥት እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። በተለያዩ ሰብሎችና ምግቦች ላይ የሚከሰተውን የአፍላቶክሲን ክምችት መቀነስ የሚያስችል ጥናት መጀመሩን የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአንድ ወቅት ማስታወቁ አይዘነጋም። ሆኖም ዛሬም ጥናቱ ከምን ደረሰ ማለት ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጥራት መንደር መገንባቱ ሳይዘነጋ።

በወተት፣ በከብቶች መኖ፣ በለውዝ፣ በበቆሎ፣ በማሽላና በሰሊጥ ላይ የተጀመረው ምርምሩ፣ ምርት በማሳ ላይ እያለ በአፍላቶክሲን እንዳይጠቃ ማድረግና ከምርት በኋላ ለውጭ ንግድ የተዘጋጁ ምርቶች ውስጥ የሚገኘውን የአፍላቶክሲን ክምችት መቀነስ የሚያስችል መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት በግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የአፍላቶክሲን የሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ብርሁን አዲሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በወተት ላይ የሚደረገው ምርምር ዚኦላይትና ቤንቶናይትን የተባሉ ማዕድናትን በመጠቀም በአፍላቶክሲን M1 የተበከለን ወተት ማከም፣ የብክለት ደረጃውን መቀነስና እንዲሁም እንዲጠፋ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተሠሩ የምርምር ሥራዎች ትኩረት ያደረጉት አፍላቶክሲን B1 ከእንስሳት መኖ አልፎ ወተት ላይ እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ከመኖ አልፎ በወተት ላይ ቢከሰት እንዴት መቀነስ ይቻላል? የሚለው ምርምር አዲስ እንደሆነ ተቋሙ አመልክቷል።ሥነ ሕይወታዊ ዘዴን በመጠቀም ሰብሎች ማሳ ላይ እንዳሉ የሚታከሙበትን ምርምር ለመጀመር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሰብል ናሙና ተወስዶ በውስጣቸው ያለውን የአፍላቶክሲን ክምችት የሚያሳይ የመነሻ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ዶ/ር ብርሁን ገልጸዋል፡፡

የሰሊጥ፣ የለውዝ፣ የማሽላና የበቆሎ ናሙናዎች ከየአካባቢው ተወስደው እየታዩ ይገኛሉ፡፡ በለውዝና በበቆሎ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን አምጭ ፈንገሶች ክምችት ታይቷል፡፡ በማሽላም እንዲሁ በአንፃራዊነት ታይቷል። ከፍተኛ የአፍላቶክሲን አምጭ ፈንገሶች ክምችት የታየውም በምሥራቅ ሐረርጌ ባቢሌና ጉርሱም አካባቢ የሚመረቱ የለውዝ ምርቶች ላይ ነው፡፡ በአካባቢው የተሰበሰቡት ናሙናዎች መቶ በመቶ የአፍላቶክሲን አምጭ ፈንገሶች ክምችት አለባቸው፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ፓዌ አካባቢ ከተሰበሰቡ ናሙናዎች መካከልም እንዲሁ በ93 በመቶዎቹ ላይ ፈንገሱ ተስተውሏል፡፡ በሥነ ሕይወት ዘዴ አፍላቶክሲን አምጭ ያልሆነ ፈንገስ አምጭ የሆነውን ፈንገስ እንዲቆጣጠር በማድረግ የምርትን ብክለት ለመቀነስ ያለመው ጥናቱ በሌሎች ሀገሮች ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ እየተደረገ የሚገኘው ጥናት ባህር ማዶ የተሠራውን ከማስገባት ሀገር ውስጥ መኖሩን ማረጋገጥና ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ምክንያቱም በሌላው የዓለም ክፍል ውጤታማ የሆነ ቴክኖሎጂ እዚህ መጥቶ ውጤታማ ላይሆን ይችላል፤›› ብለዋል ዶክተሩ፡፡

ፈንገሶቹ በተለያዩ አካባቢዎች ባህሪያቸው የተለያየና አፍላቶክሲን የማመንጨት አቅማቸው ለየቅል በመሆኑ እንደየአካባቢው ሁኔታ እየተጠና መሠራት ግድ ነውም፡፡ የአፍላቶክሲን ሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ምርምር በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚደገፍ የሦስት ዓመት ፕሮጀክት ነው፡፡ ምርቶች በእርጥበትና በታፈነ ሁኔታ ሲከማቹ አስፓርጊለስ ፍላቨስና አስፐርጊለስ ፓራሲቲከስ ለተባሉ የፈንገስ ዝርያዎች ምቹ መራቢያን ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ፈንገሶች አፍላቶክሲን የተባለውን መርዛማ ውህድ ይፈጥራሉ። ስድስት ዓይነት የአፍላቶክሲን ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ B1 የተባለው ከፍተኛ የካንሰር አምጭ ውህድ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

አፍላቶክሲን በቆሎ፣ ስንዴ፣ የጥጥ ፍሬና የመሳሰሉት የግብርና ምርቶች በይበልጥ ያጠቃል፡፡ በአፍላቶክሲን B1 የተበከለ መኖ በተመገበ ከብት አካል ውስጥ በሚካሄድ ሜታቦሊዝም ወደ አፍላቶክሲን M1 ይቀየራል፡፡ በዚህም ጊዜ ከከብቱ የሚገኝን የምግብ ተዋጽኦ የተመገቡ አፍላቶክሲን ወደ ሰውነታቸው ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የመኖ የጥራት ችግር አሳሳቢ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት እምብዛም በመሆኑ በወተት ላይ የሚታየው የአፍላቶክሲን ክምችት ከዓለም አቀፍ የደረጃ ጣሪያ በላይ እንዲሆን መንገድ ከፍቷል፡፡

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You