የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በፉክክር እና በትብብር መካከል ሚዛን በመጠበቅ፣ ተቃርኖዎችን በማስታረቅ የሚጓዝ ነው። ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን መሠረት ያደረገ ፤ ጎረቤት ሀገራትን የሚያስቀድም ፣ ለቀጣናዊ ትብብርና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ትኩረት የሚሰጥም ነው። ብሔራዊ ክብርን በማስጠበቅ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ፣ ታፍራና ተከብራ የምትኖር ጠንካራ ሀገር የመፍጠር ተልዕኮንም የተሸከመ ነው።
የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአስተሳሰብ መሠረትም ጥቅምን ማሳደድ ላይ ያተኮረ ሳይሆን ፤ ግንኙነትን እና መልካም ትብብርን የሚያስቀድም ፤ የሀገሪቷን እሴቶች ተከትሎ በትብብርና በንግግር መንቀሳቀስ ብሔራዊ ጥቅሞችን በተሻለ መልኩ ማስከበር ያስችላል ብሎ የሚነሳ እና ይህንኑ የሚያበረታታ ነው።
ይህን የውጪ ፖሊሲ እሳቤ መሠረት በማድረግም መንግሥት ላለፉት አምስት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት በመተባበር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እየሠራ ነው። የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ እጣ ፈንታ የተሳሰረ መሆኑን በአግባቡ በመረዳትም የጋራ ጥቅማችንን መሠረት ባደረገ የመተጋገዝና የትብብር መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ነው።
በቀጣናው ከሚገኙ ጎረቤት ሀገራት ጋር የሚፈጠር የትኛውም ዓይነት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ ተመስርቶ በሂደት ወደ ጠንካራ ምጣኔ ሀብታዊ ጥምረት እንዲያድግ ፤ አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገም ነው። በዚህም በተጨባጭ የሚታዩ ለውጦቶች እየተስተዋሉ ቢሆንም ፤ ፈተናዎችም አልታጡበትም፤
የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት እንደ አንድ የብሔራዊ ጥቅም ስጋት አድርገው የሚመለከቱ ኃይሎች ፤ በአንድም ይሁን በሌላ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች አበክረው የሚፈልጉት ሰላም እና ልማት እውን እንዳይሆን እየተንቀሳቀሱ ነው። የቀጣናውን ሀገራት ሕዝቦች አብሮ የመልማት ዕጣ ፈንታ የሚፈታተኑ ተግባራትን ሲከውኑ ማየትም የተለመደ ሆኗል ።
ከትናንት ስህተቶች መማር ያልቻሉ እነዚህ ኃይሎች ፤ በሌሎች ውድቀት ቆመው ተስፋ የሚያደርጉት የጥፋት ህልማቸው በየትኛውም መንገድ ማንንም ሊያተርፍ የማይችል “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አይነት የቀጣናውን ሀገራት ሕዝቦች ማህበራዊ ሥነልቦና የሚመጥን አይደለም ።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በታሪክ አጋጣሚ በድንበሮች ተካልለው ፣ ሁለት እና ሦስት ሀገር ሆነው ይቁሙ እንጂ ፤ ከድንበሩ በላይ አንድ የሚያደርጋቸው ማኅበረሰባዊ ማንነትን የሚጋሩ ፤ በባህል፣ በቋንቋ ከዚያም ባለፈ በደም የተሳሰረ ግንኙነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ።
ኢትዮጵያውያን ይህንን የአደባባይ እውነታ ታሳቢ በማድረግ ከትናንት በተሻለ መልኩ በጎረቤት ሀገራት መካከል መተማመን እንዲሰፍን ፤ ሀገራቱ ያላቸውን አቅም አቀናጅተው ሕዝቦቻቸው የሚፈልጉትን ሰላም እና ልማት በራሳቸው ማምጣት እንዲችሉ ከፍ ባለ እምነት እና መነቃቃት እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህንንም በውጪ ፖሊሲያቸው በግልጽ ከማስፈር ባለፈ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው በተጨባጭ የሚስተዋል ነው።
እንደ ሀገር በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚከፍሉት የሕይወት መስዋዕትነትም ሆነ ፤ ሀገራቱ ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎች በአግባቡ ተረድተው፤ እነዚህን ጸጋዎች በጋራ አልምተው ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት መውጣት የሚችሉበትን የጋራ አቅም ለመፍጠር የምታደርገውም ጥረት የዚሁ እውነታ አንድ አካል ነው።
ደህንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ የባህር በር እንዲኖራት ያቀረበችው ጥያቄም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚሳካ ፤ የአካባቢውን ሀገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋዎች በጋራ አልምተው፤ የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ነው። ጉርብትናቸውንም ፣ ስትራቴጂክ ወደ ሆነ አጋርነት ማሸጋገር የሚያስችል ነው ።
በቀጣናው ሀገራት መካከል በሂደት መተማመንን ከመፍጠር ባለፈ በቀጣይ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ማምጣት የሚያስችል የትልቅ ተስፋ ጅማሬም ነው። ይህንን ሰላማዊ ጥያቄ በአግባቡ ተረድቶ ምላሽ መስጠትም የቀጣናው ሰላም እና ዕድገት ከማንም በላይ ከሚመለከታቸው የአካባቢው ሀገራት መንግሥታት የሚጠበቅ ነው ።
የኢትዮጵያን ሰላማዊ ጥያቄ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከሶስተኛ ወገን አጀንዳ ጋር አስተሳስሮ ለመሄድ የሚደረግ ጥረት የቀጣናውን ሀገራት ሕዝቦች የሰላም እና የመልማት ጥያቄ ሊያስተናግድ የሚችል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ላልተገባ ችግር የሚዳርግ፤ በሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን በማደብዘዝ የጋራ እጣ ፈንታቸውን የሚገዳደር ነው።
የአንካራው ስምምነት ሆነ ስምምነቱን ለመተግበር ፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል እየተደረገ ያለው አሁናዊ ጥረት ፤ ይህን እውነታ በተጨባጭ ከመረዳት የሚመነጭ ፤ ከሁሉም በላይ የሶስተኛ ወገን አጀንዳን በመጣል ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች የሰላም እና የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ትክክለኛ አካሄድ ነው!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም