በቅርቡ በተደረገ የንግድ ቤቶች የዋጋ ተመን ማሻሻያን ተከትሎ በርካታ ቅሬታዎች ሲደመጡ፤ ዝግጅት ክፍላችንም ጉዳዩን እየተከታተለ ለአንባብያን ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ከዚሁ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የዋጋ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ «ጭማሬው ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚዳርገን ከመሆኑም በላይ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እኛን አይመለከተንምና ሙሉ በሙሉ ሊነሳልን ይገባል» በሚል፣ የአዲስ ፋና ጠቅላላ ሸቀጣ ሸቀጥና ሆቴሎች ንግድ አክሲዮን ማህበር አባላትና አመራሮች በአካል ቀርበው ቅሬታቸውን በደብዳቤና በድምፅ አድርሰውናል፡፡
ከማህበሩ የደረሰን ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ ማህበሩ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ለውጥ ተከትሎ በ1988 ዓ.ም ‹አዲስ ፋና ጠቅላላ ሸቀጣ ሸቀጥና ሆቴሎች ንግድ አክሲዮን ማህበር› በሚል ስም 1ሺ449 አባላትን ይዞ በሴፍቲኔት የተደራጀ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከአባላቱ ባለፈ 881 ሠራተኞች በውስጡ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ማህበር በአዲስ አበባ 35 መደብሮችና ሱቆች፣ 3 መጋዘኖች፤ እንዲሁም በክልሎች 12 መደብሮችና 4 ሆቴሎች ከፕራይ ቬታይዜሽን ኤጀንሲ በ42 ሚሊየን ብር በመግዛት የተቋቋመ ሲሆን፤ ይሄን ገንዘብም ከልማት ባንክ በመበደር ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ከፍሏል፡፡
ሆኖም እንደነርሱ ድርጅት የገዙት ግሎሪየስ እንዲሁም ሜጋ መጻሕፍት መደብር በስማቸው ካርታ ሲሠራላቸው እነርሱ ግን ላለፉት 22 ዓመታት የስም ማዛወሩ ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ማህበሩ ይህ ችግር እንዲፈታለት ጥያቄ እያቀረበና ምላሽ እስኪሰጠው ድረስ ኪራይ እየከፈለ ሥራውን እየሠራ ባለንበት ሂደት በእነዚህ ቤቶች ላይ የተደረገው የቤት ኪራይ ጭማሪ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፤ ድርጅቱ አንዱ ቅሬታው ሳይፈታ ወደ ሌላ ቅሬታ እንዲገባ ያደረገ፣ ህልውናውንም የሚፈታተን ተግባር ነው ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡
ምክንያቱም፤ የቀደመው ችግር ባለመፈታቱ ማህበሩ ድርጅቶቹን ሲገዛ ከከፈለው 42 ሚሊየን ብር ባለፈ፣ ባለፉት 22 ዓመታት ውስጥ 62 ሚሊየን ብር ለማህበራዊ አገልግሎት በመክፈል፣ 20 ሚሊየን ብር ንብረቶቻቸው ያለአግባብ በመወረሳቸውና በመፍረሳቸው፣ እንዲሁም 27 ሚሊየን ብር ለቤቶቹ እድሳት በድምሩ ለ135 ሚሊየን ብር ወጪ ተዳርጓል፡፡ ይህ ባለበት ደግሞ የኪራይ ጭማሪው መደረጉ የማህበሩን በንግድ ተግባር ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ አገልግሎት ላይ መሰማራትን ያለማገናዘበ፤ ምንም እንኳን አደረጃጀቱ በሴፍቲኔት ቢሆንም እንደ ሌሎቹ የመንግሥት ድጋፍ አለማግኘቱን እንዲሁም በአክሲዮን ማህበር መሥራት አለመቻላቸውን ከግምት ያላስገባ፤ ማህበሩ ከ22 ዓመት በፊት ሲቋቋም በግምት ከ40 እስከ 50 ዓመት በሆናቸው ሰዎች የተቋቋመ እንደመሆኑ አሁን ላይ ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸውን እናቶችና አባቶች በአባልነት ይዞ እየሠራ መሆኑን ያላጤነ በመሆኑ የማህበሩን ችግር ከሚቋቋመው በላይ አግዝፎበታል፡፡ ከዚህ አኳያ ጭማሪው ማህበሩን ሊመለከት ስለማይገባ ኮርፖሬሽኑ የተጠቀሱትን ምክንያቶች በማጤን ሙሉ ለሙሉ ሊያነሳለት ይገባል ይላሉ፡፡
ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የማህበሩ አባልና የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አባተ እንደሚሉት፤ ማህበሩ፣ በ1987 ዓ.ም መንግሥት የኢኮኖሚ ለውጥ ሲያደርግ በመንግሥት ይዞታ ስር የነበሩ የችርቻሮ ንግድ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮፍ፣ የምግብ ማደራጃ፣ ሕንፃ ኢንተርፕራይዝ፣ የጽህፈት መሳሪያ እና ሌሎች ድርጅቶችን በተለያዩ ምክንያቶች ከመንግሥት መዋቅር የወጡ ሰዎች በሴፍቲኔት እንዲደራጁ መንግሥት ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት በ1988 ዓ.ም የተደራጀ ነው፡፡ ማህበሩ ሲደራጅ የንግድ ሥራ ለመሥራት ቢሆንም፤ የተሰጠው ኃላፊነት ግን በውስጡ ያሉትን አባላትና ሠራተኞቹ ሥራ ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት ወይም ለእነዚህ ሰዎች ደመወዝ ያለሥራ መክፈል ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም አባላትና ሠራተኞቹ በራሳቸውም ሆነ በቤተሰባቸው ላይ የሕይወት መናጋት እንዳይከሰት ነው፡፡
አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፤ ማህበሩ ሲቋቋም በ42 ሚሊየን ብር ፕራይቬታይዜሽን በሸጠለት ግዢ ውስጥ ተካትተው የተገመቱ ንብረቶች ቤቶቹ እና በውስጣቸው ያሉ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችን ጨምሮ በተገኘ ቆጠራ የተያዘ ዕዳ ነው፡፡ ማህበሩም ይሄን ገንዘብ ከባንክ ተበድሮ ለፕራይቬታይዜሽን የከፈለ ቢሆንም፤ ንብረቶቹ በስሙ የሚዞሩት የባንክ እዳውን ከፍሎ ሲጨርስ በመሆኑ የቤቶቹን ኪራይም ሆነ የባንክ እዳውን ሲከፍል ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ማህበሩ የባንክ እዳውን ከፍሎ ያጠናቀቀ እንደመሆኑ፤ የባለቤትነት መብት የማዛወር፣ የአክሲዮን ማህበሩን አሠራር የማስተካከል ሂደት ላይ እንዳለ የቤት ኪራይ ጭማሪ መጣ፡፡ ይህ የቤት ኪራይ ጭማሪ ደግሞ በርካታ ነገሮችን ያናጋል፡፡
ምክንያቱም አንደኛ፣ ማህበሩ ዋናው የተቋቋመበት ዓላማ ከንግዱ ጎን ለጎን ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ለ22 ዓመታት ሙሉ 1ሺ449 ሰዎች ያለ ሥራ ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ በወቅቱ መንግሥት በሰጠው ትዕዛዝ እየተፈጸመ ያለ ስለሆነና ምንም መሻሻል ባለመታየቱ ዛሬም ድረስ እነዚህ ሰዎች ችግር ውስጥ ናቸው ያሉት፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ የኪራይ ጭማሪው ቢደረግ 130ሺ ብር ይከፈልባቸው የነበሩትን ቤቶች ወደ 2ነጥብ5 ሚሊየን ብር እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ ማህበሩ ደግሞ ይሄን ቢከፍል ኪራይ መክፈል በጀመረበት ቀጣይ ወር ላይ አቅም በማጣት ስለሚዘጋ 1ሺ449 ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው መንግሥት ካሰበው ዓላማ በተቃራኒ ወደ ጎዳና ስለሚወጡ፤ ሠራተኞቹም ከሥራ ውጪ ስለሚሆኑ ከፍተኛ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ ይደርስባቸዋል፡፡ እናም ኮርፖሬሽኑ ይሄንን ማህበራዊ አገልግሎቱንና የተቋቋመበትን ዓላማ ከግምት ማስገባት ይኖርበታል፡፡
በደብዳቤው ላይ የሰፈረውን ሃሳብ ከማጠናከር ባለፈ ሌላው በአቶ ሰለሞን የተነሳው ጉዳይ፤ ከማህበሩ አደረጃጀት ችግር ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን መንግሥትም ስለሚረዳ ቢያንስ አደረጃጀቱ ተስተካክሎ ወደ ማህበራዊ ዋስትና መሄድ የሚገባቸውም እስኪሄዱ፤ ወደ ማህበሩ የሚመጡትም እስኪመጡ ድረስ ኮርፖሬሽኑ ማህበሩ ያለበትን ችግር ማጤን ይገባዋል፡፡ ጭማሪው በማህበሩ ላይ ከተተገበረ ግን ማህበሩ የሚነግደው መንግሥት ባመቻቸለት ገንዘብ ሳይሆን፤ ከነጋዴዎች በሚሰጠን ሸቀጥ ላይ ተመስርቶ እንደመሆኑ ከገበያ ለመውጣት ይገደዳል፤ ሠራተኞቹ ይበተናሉ፤ አባላቱም ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ይገባሉ፡፡
ምክንያቱም አሁን ላይ አንድ ሺህ ያህል የማህበሩ አባላት ከ60 ዓመት በላይ ስለሆናቸው በግል ድርጅትነት እንዳንደራጅ ከማድረጉም በላይ የግል ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና የማይቀበላቸው ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ማህበሩ ሥራውን እየሠራ ያለው በእነዚህ አዛውንት እናቶችና አባቶች ሲሆን፤ ከ60 ዓመት በላይ የሆነን ሰው ሱቁ ውስጥ የሽያጭ፣ በር ላይም የጥበቃ ሠራተኛ አድርጎ እያሠራ ነው፡፡ ለምን ቢባል፣ እነዚህ አባላት በቤተሰባቸው የማይደገፉና ከአዲስ ፋና ውጪ ምንም መተዳደሪያ የሌላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ጭማሪው እነዚህን አዛውንቶች፣ ደካሞች ብሎም አካል ጉዳተኞች ጎዳና የሚያስወጣና ለጸጸት ሚዳርግ በመሆኑ ፈጽሞ በማህበሩ ላይ መሆን የሌለበት ጭማሪ ነው የገለጹት፡፡
የማህበሩ አባል የሆኑት አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ማህበሩ በሴፍቲኔት ሲደራጅ፣ ኢህአዴግ በደርግ ጊዜ ተይዘው የነበሩ የዋጋ ማረጋጊያ ተቋማትን ባፈረሰበት ወቅት አብዛኞቹ በፕራይቬታይዜሽን እንዲሸጡ ሲደረግ ሠራተኛውን ግን መጣያ ስለጠፋና የጡረታ መብቱም ሊከበርለት ስላልቻለ አሁን በማህበሩ ስር ያሉትን ሱቆች፣ መጋዘኖችና ሆቴሎች እንዲሁም በውስጣቸው ያሉ ንብረቶችን ይዞ እየሠራ እንዲጠቀሙ በሚል ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈም የዋጋ ማረጋጊያ ሆኖም ለመንግሥት እያገለገለ ነው፡፡ የማህበሩን አባላትና በሱቆቹ የሚሠሩ ሠራተኞችን ደመወዝ የሚከፍለውም ሠርቶ ከሚያገኘው ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ የቤቶቹን ኪራይ ብሎም የባንክ ብድር እዳ ሲከፍልም ቆይቷል፡፡
«ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ልንደገፍና ያላግባብ ያወጣናቸው ወጪዎች ሊካካሱንል ሲገባ፤ በዚህ መልኩ ማህበሩን ያላማከረና የማህበሩን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ መደረጉ ተገቢነት የሌለው ዕርምጃ በመሆኑ ጭማሪውን እንቃወማለን፤ ጭማሪውም ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳልን እንጠይቃለን፤» የሚሉት አቶ ሁንልኝ፤ ማህበሩ የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ ቤቶችን ነገ የእኔ ናቸው በሚል በከፍተኛ ወጪ እያሳደሰና እያስፋፋቸው ለዚህ የደረሱ በመሆናቸው፤ አሁን የተደረገው ጭማሪ ማህበሩን ለአደጋ አባላቱንም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያጋልጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች በማህበሩ ቤቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ ተገቢ ስላልሆነ በአግባቡ ታይቶም ሙሉ ለሙሉ መነሳት ይኖርበታል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
እንደ አጠቃላይ የማህበሩ ቅሬታ የሚያተኩረው፣ የተደረገው ጭማሪ በማህበሩ አባላት፣ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያመጣ፤ ማህበሩን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ክፍያ እየከፈለ ቢሆንም አሁን ላይ ዕዳውን ጨርሶ ወደራሱ ለማዞር እንቅስቃሴ ላይ ባለበት ሂደት ላይ የተከናወነ፤ እንዲሁም ማህበሩ ከተቋቋመለት ዓላማ አንጻር እየተወጣ ካለው ኃላፊነት ጎን ለጎን ለህዝቡ እየሰጠ ያለውን ማህበራዊ አገልግሎት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ሊነሳ ይገባል በሚለው ላይ ነው፡፡
የማህበሩን ቅሬታ አስመልክቶ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምላሽና አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም፤ በቀጣይ የሚሰጠው ምላሽ ካለ የምናቀርብ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
ወንድወሰን ሽመልስ