መርድ ክፍሉ ከ የከተማ ፕላን ማለት አስቀድሞ ለሚወሰን ዘመን የአንድ ከተማ እና አካባቢው የወደፊት ዕድገት በልማታዊ ዓላማ መሠረት እንዲመራ የሚዘጋጅ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በይዘት ደረጃ የከተማውን መሬት አጠቃቀም፣ የትራንስፖርት መስመርና ሥርዓትን፣ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ፣ ፊዚካላዊና ሌሎች ጉዳዮችንም ያካትታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ኢንስትቲዩት ኦፍ አርክቴክቸርና የሕንፃ ግንባታ ካምፓስ የከተማ ዲዛይን መምህር ዶክተር ጥበቡ አሰፋ እንደሚሉት፤ በዓለም በርካታ የፕላን ዓይነቶች ያሉ ቢሆንም፣ በአገራችን በከተማ አቀፍ ደረጃ እንዲሰራባቸው በሕግ የተፈቀዱት የመዋቅራዊ ፕላን እና የመሠረታዊ ፕላን ዓይነቶች ናቸው። በአገሪቱ ከተሞች ላይ የመንገድና የሕንፃ ግንባታ ቴክኖሎጂዎች፣ ዲዛይንና የከተሞቹ አሠራር መምሰል ባለባቸው ላይ ዶክተር ጥበቡ የሰጡንን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ለሕንፃና ለመንገድ ግንባታ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ያስፈልጋሉ
ለመንገድ ግንባታ የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የአካባቢ ለውጥን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መጠቀም ያስፈልጋል። ለምሳሌ የአስፓልት መንገድ የሬንጁን ንጣፍ ለማድረቅ ብዙ ቴክኖሎጂ ይፈልጋል። የሬንጅ አስፓልት ውሃ እንዳይሰርግ ስለሚያደርግ በአሁኑ ወቅት ተፈላጊ አይደለም። በዚህም ጎርፍ እንዲከሰት ያደርጋል። ለዚህም ውሃን ማስረግ የሚችሉ ንጣፎች እንዲሁም በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ላይ ውሃ ሊያሰርጉ የሚችሉ ከፕላስቲክ የተሰሩ ንጣፎች መጠቀም ያስፈልጋል።
መኪና የሚሄድበትን ቦታ ለይቶ ኮንክሪት ማድረግ ይገባል። ውሃን ማስረግ የሚችል ኮረት አስፓልት በመገንባት ቀላል ቴክኖሎጂ መጠቀም የግድ ይላል። በእነዚህ መንገዶች በከተሞች ላይ ውጤታማ ሥራ ማከናወን ይቻላል። ያደጉት አገራት የኮንክሪት አስፓልት እያስፋፉ ይገኛሉ። የአስፓልት መንገዶች ነጭቀለም እየተቀቡ ናቸው። በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሀገሮች በብዛትና በፍጥነት ሕንፃ ሊሰራባቸው የሚገቡ ግብዓቶች እየተስፋፋ ይገኛሉ። የሕንፃ ወለሎችና ግድግዳዎች ቀድመው ተሰርተው በሚያስፈልጉ ቦታዎች በመገጣጠም ውጤታማ ሥራ ይከናወናል። በዚህም የቤት ችግርን መፍታት ተችሏል።
በሕንፃ መገንቢያ ዕቃዎች ላይ የሚደረገው ምርምር ዝቅተኛ በመሆኑ ቤቶች በቀላሉ ሊገነቡ የሚችሉበት ሁኔታ አይታይም። እነዚህን ዕቃዎች በመጠቀም ከተለምዶ ወጣ ባለ መልኩ ግንባታዎችን ማካሄድ ያስፈልጋል። ግንባታዎችን በቀላል መንገድ መሰራትከተቻለ የአየር ንብረት ለውጥ መቆጣጠር ይቻላል። በውጭ አገራት የተሞከሩ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ የግንባታ ዘዴዎችን መጠቀም ያስልፈጋል። እንደ አልሙኒየም ምርት ያሉ ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉ ግብአቶችን ከግንባታ ውጪ ማድረግ ይገባል። አንድ የግንባታ ዕቃ ብዙ ኃይል በፈለገ ቁጥር አካባቢን የመበከል አቅሙ ያድጋል።
የአገሪቱ ከተሞች እድገት ሲገመገም
በአገሪቱ ከተሞች ግንባታ የሚካሄድበት ሁኔታ ኋላቀር ነው። ግንባታዎቹ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ካለመሆናቸው ባሻገር ለአጭር ጊዜ አገልግሎት የሚከናወኑ ናቸው። የከተሞች ግንባታዎች አስፈላጊው ምርምር ተደርጎባቸው የተሰሩ አይደሉም። ለምሳሌ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ከዲዛይን ጀምሮ ቢታዩ ፍሰትንና መቃረቢን እንዲጨምሩ ታስቦ የተሰሩ አይደሉም፤ ግንባታቸው የነዋሪዎችን ፍላጎት ያማከለ አይደለም። የተገነቡት ሕንፃዎች በረንዳ የላቸውም። ሁሉም ሕንፃ መንገድ ጠርዝ ድረስ ነው የተገነቡት።
ይህ በመሆኑም ሰዎች ከዝናብና ከፀሐይ የሚከለሉበት ቦታ የላቸውም። መንገዶች አቅጣጫን ያመለካቱ ሆነው ስላልተገነቡ ሰዎች እየተቸገሩ ነው። በከተሞች ምን ዓይነት የመንገድ ግንባታ መኖር አለበት ለሚለው ጥናቶች የተሰሩ ቢሆንም፣ ተግባር ላይ አልዋሉም። አብዛኛዎቹ መንገዶች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፤ የእግረኞችና የመኪና መንገዶች የተገጣጠሙ ናቸው። ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መንገዶች አልተገነቡም የሚያሰኝ ሁኔታ ይስተዋላል፤ የከተሞች ሕንፃ አሠራር የሸረሪት ድር እስከሚመሰል ደርሷል።
ከተሞች መኖሪያ፣ መስሪያና መዝናኛና የመሳሰሉትን በሚይዝ መልኩ መገንባት አለባቸው። ሰዎች ከመኖሪያቸው ወደ መስሪያቸው ወይም ወደ መዝናኛቸው የሚሄዱበት መንገድና ሌሎች ግንባታዎች ምቹና ሳቢ ተደርገው ሊገነቡ ይገባል። በአገሪቱ ግንባታዎች ይህን ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም። ለእዚህም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መጥቀስ ይቻላል። ቤቶቹ በዘፈቀደ የተገነቡ በመሆናቸው መኖሪያና መስሪያ የተራራቀበት ሁኔታተፈጥሯል። ይህ መሆኑም የትራንስፖርት ማጨናነቅን አስከትሏል።
በከተሞች የመስሪያና መኖሪያ አካባቢዎች መቀራረብ አለባቸው። ወደፊት የመኖሪያና የመስሪያ ቦታዎች እንዲቀራረቡ ማድረግ ይገባል። በከተሞች ላይ የሚከናወኑ ግንባታዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ብቻ በመሆኑ አረንጓዴ ቦታዎችን ለመፍጠር ታስቦበት የሚሰራ አደለም። የሕዝቡን አሰፋር ሁኔታ እንኳ ቢታይ የእርሻ መሬቶች ለከተማነት እየዋሉ እንደሚገኙ መታዘብ ይቻላል። አሁን ባለው ሁኔታ ለም መሬትን ወደ ከተማነት እየተቀየረ ይገኛል። ይህ የሚያሳየው የመሬት አጠቃቀም ላይ ችግሮች እንዳሉ ነው።
የከተማ ዲዛይኖች ምን ይምሰሉ
በከተሞች መኖር ከሚገባቸው የመንገድ ዲዛይኖች መካከል ዋነኛው የውስጥ ለውስጥ መንገድ እና መቃረቢያ ነው። ኅብረተሰቡ በቀላሉ ከቤቱ ወጥቶ የሚፈልግበት ቦታ ወይም ወደ ዋና መንገድ ማድረስ የሚያስችሉ አቋራጮች በዲዛይን ላይ ጭምር መሰራት አለባቸው። ሌላው ለትራንስፖርት ፍሰት ጠቃሚ የሚሆኑ መንገዶች ዲዛይን ነው። በከተሞች ላይ በትክክለኛ ዲዛይን መንገዶች ካልተሰሩ መጨናነቅና አንድ ቦታ መቆየትን ይፈጥራሉ። በመንገድ መራዘም የደከመ ሰው መስሪያ ቤቱ ገብቶ ውጤታማ ሥራ ማከናወን አይችልም።
በከተሞች ላይ ውጤታማ የመንገድ ዲዛይኖችን በመቀየስ ለመንገድ የሚውሉ መሬቶችን መቀነስ ያስፈልጋል። በአነስተኛ መሬት እንዴት ውጤታማ ሥራ ማከናወን ይቻላል የሚለው መታየት አለበት። ውጤታማ የመንገድ ዲዛይን ሲኖር መዘጋት ያለባቸው መንገዶች እንዲዘጉም ያደርጋል። የመኖሪያና የመስሪያ ቦታዎችን የሚያቀራርቡ የከተማ ዲዛይኖች ትኩረት ሊሰጣቸው ያስፈልጋል። የትራንስፖርት መጨናነቅ ሳይኖር ሰዎች በሰላም ሰርተው ያለ ድካም ቤታቸው እንዲገቡ ያደርጋል። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ ቅድሚያ አብዛኞቹ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የት አካባቢ እንዳሉ መታየት አለበት። የትራንስፖርት ፍላጎት ከፍተኛ የሆነባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው የሚለውም መታየት አለበት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
መርድ ክፍሉ