የአየር ንብረት ለውጥ ስጋትና መፍትሄው

“የአየር ንብረት ማለት በአንድ ሥፍራ ያለው የአየር ፀባይ በዓመታት የሚያሳየው አማካይ ውጤት ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ የዚህ አማካይ አየር ፀባይ መቀየር ማለት ነው።” የሚለውን፤ እንዲሁም፣ “የአየር ንብረቱ በፍጥነት እየተለዋወጠ የመሄዱ ምክንያት የሰው ልጅ ነው።” የሚለውን የባለሙያዎች ብያኔ በጠቅላላ እውቀትነቱ ይዘነው ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንዝለቅ።

የሰው ልጅ ነዳጅ ይጠቀማል፤ ጋዝና ከሰል ያቀጣጥላል፤ በድንጋይ ከሰልና በጋዝ ለቤቱ ብርሃን ያጎናፅፋል፤ ፋብሪካ ያንቀሳቅሳል፤ መጓጓዣ ያበጃል። እነዚህ ኃይል አመንጪ ንጥሮች የሚለቁት ጭስ ግሪንሃውስ ጋዝ ይባላል። አብዛኛው ክፍሉ ካርበን ዳይኦክሳይድ [CO2] ነው። ይህ ጋዝ ከፀሐይ የሚመጣውን ሙቀት አምቆ የፕላኔታችን የሙቀት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። ዓለማችን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን በ1.2 ድግሪ ሴልሺዬስ ጨምራለች። ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን ደግሞ 50 በመቶ ጨምሯል።

እ.ኤ.አ. ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ይበልጥ ጎልቶ የታወቀው የዓለም አቀፍ አማካይ የሙቀት መጠን በ0·7 ዲግሪዎች አድጓል፡፡ የምድራችን ሙቀት መጠን በ2100 አሁን ባለበት 1.5 ድግሪ ሴልሺዬስ መቆየት የሚገባው ሲሆን፤ በዚህ አካሄድ 2100 ላይ የዓለም ሙቀት ከ3-5 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚጨምር ይሆናል። የአፍሪካን እንመልከት።

አፍሪካ

ከ20 የሚበልጡ የአፍሪካ መሪዎች፣ የበርካታ ሀገራት ሚንስትሮች፣ ልዑኮችና የአየር ንብረት ተሟጋቾች በተሳተፉበት በኬንያ/ናይሮቢ በተካሄደውና ከድርቅ ጀምሮ እስከ በርሃማነት በተደቀነባት የአፍሪካ አህጉር የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ በመከረው፣ የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢንዱስትሪ ሚንስትርና የኮፕ28 ፕሬዚዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር እንደተናገሩት የአህጉሪቱ 1/5ኛ ሕዝብ እንደ ድርቅ እና ጎርፍ ባሉ አደጋዎች ለረሃብ ተጋልጧል። በድርቅና ጎርፍ አደጋዎች ምክንያት የተፈናቀሉ አፍሪካውያን ቁጥርም በሶስት እጥፍ ጨምሯል።

የስታቲስታ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ብቻ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ 1 ሺህ 700 የተፈጥሮ አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው በጎርፍ ምክንያት የተከሰተ ነው።

እንደዚሁ ድረ-ገጽ መረጃ በአህጉረ አፍሪካ በአጠቃላይ 38 ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ሲደርስ ጎርፍና አውሎ ንፋስ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ከ730 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን፤ ከ90 በመቶ በላዩ በተፈጥሮ ውድመት ምክንያት የተከሰተ ነው። 20 ሺህ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ሲሞቱ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ እንስሳትም ለሞት ተዳርገዋል። “ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አይነት አደጋ እስኪደርስ ነው የምንጠብቀው?” የሚለው የበርካታ አፍሪካዊያን ጥያቄ ነው።

ዓለም አቀፍ ምንጮችንና በአዲስ አበባ የተካሄደውን 19ኛውን የአፍሪካ የአካባቢ ሚንስትሮችን ጉባኤ ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ ለንባብ እንዳበቃው ከሆነ ከ60 በመቶ በላይ አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

ቢቢሲ ኦክስፋምን ጠቅሶ እንዳሰፈረው እአአ በ2019 ብቻ በአፍሪካ በ18 ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተከሰተ ድርቅ ከ52 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሀብ ተጋልጠዋል። ሀገራቱም ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጥተዋል።

ከተፈጥሮ አደጋ ጋር በተያያዘ ከተከሰቱ ህልፈቶች 70% የተከሰቱት በደሃ ሀገራት ነው። በችግሩ ምክንያት የአፍሪካ የጠቅላላ ምርት ወይም ጂዲፒ እድገት በየዓመቱ በአማካይ የ5 በመቶ ቅናሽ እያሳየ በመምጣት ላይ መሆኑም ይነገራል።

ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ከፀሐይ ኃይል የሚያገኙት ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት ዓመታት በስድስት እጥፍ ማደጉም አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ለመቀነስ እየሄደችበት ያለውን ርቀት ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቬሪስክ ማፕልክሮፍት የተባለ ድርጅት ጥናት ይፋ እንዳደረገው፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠባቸው 95 በመቶ የሚሆኑት ከተሞች በአፍሪካ ወይም በእስያ የሚገኙ ናቸው።

የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ለመቀነስ 250 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ቢባልም አህጉሪቱ ያገኘችው ድጋፍ 12 በመቶ ብቻ መሆኑም በኬንያው ጉባኤ ላይ የተነሳ ሲሆን ቃላቸውን እንዲያከብሩም ጥሪ ተላልፏል።

በተለያዩ ሰነዶች ላይ ተጠቅሶ የምንመለከተው የዓለም አቀፉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋም ሪፖርት “አፍሪካ ውስጥ ካሉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋሞች ደረጃቸውን የጠበቁት 26% ብቻ ናቸው።” ያለውም ትኩረት ሳይሰጠው የሚታለፍ አይሆንም።

የአፍሪካ ቀንድ

የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሀመድ አብዲ ዋሬ በ70ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ምልከታ መድረክ ላይ እንደተናገሩት በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

የኢጋድ አባል ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ የውኃና ኢነርጂ ሚንስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዚሁ መድረክ ላይ እንዳሉት በአፍሪካ ቀንድ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅና ጎርፍ በርካቶችን እየፈተነ ነው። ይህንንም ለመቋቋም በኢትዮጵያ አስተማማኝና ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃን መተንተንና ማሰራጨት የሚያስችል ተቋምን ለማዘመንና ጠንካራ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ ይገኛል።

እንደዚሁ የኦክስፋም ሪፖርት በምዕራብ ኬንያ የሰብል ስብሰባው 25 በመቶ ቀንሷል፤ በሶማሊያም በ60 በመቶ አሽቆልቁሏል። በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የእንስሳት እርባታና የወተት ምርት እጅጉን ወርዷል።

ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ፣ “አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ቢሆንም ለሌላው ዓለም አርአያ የሚሆን ተግባርም አላት · · · የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ ለበርካቶችም የሥራ እድል እየፈጠረ ይገኛል” ያሉት የኮፕ 28 ፕሬዚዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ኬንያ በ2030 ሁሉንም የኃይል ምንጯን የታዳሽ ኃይል ለማድረግ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እስከ 2050 ድረስ 170 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት የገለፀችው፤ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ልማቷን ትመራበታለች የተባለና የአየር ንብረት ለውጥን ያማከለ እቅዷን (የረጅም ዓመት ዝቅተኛ ልቀትና የአየር ንብረት ተቋቋሚ የልማት ስትራቴጂ) ባለፈው ሀምሌ ወር ይፋ ያደረገችው ኢትዮጵያ፣ ከእዚህ ውስጥ 20 በመቶው (1.9 ትሪሊዮን ብር ገደማ) በሀገሪቱ አቅም (ፐብሊክ ፋይናንስ) እንደሚሸፈን እቅዱን የነደፈው የፕላንና ልማት ሚንስቴር ሚንስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በናይሮቢ/ኬንያ በተካሄደ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ተናግረዋል። ይህም በቀጣናው የአየር ንብረት ለውጥ ላይ እየሰሩ ካሉት ሀገራት ፊት መሪ እንድትሆን ያደረጋት መሆኑ በጉባኤው ተወስቷል።

ኢጋድ የድርቅ አደጋ መቋቋምና ዘላቂነት ተነሳሽነት (IDDRSI) በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የአርብቶ አደር ምግብና ሥርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮግራም ሰነድ በሆነው የአካባቢ እና ማህበራዊ አስተዳደር/አያያዝ ማዕቀፍ (ESMF) መግቢያ ስር እንደ ሰፈረው የአፍሪካ ቀንድ ደረቃማ እና ከፊል ደረቃማ መሬት (ኤኤስኤልኤስ) የድርቅ፣ እየጨመረ የመጣ አስከፊ ድህነት እና የምግብ ዋስትና እጦት እና ሌሎች የኑሮ ስጋቶች ተጋርጦባቸዋል። በኢጋድ ክልል ውስጥ ከተፈጥሮ ሥነ-ምህዳሮችና መኖሪያ አካባቢዎች ጉዳት ያልደረሰበት 5% ያህሉ ብቻ ነው። ይህም 95% የሚሆነው ኦሪጅናል ስነ-ምህዳር በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ወደ ሌላ የመሬት አጠቃቀም በተለያዩ ምክንያቶች በከፍተኛ ሁኔታ ወይም በመጠኑ የተቀየረ፣ የተጎዳና የተራቆተ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

በዚሁ በኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ፕሮግራም ትግበራ ወቅት ለሚቋቋሙ የአካባቢ እና ማህበራዊ ግምገማ እና ሌሎች የጥበቃ ርምጃዎች ማሕቀፍ ሆኖ በሚያገለግለው ሰነድ ላይ እንደ ተዘረዘረው ለዚህ የአካባቢና ተፈጥሮ ኃብት መራቆት ዋና ዋና መንስኤዎች የአየር ንብረት ለውጥ፣ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ልቅ የሆነ የግጦሽ መሬት አጠቃቀም፣ የደን እና ቁጥቋጦዎች መጨፍጨፍ፣ የአፈር መሸርሸርና የውሃ ብክነት፣ የዱር እንስሳት አደን፣ የበረሃማነት መስፋፋት ወዘተ ናቸው።

ድርቅ በብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ህይወት እና ኑሮ ላይ ባደረሰው አሉታዊ ተፅእኖ እና በሰዎች እና በእንስሳት ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን የሚያስረዳው ሰነዱ፣ በቀጣናው ያለው ሁለገብ ድርቅን የመቋቋም እና ቀጣይነት ያለው የኑሮ መተዳደሪያ ፕሮግራም (DRSLP) በሦስት ምዕራፎች ተመድቦ በአምስት ዓመታት ውስጥ እንዲተገበር ተነድፏል። የDRSLP መርሃ ግብር ዓላማ በገጠር የድህነት ቅነሳ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለተፋጠነ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። DRSLP-1 እ.ኤ.አ. በ2020 ተጠናቅቋል። ይህ የክትትል መርሃ ግብር “በአፍሪካ ቀንድ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትናን የመቋቋም አቅምን የመገንባት ፕሮግራም (BREFONS)” እንደ DRSLP 2ኛ ደረጃ (DRSLP-II) እና የPPCI-Sahel 2020 እንደ መጀመሪያ ፕሮግራም ይቆጠራል።

ይህ በአፍሪካ ቀንድ የምግብ እና የሥነ-ምግብ ደህንነትን የመቋቋም አቅምን የመገንባት ፕሮግራም (BREFONS) የአፍሪካ ልማት ባንክ የሳህል ክልል የአየር ንብረት ኢንቨስትመንት ዕቅድን (PIC-RS 2018-2030) በገንዘብ ለመደገፍ በየካቲት 2019 ባካሄደው ስብሰባ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው። የአፍሪካ ቀንድ ፕሮግራም በምድብ ሁለት የተመደበ ፕሮጀክት ሲሆን (classified as Category Two project) ይህም ሰንድ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እና ማህበራዊ አስተዳደር ማሕቀፍ ሆኖ የሚያገለግል ነው።

በያዝነው ግንቦት ወር ኢጋድ 70ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት የተቋሙ “የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል ወቅታዊና አስተማማኝ የአየር ጠባይ መረጃ በማቅረብ የአባል ሀገራቱ የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም ለማጎልበት የሚሠራው ሥራ የሚደነቅ መሆኑ” የተነገረለት ኢጋድ “አባል ሀገራቱ አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ማመንጨት የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር አለባቸው።” የተባለውንም አብሮ ማየት ይቻላል።

የአባል ሀገራቱን (ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ እና ኤርትራ) ጠንካራና ድግግፍ፣ ትብብርና ተሳትፎ አስፈላጊነት የሚያሳስበው ሰነድ (ESMF) የክልሉን ችግሮችም ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

የመረጃ ክፍተት

እንደ ባለሙያዎች አስተያየት የከፋ የአየር ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት በተገቢው መንገድ ማስጠንቀቂያ መሰጠት አለበት። ይህም የአየር ሁኔታ ምን እንደሚመስል ከመተንበይ ባለፈ፤ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ያካተተም መሆን ይገባዋል።

እንደ ተመድ ሪፖርት ዓለም ላይ ከሦስት ሰዎች አንዱ/አንዷ የአየር ሁኔታ ማስጠንቀቂያ አይደርሰውም/ሳትም። ይህን አይነቱን ክፍተት ለመሙላትም ኢጋድም ሆነ አባል ሀገራቱ በተደራጀና በተናበበ ሁኔታ ሥራዎችን ሊሠሩ ይገባል። ኢጋድም ይህንኑ ሲያበረታታ ይታያልና እድሉን መጠቀም ተገቢ ነው። በተለይም “ማስጠንቀቂያዎች በታዳጊ ሀገራት፤ እንዲሁም በደሴቶች የበለጠ አስፈላጊ ናቸው። በተለይም በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የመረጃ ክፍተት መሞላት አለበት።” የሚለውንም በቸልታ አለማለፉ ይመከራል።

ምን ይደረግ?

የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ አማርኛ ክፍል የሚመለከታቸውን አካላት መረጃዎች ጠቅሶ ለአየር እንዳበቃው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ አደጋ የመከሠቱ ዕድል እና የጥንካሬው መጠን በ50 በመቶ ጨምሯል። ሥራዎች ካልተሠሩ በቀጣይ አሥር ዓመታት በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል።

ቪኦኤ (ዲሴምበር 22, 2024) የጠቀሳቸው የ“ወርልድ ዌዘር አትሪቢዩሽን” ተቋም መሪ ፍሬድሪክ ኦቶ እንደሚሉት ከሆነ ድርቁ፤ በየአካባቢው ያሉ ሰዎች የሚፈተኑበትን የአደጋ ጫፍ እያሳያቸው ይገኛል። በዚያው ላይ ጎርፉ ሲታከልበት፣ በዓለም የሚኖሩ ሰዎች በቀላሉ ከማይቋቋሙት የአደጋ አፋፍ ላይ ያደርሳቸዋል። የዕጽዋት እና የእንስሳት ቅሪቶችን በማቃጠል ነዳጅ ማምረታችንን እስከቀጠልን ድረስ፣ አደጋዎቹ እንደሚደጋግሙን የታወቀ ነው። ሉላዊቷን ዓለም እያጋምን በቀጠልን ቁጥር፣ አልፎ አልፎ የምናየው አደገኛ የአየር ክሥተት፣ በአጭር ጊዜ ልዩነት እየደጋገመን አዘቦታዊ ሳይሆን የሚቀር አይመስልም፡፡ ይህንን የኢጋድ አባል ሀገራትን ጨምሮ ሌሎችም ልብ ይሉት ዘንድ የብዙዎች ማሳሰቢያ ነው።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ሀገራት የጋራ ስትራቴጂያዊ እቅድን አዘጋጅተው አካባቢያቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ከሚያስከትለው አደጋ ሊታደጉና ቀጣናዊ ደህንነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባቸዋል። የመጀመሪያ አላማው የአካባቢው ሀገራትን በተደጋጋሚ የሚያጠቃውን ድርቅ በጋራ መከላከል እና የጋራ ስትራቴጂ እየነደፉ ለልማት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የሆነው ኢጋድም ለአባል ሀገራቱ የዘረጋው ሀሳብ ይህንኑ ነው።

በርካታ ሀገራት በ2050 የካርበን ልቀት መጠኑን ዜሮ ለማድረግ ተስማምተዋል። ባለሙያዎች ይህ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ነው ይላሉ። ነገር ግን መንግሥታት፣ ቢዝነሶች እንዲሁም ግለሰቦች አንድ ላይ ካልሠሩ ዋጋ የለውም የሚለው የባለሙያዎች ምክረ-ሀሳብ ተገቢውን ትኩረት ሊያገኝ ይገባል እንላለን።

የቅርቡ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የጋራ አቋም በመሆን የፀደቀውንና በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ንግግር ለአፍሪካ የጋራ አቋም መሠረት ሆኖ ያገለግላል የተባለለት “የናይሮቢ ስምምነት”ን ጨምሮ፣ የኪዮቶ ፕሮቶኮል፣ የፓሪስ ስምምነትና ሌሎችም ወደ መሬት ይወርዱ ዘንድ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግድ ይላል። ወደ ግለሰብ እንምጣ።

ከላይ የፈተሽናቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ አንድ ግለሰብ የአኗኗር ዘዬውን በመቀየር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስ የሚችል ሲሆን፤ ለመቀነስም ስጋ፣ ወተት፣ አይብ እና ቅቤ በትንሹ መጠቀም፤ በአካባቢያችን የሚመረቱ ወቅታዊ የሆኑት አትክልት እና ፍራፍሬዎችን አዝወትረን መመገብ፤ በተቻለ መጠን የምግብ ብክነትን መቀነስ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ መኪኖችን ማሽከርከር፤ አጭር እርቀቶችን በእግራችን መጓዝ፤ ወይም ሳይክል መጋለብ፤ ከአወሮፕላን ይልቅ የባቡር እና አውቶብስ አማራጮችን መጠቀም፤ ለስብሰባ ረዥም ጉዞዎችን ከማድረግ ይልቅ በቪዲዮ ኮንፍረንስ መገናኘት፤ አነስተኛ የካርበን ልቀት ያላቸውን የቤት ውስጥ መገልገያዎችን መጠቀም እና የመሳሰሉትን ተግባራት መፈፀም ናቸው።

“ሰዎች አነስተኛ ስጋ እና የስጋ ውጤቶችን ቢመገቡ በከፍተኛ ደረጃ የአየር ብክለትን መቀነስ ይቻላል። አነስተኛ ስጋ እና የስጋ ውጤቶችን በመጠቀም የስጋ ማቀነባበሪያ ኢንደስቱሪዎች የሚለቁትን የካርበን ልቀት መጠንን መቀነስ ይቻላል።” የሚለውና “የአየር ንብረት ለውጥ ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት መፈፀም ያለብን ተግባር ቢኖር የሙቀት መጠንን መቀነስ ነው።” የሚለው የባለሙያዎቹ ምክር ነው።

በድርቅ፣ በሜቲዮሮሎጂ እና የአካባቢ አየር ጥበቃ ጉዳይ ላይ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራቱ፤ ዕውቀት በማስፋት ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ኃይል አቅም እንዲጠናከር ሥልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም በሀገራቱ መካከል መተባበር እንዲኖር ሲሠራ መቆየቱ የሚነገርለት ኢጋድም ቀንዱን (አባል ሀገራቱን) እየፈተነ ያለውን ጎርፍና ድርቅ መከላከል እንዲቻል በተቋሙ የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል አማካኝነት እየሠራ ያለው ተግባርም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ሌላው መደረግ ያለበት፣ የኢጋድ የድርቅ አደጋን የመቋቋም እና ዘላቂነት ተነሳሽነት (IDDRSI) የተጋላጭ ማህበረሰቦችን ተደጋጋሚ የድርቅ ተፅእኖዎች የመቋቋም አቅም ለመገንባት እና በኢጋድ ክልል እድገት እና ዘላቂ ልማት ለማምጣት ያለመውን የድርቅ አደጋ መቋቋም እና ዘላቂነት ተነሳሽነት (IDDRSI) ስትራቴጂን ተግባራዊ ማድረግ ነው።

ይሄው ተቋም “የአየር ንብረት አገልግሎት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍተቶችን በጋራ መሙላት” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው 69ኛውን ጉባኤ ላይ “የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትለው ጫና ተጠያቂ የሆነው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከልን ማጠናከር እንደሚገባው፤ ለዚህ ስኬታማነትም አባል ሀገራቱ በትብብር፣ በጋራ መሥራት የሚገባቸው ስለመሆኑ መግባባት ላይ መደረሱንም የዚሁ የመፍትሄው አካል አድርጎ መውሰድ ተገቢ ሲሆን፤ ለበለጠ መረጃም ሰነዱን መመልከት ይቻላል።

የአፍሪካ ህብረት የፍልሰት ታዛቢ (አማኦ) ዳይሬክተር አምባሳደር ናሚራ ነሂ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌሎች መስኮች የምታከናውናቸው ተግባራት ድርቅን በመቀነስ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚፈጠር ፍልሰትን እያስቀሩ ነው” በማለት የተናገሩትንም ሌሎች (በተለይም የኢጋድ አባል) ሀገራት ይከተሉት ዘንድ እዚህ መጥቀስ ይገባል።

በመጨረሻም፣ ግብርና፣ የምግብ ሉአላዊነት፣ የውሃ ኃብት፣ ቱሪዝም እና ጤና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ ከሚደርስባቸው ዘርፎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You