
ጸሀዬ ቦጋለ ይባላል ትውልድና እድገቱ በአሰላ ከተማ ሲሆን ፤ ኑሮውን በአዲስ አበባ ካደረገ ዓመታት ተቆጥረዋል። የራሱን የትዳር ሕይወትም መስርቶ የሚኖር እድሜው ወደ ጎልማሳ የሚጠጋ ነው። ለወላጆቹ ብቸኛ ልጅ የሆነው ጸጋዬ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ወላጆቼ በገዙት መኖርያ ቤት ውስጥ የራሱን ሥራ እየሠራ ይኖር ነበር። ከባለቤቱ ወይዘሮ አልማዝ እሸቱ ጋርም የተዋወቀው በዚሁ አጋጣሚ ነው።
አልማዝ በወላጆቹ መኖሪያ ቤት ተከራይታ በምትኖርበት ጊዜ ይተዋወቁ የነበረ ቢሆንም ሰላምታ ከመለዋወጥ የዘለለ የጠበቀ ግንኙነት አልነበራቸውም። ነገር ግን በጊዜ ሒደት ይህ ግንኙነታቸው እያደገ በመካከላቸው በተፈጠረ መግባባትና ወዳጅነት ግንኙነታቸው ወደ ትዳር ሊቀየር ችሏል። ኑሯቸውንም ያደረጉት እሱም በወላጆቹ ቤት እርሷም እዚያው ተከራይታ ትኖርበት የነበረ ቤት ውስጥ ነው።
ትዳር በፈጣሪ ዘንድ የተባረከ እና የሚመከር ሲሆን በሀገራችን ብሂል እንዲሁ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ እንደሚባል ሰዎች በሕይወታቸው መድረስ የሚገባቸው የስኬት ደረጃ ፤ማሳካት የሚገቧቸውን ግቦች ካሳኩ በኋላ የራሳቸውን ቤተሰብ እንዲመሰርቱ ይደረጋል። ጸሀዬ የመጀመርያ ዲግሪውን ጨርሶ ረጅም የሚባል የወጣትነት ጊዜውን በተለያዩ ሥራዎች አሳልፏል። ነገር ግን ትዳር መመስረት የወላጆቹ የሁልጊዜ ፍላጎት እና ልጆቻቸውን አብዝተው የሚጠይቁት ነው። ሰርግህ መቼ ነው፤ መቼ ነው ምታገቢው የሚለው ጥያቄ ወላጆች ለደረሱ ልጆቻቸው በየቀኑ የሚያቀርቡት ነው።
ወይዘሮ አልማዝ እሸቱ በአንድ ባንክ ውስጥ የሒሳብ ሰራተኛ ስትሆን ባለቤቷ ደግሞ በግል ሥራ የሚተዳደር ነው። ታዲያ ባለቤቱ አልማዝ በምትሠራበት ቦታ ባፈራቻቸው ጓደኞች ጋር በምታደርገው ግንኙነት እምብዛም ደስተኛ አይደለም። ይህንን አልፎ አልፎ ለባለቤቱ ቢነግራትም መልሷ ግን የሥራ ባልደረቦቼ ናቸው የሚል ነበር። ጸሀዬ ከጥርጣሬ የዘለለ የሚጨበጥ መረጃ ባይኖረውም ነገር ግን ባለቤቱ ከሌላ ወንድ ጋር የምታደርገው የሰላምታ ልውውጥም ሆነ ንግግር ሙሉ ለሙሉ የሚቀበለው አይደለም።
አልማዝ በአንጻሩ ከሰዎች ጋር በቶሎ የምትግባባ እና በቀላሉ መልካም የሚባል ወዳጅትን የምትመሰርት ናት። ታዲያ ከባለቤቷ ጋር ትዳር ከመሰረቱ ገና የወራት እድሜ ቢቆጠርም ቅናትን መነሻ ያደረገ አለመግባባታቸው እያደገ እርስ በርሳቸው በየእለቱ ጥሩ ያልሆነ ቀናትን ያሳልፉ ጀመር። የሚኖሩት በባለቤቷ ወላጆች ቤት ነውና አልፎ አልፎ በመሀከላቸው ለሚፈጠረው ጭቅጭቅ አስታራቂ ሆነው መግባታቸው አልቀረም፤ ነገር ግን አልማዝ ያገባችው ሰው ያለው ግልፍተኝነት የምትቋቋመው አልሆነም። ጸሀዬ ለዚህ ባህሪው በተደጋጋሚ ቢመከርም እንዲህ በቀላሉ የሚለቅ ባህሪ ባለመሆኑ ለመለያየት እንዲወስኑ አደረጋቸው። አልማዝም ቤቱን ለቃ ሌላ አካባቢ ሄዳ እንደ አዲስ ሕይወትን መኖር ጀመረች።
ሌላ እድል
ጸሀዬ በጎልማሳነት እድሜው የጀመረው ትዳር እንደታሰበው ባለመቀጠሉ እንደገና የብቸኝነት ሕይወቱን ለመቀጠል ተገዷል። ነገር ግን የትዳርን መፍረስ ማንም ይሁን ብሎ የሚፈቅደው አይደለም እና ከሶስት ወር ቆይታ በኋላ በድጋሚ ታቀርው እሷ ወደምትኖርበት ቤት በመሄድ አብረው እንደገና መኖር ጀመሩ። ተለያይተው የቆዩበት ጊዜ ትምህርት የሆናቸው ይመስላል፤ ያለባቸው ችግር በንግግር ለመፍታት ተስማምተው ሕይወታቸውን ቀጠሉ። በዚህ ሁኔታ ግን አልማዝ ተመልሳ እርሱ ወደሚኖርበት አልሄደችም፤ ጸሀዬ ተከራይታ ወደምትኖርበት ቤት በመሄድ ኑሯቸውንም በድጋሚ ጀመሩ፡፡
አንድ ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ የያዘው ሀሳብ፣ ልምድ፣ ባህሪ እንዲሁ በቀላሉ የሚለቅ አይደለምና የባለቤቷ ግልፍተኝነት አሁንም አብሮት ነበር። ታዲያ ይህ የግልፍተኝነት ባህሪው ላይ ቅናት ተደምሮበት ለአልማዝ የተጨዋችነት ባህሪ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አልነበረም። በተደጋማሚ ስልክ በምታወራበት ጊዜ ከማን ጋር ነው የምታወሪው ማነው የሚል ጭቅጭቅ የሀይለ ቃል ልውውጥ በመካከላቸው አይጠፋም።
ጸሀዬ እና ባለቤቱ አልማዝ የሚኖሩት ብቻቸው ሙሉ ጊቢ ውስጥ ሲሆን አልፎ አልፎ ቤታቸው መጥተው ከሚጠይቋቸው በአከባቢያቸው ካሉ ወዳጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው በቀር የሚኖሩት ለብቻቸው ነው። በዚህ ሰሞን ግን ጸሀዬ ብቻውን ወጥቶ ይገባል፤ አልማዝ የት ሄደች ብሎ የሚጠይቀው ሰው ቢኖርም ወደ ገዳም ለጸበል መሄዷን ይናገራል። አልማዝ አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ የሀይማኖት ሥፍራዎች የመሄድ ልምድ ያላት በመሆኑ ይህ አዲስ አልነበረም። ነገር ግን በተደጋጋሚ ስልኳን ከጽሁፍ መልዕክት ባሻገር ሲደወልላት የማትመልስ በመሆኑ የት ሄደች የሚለው ጥያቄ ወደ ባለቤቷ ጸሀዬ መምጣቱ አልቀረም።
ጥርጣሬ
ጸሀዬ ያለፉትን ሶስት ቀናት ከቤቱ ወጥቶ ወደሌላ ስፈር በመሄድ ከጓደኛው ጋር አልጋ ይዞ ካደረ በኋላ ከባለቤቱ ወንድም ጋር ወደቤቱ ተመለሰ። ወንድም አልማዝ ገዳም እንደሄደች ቢነገረውም ከእርሷ ጋር በአካል ካወሩ በመቆየቱ እንዴት ሳትነግረኝ ሄደች የሚለው ጥያቄ ፈጥሮበታል። የእህቱ ቤት ከባለቤቷ ጋር ባደረበት ወቅትም ቤቱ የነበረው መዘበራረቅ ተጣልተው ይሆን ወይ የሚል ጥያቄ ፈጥሮበታል።
በሌላኛው ቀን ጉዳዩ ያልጣማቸው የአልማዝ እህት እና ወንድም እንዲሁም ከቤታቸው አቅራቢያ የሚኖር ጎረቤታቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁት የሚመልሰው መልስ ገዳም ሄዳለች የሚል ነበር ፤ ገዳም የሄደችውም በምትሠራበት ቦታ ባገኘችው መኪና ነው የሚል የጽሁፍ መልዕክት የደረሳት እህት ጉዳዩን ከሥራ ቦታዋ ለማጣራት ብትሞክርም አላየናትም የሚል መልስን አገኘች።
ያልታሰበ ግፍ
ጉዳዩ ያልጣማት የወይዘሮ አልማዝ እህት በቦሌ ቡልቡላ አርሴማ ጸበል አቅራቢያ ለሚገኘው ፖሊስ እህቴ ጠፍታብኛለች በማለት ታመለክታለች። የእህቷን ባለቤት ጸባይ የምታውቀው እህት ምናልባት የደበቀው ነገር ካለ በሚል የእህቷ አድራሻ ለማወቅ በማሰብ እና ወንድሟ ያደረበትን ጥርጣሬ ለማረጋገጥ ነበር ይህንን ያደረገችው። የእለቱ ተረኛ ፖሊስም ወይዘሮ አልማዝ ጽምጹዋ ሳይሰማ የቆየበትን ጊዜ ካጣራ በኋላ የመኖርያ ቤቷን ለመፈተሽ እና ባለቤቷን ለመጠየቅ ወሰነ ።
ፖሊስ በመኖርያ ቤቱ ፍተሻ ባደረገበት ውቅት የተገኘው ግን ከእህትና ከወንድም አቅም በላይ የሆነ እና ማንም ያልገመተወ ነበር ። የአልማዝ ወንድም ምንም እንኳም በቤቱ ባደረበት ወቅት ጤናማ የማይመስሉ ነገሮችን ቢመለከትም ይህ ይሆናል ብሎ ግን አልገመተም። ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ በመኖርያ ቤቱ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ገዳም ሄዳለች በሚል ስትፈለግ የነበረችውን ወይዘሮ አልማዝ እሸቱ አስክሬን አገኘ። በመሆኑም አቶ ጸሀዬ ቦጋለን ከ2015 መስከረም 16 ጀምሮ በቁጥጥር ስር በማዋል ቀጣይ ማጣራት ማድረጉን ቀጠለ።
ማስረጃ አንድ
ፖሊስ የሟች ወይዘሮ አልማዝ እሸቱ በመኖርያ ቤቷ ውስጥ አስክሬኗን ካገኘበት ቀን ጀምሮ የመጀመርያ ተጠርጣሪውን ባለቤቷን ሰቶ ጸሀዬ ቦጋለን በቁጥጥር ስር በማዋል ማጣራት ጀመረ። በምርመራውም ሟች ቤት ውስጥ አስክሬንዋ በተገኘበት ወቅት የተነሳ 27 ፎቶግራፍ መግለጫ፣ ሟች እና ተከሳሽ አብረው የተነሱት የጋብቻ ፎቶግራፍ ፣የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ በኤግዚቢትነት የተያዘ መክተፊያ ጣውላ ላይ ያለ ደም የሰው መሆኑን የሚያረጋግጥ የምርመራ ውጤት፤ ወይዘሮ አልማዝ እሸቱ የአስክሬን ምረመራ ውጤት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲሲንና ቶክሲኮሎጂ ማስረጃን በማያያዝ ክስ መስርቶ ሌሎች ማጣራቶችን ማድረጉን ቀጠለ።
የወንጀል ዝርዝር
ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1)ሀ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሽ ቀኑ ተለይቶ ባልታወቀ ከ27/12/2014 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት እስከ 28/12/2014 ዓ.ም ምሽት 12፡ 30 ባለው ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው አርሴማ ጸበል ተብሎ የሚጠራው አከባቢ ሰውን ለመግደል አስቀድሞ በማሰብና ፍቃደኛ በመሆን ጨካኝነቱን እና ነውረኛነቱን በሚያሳይ ሁኔታ ሟች ባለቤቱ የሆነችውን ወይዘሮ አልማዝ እሸቱን ከመኖርያ ቤታቸው ውስጥ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ጫማዋን እየፈታች ባለችበት ሁኔታ ተከሳሽ ከጀርባዋ በመሆን ሳታየው ለሊጥ መዳመጫ እንጨት (ዱላ) ማጅራቷ አካባቢ አንድ ጊዜ መትቷት እረሷን ስታ መሬት ላይ ስትወድቅ በወደቀችበት ትቷት ከቤት ወጥቶ ከሄደ በኋላ የተወሰኑ ሰዓታት ቆይቶ ወደቤት ሲመለስ ሟች ራሷን ስታ መሬት ላይ በወደቀችበት መሬት ለመሬት እየጎተተ ቤት ውስጥ ወደሚገኘው መታጠቢ ቤት በማስገባት የሟችን ግራ እግር ከዳሌዋ በታች በጭኗ እስከ ባቷድረስ በቢላ በመቁረጥ ስጋዋን ሽንት ቤት በመጨመር አጥንቷን በፌስታል ውስጥ አድርጎ መታጠቢ ቤት ውስጥ በማስቀመጥ አስክሬኗን በተለያየ ጨርቅና የፕላስቲክ መዘፍዘፊያዎች በመጫን መታጠቢያ ቤት ውስጥ በማስቀመጥ ለሟች ቤተሰቦች እና ሌሎች ሰዎች ገዳም ሄዳለች በማለት በአካልና በሟች ሞባይል ስልክ እንደሟች አስመስሎ የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ሲያሳውቅ ቆይቶ ከ1/13/2014 ዓ.ም እስከ 16/01/2015 ዓ.ም ቤቱን ዘግቶ ከተሰወረ በኋላ በክትትል የተያዘ ሲሆን በሟች ላይ በደረሰው የደም ቧንቧ መዋቅሮች ከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ማድረስ ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ ከባድ ሰው መግደል ወንጀል ተከሷል፡:
ማስረጃ ሁለት
ፖሊስ ክስ መስርቶ በሚያደርገው ማጣራት ውስጥ ከሟች ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 20 የሰው ምስክር ማስረጃዎች ያቀረበ ሲሆን፤ ከምስክሮቹ ውስጥ በሚኖርበት ቤት አቅራቢያ የሚገኝ ጥበቃ፣ የሟች እህትና ወንድሞች በሰው ምስክር አቅርቧል። በሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁ በኢፌዴሪ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር ሟች ስትጠቀምበት የነበረው ሞባይል ስልክ የት እንደነበረ የሚያስረዳ ኮፒ፣ ተከሳሽ የሰጠው ቃል፣ ተከሳሽ የተከሰሰበትን ወንጀል ከፈጸመ በኋላ በሌላ ሰው ስም አልጋ ይዞ ያድር የነበረ ለመሆኑ የሚያስረዳ መረጃ አካቷል።
ሌላኛው ዓቃቤ ሕግ ያካተታቸው ገላጭ ማስረጃዎች ሲሆኑ፤ ተከሳሽ የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት እንዴት እንደፈጸመው በራሱ ፈቃድ ሲሳይ የሚገልጽ ፎቶግራፍ ብዛት 14፣ ተከሳሽ የተከሰሰበት ወንጀል የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን አምኖ በነጻ ፍቃድ ለመርማሪ ቃሉን ሲሰጥ የሚያሳይ ሲዲ አያይዟል። ተከሳሽ በተከሰሰበት መዝገብ ላይ ለማየት እንደተሞከረውም ተከሳሽ ከዚህ ቀደም በ1999 ዓ.ም በክርስትና አባቱ ልጅ ላይ በፈጸመው የግድያ ወንጀል እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈርዶበት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለ12 ዓመት ከሶስት ወር ከታሰረ በኋላ ወደ አሰላ ማረሚያ ቤት ተዛውሮ ባቀረበው የይቅርታ ደብዳቤ መሰረት በ2013 ዓ.ም መስከረም አምስት በይቅርታ ከእስር ሊፈታ ችሏል።
ከባለቤቱ ጋርም የነበራቸው ትውውቅ በእስር ቤት ሳለ እርሷ የወላጆቹ ቤት ተከራይታ ትኖር የነበረ ሲሆን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከወላጆቹ ጋር በተደጋጋሚ በመሄድ ስትጠይቀው መተዋወቃቸውን በሰጠው ቃል ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
ውሳኔ
በከሳሽ ፌደራል ዓቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ጸሀዬ ቦጋለ በየነ መካከል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ተኛ ወንጀል ችሎት የነበረው ክርክር በ2016 ዓ.ም ሰኔ 28 በዋለው ችሎት ተከሳሽ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ከተሰጠው በኋላ ውሳኔውን በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጥር 12 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ውሳኔ ተሰጥቷል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም