
የአንድ ሕዝብ የለውጥ መነሳሳት ድንገት የሚፈጠር የሁኔታዎች ግጥምጥሞሽ አይደለም። ከትናንት ጋር አብሮ ላለመቀጠል የሚደረግ ተፈጥሯዊ ትግል የሚፈጥረው ውስጣዊ መነሳሳት ነው ። ይህን መነሳሳት ትርጉም ወዳለው ለውጥ በመቀየር ዛሬን ከትናንት የተሻለ ለማድረግ ከሁሉም በላይ ትናንቶችን በሁለንተናዊ መገለጫቸው በአግባቡ መረዳት እና መግራት ያስፈልጋል።
እንደኛ ያሉ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ያላቸው ፤ በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በብዙ ፈተናዎች ለማለፍ የተገደዱ ሕዝቦች ፤ በየትኛውም መንገድ በውስጣቸው የሚፈጠረውን የለውጥ መነሳሳት ትርጉም ወዳለው ሽግግር ለመለወጥ ትናንቶችን በሰከነ መንፈስ መመርመር ይኖርባቸዋል ።
በተለይም ብዙ የለውጥ የታሪክ ምዕራፎችን በክሽፈት ለማለፍ የተገደዱ ፤በእያንዳንዱ የለውጥ ክሽፈት ትርክት ውስጥ ያልተገባ ዋጋ በመክፈል ፤ ለአስከፊ ማኅበራዊ ቀውስ የተዳረጉ ሀገራት እና ሕዝቦች ፤ ከክሽፈቶች በስተጀርባ ላሉ እውነታዎች ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል ። ከለውጥ ክሽፈት አዙሪት መውጣት የሚችሉትም ይህንን ማስተዋል የሚያስችል ስክነት ሲፈጥሩ እንደሆነ ይታመናል።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ካለን የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ አኳያ አሁን ያለንበት ሀገራዊ ቁመና ታሪካችንን ፤ በታሪካችን ውስጥ ያሳለፍናቸውን የከፍታ ዘመናት የማይመጥኑ ናቸው ። ይህንን ታሳቢ ባደረገ መንገድም በየዘመኑ የነበረው ትውልድ ከነበሩበት ያልተገባ ሀገራዊ እውነታ ለመውጣት በለውጥ መነሳሳት የተለወጠች ሀገር ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል።
እንደ ሕዝብ የተፈጠረው ሀገራዊ የለውጥ መነቃቃት በየዘመኑ በነበሩ ማኅበረሰባዊ ስክነት ማጣቶች በተፈጠሩ ግራ መጋባቶች እና ተስፋ መቁረጦች ሀገር በብዙ ትናንቶች ውስጥ ለመኖር ተገዳለች ። ይህም ሕዝባችንን ዛሬን ከማሳጣት ባለፈ ነገዎቹ ላይ ተስፈኛ እንዳይሆን አድርጎታል።በቀደሙት ዘመናት የተገነባ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲደበዝዝም አድርጓል።
በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ያለ እና የነበረውን የለውጥ ትርክት እንኳን ብንመለከት ፤በብዙ የለውጥ መነቃቃት የተነሳ ትውልድ ሀገሪቱን እንደ ሀገር ከትናንቶች አስፈንጥሮ ለማውጣት የሄደበት የለውጥ መንገድ ያሰበውን እና የተመኘውን ያህል ሀገርን ሊያሻግር አልቻለም። የለውጥ መስዋዕትነት ትርክቱ ከፍያለ ቢሆንም የተከፈለለትን ያህል ሕዝባችንን አልጠቀመም።
እንዲያውም በእያንዳንዱ የለውጥ የታሪክ ምዕራፍ የተፈጠሩ የለውጥ ተቃርኖ አስተሳሰቦች በራሳቸው ተጨማሪ ፈተናዎች በመሆን ፤ በየራሳቸው የሚሰላ የጥፋትን እና የውድቀት ትርክት ይዘው መጥተዋል። ይህም ”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” እየሆነ የሕዝባችን የለውጥ መነሳሳት ትርጉም ያለው የሚጨበጥ ለውጥ ሳያመጣ እንዲኖር አድርገውታል።
ከ1950ዎቹ የሚነሳው ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳት ፤ በ1966 ዓ/ም አብዮት ፤በ1983 ኢህአዴግን ወደ ስልጣን ባመጣው የትጥቅ ትግል ቢሰላሰልም በተጨባጭ ሀገርን ከአንድ የውድቀት የታሪክ ምዕራፍ ወደ ቀጣይ የውድቀት ምእራፍ ከማሸጋገር ባለፈ ሀገርን ከትናንት ተናጥቆ ዛሬ ላይ ማቆም ያስቻለ እና ሕዝባችንን የነገ ባለተስፋ ያደረገ አልነበረም።
ኢህአዴግ ሀገር ያስተዳደረባቸው 27 ዓመታት እንደ ሀገር ማኅበረሰባዊ የጋራ እሴቶችን በተጠናና እና በተደራጃ መንገድ በማጥፋት ሀገር ማብቂያ ወደማይኖረው ግጭት ውስጥ በሚከት የቤት ሥራ ውስጥ የቆየችበት ነው።
ከለውጡ ማግስት እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎችም ከዚህ የትናንት ያደሩ ተግዳሮቶች ምክንያት የመጣ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው ። ለውጡ ተሸክሞት የመጣውን ሕዝባዊ የለውጥ መነቃቃት ወዳልተገባ መንገድ በመውሰድ ሀገርን እንደ ሀገር ፈተና ውስጥ ያስገባውም ይህ የትናንት እውነታ ነው። ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደድነውም ለዚህ ተጨባጭ እውነታ ትኩረት ባለመስጠታችን ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት መሆናችን፣ ብዙ ልንማርባቸው እና ልናርማቸው የሚገቡ መልካም እና መጥፎ ሊባሉ የሚችሉ ተጨባጭ ተሞክሮዎች ባለቤት ነን ፣ ለዛሬ የለውጥ ጉዟችን ስኬት ዋነኛ አቅም ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ያልተገባ ዋጋ የከፈልንባቸው ተሞክሮዎች ባለቤት ነን።
እነዚህን ተሞክሮዎች በሰከነ መንፈስ ተመልሰን በማየት ብቻ የዛሬ ፈተናዎቻችንን መሻገር የሚያስችል አቅም መፍጠር እንችላለን። ትናንቶችን ለለውጥ ተስፋዎቻችን አቅም እንዲሆኑ በመሥራት የግጭት እና የግራ መጋባት ምንጭ መሆናቸውን ልናስቆም እንችላለን ። ለዚህ ግን ከትናንት ከዛሬ እና ከነገዎቻችን ጋር እርቅ መፍጠር የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ስክነት ያስፈልገናል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም