ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸርና በኧርባን ፕላኒንግ (በከተማ ፕላን) በ2000 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቀዋል። የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን በስፔሻላይዝድ ፓሳድ ኢንጂነሪነግ በጣሊያን ሀገር ተከታትለዋል፤ በዚያው በጣሊያን ሀገርም በተመረቁበት ሙያ ሰርተዋል። በኡጋንዳም ሦስት ፕሮጀክቶችን መርተዋል፤ አርክቴክት ቴዎድሮስ ሙሉጌታ። በኢትዮጵያም የደሴና የጅማ ከተሞች ፕላንን ከሌሎች ሲቪል መሐንዲሶችና አርክቴክቸሮች ጋር በመሆን ተከታትለዋል። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ውስጥ በግላቸው እየሰሩ ይገኛሉ። ወጣቱ አርክቴክ የሀገራችን ከተሞች ፕላን በሚስተዋሉባቸው መሠረታዊ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቃለምለልስ ይዘን ቀርበናል። ይከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡-በከተማ ፕላን ላይ ብዙ ሰርተዋል፤ የሙያ መስኮም በዚሁ ላይ የተመሰረተ ነው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና አሁን ያላትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡-አዲስ አበባ ከተማ ሊገመት ባልተቻለ መጠን ስፍታለች። የሕዝቡ ብዛት ጨምሯል። የመሬት አስተዳደርና የመሬት ማግኛዎቹ አሠራሮችና ሂደቶች ተቀይረዋል። ይህም የመሬት ዋጋን የመሬት ቦታ እጥረትን እንዲሁም አዳዲስ ማስፋፊያ ቦታዎች እየሄዱበት ያለውን አቅጣጫ ያካትታል። የቀድሞዎቹ ሦስት የከተማ ማስተር ፕላኖች በአሁኑ አጠራር ስትራክቸራል ፕላኖች ከአለው የከተማው ሶሽዮ ኢኮኖሚክ ለውጥ ጋር እኩል ለመራመድ የተቸገሩበት ሁኔታ ያለ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- የከተማው ፕላን እነዚህን ያልታሰቡትን ለውጦች ለምን ሊሸከም አልቻልም ይላሉ?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- አንደኛው ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት ከሚገመተው በላይ መሆኑ ነው። በዚህም ሳቢያ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ወደ ሁለት አሀዝ (ደብል ዲጂት) የተጠጋበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከተማው እንዲህ ይሰፋል ተብሎ አልተጠበቀም። ለዚህም ዝግጅት አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- ከከተማው ማስተር ፕላን ውጪ የከተማው መለጠጥና መስፋፋት፤ ከፕላን ውጪ የሚሰሩ ቤቶች፤ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ወዴት ሊያመራ ይችላል?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- በከተማው ፕላን ላይ ጊዜያዊ አቀራረቦች ነበሩ። የከተማ ፕላን ብቻውን አይሰራም። የከተማና የሪጅናል ፕላኒንግ እንበለው። አንድ የከተማ ማዕከል ሲሰራ አብሮ የሪጅኑ ይሰራል። አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ከተሜነት (ኧርባናይዜሽን) የመቀየር ዝንባሌ በከፍተኛ ደረጃ ይታያል። ይሄን ድንገተኛ ለውጥ ከተሞቹ መሸከምና አብረው መራመድ አልቻሉም።
ከተሞች ልማታቸው የሚተሳሰረው በአካባቢያቸው ያሉ ትናንሽ ከተሞችን በዙሪያቸው በማድረግ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም በ150 እና 200 ኪሎሜትሮች ሌላ ከተማ በመፍጠር፤ አሊያም ወደከተማ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቆጣጠር በገጠሩ አካባቢ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ሊሆን ይችላል።
ከነዚህ ጋር አብሮ በተያያዘ ማዕቀፍ (ፍሬም ወርክ) ካልሆነ በስተቀር በማስተር ፕላን የተደገፈ የከተማ ልማት ብቻ አሁን የምናየውን የከተሞች እድገት ጥያቄ ሊመልስ አይችልም። የመጀመሪያው ክፍተት የሚመስለኝ የከተማው እድገት በሪጅናል ፕላኒንግ የታገዘ አይደለም። በመርህ ደረጃ ከተማው ሊቀበለው የማይችለው ፍልሰት ሲኖር አካባቢውም አብሮ መልማት አለበት።
ወይንም ደግሞ ፍልሰቱን ባለበት መግታት የሚያስችሉ አማራጮች መታየት (መፈተሽ) አለባቸው። የገጠር ከተሞችን ማስፋፋት፤ የገጠሩን የሥራ ዕድል ማሳደግና መጨመር ሊሆን ይችላል። ዛሬ ተመራጭ ባይሆንም ሶሻሊስት ሀገሮች ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በሕግ እና በፖሊሲ ለመቆጣጠር ሞክረዋል።
ለዚህም የላቲን አሜሪካ ሀገሮች ይጠቀሳሉ። መታየት የነበረበት ከተማው በዚህ ደረጃ የሚሰፋ ከሆነ ከተማ ውስጥ ብቻ በሚደረግ የማስተር ፕላን ጥናት የከተማው እድገት የሚያመጣቸውን ሶሽዮ ኢኮኖሚክ ችግሮች መሸከምና መፍታት አለመቻሉ ነው። የመጀመሪያውን ችግር ስናይ ከተማው እየተገደደያለው ከአቅሙና ሊቀበለው ከሚችለው በላይ እድገት እንዲሸከም እየተደረገ መሆኑ ነው። ፈተናዎቹ እነዚህ ናቸው።
ችግሮቹ በማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲው፤ የገጠር ሥራ ዕድል በመፍጠር፤ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሊፈቱ ይችላሉ። እነዚህ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ የሚከናወኑ ተግባሮች ስለሆኑ በአጠቃላይ የከተማ ፕላን ውስጥ ማካተት ይከብዳል።የከተማው ፕላን ምን ጉድለቶች አሉበት ብሎ መፈተሸም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ሁሉም የከተማዋ ማስተር ፕላኖች ምን ክፍተት ነበራቸው ይላሉ?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- ማስተር ፕላኑ በከፍተኛ ደረጃ የመሬት አቅርቦትን ለመፍታት የሞከረበት መንገድ ወደጎን መስፋፋትንና መሀል ከተማ ላይ ያሉ መንደሮችን ማፍረስ ነበር። ሁለቱ ጉዳዮች በራሳቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የመሠረት ልማት ችግሮችን ይፈጥራሉ።
አንደኛው ወደጎን መስፋቱና መለጠጡ ሲሆን በቅርብ ዓመታት እንደተፈጠረው በማስፋፊያ አካባቢዎች ላይ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄ ችግሮችን ይዞ ሊመጣ ይችላል። ሁለተኛው ችግር ከተማውን ከመጠን በላይ ወደጎን ስንለጥጠው ለሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን የመሠረተ ልማት፤ የትራንስፖርት አቅርቦቶች መስጠት አለብን። እነዚህን ለማሟላት ከፍተኛ በሆነ ደረጃ በውጭ ምንዛሬ፤ በውጭ ኤክስፐርቲዝ፤ በውጭ ኮንትራክተር የሚሰሩ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን ያመጣሉ።
ይሄ ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስለሚጠይቅ የበጀት ጫና ያመጣል። ከተማውን ወደጎን ማስፋት ይቻላል፤ በበቂ ሁኔታ ማኔጅ ማድረግ ግን አይቻልም። ብዙዎቹን የአዲስ አበባ ማስፋፊያ አካባቢዎች ብናያቸው ዋናው አላማቸው ለ10፤15፤20 ዓመታት የመንገድ መሠረተ ልማት በደንብ ያልተሟላላቸው አካባቢዎች እንዲሟላላቸው ማድረግ ነው። ሁለተኛውና ትልቁ ነጥብ ደግሞ አንድን ከተማ በምንሰራበት ጊዜ ወደጎን ሲሰፋ ብዙ ማዕከሎችን መፍጠር ያለብን መሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡-ምን ዓይነት ማዕከሎች ናቸው?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- እነዚህን ሲ. ቢ. ዲ እንላቸዋለን። (ሴንትራል ቢዝነስ ዲስትሪክት) ማዕከላዊ የቢዝነስ ቀጣና ማለት ነው፤ ከተማው ማዕከላዊ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፤ ትላልቅ የንግድ ተቋማት ያሉበትና እርስ በእርሳቸው በትላልቅ መንገዶች የተገናኙ እንዲሆኑ የሚደረግበት ነው። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ አሊ አብዶን የመጀመሪያውን ማስተር ፕላን ብናይ አምስት ያህል ማዕከላዊ የቢዝነስ ቀጣናዎች /ስታዲየም፣ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ እና መገናኛን ያካተተ ሲቢዲ አካባቢዎች ነበሩት። እነዚህ በከተማ ፕላን ውስጥ መልታይ ፖይንት ፎካል ዴቨሎፕመንት ይባላሉ።
አንድን ትልቅ ከተማ ለማልማት ስንፈልግ ከተማውን ሁሉ ለማልማት ስለማይቻል የሚሰራባቸውን አካባቢዎች (ኢንተርቬንሽን ኤርያስ) መርጦ እነዛ አካባቢ ልማት ለማምጣት ይሰራል ማለት ነው። አካባቢው ደግሞ በራሱ መንገድ ልማትን ያመጣል። ከተማው በጣም እየሰፋ ሲሄድ ብዙ ማዕከላዊ የልማት ቀጣናዎች (ሲቢዲ) እየፈለገ ይመጣል። በሁለተኛው የከተማዋ ማስተር ፕላን ላይ 10 አካባቢዎች (ሲቢዲ) ነበሩ። በሦስተኛው ላይ 15 ነበሩ። አሁን አዳዲሶቹ የማዕከላዊ ልማት ቀጣና አካባቢዎች (ሲቢዲዎች) በትክክል እንደ ቀድሞዎቹ ማደግ አልቻሉም። የራሳቸው ብዙ ማነቆዎች ሊኖርባቸው ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ከሕዝቡ ኑሮ፤ ከከተማው መስፋት፤ ከተለያዩ መሠረታዊ ጉዳዮች አንጻር ያለውን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል ብለው ያስባሉ?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- የመጀመሪያው ነጥብ የከተማ ፕላን የምናቅድበትን መንገድ ማስተካከል የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም ብዙ ዓይነት የከተማ ፕላን ናሙናዎች አሉ። አዳዲስ ከተሞችን መገንባት ሊሆን ይችላል፤ ወይንም ሶሽዮ ኢኮኖሚውና የማህበረሰቡ የልቀት ደረጃ ከእኛ ሀገር የተሻለ ከሆነ ደግሞ በትልቅ መጠን ኢንዱስትራላይዜሽንን እየመሰረቱ ይሄዳሉ።
ይሄንን የምለው የምዕራባውያንን ብቻ አይደለም። ብዙዎቹ ሀገሮች በኢንዱስትሪ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱና ከእኛ በጣም የላቁ ናቸው። እነሱ የሄዱበትን መንገድ መከተል ብቻ ለእኛ አዋጪ አይደለም። ኢንዱስትራላይዜሽን ብዙ የሥራ ዕድልና የካፒታል ክምችት ይፈጥራል። የካፒታል ክምችቱ መኖርና ማደግ ከተማ ለማሳደግ ችግር ላይሆንይችላል።
በብድርና ሀገር ውስጥ ከናሽናል ትሬዠሪ በሚገኝ በጀት ለመስራት ሲሞከር የዋጋ ግሽበትና የብድር ጫና ይፈጥራል። ይሄ ራሱን ችሎ የልማቱን ቀጣይነት አጠራጣሪ ሊያደርገው ይችላል። ለመንግሥት ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምን ቢያደርግ ይሻላል ይላሉ?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- እያንዳንዱን ነጥብ በጥናት ተደግፈን ማቅረብ ይገባል። ጥናቶችም ይኖራሉ። እንደ ባለሙያ የምሰጠው ሀሳብ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ባለው የመሬት ባለቤትነት ይዞታ ላይ በተቻለ መጠን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የግለሰብ ባለቤትነትን ማበረታታት ይገባል።
ምክንያቱም የግለሰብ ባለቤትነት የገበያ ፍሌክሰቢሊቲን ይፈጥራል። መሬት በሚገባ ሲገኝ የልማት እምቅ አቅም ይጨምራል። አንደኛው ይሄ ነው። ሁለተኛው መንግሥት ለመሰረተ ልማት የሚያደር ጋቸውን ወጪዎች በተቻለ መጠን በአግባቡ መያዝ (ማኔጅ ማድረግ) እና የተጀመሩ ሥራዎች እንዲያልቁ ለማድረግ መስራት ይኖርበታል። ቀጥሎም የሀገር ውስጥ የበጀት አቅምን በመጠቀም የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ መስራት ያስፈልጋል።
አሁን መንግሥት እየተከተለ ባለው ሞዴል መቀጠል እንኳን ቢኖርብን ቢያንስ የኮንስትራክሽን ዘርፉ (ሴክተሩ) በጣም ግልጽ የአሠራር መርህን መከተል አለበት። የግንባታ ፕሮጀክቶችን በተቻለ መጠን ከብድር ማላቀቅ ይገባል፤ የበለጠ ለመገንባትም የብድር ጫናው ሊቀንስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሁንም ከፍተኛ ብድር እየተገኘ ነው። የብድር ሸክሙን በምን መልኩ ማቃለል ይችላል?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- ብድሩን ለመቀነስ የሚያስችሉ አማራጮችን (ኦፕሽንስ) ማስቀመጥ ያስፈልጋል። አብዛኛውን መንገድ የምንሰራው ከውጭ በሚገኝ ብድር ነው። ባለፉት አስርት ዓመታት በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከፍተናል። ፋብሪካዎቹ በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅማቸው እስከ 30 በመቶ ነው።
የደርባንና የዳንጎቴን ሲሚንቶ ፋብሪካ በቅርብ አውቃለሁ። የማምረት አቅማቸው ከ30—33 በመቶ ነው። እነዚህን ወደ መንገድ ግንባታ ብናስገባና መንገዶቻችንን ኮንክሪት ለማድረግ ብንሞክር መንገዶቹ የአገልግሎት ዕድሜያቸውና ጥራታቸው ይጨምራል። የአውሮፕላን መንደርደሪያውን ካየን በሬንጅ ሳይሆን በኮንክሪት ነው የሚሰራው።
የፋብሪካዎቹ መኖር በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የምናስገባው ሲሚንቶ እንዲቆም ያደርጋል። ከውጭ ከመግዛት ይልቅ ይሄ አንድ አማራጭ ነው። ሁለተኛው የኮንስትራክሽንና ኢንቨስትመንት ሥራዎ ችን ዋና ግብአት ብረት በብዛትና በጥራት ሀገር ውስጥ እንዲመረት ማበረታታት ነው።
በተለይ ለብዙ ዓይነት የኮንስትራክሽን ሥራዎች ወሳኝ የሆኑት ሀገር ውስጥ ያሉ የብረት ፋብሪካዎች በቂ ብረት የማምረት አቅም እያላቸው በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የሚያመርቱት ትንሽ ነው። ጥሬ ዕቃዎችንና በተለይ አይረን ኦር ለማስገባት ዶላር አይኖረንም። ብረት ከውጭ ሀገር ለማስገባት ብዙ ዶላር አውጥተን እናስገባለን። ይህን መሠረታዊ ችግር መፈተሽ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለኮንስትራክሽን ሥራ ወሳኝ የሆነውን ብረት በእርግጥ በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት እንችላለን?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- አይረን ኦሩ ከተገኘ እንችላለን። የተሻለ ከተሰራ ብረቱን ቆፍሮ አውጥቶአይረን ኦሩን አምርቶ ቀጥሎ ብረት ማምረት እንችላለን። እንደዚህ ስትራቴጂክ በሆኑ ሴክተሮች ውስጥ ልክ ሲሚንቶን ለመደገፍ መንግሥት የሄደውን ርቀት ያህል ብረትን ለመደገፍ ቢሰራ ከፍተኛ ለውጥ ይመጣል።
አዲስ ዘመን፡- ከከተማ ልማትና ግንባታ አንጻር ተናበው የማይሰሩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አሉ። ሁሌም አንዱ የሰራውን ሌላው ያፈርሳል፤ ብክነትም ይደርሳል። አዲስ የተሰሩ መንገዶች ብዙ አገልግሎት ሳይሰጡ ይቆፈራሉ፤ ወዘተ.ይሄን እንዴት ያዩታል?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- ጥናቶች ይካሄዳሉ። አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች አሉ። ጥናቶቹ በትልቅ ደረጃ የተሰሩ ሕጋዊ ዶክመንቶች ናቸው። ማስተር ፕላኑ በከተማው ምክር ቤት ገብቶ ከጸደቀ በኋላ ሕጋዊ ዶክመንት ነው። የጥናቶች ችግር አይመስለኝም። የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሥራቸው ለሀገርና ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ ተናበው መስራት ነበረባቸው፤ ይህ ግን እየሆነ አይደለም። ይህም ዋናው ችግር ነው።
እንደ ከተማዋ ነዋሪ ሆኜ ሳየው የመጀመሪያው ችግር ያለው መንገዶች ባለሥልጣን ላይ ነው። ባለሥልጣኑ የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ ማስተር ፕላኑን ሳይከተሉ ቅድሚያ የማይሰጣቸውን መንገዶች እየገነባችሁ ነው የሚል ጥያቄ በተጠናከረ መንገድ ባቀረበበት ጊዜ የወቅቱ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ የከተማውን ማስተር ፕላን መከተል ግዴታችን አይደለም የሚል ትንሽ ግር የሚያሰኝ አስተያየት ሰጥተው እንደነበር አሰታውሳለሁ። እነዚህ መስሪያ ቤቶች በማስተር ፕላን ጥናት ቢሮ ወይንም በከተማ ልማት ቢሮ አንድ ላይ ተናበው መስራት ነበረባቸው። ብቻቸውን ሲሰሩ ከሌላው ጋር አይናበቡም።
እያንዳንዱ መንገድ የሚሰራ ድርጅት ሁልጊዜ ቅድሚያ የሚሰጠው የራሱን ሥራ መስራቱን እንጂ ስለኢኮኖሚ ጠቀሜታውና ተያያዥነት ስላላቸው ጉዳዮች፤ ስለአዋጪነት፤ በጥናቱ ያ መንገድ ሲሰራ ከመሠረተ ልማት ጋር ስለመጋጨቱ ቀድሞ ላያቅድ ይችላል። ችግሩ ይሄ ነው። ታስክ ፎርስ /ግብረ ኃይል/ ይኖራል፤ በዚህ ውስጥ ያሉ አካላት ስብሰባዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ። የመቀናጀት ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ተቀናጅተው ግን እየሰሩ አይደለም፤ በዚህም ሀገርና ሕዝብ ይጎዳሉ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ክፍተት እንዴት ይሞላ?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- አካሄዳችንን መፈተሽ አለብን። እያንዳንዱን ድርጅት ተጠያቂ ማድረግ አይጠቅምም። የሚሻለው ለምንድነው ድርጅቶቹ በዚህ መንገድ የሚሰሩት ብሎ መጠየቅና መፍትሄ ማስቀመጥ ነው።
አንድ ሰው እጁና እግሩ ለየብቻው የሚታዘዝ ከሆነ አንድ አላማ መፈጸም የሚችል አይመስለኝም። እነዚህን ድርጅቶች (መብራትኃይል፤ ውሃ ክፍል፤ ቴሌ፤ የመንገዶች ባለሥልጣንን) በአንድ የተጠናከረ ማዕከል ሰብስቦ ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ ተናበው የሚሰሩበትን መንገድ መፍጠር ይሻላል።
ተቀናጅተው ቢንቀሳቀሱ አንዳቸው የአንዳቸውን ሥራ ሳያፈርሱ ሊሰሩ ይችላሉ። በተጠና ሁኔታ አንደኛው ከፍተኛ በጀት በሚያስፈልገው ጊዜ ሌሎቹ ፕሮጀክቶቻቸውን አጥፈው ለሌላው እያዛወሩ ጥናቶችንም አብረው ቢያሰሩ ብዙዎቹን ችግሮች የማይፈቱበት ሁኔታ አይኖርም። መብራት ኃይል ትላልቅ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለማሳለፍ (ሀይ ቴንሽን ላይኖችን) ትላልቅ ታወሮች ያቆማል። ለዚህም ብዙ ቦታ ይፈልጋል፤ እነዚህን ከመንገድ ፕላን፣ ከውሃ፣ ከፍሳሽ፡ ከቴሌ መስመር ጋር አቀናጅተው አብረው ቢሰሩ ከፍተኛ ለውጥ ይመጣል።
አዲስ ዘመን፡-ይሄንን የሚቆጣጠር መንግሥታዊ ማዕከል የለም?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- በመርህ ደረጃ እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች በከተማው አስተዳደር ወይንም በከንቲባው ስር ናቸው። ለምሳሌ ውሃና ፍሳሽን ብናይ በ150 ሚሊዮን ብር የሁለት ኪሎ ሜትር የውሃ ፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ሥራ ሊኖረው ይችላል። ከበጀቱ አንጻር በጣም ትንሽ ነው። ከሚያደርሰው ጥፋት አንጻር ደግሞ የያዘው ሥራ ትልቅ ነው።
በማዕከል ደረጃ እያንዳንዳቸው 70 እና 80 ፕሮጀክቶች የያዙ ድርጅቶችን ስታይ ፕሮጀክቶቹን ማቀናጀት በጣም ይከብዳል። የተሻለ የሚሆነው የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባለው መዋቅርናአደረጃጀት ውስጥ ራሳቸውን የቻሉ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ ዘርፍ ተፈጥሮ ፕሮጀክት ከመተግበሩ በፊት እየተናበቡ ቢሰሩ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፤ ይህ ሲሆን ወጪም ይቀንሳል።
አዲስ ዘመን:- በሌሎች ሀገሮች የመንገድ ሥራ ጨረታዎች ከከተማ ፕላን አንጻር እንዴት ነው የሚካሄዱት?
አርክቴክት ቴዎድሮስ:- እኔ በነበረኝ የውጭ ልምድ ሌላ ሀገር መንገድ ለመስራት ሁለት ጨረታ ብቻ ነው የሚወጣው። የመጀመሪያው ጨረታ ዩቲሊቲስ (መብራት፣ ውሃ ፍሳሽ፣ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ መስመሮች) ካሉበት ወደ ዳር የማውጣት ሥራ ነው። እነዚህን ለመንገድ ከሚፈለገው ቦታ ውጪ ለማድረጉ ሥራ ብቻውን ጨረታ ይወጣል። ከአንድ ዓመት ሁለት ዓመት በፊት ያ ጨረታ ወጥቶ ቦታ ይቀየርላቸዋል፤ በመቀጠል መንገዱን መስራት ይጀመራል። እኛ የምንጀምርበትን መንገድ ስናይ ከመንገዱ ጋር አብሮ የሚያያዘው ይዞታ ማስከበር፤ ዩቲሊቲዎችን የማንሳትና እንደገና ሌላ ቦታ የመትከሉ ሥራ በሙሉ ለየብቻቸው ይከናወናሉ። የጣሊያንን ስለነበርኩበት አውቃ ለሁ። በአውሮፓ ደረጃ 200 ዓመት አካባቢ የከተማ ልምድ ያላቸው ሀገሮች ለምንድነው መንገድ የመስራትና የመንገድን ጨረታ ብቻውን የሚያደርጉት የሚለውን ማየት ይጠቅማል።
እንደ እስራኤል ያሉ ሀገሮች መንገድ ሲሰሩ ለዩቲሊቲ ለብቻው ጨረታ ያወጣሉ። ሥራው ይሰራል። መንገድ ሥራውም ቀድሞ ያልቃል። ይህን የመሰለ አሠራር መከተል ይኖርብናል። ዋናው ግን በአንድ ማዕከል መቀናጀት፤ ተናቦ መስራት ነው፤ ይህም ውጤታማ ያደርጋቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በኮንስትራክሽን ዘርፍ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሲሰሩ የቤት ችግርን ከመፍታት አኳያ በይድረስ ይድረስ ስለሚሰሩ ጥራት የላቸውም፤ መሠረታዊ አገልግሎት ይጎድላቸዋል የሚሉ አሉ። ይህን እንዴት ያዩታል?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡-ችግሮቹ ከተለያየ ምንጭ ነው የሚቀዱት። የመጀመሪያው ከከተማ ፕላን፣ ሁለተኛው ከግንባታ ጥራት ጉድለት፣ ሦስተኛው ሕንፃዎቹ ከሚታቀዱበትና ከሚሰሩበት መንገድ፣ አራተኛው ከሰፈራ አካሄዱ ሊሆን ይችላል። በየደረጃው የተጠረቃቀሙ ችግሮች ናቸው አፍጠው የወጡት። 500 ሺ ተጨማሪ ቤቶችን አጠቃላይ ከ700 ሺ ላያንስ ይችላል ለመስራት ስናስብ ይሄንን ለመስራት መነሳት በየትኛውም ሀገር ደረጃ አቅም ቢሆን በጣም ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ከባባድ ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉ ማመን ጥሩ ነው።
ትልቅ ስኬት ብለን ልንቆጥረው የምንችለው መጀመሪያ እነዚህ ቤቶች በሚሰሩበት ወቅት በቂ አማካሪ፤ በቂ የምህንድስና፣ የግንባታ ድርጅቶችና ባለሙያዎች አልነበሩንም። ይህን ክፍተት በተወሰነ ደረጃ ለመሙላት ሲባል መንግሥት የሄደበት አቅጣጫ ጥሩ ነው። የግዢ ሥርዓቱን ከጊዜ በኋላ ማዕከላዊ ለማድረግ (ብረት፣ ሲሚንቶ፣ወዘተ) መሞከሩም ጥሩ ነው። እንደ ባለሙያ እነዚህ ቤቶች በመንግሥት ደረጃ መሰራታቸው ይገርመኛል። አንድን ቤት ሰርቶ ማስረከብን ስናይ የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ፈተና መሬቱን ለልማት ዝግጁ ማድረግ ነው።
ይሄ ታልፎ መሬቱ ለግንባታ ከተዘጋጀ በኋላ የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት በጣም ብዙ የጨረታና የግዢ ሂደቶች አሉ። የምንገዛው ከአንድ ተቋራጭ (ኮንትራክተር) አይደለም። የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ለመቆጠብም ቢፈለግ ግዢው በማዕከል ደረጃ ነው የሚደረገው። እነዚን ሁሉ ግዢዎች እንደ መንግሥት መምራት ይከብዳል። ብዙ ጊዜ ሙስና (ኮራፕሽን ) ሌላው ደግሞ የብቃት ችግርም ይፈጥራል። የዋጋ ንረት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት እኛን በመሰለ ሀገር ላይ ፕሮጀክትን ማቆየት ማለት የፕሮጀክቱን ዋጋ እጥፍና ከዚያ በላይ ማስኬድ ማለት ነው።
የመጀመሪያው ስህተት የሚመስለኝ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ውስጥ መግባት አልነበረበትም። መንግሥት ቢቻል መሬቱን እስከማቅረብ ቢደርስ የግንባታ አቅርቦቶችና የተወሰኑ የውጭ ምንዛሬ ድልደላዎችን ማድረግ ቢችል መልካም ነው። የግዢ ፕሮኪዩርመንትን በተመለከተ አንድ ግለሰብ በግማሽ ቀን ከተማው ውስጥ ያለውን የብረት ዋጋ ዞሮ ሊያውቅ ይችላል። ያንን ተመርኩዞ ርካሹን ወይንም አዋጪውን (ሁልጊዜ ርካሹ አዋጪ ላይሆን ይችላል) ውሳኔ ሊወስን ይችላል።
እነዚህን ማድረግ ያልተቻለው ሥራው በመንግሥት ማዕከል ስለሚመራ ነው። መንግሥት በመንግሥት የግዢ ሕግ ስለሚገዛ እዚህ ውስጥ ገብቶ ውጤታማ መሆን አይችልም። እስከ መሬት ማቅረብ ሄዶ ከዚያ በኋላ ያለውን በፖሊሲ ድጋፍ፣ በፋይናንስ፣ በታክስ ቅነሳና በመሳሰሉት መንገዶች ኮንዶሚኒየም ገንቢዎችን ቢያግዝ ይሻላል። እነሱን አግዞ ከመሬትና ሕንፃ ነጋዴ ደላላዎች መጠበቅ ከቻለ አንድ ኮንዶሚኒየም ቤት ለመስራት ቤት ሰሪዎች ቢተባበሩ ከመንግሥት በተሻለ ሁኔታ ሰርተው ሊጨርሱት ይችላሉ። እነሱን ማበረታታት ሁለተኛው ደግሞ ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ባለቤቶች የሚገነቡበትን የፖሊሲ ማዕቀፍ ማስቀመጥ ይሆናል። የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አቅጣጫ እየሄደ መሆኑን የተወሰኑ አመላካች ሁኔታዎች አሉ።
በዚህ መንገድ መጨረስ ከተቻለ ጥሩ ነው። መንግሥት በራሱ መገንባትን ትቶ ከመሬት አቅርቦት በኋላ ያለውን ነገር በባለቤቶች እንዲገነባ ቢያደርግ ውጤቱ ከፍተኛ ነው። የመሬት አቅርቦቱ ችግር ካልተፈታ ባለቤቶቹ ቦታ ይዘው ተንሳፈው ሊቀሩ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡- በከተማ ፕላን እቅድ የአዲስ አበባን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት የሚቻለው በምን መልኩ ነው?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- በደሴና በጅማ ከተማ ስትራክቸራል ጥናት ላይ ተሳትፌአለሁ። በተለይ በደሴ ያየናቸውንና ከተማውም ላይ የተደረጉትን እንደ ግብአት ይዤ መናገር የምችለው የመጀመሪያው ጉዳይ የከተሞችን ፕላን ለመለወጥም ሆነ ለማሻሻል ከዚህም ጋር የተሳሰረውን የሕዝቡን ችግር ለመፍታት በጣም ሰፊና የተለያዩ ባለሙያዎችን የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን ነው። የሶሽዮ ኢኮኖሚክ ጥናት፣ የፖሊሲ ድጋፍ፣ ቁርጠኝነት፣ የብዙ ሀገር ሞዴሎችን ማየት መፈተሽ ይፈልጋል።
ከተማውን ስለማስተካከል ስናስብ ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ነገር በትንሹ የ10፣ የ15፣ የ20 ዓመት እቅድ ነው የሚሆነው። በከተማ ደረጃ በአንዴ ማስተካከል የሚባል ነገር የለም፣ አይቻልም። ማስተር ፕላኑን ጥሩ ለማድረግ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ማሳተፍ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አርክቴክትና የከተማ ፕላን ባለሙያ ስለሆኑ በእርስዎ እምነት ጥንታዊ ከተሞች መጠበቅ ወይስ መፍረስ ነው ያለባቸው?
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በልማት ስም ብዙ ጥንታዊ ከተሞች አፍርሰናል። ትልቅ ስህተት ነው። ለ60 እና 70 ዓመት የተኖረበትን አካባቢ ማፍረስ ጥሩ አማራጭ አይደለም። ለማልማት እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች ናቸው በመልሶ ማልማት ይያዙ የሚባለው።
መልሶ ማልማት በሚሰራበት ደረጃ አንድ አካባቢ በሙሉ መፍረስ ሊኖርበት ይችላል። ግን ሌላ አማራጭ አለ። እዛው አካባቢ መንገድ ማውጣት ፤ መሠረት ልማት ማስፋፋት፤ ውሃ እንዲገባ ማድረግ ይሻል ነበር። ሕዝቡን ከማፈናቀል የአካባቢውን የመሬት ዋጋ ሕዝቡ እንዲቀበለው በማድረግ ሕንፃዎችን መጠገን፣ መጸዳጃ ቤቶችን መስራት፣ የውሃ መስመር መዘርጋት ይሻል ነበር። እነዚህ ሥራዎች የአካባቢውን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደርጋሉ።
ሁለተኛው ትውልድ በማልማቱም ይሆናል እድገቱ የመጣው። ጥንታዊ ሰፈሮችን ከተሞችን ከማፍረስ ይልቅ ኢንተርቬንሽን ነው መደረግ ያለበት። በጣም የወደቁትን የመሠረተ ልማት መዋቅሮች በማስተካከል የከተማውን ደረጃ ከፍ ማድረግ ይቻላል።
ኒውዮርክና ማንሀተን በዚህ መንገድ ነው የተገነቡት። ማንሀተን ከተማ ከነዶናልድ ትራምፕ ሆቴሎች ጀርባ 2 ብሎክ ወደኋላ ድሆች በ500 እና 600 ዶላር ተከራይተው በአሮጌ አፓርትመንቶች ውስጥ ይኖራሉ። በዚህ ደረጃ ነው የሚለማው። የከተማ መልሶ ማልማትን ሥራ ሶሻሊስቶች ሞክረውት አልተሳካም፤ ለድሀ ሀገር አይሆንም። ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ አደጋ ጭምር ያስከትላል። በትንሹ በኖረበት አካባቢ ከኅብረተሰቡ ጋር ባለው ቅርርብና ቁርኝት ሰርቶ የሚኖርን ሰው ከቦታው ስታፈናቅለው ካሳ ብትሰጠው እንኳን ሌላ ቦታ ሄዶ መስራትና መኖር አይችልም።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለምልልሱ ላደረጉልን ትብብር እናመሰግናለን።
አርክቴክት ቴዎድሮስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
ወንድወሰን መኮንን