የኮረና ቫይረስን ለመከላከል መንግስት ሀገር አቀፍ ግብረ ሀይል በማቋቋም የተለያዩ እርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል። የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን በማውጣት ህዝቡ እንዲተገብራቸው እያደረገ ነው። ህዝቡም አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩበትም፣ እነዚህን ምክረ ሀሳቦች ተቀብሎ እየተገበረ ነው፤ በሆነ መልኩ ለውጥ እንዳለም መግለጽ ይቻላል። የኮረናን ጉዳይ መንግስትና የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ሊይዙት የሚገባ ተግባር አይደለም።
የሁሉንም ትብብርና ርብርብ የሚጠይቅ እንጂ! መንግስት ምክረ ሀሳቦች በአግባቡ እንዲተገብሩ ከማሳሰብ በተጨማሪ በአፈጻጸማቸው ላይ ክትትል እና ግምገማ እያደረገ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአግባቡ የተከናወነና ያልተከናወነ እየለየ መከናወን ባለባቸው ላይ ተጨማሪ እርምጃ መውሰዱን ተያይዞታል። እያንዳንዱ ዜጋ ምክረ ሀሳቦቹን በመፈጸምና ሌሎችም እንዲፈጽሙ ለማድረግ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይኖርበታል። ህዝቡም አሁንም ምክረ ሀሳቦቹን በአግባቡ ለመተግበር በሁሉም መስኩ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ለመቋቋም መንግስት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገ ነው። ኮሮና የጤና ችግር ብቻ አይደለም። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግርንም ያስከትላል፤ እያስከተለም ይገኛል። መንግስት ይህን አስቀድሞ በመገመት ህብረተሰቡ ፣ባለሀብቶች ድርጅቶች ኮረናን የመከላከል ርብርብ እንዲቀላቀሉ ጥሪ እያቀረበም ነው። ይህን ተከትሎም ባለሀብቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ ህብረተሰቡ ወዘተ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ።
ቤታቸውን፣ ተሽከርከሪያቸውን፣ ህንጻዎቻቸውን ወዘተ መንግስት ለበሽታው መከላከል እንዲጠቀምባቸው እየሰጡ ናቸው። ይህ ምላሽ ሊበረታታ የሚገባው የክፉ ቀን ደራሽ ተግባር ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል ይኖበታል። ህብረተሰቡ ምንም እንኳ የራሱ ገበና ቢኖረውም አንዱ የአንዱን ገበና አያውቀውም ሊባል አይችልም፤ አሳምሮ ያውቀዋል። የአዲስ አበባን ህዝብ እንኳ ለአብነት ብንወሰድ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ የሆነበት እጅግ በርካታ ነው፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ።
በእለት ስራ በልተው የሚያድሩም በርካቶች ናቸው። ጠጉራም ውሻ አለ ሲሉት በራብ ይሞታል እንደሚባለው አላቸው ብለን የምናስባቸው ራሳቸው በእንዲህ አይነቱ ቀን የላቸውም። በሽታው በዓለም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰራተኞች መሰናበት ምክንያት እየሆነ ነው። ምንም እንኳ በሀገራች ከችግሩ ጋር በተያያዘ በይፋ ከስራ የተፈናቀለ ስለመኖሩ መረጃው ባይኖርም፣ ሰራተኞች ላይ ጫና ሊኖር ስለመቻሉ መገመት አይከብድም። ሆቴሎች፣ ካፍቴሪያዎችና እና የመሳሰሉት በከፊልም ይሁን ሙሉ ለሙሉ ሲዘጉ ሰራተኞች አይጎዱም ተብሎ አይታሰብም።
ከደንበኞች የምትሰጥ ጉርሻ በስንቶች ህይወት ላይ ለውጥ እንደምታመጣ ይታወቃል። ተመሳሳይ ችግር በየዘርፉ በሚንቀሳቀስ ህብረተሰብ ውስጥ ይስተዋላል። መንግስት ይህን ቀውስ በመገንዘብ ህብረተሰቡ የከፋ ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ በሚል በጀት መድቦ እየሰራ ነው። ለህብረተሰቡ የሚያስፈልገው ድጋፍ ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ችግሩን ለመቋቋምና ይህን ክፉ ቀን ለማለፍ የመንግስት በጀት እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። ይህን ችግር ለመፍታት ህዝቡ በሚችለው አቅሙ ለችግር ሊጋለጡ የሚችሉ ዜጎቻችን በተደራጀም ይሁን በተናጠል ለመደገፍ መዘጋጀት ይኖርበታል።
ይህም ህገወጥ ግብይት የሚፈጽሙ አካላትን ከማጋለጥ አንስቶ ተካፍሎ እስከ መብላት ድረስ ሊዘልቅ ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ቢያንስ አንድ ቤተሰብ ለመደገፍ መዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ ያስገነዘቡትም ይህንኑ ያመለክታል። ይህ ክፉ ቀን ያልፋል። ተመሳሳይ ክፉ ቀናት እየመጡ አልፈዋል፤ እኛ ደግሞ በዚህ ልክ ባይሆንም በግጭትና በመሳሰሉት ጊዜያት ሁሉ ተካፍሎ በመብላትና በመጠጣት እና በመደጋገፍ ተመሳሳይ ቀናትን ስናሳልፍ ኖረናል።
በዚህ ወቅት የሚያስተዛዝብ ተግባር መፈጸም የለበትም። ነጋዴ ከሚገባው በላይ ጥቅም መፈለግ የለበትም፤ ሸማቹም ከሚያስልገው በላይ ሸቀጣ ሸቀጥና የግብርና ምርቶችን ማከማቸትም የለበትም። አይቶ እንዳላየ ማለፍም አይገባም፤ ማጋለጥ ይገባል። አሁን ተረባርቦ ኮረናን መከላከል የግድ ነው። ይሁንና እዚህ ላይ ሊተኮርበት የሚገባው ዋና ጉዳይ ለመርዳትም ሆነ ለመረዳት ቅድሚያ ራስን መጠበቅ እንደሚገባ ነው።
አርግጥ ነው አሁን ላይ ኮሮና ምንም ዓይነት መድሃኒትም ሆነ መከላከያ ክትባት አልተገኘለትም። ይሁንና ከዚህ ቀደም እንደተከሰቱት ወረርሺኞች በጊዜ ሂደት መድሃኒትም ሆነ ክትባት እንደሚገኝለት ጥርጥር የለም። ይሁንና ይህ ሂደት ላይ እስኪደረስ ብቸኛው የመፍትሄ መንገድ ጥንቃቄና ጥንቃቄ ብቻ ነው። አበው ሲትረቱ የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ ይላሉ። መልዕክቱ ከትንሽ ጊዜ በኋላ በሚቆም ዝናብ መመታት የለብህም ትንሽ ታግስህ ታልፈዋለህ የሚል ነው። ኮሮናም እንዲሁ የሚያልፍ ችግር ነው ስለሆነም አሁን ላይ ባለመጎዳት ጠንቀቅ ብለን ልናሳልፈው ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012