ኢትዮጵያን በመወከል በቶታል ካፍ የ2018/19 የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ጅማ አባጅፋር ዛሬ የሞሮኮ አቻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም 10 ሰዓት ላይ ይገጥማል።
የጅማ አባጅፋር ተጋጣሚ የሞሮኮው ሀሳኒ አስ አጋዲር ተጫዋቾች አዲስ አበባ ገብተው ልምምዳቸውን እያከናወኑ ይገኛል። ጨዋታውን ለመዳኘት የተመደቡ ዳኞችን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል። በዚህም የመሃል ዳኛ በመሆን ጨዋታውን የሚመሩት የማሊ ዜግነት ያላቸው ኢንስትራክተር ቦቡ ትራወሬ ሲሆኑ፤ በመጀመሪያ የመስመር ረዳት ዳኛነት ኢንስትራክተር ባባ ዮምቦሊባ እንዲሁም በሁለተኛ የመስመር ረዳት ኢንስትራክተር ድሪሳ ካሞሪ ኒያሪ ናቸው። በአራተኛ ዳኛነት ጎይሱ ሰይቦ ካኔ ሁሉም ከማሊ ተመርጠዋል። የጨዋታው ኮሚሽነር ለመሆን ደግሞ በብቸኝነት ከኬኒያ ኮሚሽነር ሲልቬስተር ኪራው ተመርጠዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን አራት ሀገራት ይካፈሉበታል ተብሎ በሚጠበቀውና በአሥመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ‹‹የሠላም እና የወዳጅነት ዋንጫ›› ላይ እንደሚሳተፍ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማረጋገጫ ሰጥቷል በማለት ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገፁ ላይ ዘግቧል።
በየካቲት ወር በአሥመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደውና በኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ወጣት ቡድኖች መካከል በሚደረገው ‹‹የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ›› ላይ የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን እንደሚሳተፍ ቀደም ብሎ ሲገለጽ የቆየ ቢሆንም ማረጋገጫ ሳይገኝ ቆይቷል። የአራቱን አባል ሀገራት ወዳጅነት እና የዞኑን የእግር ኳስ ትስስር ለማጠናከር ታስቦ ለመጀመርያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደሚካፈል እና ከቀናት በኋላ ዝግጅት እንደሚጀምር ተነግሯል።
ድረ ገፁ ከፌዴሬሽኑ አገኘሁት ባለው መረጃ ከሴካፋ ውድድር ብሔራዊ ቡድን ቀርቶ በአሥመራ በሚካሄደው የሠላም እና የወዳጅነት ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል። ከሴካፋ ውጪ የሆነውም የውድድር መደራረብ እንዳይፈጠር በማሰብ ነው። በተጨማሪም ሴካፋ የውድድሩን መርሐ ግብር እንደፈለገ የሚቀይርና ውድድሩን የሚያካሂድበት ቦታ እና ጊዜ በይፋ ግልጽ ባለማድረጉ ሌላ ምክንያት እንደሆነ ተረጋግጧል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
ዳግም ከበደ