በዓለም ዙሪያ ያሉ ሳይንቲስቶችና ተመራማ ሪዎች ዓለምን አስጨንቆ ስጋት ላይ የጣለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መድኃኒትና ክትባት ለማግኘት የተለያዩ ሙከራ ዎች እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህም አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። በሳይንስ አምዳችን ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ያገኘናቸው ሳይንሳዊ ውጤቶችን በዚህ መልክ አቅርበናል።
ቱኒዚያ 18 በላይ ሰዎች የገደለባትን ወረርሽኝ ለመግታት እንቅስቃሴ ገድባለች። የምግብ የህክምና አሊያም አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ነዋሪ ከቤት መውጣት አይችልም። ይህን ለመቆጣጠር የሀገሪቱ ፖሊስ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ሮቦት በመዲናዊ ቱኒዚያ ማሰማራቱ ተገልጿል። ሮቦቱ ልክ እንደ ፖሊሲ ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን መገደብ አለመገደባቸውን ይቆጣጠራል።ጭር ባሉበት ጎዳናዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ ከተመለከተ ወደ ግለሰቦቹ በመቅረብ ለምን ከቤት እንደወጡ ይጠይቃል።
ሰዎቹም መታወቂያቸውን እና ሌሎች የፈቃድ ወረቀቶችን ወደ ሮቦቱ ካሜራ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ፖሊሶች ካሉበት ሆነው መቆጣጠር ያስችላቸዋል ማለት ነው። ባለ አራት እግሩ ሮቦት መብራት በመጠቀም እንደራዳር መቆጣጠሪያ ይሰራል። አንዳንዶች ሮቦቶችን መጠቀም ያደነቁ ሲሆን ሮቦቱ በዝግታ እንደሚንቀሳቀስ በመጥቀስ ውጤታማ ላይሆን እንደሚችል የገመቱም አሉ። ሮቦት ሰዎችን በማስቆም ሲጠይቅ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ተሰራጭቷል።አንድ “የሰው እንቅስቃሴ ተገድቧል ግን ሲጋራ መግዛት ፈልጌ ነው” ሲል ለሮቦቱ የመለሰለት ሲሆን “እሺ ሲጋራህን ግዛና በፍጥነት ወደ ቤትህ ተመለስ” በማለት ሮቦቱ ሲያስጠነቅቅ ያሳያል።
ሌላኛው በዩናይትድ ኪንግደም ተስፋ የተጣለበት የኮሮናቫይረስ መድኃኒት ሙከራ መጀመሯ መሰ ማቱ ነው። በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የኮሮና ቫይረስን በሽታ የሚከላከል መድኃኒትም ሆነ ክትባት ሰፊ ጥረቶች ቢደረጉም እስካሁን ግን ውጤት አልተገኘም። የዓለም አቀፍ ሙከራው አንዱ አካል የሆነና ተስፋ የተጣለበት የመድኃኒት ሙከራ በዩናይትድ ኪንግደም ተጀምሯል።
በመንግሥት የተለየው ይህ ጥናት በመጀመሪያው ዙር 15 ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ማዕከሎችን ያካትታል ተብሏል። ‘ሬምደሲቪር’ የተባለውና ጊሌድ በሚባለው የመድኃኒት አምራች ኩባንያ የሚ መረተው መድኃኒት ነው የኮሮናቫይረስን ሊከላከል ይችላል ተብሎ በዩናይትድ ኪንግደም ሙከራው የተጀመረለት። በዚሁ መሰረት በዩናይትድ ኪንግደም ሁለት መድኃኒቶች ሙከራ ላይ የሚውሉ ሲሆን አንደኛው በሽታውን በመካከለኛ ደረጃ ያጠቃቸው ሰዎች ላይ ይሞከራል፤ ሌላኛው ደግሞ በጽኑ የታመሙ ሰዎች ላይ የሚሞከር ነው። በቻይናና አሜሪካ ሙከራዎች በሂደት ላይ ሲሆኑ በሚቀጥለው ሳምንት የመጀመሪያው የሙከራ ውጤት ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። በዩናይትድ ኪንግደም የሚካሄደው ሙከራ፤ የተላላፊ በሽታዎች አማካሪ በሆኑት ዶክተር አንድሪው ኡስቲያኖውስኪ የሚመራ ሲሆን ለጊዜው የሙከራ አድማሱ በእንግሊዝና ስኮትላንድ ብቻ የሚወሰን ይሆናል።
ጸረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ጊሌድ የጸረ-ቫይረስ መድኃኒቶችን በማምረት የታወቀ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ነው። ዶክተሩ ባለፉት ሳምንታት በሽተኞችን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን፤ በሽታው በታማሚዎች ላይ የሚያመጣውን ስቃይ በቅርበት ሆነው ተመልክተዋል። “የምንፈልገውና የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር፤ የኮሮናቫይረስን የስርጭት መጠን የሚገታ፣ ታማ ሚዎችን የሚፈውስና ሰዎችን የመዳን ተስፋ የሚያሳ ድግ መድኃኒት ነው” ያሉት ዶክተር አንድሪው “ይህ መድኃኒት በላቦራቶሪ በጣም ተስፋ ሰጥቶናል፤ በሰው ላይ ሲሞከርም ተስፋችን እውን እንደሚሆን አምናለሁ” ብለዋል።
እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች ለተመራማሪዎቹ ትልቅ ተስፋ እንደሆነ በመነገር ላይ ነው። “ልቤ በተስፋ ተሞልቷል፤ ነገር ግን መድኃኒቱ እንዴት በአግባቡ ሊሰራ እንደሚችልና በተሻለ ሁኔታ ልንጠቀምበት የምንችልበትን መንገድ ለማረጋገጥ ግን በደንብ መስራትን ይጠይቀናል” ብለዋል። የመድኃኒት አምራች ኩባንያው የዩናይትድ ኪንግደምና የአየርላንድ ሥራ አስኪያጅ ሂላሪ ሀተን ስኳይር እንዳሉት ደግሞ አሁን ሙከራው የተጀመረለት መድኃኒት፤ ሙከራው ከ10 ዓመት በፊት ተጀምሮ በሥራ ላይ የነበረ ነው።”ለዓመታት እየተፈጠሩ ያሉ ቫይረሶችን ምናልባትም አሁን ጉዳት ማድረስ ያልጀመሩ ነገር ግን ወደፊት ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ቫይረሶችን ታሳቢ በማድረግ ላለፉት አሥር ዓመታት ስንሰራ ቆይተናል” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።
“በዚህ ረገድ ኮሮናቫይረስ እኛ ከለየናቸው የቫይረስ አይነቶች ጋር የሚመደብ ነው። ምክንያቱም ከእንስሳት ወደ ሰው በሚሸጋገርበት ወቅት ልክ እንደ ሳርስ እና ሜርስ ቫይረሶች ሁሉ ትልቅ ችግር የሚፈጥር ነው” በማለት ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል። “ሬምደሲቪር መድኃኒት ለሳርስ እና ሜርስ ቫይረሶች ብለን ያበለጸግነው ነበር፤ ጥሩ ውጤትም ነበረው፤ ለዚያም ነው አሁን ለኮቪድ-19 ሊሰራ ይችላል ብለን በድጋሚ እየሞከርነው ያለው” ብለዋል። የመድኃኒት ሙከራው በፍጥነት ተጠናቆ አገልግ ሎት መስጠት እንዲጀምር መንግሥት ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ የእንግሊዝ የመድኃኒትና የጤና መጠበቂያ ምርቶች ቁጥጥር ባለስልጣንም ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነቱን ገልጿል።
“ለሳይንሳዊ ምክሮች ሚሆን ፈጣን ሂደቶችን፣ ዳሰሳ የማድረግና ቶሎ የማረጋገጥ እንዲሁም ለኮሮናቫይረስ ለሚሰጠው አገልግሎት ፈጣን አሰራ ሮችን አስቀምጠናል” ብለዋል ዶክተር ሲዩ ፒንግ ላም። ሬምደሲቪር ለኢቦላ ሕክምና ተስፋ ያለው መድኃኒት እንደነበር ተነግሯል። መድኃኒቱ ምላሽ የሚሰጠው ቫይረሱ እራሱን በሚያራባበት ወቅት ነው፤ በዚህ ምክንያትም ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ የሚያደርገውን የመባዛት ሂደት ያስቆመዋል ማለት ነው። አሁን ምንም ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ባለመኖሩ ብዙው ሰው ተስፋ የሚያደርገው የሙከራ ሂደቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቅና ማረጋገጫ እንዲያገኝ ነው። የአሜሪካ ተመራማ ሪዎች የወባ በሽታ መድኃኒት የሆነው ክሮሎኪን የኮሮናቫይረስንም መከላከል እንደሚችል ለማረጋገጥ በሂደት ላይ እንደሆኑ መነገር ከተሠማ ቀናት ተቆጥረዋል።
ምንጭ፡- ቢቢሲ አማርኛ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2012
ወርቅነሽ ደምሰው