ጎበዝ ይሄን ነገር እንደቀላል እንዳታዩት፡፡ በእርግጥ እኔም እንደቀላል ነበር ሳየው የቆየሁ፡፡ ኧረ እንዲያውም አሁን ራሱ ስፈራ ነበር፡፡ እንዴት ስንት የጥናትና ምርምር ሥራ እያለ ሰው ስለመጸዳጃ ቤት ይጽፋል እያልኩ ነበር፡፡ ሳስበው ሳስበው ግን ያጽፋል፡፡ ለነገሩ ጥናትና ምርምር ተብለውም ከመጸዳጃ ቤት ጽሑፍ የማይሻሉ አሉ፡፡
ውይ አንዳንድ ጥናት እንዴት እንደሚሰለቸኝ! በጣም ግልጽ የሆነን ነገር እንደትልቅ ግኝት ተደርጎ ይወራል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አቀራረባቸው፡፡ የተሰጠው 30 ወይም 20 ደቂቃ ይሆንና ሁሉም መግቢያው አካባቢ ያልቃል፡፡ የጥናቱ የአሠራር ዘዴ፣ የናሙና መረጣ…. እነዚህ እነዚህ እኮ ለጥናቱ (ለወረቀቱ) እንጂ መድረክ ላይ ባይቀርቡ ምን ችግር አለው? የሚፈለገው ግኝቱ አይደል? ለነገሩ አዲስ ግኝት ከሌለው መቼስ ምን ይደረጋል!
የመጸዳጃ ቤት ጽሑፍን ከጥናት ጋር አገናኘሁት አይደል? አትናቁት ብያችኋለሁ፡፡ ስንትና ስንት የፈጠራ ሃሳብ ያለበት ነው፡፡ ቆይ ግን ሰው ሃሳብ የሚመጣለት መጸዳጃ ቤት ውስጥ ነው እንዴ? ሳስበው ግን ደራሲዎች ራሱ የመጽሐፋቸውን ሃሳብ የሚያገኙት ከደመናማ ቀን ይልቅ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይሄን ነገር ግን ያለውን የተፈጥሮ ትስስር ምሁራን ሊነግሩን ይገባል፡፡ እኮ የመጸዳጃ አካላት ከአዕምሮ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው? ወይኔ ሳይንቲስት በሆንኩ!
ለዚህ ይሆን ግን አንዳንድ ሰዎች እኮ ‹‹መጸዳጃ ቤት ልሂድ›› ለማለት ‹‹እስኪ ትንሽ ልመሰጥ›› የሚሉ አሉ፡፡ ይሄ ነገር እንደመዝናኛም ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ ምን ዋጋ አለው የከተሞቻችን መጸዳጃ ቤት እንኳን የሚመሰጡበት የሄዱበትን የተፈጥሮ ጥሪም ሳያስተናግዱ የሚመለሱበት ነው፡፡ እዚያ ውስጥ የሚዝናና ካለ ይሄ ሌላ ተፈጥሮ ነው፡፡
እኔ ግን አንድ የምጠረጥረው ነገር(ባካችሁ እንደ ጥናት ያዙልኝ) በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ በጣም የዋከብን ነን ማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት ተረጋግተን የምናስብበት ጊዜ የለንም ማለት ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው አንድ ነገር ስንሠራ አያይዘን ሌላም ነገር እየሠራን ነው፡፡ ለምሳሌ ስልክ እንኳን ስናወራ በጉንጫችን አስደግፈን እየሠራን ነው፡፡ የቢሮ ሥራ ከሆነ ‹‹ማውዝ›› ይዘን፣ ሱቅ ውስጥ ከሆነ ዕቃ እያነሳን እያስቀመጥን…. ብቻ የሆነ ነገር እየሠራን ነው፡፡ ይሄ ነገር ግን ‹‹ኢትዮጵያውያን ሥራ አይወዱም›› ከሚለው ጋር ይጣረስ ይሆን? ብቻ ግን በሆነ ነገር የዋከብን ነን፡፡
ማህበራዊ መገናኛዎችን እንኳን የምናነበው ወይ ከሰው ጋር ሆነን ነው ወይም ጉዞ ላይ ሆነን ነው፡፡ ጉዞ ደግሞ ራሱን የቻለ ሥራ ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለይም በከተማ ውስጥ ከመጸዳጃ ቤት በስተቀር ብቻችንን የምንሆንበት ዕድል የለም፡፡ ለመመሰጥ ደግሞ ብቻ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ውይ! እኔ ግን አዲስ አበባ ውስጥ የናፈቀኝ ነገር ቢኖር ጸጥ ያለ ቦታ! በቃ ከቤት ውጪ ከሆንን እኮ ስልክ ማውራት የማይታሰብ ሆነ፡፡
ያለምንም ምክንያት ‹‹ክላክስ›› የሚያጮህ ሹፌር፣ ያለምክንያት የሚለቀቅ ሙዚቃ… እዚህ ላይ ያለምክንያት ያልኩት ምንም ሙዚቃ የማያስፈልግበት ቦታ ሁሉ ስለሚለቀቅ ነው፡፡ ሙዚቃ የተለመደው መጠጥ ቤት፣ ይሁን ከተባለም ምግብ ቤት፣ በዋናነትም ሲዲ የሚሸጥበት አካባቢ ነው፡፡ አሁን ቡቲክና መጽሐፍ ቤት ውስጥ ሙዚቃ ያስፈልግ ነበር? እሺ እሱም ይሁን! ምናለ አካባቢውን ሁሉ የሚያናውጥ ባይሆን?
በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የኪራይ ቤት ከሆነ ቤት ውስጥ ሆኖም በነፃነት ስልክ ማውራት አይችልም፡፡ ግድግዳ ለግድግዳ የተደጋገፈ ነው፤ አንዱ ቤት ነው ሁለት በር ያለው፤ ታዲያ ይህ ብቻዬን ነኝ ያሰኛል? እንግዲህ ይህን ውጪ ያጣነውን ጸጥታ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ስለምናገኝ ነው መሰለኝ ሃሳብ ይመጣልናል፡፡ «ቀኑ ደመናማ ነበር» ከሚለው የልቦለድ የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ወደ «መጸዳጃ ቤት ነበርኩ» ልንለወጥ ነው ማለት ነው፡፡
በእውነት መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሚጻፉ ጥቅሶች እኮ አዝናኝ ብቻ ሳይሆኑ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ናቸው፡፡ አስጠሊታው ነገር ግን አንዳንዶቹ ስድ መሆናቸው ነው፡፡ ከብሄር ጋር የተያያዘ ነገር የሚጻፉት ሌሎች አዝናኝ ጽሑፎችን ጭምር እንዲጠሉ ያደርጋሉ፡፡ የጻፈው ሰው የሚያውቀኝ ሰው የለም ብሎ ይሆናል፤ ዳሩ ግን ምን ፈሪ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ተደብቆ የሚሳደብ የመጨረሻው ፈሪ ነው፡፡ ስድብ ፊት ለፊትም ቢሆን ጥሩ ነው ማለቴ ሳይሆን ግን ይለያያል፡፡ ፊት ለፊት የሚሳደብ ባለጌ ነው፤ ተደብቆ የሚሳደብ ግን ቦቅቧቃ ፈሪ ነው፡፡
ሌላው ነውር ነገር ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተያይዞ የሚጻፉት ናቸው፡፡ እነዚህ ግን በመስሪያ ቤቶችና በትልልቅ ሆቴሎች ሳይሆን በትንንሽ ሆቴሎችና መጠጥ ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ የባሰው ነውር ስልክ ቁጥር የሚያስቀምጡት ናቸው፡፡ የሚያስቀምጡት ራሳቸው ባለቤቶችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የራሴን ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡ በአንድ መጸዳጃ ቤት ውስጥ በተለጠፈ ስልክ ቁጥር ደወልኩ፡፡ ያነሳችው ሴት ናት፤ ከአጠገቧ ግን የብዙ ሴቶች ድምፅ ይሰማል፡፡ ዋና ዓላማውም የደወለውን ወንድ እያፋዘዙ መቀለድ ነው፡፡ ይቺኛዋ ዘዴ ግን ትንሽ ዘናም አድርጋኛለች፡፡ ወንዶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከሴቶች ላይ ስልክ እየተቀበሉ መሟዘዝ ይወዳሉ፡፡ ስለዚህ ለእነርሱ ቅጣት ከሆነ አይከፋም ባይ ነኝ፡፡
የመጸዳጃ ቤት ጽሑፍ ስል የሚጻፈውን ብቻ መስሏችሁ ነው? የሚነበበውንም ማለቴ ነው፡፡ የሚነበበውንም ስል ግድግዳው ላይ የተጻፈውን አይደለም፤ ጋዜጣና መጽሔት፡፡ አንዳንድ ሰዎችን ለማድነቅ ‹‹እገሌ እኮ መጸዳጃ ቤት ሲገባ እንኳን ያነባል›› ይባላል፡፡ ይሄ አድናቆት ስህተት ነው፡፡ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሚያነበው ብዙ ሰው ነው፡፡ ችግሩ ሊጠቀምበት ይዞት የገባውን ወረቀት ነው የሚያነበው፡፡ ግን ያንኑም ቢሆን ዝም ብሎ ከሚጥለው ማንበቡ ጥሩ ነው፡፡ መጸዳጃ ቤትም ባይገባ አያነበውም ነበርና!
ፈረንጆች ‹‹ከኢትዮጵያውያን ብር መደበቅ ከፈለክ መጽሐፍ ውስጥ አድርገው›› አሉ ተባለ፤ ምናልባት ‹‹ኢትዮጵያውያን እንዲያነቡ ከፈለክ መጽሐፉን መጸዳጃ ቤት አድርገው›› ይሉ ይሆን? ከማለታቸው በፊት ሌላ ቦታም እናንብብ!
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
ዋለልኝ አየለ