ኢትዮጵያ ባህል የበረከተባት፣ የተዋበ ማንነት ያነፃት ውድ ምድር ናት። ኢትዮጵያዊነት የባህል ድርብርብነት፣ የመከባበር ተምሳሌት፣ የውህደት፣ የአብሮ መኖር ውጤት ነው። ማህበረሰባዊ እሴቶቻችን፣ የእርስ በርስ መከባበራችንን የሚያጎሉ የአብሮ መኖር ትስስራችንን የሚያደምቁ ትልቅ ሀብቶቻችን ናቸው።
አገሪቱ በተፈጥሮ ውበቷ በታሪክ ቅርስ በበርካታ ብሔር ብሄረሰቦች መገኛ በቱሪዝም ሀብቶቿ የምትታወቅ አገር እንደሆነች ሳይታለም የተፈታ ነው። ከእነዚህ መካከል ባህል አንዱ እና ዋነኛው ነው። ባህል ሲባል በመሰረቱ እጅግ ክቡር ነው፤ የአንድ ህብረተሰብ ባህል በራሱ የህብረተሰቡ እንክብካቤ መጠበቅ፣ መዳበር፣ መሻሻልና የላቀ ዕድገት ማሳየት እንዳለበት ይታመናል። ባህልን የመንከባከብ ኃላፊነት የሚወድቀው ባለው ትውልድ ላይ ሲሆን እንክብካቤ የሚሹ መሆናቸውም እሙን ነው።
ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል ባህልና ወግ እንዳይረሳና በሌሎች ተውጦ እንዳይቀር የማንነታቸው መገለጫ የሆኑት ታሪኩን፣ ባህሉንና ቋንቋውን ጠብቆ በማቆየት ከዘመን ወደ ዘመን የሚሸጋገረው ትውልድ እንዲጠቀምበት ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ህብረተሰቡ ባህሉና ቋንቋውን የመጠቀም ጽኑ ፍላጎት ሲኖረው መሆኑ ቢታወቅም በራሱ ባህልና ቋንቋ የመገልገል ማህበራዊ ግዴታዎች ሲፈጠሩም ጭምር መሆኑ ይታወቃል።
አንድ ህብረተሰብ እራሱን የሚያስተዳድርበት ባህላዊ ስርዓቶችና ደንቦች ቀርጾ በእነዚህ በቀረጻቸው መተዳደሪያ ደንቦች መመራት እና መገልገል ሲጀመር ባህሉንና ቋንቋውን መቻሉን ያመለክታል። ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ እየተጠቀመባቸው ያሉት ባህሉንና ቋንቋውን የመጠበቅ ማህበራዊ ግዴታውን ያመለክታል። ታዲያ እንዲህ ያሉ ባህል ባለቤቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ጊዜውን ባገናዘበ መልኩ እንዴት እንዲህ ያሉ ወርቃማ እሴቶቻችንን እንጠብቃለን እንዲሁም እንከውናለን ብለን ስናስብ አስተዋይ ሰው በመሆን ነው። አስተዋይ ሰው ማለት ትክክለኛውን ጊዜ ያወቀ፤ በጊዜው ላይ አስፈላጊ ሰው የሆነ ነው። አንዳንድ ልማዳዊ ነገር ግን በጎ የሆኑ ባህሎች በተመሳሳይ እና በለመድነው መንገድ የምንተገብረው ከሆነና ጊዜውን ያላገናዘቡ ከሆነ ራስን፣ ቤተሰብን እና አገርን ለኪሳራ ና ለሞት የሚዳርግ ነው፤ ስለዚህ ትክክለኛ ጊዜን በማወቅ ራስን፣ ቤተሰብንና አገርን ማትረፍ ይቻላል።
አልፎ ሂያጅ ሰውን አሊያም ወዳጅን ሲያገኙ እቅፍ አድርጎ መሳም በደስታ ቤት አስገብቶ ሻይ ቡና መጋበዝ እና ጎንበስ ቀና ብሎ ማስተናገድ የተለመደ እና በዓለም አቀፍ ዘንድ የተመሰከረ ኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ተግባር ነው። ነገር ግን ይህ ተግባር ጊዜን ያገናዘበ ካልሆነ ወዳጃችንንም ሆነ ራሳችንን አደጋ ላይ ይጥላል።
ከሰሞኑ ታዲያ ኃያላኑን ሳይቀር አንገት ያስደፋ፣ የጠቢባንን ጥበብ የፈተነ፣ ስልጣን ያልበገረው ሀብት ያልመከተው ወረርሽኝ በመላ ዓለም ተንሰራፍቷል። የብዙ ሰዎችን ነብስ የነጠቀ፣ የዓለም አገራትን ኢኮኖሚ ያሽመደመደው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) የኢትዮጵያውያንን የማህበራዊ ግንኙነት፣ መሰባሰብና አብሮ መብላት ተሳስሞና ተጨባብጦ ሰላምታ መለዋወጥ በመሳሰሉት ባህሎቻችን ላይ ፈተና ሆኖ ተጋርጧል፤
ይህ ወረርሽኝ የሰው ህይወት ከመንጠቅ ጀምሮ እስከ ኢኮኖሚ ውድቀት እና ውድመት ብቻ የዘለቀ ችግር አይደለም ያመጣው። የአብሮ መኖር እሴታችንን ጭምር ነው የለወጠው። የኮሮና ወረርሽን የመተላለፊያው ዋነኛው መንገድ ንክኪ በመሆኑ የቆየው ባህላዊው የሰላምታ አሰጣጥ ሂደታችንን ጨምሮ፣ ተቀራርቦ የመኖር፣ በህብረት የመብላት የመጠጣት ባህላችን፣ የአምልኮ ስርዓታችንን፣ ኢ-መደበኛ የመረዳጃ ህብረቶቻችንን ማለትም እንደ እድር፣ እቁብ፣ ወንፈል፣ ጅጌ፣ ደቦ ….ብቻ አያሌ ተግባሮቻችንን ለውጦታል።
ራሳችንና ወዳጆቻችንን ለማዳን ስንል እንዲህ ያሉ የህብረት ተግባሮቻችን እንደቀድሞ መከወን አይቻልም። በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት በህብረት የሚከወኑ ተግባራቶቻችን ገታ በማድረግ ለጊዜው የባለሙያዎችን ምክር መስማትና ተግባራዊ ማድረግ ግድ ይላል። ባህላዊ ሰላምታዎቻችን ጨምሮ ህብረቶቻችንን እንዲሁም ወዳጆቻችን የትም አይሄዱም። በጎ ጊዜ እስኪመጣ ይህንን ክፉ ወረርሽኝ ለመከላከል ባህላዊ የሆኑትን አብሮ የመኖር እና በጋራ የምናደርጋቸውን ተግባራት ለጊዜው በመተው ሰላምታችንንም ቢሆን ከንክኪ በራቀ እጅ ባለመስጠት፤ እጅ በመንሳት ቢሆን ይመረጣል፤ ምክንያቱም ጊዜው የሚጠይቀው እንዲህ ያለውን ተግባር ስለሆነ ይህንን ማድረግ ግድ ይላል።
አንድ ማህበረሰብ የለመደውን ተግባር አቁመህ ወደ አዲስ የኑሮ ዘይቤ ግባ ሲባል አይከብደውም ወይ (ግር አይሰኝም ወይ) የሚለው የአብዛኛው ሰው ጥያቄ ሊሆን ይችላል፤ እኛም እንደ አንድ ማህበረሰብ እንዲህ ያሉ ጠንካራ በህብረት ውስጥ ያሉ ተግባራትን በመተው ወደ ግል ህይወት አዘንብሉ ሲባል ሊከብድ እንደሚችል መገመት እንችላለን። ነገር ግን ከመሞት መሰንበት ነውና ራስንም ሆነ ሌላውን ማህበረሰብ ለችግር ላለማጋለጥ የለመድነውን ባህልም ቢሆን ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ብዙ ሰዎች በተለይም ወንዶች በቤት ውስጥ የማሳለፍ ልምድ የላቸውም። ብዙውን ጊዜ ማለትም ከሥራ ሰዓት፣ ከትምህርት ቤት ያሉ ጊዜያትን የሚያሳልፉት ተሰባስበው በመጨዋወት፣ በህብረት ተቀምጠው ፊልም፣ ከረንቡላ፣ ኳስ የመሳሰሉትን በማየትና በመጫወት ነው የሚያሳልፉት። አሁን በኮሮና ዘመን ታዲያ ይሄንን ልማድ ማስቀጠል አደጋው የከፋ ነውና እንደነዚህ ያሉ ክፉ ጊዜያትን ያለአንዳች የስነ ልቦና ተጽዕኖ እንዴት ልናልፋቸው እንችላለን ስንል አንድ የስነልቦና ባለሙያ አነጋግረናል ።
የአካል መራራቅ ወዳጅነት አይቀንስም
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ወጣት ናሆም ሰለሞን እንደሚለው ባህል ፣ወግ፣ስርዓት ብሎም አገር የሚኖረው ሰው ሲኖር ነው፤መልካም ባህሎቻችንንና እሴቶቻችንን የሚወስድብን የለም፤ አሁን ከተከሰተው በሽታ ለመጠበቅ ሁሉም ሰው በመጀመሪያ ትኩረት ማድረግ ያለበት ራሱን ከኮሮና ቨይረስ በመከላከል የሚሰጡ መመሪያዎችን በመተግበር ላይ መሆን እንዳለበት ይናገራል።
አቶ ናሆም አክለውም በሽታው የእያንዳንዱን ግለሰብ ጥንቃቄ እና ትኩረት ስለሚሻው ሁሉም ራሱን ሊጠብቅ ይገባል፤ ይህ መራራቅ ደግሞ አካላዊ ነው እንጂ ማህበራዊ አይደለም፤ ማህበራዊውን ህይወት ለማስጠበቅ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ወዳጆቻችን ማግኘት እንችላለን ይላሉ። በዚህም የምንፈልገውን ማህበራዊ አገልግሎት በእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማከናወን ይቻላል፤ ስለዚህም አካላዊው መራራቅ ማህበራዊ የሆነውን ወዳጅነት እና የተለያዩ ተግባራትን አያጠፋም። ምናልባት ከዚህ ቀደም ከምናደርገው በተለየ መንገድ እንድናደርግ ሊያስገድደን ይችላል።
አካላዊው ርቀት መጠበቅ ብሎም ቤት መቀመጥ ለወዳጅዎ ያደረጉት መልካምነት እንደሆነ ማሰብ ተገቢ እንደሆነ የስነ ልቦና ባለሙያው ያስረዳል።
ባህልና ልምዳችንን እንዴት እንከውን?
መቀራረብም ሆነ መራራቅ ያለው አእምሮ ውስጥ ነው የሚሉት የስነ ልቦና ባለሙያው ወጣት ናሆም አሁን በአካል ርቀታችንን ጠበቅን እንጂ ማንኛውንም ተግባራት ከንክኪ በጸዳ መልኩ ማድረግ ይቻላል። በተለይ በአሁኑ ዘመን ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ማንኛውም ማህበራዊ የሆኑ ተግባራቶቻችን በቴክኖሎጂ ታግዘን ማድረግ እንችላለን። ወጣቱ የስነ ልቦና ባለሙያው አሁንም ይናገራል እስከአሁን ከምናደርጋቸው ነገሮች ያጎደልነው አንዲት ነገር አካላዊ መራራቅ ብቻ ነው። ሌላው ባህላዊ እሴቶቻችን እንዳሉ ይቀጥላሉ። ለምሳሌ በስልክ እየተደዋወሉ ጤናን መጠያየቅ፤ መረጃን መለዋወጥ እና የመሳሰሉትን ተግባራት ማድረግ ይቻላል።
ሌላው የሚለው የስነልቦናው ባለሙያው ማህበራዊ ህይወታችን ምንም ርቀት እንደሌለው ማሳያ በየቦታው የምናያቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት ናቸው፤ አቅመ ደካማና የኢኮኖሚ ደረጃቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሰዎች የተለያዩ የምግብ ፍጆታዎችን በልግስና እስከ ማቅረብ፤ ቤት አከራዮች ለተከራዮቻቸው ወርሃዊ ክፍያን እስከመተው የደረሱ እርምጃዎችን እያደረጉ ናቸው። ወጣቱ የኮሮና መከላከያ ከሆኑት ተግባራት አንዱን በተለይም እጅን ማስታጠብ የመሳሰሉ ሥራዎችን በየአካባቢያቸው ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች እንዲሁም ትራንስፖርት መጠበቂያ ቦታዎች ላይ ሁሉ እያቀረቡ ሰዎች ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ እያደረጉ ናቸው። በህብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዙሪያ ብቻ ብዙ ማንሳት እንችላለን። ይሄ የሚያሳየው አሁንም ቢሆን የቀደመው የመተሳሰብ የመረዳዳት ባህላችን መቀጠሉን ነው። የቀረው ሲገናኙ መጨባበጥ እና መሳሳም ብቻ ነው። ይሄ ደግሞ በአይን የሚታይ ባይሆንም በልብ በተግባር እየታየ ያለ ነው።
መጥፎውን ጊዜ እንደመልካም አጋጣሚ
ይህንን ጊዜ እንደ ችግር ብቻ ሳይሆን እንደ መልካም አጋጣሚም መጠቀም ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ በተለያዩ የሥራ ጫናና በኑሮ ሩጫ ምክንያት ጊዜ ላልሰጠናቸው ቤተሰቦቻችን ይህ መልካም አጋጣሚ ነው። ልጆች ያላቸው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የመመካከሪያ የመወያያ እና የቤተሰብ ፍቅር ማጣጣሚያ ወቅት አድርጎ መውሰድ ይቻላል። እንዲሁም የማንበቢያ ጊዜ የመጻፊያ ጊዜ ያጣ ሰው ይሄንን ጊዜ ለእነዚህ አገልግሎቶች ያውላል። በቤት ውስጥ የሚሰሩ በርካታ ሥራዎች ይኖራሉ። እነዚህን ሁሉ በየቀኑ ፕሮግራም በማውጣት ማከናወን ሌላኛው የመጥፎ ጊዜ መልካም አጋጣሚ ነው ሲል የስነ ልቦና ባለሙያው ይመክራል።
ይህንን ጊዜ ለበጎ በማዋል ነገአችንን መስራት እንችላለን፤ በዚህ አጋጣሚ ያገኘናትን ጊዜ ያለአንዳች ሥራ በእንቅልፈ ማሳለፍ ለጤናም ጠንቅ መሆኑን ሁሉም ሰው መገንዘብ እንዳለበት ይነገራሉ። በቤት ውስጥ ሊሰሩ የሚችሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግም ተገቢ ነው ፤ ያለንን ትርፍ ጊዜ እንደ እረፍት ሳይሆን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ማትረፊያችን ይሆናል።
የስነ ልቦናው ባለሙያው እንደሚለው ማንኛውም ሰው የትናንት አሊያም የነገ አይደለም የዛሬ ነው፤ ዛሬ ከሁሉም በላይ እጅግ አስፈላጊው ጊዜ የሆነበት ምክንያት ደግሞ አንድን ነገር ለማድረግ አንዳች ሀይል የተጎናጸፍንበት ብቸኛው ጊዜ ስለሆነ ነው። አንድን ነገር ለማድረግ ተነስተህ የምታደርግበት ወቅት ስለሆነ ነው፤ ከሁሉም በላይ እጅግ አስፈላጊው ሰው ደግሞ በዚች ቅጽበት አብሮህ ያለው ሰው ነው፤ ምክንያቱም ማንም ሰው ከዚያ በኋላ ከሌላ ሰው ጋር የሆነ ነገር ለማድረግ መቻሉን አያውቅም።
ከሁሉም በላይ እጅግ አስፈላጊው ጉዳይም በጎ ማድረግ ነው፤ ሁላችንም የአሁን ሰው እንደሆንን በመረዳት ጊዜን በማወቅ፣ ከንክኪ ርቀንና በሳሙናና በውሃ በመታጠብ አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ከቤት ባለመውጣት ራሳችንን እና ወዳጆቻችንን እንጠብቅ የሚለው የስነ ልቦና ባለሙያው ምክር አዘል ማሳሰቢያ ነው።
የስነልቡና ባለሙያው ወጣት ናሆም የጠቆመንን በቤት ውስጥ ልናደርጋቸው የተገቡ ተግባራትንና እኛም ልንከውን ያሰብናቸውን ሌሎች ፕሮግራሞችን በማከል ጊዜያችንን ጥቅም ላይ ማዋል አለብን። በተጨማሪ ደግሞ አቅም ለሌላቸው ጎረቤቶቻችን መልካም በማድረግ ይህንን ክፉ ጊዜ እንሻገር፤ አየሩ ጤናማ ምድሪቷም ወደ ቀድሞ ጤናማ የአኗኗር ሁኔታዋ ትመለሳለች፤ ሁሉም ነገር ሰላም እና በጎ ይሆናል፤ ኢትዮጵያም የፍቅር፣ የበጎነት፣ የመቻቻል አገርና ምድርነቷ ይቀጥላል። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2012
አብርሃም ተወልደ