አንድ ሙያ በመልካም ሥነ ምግባር ካልተደገፈ ከቶም የተሟላ ሊሆን አይችልም። ሙያው የሚወደደው በባለሙያው ማንነት ላይ ተመስርቶ፤ ሙያው በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጥረው በጎ ተፅዕኖ መነሻ ተደርጎ ነው። የፊልም ትወና የራሱ የሆነ ልዩ እውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ሙያ ነው። በዘርፉ ትልቅ የተባሉ ተዋንያን በስነ ምግባራቸው የታነጹ፤ በፊልም ስራ ሙያ የሰለጠኑና ሙያቸውን አፍቃሪ እንዲሁም አክባሪ ሲሆኑ ነው። ነገር ግን ይህ ካልሆነ የፊልም ኢንዱስትሪው ወደፊት ይራመዳል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።
አርቲስት ብርሀኑ ሽብሩ በብዙ የፊልም ሥራዎቹ እናውቀዋለን። በተለይም በሱ የተዘጋጀው “ዜማ ህይወት” የተሰኘ ፊልሙ ከፊልም አፍቃሪያን ትውስታ እንዳይጠፋ አድርጎ የፊልም ሙያ ችሎታውን ያስመሰከረበት ነው። ብርሀኑ የተዋንያን ስነ ምግባር ጉድለት ለፊልሙ ኢንዱስትሪ አለማደግ የራሱ የሆነ አሉታዊ ድርሻ እንዳለው ይገልፃል። የቀረጻ መርሀ ግብርን አለማክበር፣ ተዋናዩ/ተዋናይዋ/ ቀድሞ አንብቦ የተስማማበት የፊልም ጽሑፍ ላይ ያሉ ተግባራት ለመተግበር ፍቃደኛ አለመሆን፣ ክፍያን ያለወቅቱ መጠየቅና ከፊልም አዘጋጅና ፕሮዲዩሰሮች ጋር ተግባብቶ አለመስራት ዋንኛ የተዋንያን የስነ ምግባር ችግር ማሳያዎች ናቸው ይላል።
በሌላው ዓለም የፊልም ኢንዱስትሪ ላይ የሚሳተፉ ተዋንያን የሙያውን ስነ ምግባር መጠበቅ ወደ ሙያው ለመቀላቀል ወሳኙ ነጥብ እንደሆነ የሚገልጸው አርቲስት ብርሀኑ፤ ለፊልም ስራው ስኬታማ መሆን የፊልም ባለሙያዎች የሙያ ፍቅርና ጥሩ ስነ ምግባር ወሳኝነቱ የማያሻማ መሆኑን ያስረዳል። በስርዓት ቢመራ ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ ቢሆንም አልተጠቀምንበትም ባይም ነው።
የተለያዩ የፊልም ስራ ውሎችን በአንድ ጊዜ መዋዋል፣ ከቀረጻ ቦታ ስልክን አጥፍቶ መጥፋት፣ የአዘጋጁን የስራ ትዕዛዝ አለመቀበልና መናቅ፣ ከውል ውጪ ገንዘብ መጠየቅ፤ የጠየቀው ገንዘብ ካልተከፈለው ስራውን ማቋረጥ፣ ቀረጻ ቦታ ላይ ተገቢ የቃለ ተውኔት ልምምድ ሳያደርጉ መገኘትና መሰል የስነ ምግባር ችግሮች በተዋንያኑ ይታያል ተብለው የተቀመጡ መሆናቸውንም ያነሳል።
ሙሐመድ ኢብራሂም የፊልም ደራሲና ፕሮዲውሰር ነው። ከ3 ያላነሱ ፊልሞች ላይ በዋና አዘጋጅነት እና በረዳት አዘጋጅት /ዳሬክቲንግ/ ሁለት ፊልሞችን ደግሞ በድርሰት ተሳትፎ ለእይታ አብቅቷል፡፡ “የቀጠርኩት”ና “ስጪኝና” ፊልሞቹ በተመልካቹ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙለት ስራዎቹ ናቸው፡፡ ታድያ በብዙ የፊልም ስራዎች ላይ ሲሳተፍ የተመለከተውን የተዋንያ ስነምግባር መጓደል በትዝብት ይዘረዝራል፡፡ የተዋንያን ስነ ምግባር መጓደል ወይም ደግሞ ጥሩ መሆን ለፊልሙ ኢንዱስትሪ መክሰምም ሆነ ማበብ ወሣኝ መሆኑን ያነሳል። በቁጥር የበዙ ፊልሞች በተዋንያን ምክንያት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ መቅረታቸው በቅርበት መታዘብ እንደቻለና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሄደውን የስነ ምግባር ችግር የዘርፉ ዋንኛ የእድገት ማነቆ መሆኑን ይናገራል፡፡
በፊልም ሙያ ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያን ሁሉም ባይሆኑም አብዛኛዎቹ በዘርፉ እውቀትና ክህሎት የሌላቸው መሆኑ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ በእውቀትና በስነ ምግባር የታነጹ ተዋንያንና የፊልም ባለሙያዎች በማፍራት በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ላለመሆኑም ይህ ማሳያ ነው ይላል። እንደ ሌሎች በፊልም ኢንዱስትሪው እምርታን እንዳገኙ ሀገራት በዘርፉ በስነ ምግባር የታነፀና በፊልም ስራ እውቀትና ክህሎት የሰለጠነ ባለሙያ ማፍራት አለመቻላችን ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን ይገልጻል።
ከካሜራ ጀርባ በፊልም ስራ ዝግጅት ወቅት የሚገጥሙ በጎ ክርክርና ሙግቶች ለፊልሙ ስራ አምሮ ደረጃውን ጠብቆ ታዳሚው ጋር መድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ በፊልም ሰሪዎቹ ንትርክና ጭቅጭቅ በፊልም አሰሪውና በተዋንያን መካከል የሚፈጠር አለመግባባት የብዙ የፊልም ስራዎች መስተጓጎልን ያመጣልም ይላል። አንዳንዶቹም ከሚጠበቀው በላይ ጎድለው ለህዝብ የመቅረባቸው ምስጢርም ይህ ነው የስነምግባር ጉድለቱ።
ገና ወደ ስራው የገባ አዲስ ተዋናይ ጀምሮ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅና ታዋቂ እስከተሰኙት ተዋንያን ድረስ በስነ ምግባር ጉድለቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አይብዙ እንጂ በዚህ ሙያ አንቱ የተባሉ ምስጉን ተዋያን መኖራቸው ባይካድም በፊልም ሰሪዎች ዘንድ በምሬት የሚነሱት በቁጥር ያይላሉ።
አንድ ተዋናይ ነው በየአመቱ በሚዘጋጁ የፊልም ተዋንያን ሽልማት ላይ በተደጋጋሚ ምርጥ ተብሎ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የሚገርመው ግን ባሸነፈበት ፊልም ላይ ተሳታፊ የሆኑ ባለሙያዎች ማለትም የፊልሙ አዘጋጅ ሌሎች ተዋንያንና የፊልሙ ፕሮዲዩሰር የተሸላሚው ተዋናይ ሽልማት ከፊልሙ ስራ በስተጀርባ ከካሜራ ጀርባ ያለው የተበላሸ ባህሪውና ያልተገራ ጸባዩ አብጠርጥረው ስለሚያውቁት መሸለሙን ፈፅሞ አይቀበሉትም፡፡
ምንም እንኳን በውድድሩ ላይ የተሸለመው የአሸናፊነት ክብርና ሽልማት ማስቀረት ባይችሉም የተሸለመው ሽልማት የውሸት እሱን የማይገልጸው እንደሆነ አሳምረው ያውቁታል፡፡ የተዋንያን ምርጫ መስፈርት የተዋንያኑ እውናዊ ባህሪና ስራውን በሚያከናውንበት ወቅት ለስራው ያበረከተው በጎ ነገር ምንነት በመጠኑም ቢሆን መስፈርት ሊደረግ እንደሚገባ የፊልም ባለሙያዎቹ ያስገነዝባሉ፡፡
አትሂጅብኝ፣ ፍቅሬን ላድን፣ በሳምንት ስምንት ቀን፣ ወራጅ አለ ፊልሞች በፕሮዲውሰርነት ከተሳተፈባቸው መካከል ይገኙበታል፤ ዮሐንስ መራዊ። እርሱ እንደሚለው ደግሞ፤ በፊልም ስራ ውስጥ ከባዱ ነገር የፊልም ተዋንያኑ በቀረጻ ወቅት የሚያሳዩት የስነ ምግባር ችግር ነው። የፊልሙ ፕሮዲዩሰር ጠንከር ያለ ውል ከተዋንያኑ ጋር አለመዋዋሉ እና እስካሁንም በፊልም ስራ ላይ በፈጠረው ማስተጓጎል የተጠየቀና ጠንከር ያለ እርምጃ የተወሰደበት አለመኖሩ የፊልም ተዋያን ስነ ምግባር ይበልጥ እየተባባሰ እንዲሄድ አድርጓል። የፊልም ስራ ችሎታንና የሙያው ተሰጥኦን መሰረት አድርጎ መሰራት ሲገባው አብዛኛው በትውውቅና ፊልም ሰሪዎች ባላቸው ቀረቤታ ተዋንያንን እንዲመርጡ ይደረጋል። ይህ ደግሞ በፊልም ስራ አዲስና ሙያውን አክብረው የሚሰሩ ጎበዝ ተዋንያን እንዳናይ አድርጎናል።
ስነ ምግባር የጎደላቸው የፊልም ተዋንያን ስርዓት ለማስያዝና ለሙያው ተገቢውን ክብርና ፍቅር ሰጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ የፊልም ሰሪዎች በሙያ ማህበራት በመደራጀት የቁጥጥርና ክትትል ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ የፊልም ባለሙያዎች ይናገራል። አንዱ ጋር የጀመረውን የፊልም ስራ ሳያጠናቅቅ ሌላ ጋር መዋወል፣ ከአንዱ ጋር የነበረውን የቀረጻ መርሀ ግብር ሰርዞ ሌላው ጋር መገኘት ሊቆም የሚችለውም በፕሮዲዩሰሮቹ የጋራ ጥምረት ነው ይላል።
የፊልም ስራ ውል ሲፈራረም አመሉን አሳምሮ የተሰጠውን ገጸባህርይ በብቃት እንደሚወጣው በመግለጽ ከፕሮዲዩሰሮች የሚቀርብለትን የአብረን እንስራ ጥያቄ በክብር የሚቀበለው ተዋናይ ከፊርማና ብር ርክክብ በኋላ አድራሻና ስልክ በማጥፋት ድብብቆሽ ውስጥ እንደሚገባም ሙያተኞቹ በትዝብት የሚያነሱት ገጠመኛቸው ነው። በዚህም የፊልም ስራ ሙያ በስነ ምግባር ካልተደገፈ ኪነ ጥበቡ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ነገር ይበዛል ይላሉ።
አንድ ተዋናይ ምንም ያህል ችሎታ ኖሮት የሙያው ስነ ምግባር ከሌለው የትወና ብቃቱ ብቻ ውጤታማ ሊያደርገው ፈጽሞ እንደማይችልም ይናገራሉ። ምን አልባትም ለጊዜው በፊልሙ አዘጋጅና የፊልም ፕሮዲዩሰሩ ትዕግስትና ጥረት ፊልሙ ተጠናቆ ለእይታ ቢበቃ እንኳን ስራው ላይ የተፈጠሩ ችግሮች በፊልሙ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮበት በጉልህ የሚታይ ስህተቶች ሊስተዋሉ ይችላሉና ስነምግባር ይቅደም ባይ ናቸው። ውሎ አድሮም የፊልም ተዋናይ ከፊልም ሰሪው ጋር ተግባብቶ ካልሰራና እንደ አርዓያ የሚቆጥረው የፊልም ተመልካችና ህዝብ ተገቢ ባልሆነ ቦታና ሁኔታ ከተመለከተው አንቅሮ መትፋቱ ስለማይቀር ልብ ያለው ልብ ይበል ይላሉ።
እታፈራው ኃይሉ በብዙ ፊልሞች ላይ ተሳትፎ ብታደርግም በድርሰትና ዝግጅት የተሳተፈችበት “ከባድ ሚዛን” በተሰኘው ፊልምዋ ነው። የተዋያን ስነ ምግባር መጓደል የፊልም ስራን የሚያስተጓጉል ፕሮዲዩሰሮች ያሰቡትን የፊልም ስራ መርሀ ግብር አሰርዞ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግና ለፊልሙ ጥራት መጓደልም ዋንኛ ሰበብ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡
እስካሁን የሚገኘው ገቢ ምንም ያህል ቢገዝፍ ተዋንያን ከፊልም ትወና ከሚያገኙት ገቢ ለመንግስት በግብር መልክ እንዲከፍሉ የሚጠይቅም ሆነ የሚቆጣጠር አንድም አካል የለም፡፡ ያለ ግብር የሚሰበስቡት የበዛ ገቢ ቢያንስ በጥሩ ስነ ምግባር ታግዘው እውቅናቸውን ተጠቅመው ለህብረተሰቡ መልካም የስነ ምግባር አርዓያ መሆን አይገባቸውም ነበርን? የሚገኙበት ሁኔታ ግን ከዚህ ተቃራኒ መሆኑ እሱንም ለትዝብት የፊልም ስራ ኢንዱስትሪውም ለክስረት ይዳርገዋል፡፡
ከላይ ለተዘረዘሩት የፊልም ተዋናዩ የስነ ምግባር ችግሮች መፍትሄው ለዘርፉ ትኩረት መስጠት፣ የፊልም ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ፣ ጠንካራ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና መተግበር፣ በሙያው የሰለጠኑና በስነ ምግባር የታነጹ ተዋንያንን ማሳተፍ፣ የፊልም ሰሪው የእርስ በእርስ ግንኙነትና ማህበራትን ማጠናከርና ስራው ሙያና ስነ ምግባር መር እንዲሆን ማድረግን ነው ትላለች።
አዲስ ዘመን ጥር 5 /2011
ተገኝ ብሩ