የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ ዕለት ጀምሮ ስለበሽታው ሳናስብ አምስት ደቂቃ እንኳን የቆየንበት ጊዜ አይኖርም። ምናልባት ግን ከሰው ሰው ይለያያል። የመገናኛ ብዙኃንም ሆነ ማህበራዊ ገጾችን የሚከታተሉ ሰዎች ስለዚህ በሽታ ሳያስቡ የሚቆዩበት ጊዜ የለም። ምክንያቱም መገናኛ ብዙኃን ላይ በየደቂቃው የሚያዩት ስለዚሁ ጉዳይ ብቻ ስለሆነ ነው። ከመገናኛ ብዙኃንም ሆነ ከማህበራዊ ገጾች ውጭ የሆኑት ግን ስለቫይረሱ በተደጋጋሚ የሚሰሙበት አጋጣሚ እምብዛም ነው።ምናልባትም በማይክራፎን እየተዞረ ሲነገር፣ በየመንገዱ እጃችሁን ታጠቡ ሲባልና በሌሎች አጋጣሚዎች ነው ሊሰሙ የሚችሉት።
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በየደቂቃው ሌላ ወሬ የላቸውም። በአገራችንም እንደዚሁ ነው። በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ሌሎች ጉዳዮች ተረስተዋል፡፤ ለምሳሌ ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 9ኛ ዓመት ነበር። ነገር ግን ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም ይሄንኑ ትኩረት ማጣቱን በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈውታል። በወቀሳ መልክ ሳይሆን በኮሮና ምክንያት መሆኑን ገልጸው ማለት ነው።
የኮሮና ወረርሽኝ የሁሉንም ሰው አስተሳሰብ አንድ አይነት አድርጎታል። ሌሎች ያከራክሩ የነበሩ የፖለቲካና የብሽሽቅ ነገሮች ለጊዜው ተረስተዋል።
ሆኖም ግን ባለፈው ሳምንት አንድ አጀንዳ ተከፍቶ ነበር። እርግጥ ነው ይሄም ከኮሮና ውጭ ሳይሆን ራሱ ኮሮና ያመጣው አጀንዳ ነው። ይሄውም ኢትዮጵያ ለኮሮና ቫይረስ መድኃኒት ለማግኘት በምርምር ሂደት ላይ መሆኗ መገለጹ ነው። ግማሹ በደስታ ግማሹም በማሾፍ ብዙ ሲል ነበር።
በደስታ ሲባል ከነበረው ልጀምር።
ኢትዮጵያ ስሟ የሚታወቀው በድህነትና በስደት ነው። ሲቀጥል ፈረንጆቹ ለአፍሪካ አገራት ዝቅተኛ ግምት ነው ያላቸው። ዓለም ጭንቅ ላይ በሆነችበት በዚህ ወቅት ይቺ አገር መፍትሔ ልታመጣ ነው ሲባል ብዙ ሰው በስሜት ይፈነድቃል። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ነገሮች ተጋነኑ። ፉከራው በዛ። አንዳንዶች መድኃኒቱ ገና ለምርምር ቤተ ሙከራ የገባ መሆኑን እስከሚዘነጉ ድረስ ደስታ አሰከራቸው። መድኃኒት ደግሞ በባህሪው ብዙ ደረጃዎችን የሚያልፍና ብዙ ጊዜ የሚወስድ ነው። ለዚያውም ገና ሊሆንም ላይሆንም ለሚችል ነገር።
በዚህ ደስታ ምክንያት ልማዳዊ ድርጊቶችን ጭምር ማስተዋወቅ ተጀመረ። መድኃኒቱ ከባህል መድኃኒት የሚቀመም መሆኑ ደግሞ ገፊ ምክንያት ሆነ። ይሄን ሲሰሙ ቅጠላቅጠልና ሥራሥሩን ሁሉ መድኃኒት ነው መባል ጀመረ። በዚህ በጭንቅ ወቅት ይህንን አይነት አሳሳች መልዕክት ማስተላለፍ በሰው ህይወት ላይ ከመቀለድ አይተናነስም። ከባህል መድኃኒት የሚቀመመው ዘመናዊ መድኃኒት ብዙ ምርምር የተደረገበትና በቤተ ሙከራ ዘመናዊ መሳሪያዎች የታየ እንጂ ዝም ብሎ እንደወረደ አይደለም።
በሌላ በኩል አሁን ባለው ከፍተኛ የጥንቃቄ መልዕክት ላይ መድኃኒት ተገኘ ማለትም ማዘናጋት ነው፤ ሲቀጥልም የሀሰት መረጃ ነው። ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተመራመርኩ ነው እንጂ ያለው መድኃኒት አገኘሁ አላለም፤ አዛብተው ያራገቡት አንዳንድ መገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ ገጾች ናቸው።
ሲያሾፉና ሲሳለቁ ወደነበሩት እንሂድ።
በእነዚህ ሰዎች የታዘብኩት የምር አገሩን የሚጠላም እንዳለ ነው። የበታችነት ስሜት የሚያርመጠምጠው ብዙ ሰው መኖሩን ተረድቻለሁ። አንዳንድ ሰው በራሱ የዕውቀት ልክ ብቻ ሌላውንም ይለካል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ምንም መሥራት ስለማትችል አርፋ ትቀመጥ የሚሉም ነበሩ። ይሄ የበታችነት ነው፤ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ አስጀማሪ የሆነችና ብዙ ጠቢባን ያሏት ናት። ዓለም እየመጣ የሚመራመርባት ሀገር ነች።
ይሄ ሁሉ የሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሆነ ነው። ብዙዎቻችን ከውጭ ሲሆን እንጂ የራሳችን የሆነ ነገር አያኮራንም። ብዙ አገራት እየሞከሩ እንደሆነ ሰምተናል፤ ያኔ ‹‹ምነው ቶሎ በደረሱልን!›› ነበር የተባለው። የኃያሏ አገር አሜሪካ መሪ በሐኪም ያልታዘዘ መድኃኒት አዘው ሰው አስገድሏል። ይሄን ያህል ወንጀል ይዞ ምንም አልተባለም፤ ለዚያውም እንኳን ተገቢው ወቀሳ እንኳን አልተወቀሰም። እነርሱ ሲያደርጉት ሰው መግደልም ትክክል ይሆናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን መመራመርም
ወንጀል ይሆናል።
ኢትዮጵያ አገር በቀል የባህል መድኃኒቶችን በዘመናዊ መንገድ በመቀመም ብትመራመር ምን ችግር አለው? ከተሳካ ይሳካል፤ ካልተሳካም እንደማንኛውም ምርምር ውድቅ ይሆናል። ሁሉም ነገር በሙከራ ነው የሚረጋገጠው።
አንዳንዶቹ ደግሞ (ትንሽ ለዘብ ያሉት) ገና ያልተጠናቀቀ ነገር ለምን ዜና ሆነ የሚል ነው። ሙከራው በራሱ እኮ ዜና ነው። እስካሁን መድኃኒት ያገኘ አገር የለም፤ ሙከራቸው ግን ዓለም አቀፍ ዜና ነበር፤ ታዲያ የኢትዮጵያ ሙከራስ ዜና ቢሆን ምን ችግር አለው? ለዚያውም መሰረታዊ የቤተ ሙከራ ደረጃዎችን አልፏል የተባለ መድኃኒት። ማን ያውቃል እውነት ሆኖ አገሪቱ ታሪክ ብትሰራስ?
እንዲህ አይነት ተመራማሪዎች ሲገኙልን ‹‹አይዟችሁ! በርቱልን!›› ማለት ይሻላል ወይስ ማንቋሸሽና ማጣጣል?
የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የትኛውም መድኃኒት የሚዘጋጀው ከእፅዋትና እንስሳት ውጤት ነው። ታዲያ እንዲህ ከሆነ የኢትዮጵያ እጽዋት መድኃኒት የማይሆንበት ምክንያት ምንድነው? ዋናው የመድኃኒት አሰራር ሂደቱን ጠብቆ ይሂድ ነው። የተለያየ አይነት የመድኃኒት አመራረት ሂደት አለ። አንዳንዱ ረጅም ዓመታት የሚወስድ ነው፤ አንዳንዱ ደግሞ በጥቂት ዓመታት የሚሳካ ነው። ይሄ የኢትዮጵያ ዜና በተሰማበት ባለፈው ሳምንት አንድ የህክምና ባለሙያ ‹‹ሀኪም›› ገጽ ላይ ተከታዩን ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል።
‹‹ነገረ መድኃኒት›› ዶክተር ሲሳይ ለማ ጨመዳ
እኔና መሠል የህክምና ባለሙያ ጓደኞቼ ሰሞኑን በተለያየ መንገድ ህዝቡን ለማስተማርና ለማንቃት ስንቀሳቀስ ነበር፤ የትላንትናው የመድኃኒት አገኘን መግለጫ ግን ብዙ ጥረታችን ላይ ውሃ ቸልሶበታል።
የመጀመሪያ ነገር የኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ምንም አያውቁም ማለት አይቻልም። ዘመዶችም ጭምር የባህል ህክምና ቀማሚ አሉኝ… We are not simply ignorant to exist thousands of years; We do have an indigenous knowledge. ነገር ግን የእኛ የባህል ህክምና ከዚህ በፊት ከሳይንስ ጋር ሳይተዋወቅ እና ሳይዘምን ቆይቶ ዛሬ ገና በሁለት ሳምንት ውስጥ ቫይረሱን እንኳን ለይቶ ለማውጣት ባልተቻለበት አኳኋን መድኃኒቱ ተገኘ ማለት ባዶ ተስፋን መመገብ ነው::
1) እኛ ሀገር አድቫንስድ ላብራቶሪ የሌለን አብዛኛው የgenetic study ወደ ውጭ ሀገር ተልኮ በሚሠራበት ሁኔታ ቫይረሱን ለይተው የተሳካ የላብራቶሪ ምርምር አካሂደዋል የሚለው እና በሁለት ሳምንት ውስጥ መጠናቀቁ እራሱ አጠራጣሪ ነው።
2) ሌላኛው ቫይረስ ካለው አስቸጋሪና ተለዋዋጭ ባህሪ አንጻር መድኃኒት ለኖቬል ኮሮና ቫይረስ ማግኘት ከባድና ዘላቂ ምርምር ይጠይቃል:: HIV, Ebola ልብ ይሏል።
3) በቲዮሪ ደረጃ ያለን ነገር ወደ ህዝብ በዚህ ጊዜና ሁኔታ መግለጽ ትክክል አይደለም።
4) አንድ ምርምር ሲካሄድ የዓለም አቀፉን የWHO መመሪያ ማሟላትና የጊዜ ገደቡንም አብሮ ማውጣት ያስፈልጋል፤ ቢያንስ ይሄ ምርምር በትንሹ ከአንድ ዓመት በላይ ይፈጃል።
5) አብዛኛው በሳይንስ ባልተደገፈ የባህል ህክምና ለሚያዘወትረው ህብረተሰብ በዚህ ጊዜ ወጥቶ ያልተጨበጠ ተስፋ መስጠት የህብረተሰብ የበሽታ መከላከያ መንገዶች እንዳይተገበር እና ከታመመም ወደ ባህል መድኃኒት ፍለጋ እንዲሄድ ያደርጋል።
ማሳሰቢያ አሁንም መከላከል ከማዳን በጣም ይሻላል እራሳችንን እንጠብቅ!
ፍስሐ ሽፈሬ (MPH, MPham) የተባሉ ባለሙያ ደግሞ የሚከተለውን ሙያዊ ማብራሪያ ጽፈዋል።
የጤና ሚኒስትር እና የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ትናንት ባበሰሩን ዜና ተደስቻለሁም፤ ተሳቅቂያለሁም። ለምን አላችሁ? ጥሩ ጥያቄ ነው።
እኔ ያጠናሁት ፋርማኮሎጅ እና ኤፒዲሚዮሎጅ ነው። የመድኃኒት ግኝት ደሞ ከፋርማኮሎጅ ጋር በቀጥታ ስለሚገናኝ ከማውቀው እና ካነበብኩት ትንሽ ላካፍላችሁ ወደድኩ። በማህበራዊ የትስስር ገፆች ላይ ያለውን ውዝግብም ትንሽ ረገብ ያደርገዋል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ (ገበያ ላይ ያለ እንደ azithromycin and hy¬droxychloroquine አላልኩም) መድኃኒት ተመርቶ ወደ
ገበያ የሚቀርብበትን ሂደቶች ባጭሩ ላስቃኛችሁ። ሁለቱ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችም ያወሩት ስለ አዲሱ መድኃኒት ነው።
አንድ አዲስ መድኃኒት ተመርቶ ወደ ገበያ ወጥቶ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ከ 10 እስከ 15 ዓመታት ይፈጃል። ዝርዝሩን አጠር አጠር አድርጌ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።
1) Drug discovery and Development፡ ከ 2 እስከ 5 ዓመታት ይወስዳል።
1.1. Discovery: አዲስ መድኃኒት መፍጠር
ተመራማሪዎች አዲስ መድኃኒት ሊፈጥሩ የሚችሉባቸው መንገዶች
- ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ በመያዝ
- የተለያዩ አይነት ንጥረ ነገሮችን (Molecular com¬pounds) የተለያዩ በሽታዎች ላይ በመሞከር
- በገበያ ላይ ያለ መድኃኒት በሚያሳየው ያልተጠበቀ ውጤት ምክንያት ለሌላ ጥቅም በማዋል ወዘተረፈ
1.2. Development: ምርምር መስራት
• ከላይ ከተገለፁት መንገዶች ውስጥ በአንዱ ተስፋ ሰጪ ንጥረ ነገር (promising compound) ካገኙ በኋላ ቀጣዩ ሂደት የሚሆነው ስለ ንጥረ ነገሩ የሚከተሉት ነገሮች ላይ ምርምር መስራት ይሆናል። - ይሄ ንጥረ ነገር ወደ ደም እንዴት ይገባል (absorption)? በደም አማካኝነት ወደ ተለያዩ ህዋሳቶቻችን እንዴት ይሰራጫል (distribution)? እንዴት የመድኃኒትነት ሥራውን ለመጀመር ራሱ ያዘጋጃል(Metabolism)? እንዴትስ ከሰውነታችን ይወገዳል (excretion)?
- ሰውነታች ውስጥ ገብቶ ሥራውን የሚሰራው እንዴት ነው (mechanism of action)
- መጠኑ (dosage)
- የመውስጃ መንገዱ (route of administration) ወዘተ የሚጠኑበት ደረጃ (step) ነው።
2) Preclinical Research: ከ1 -1.5 ዓመታት ይወስዳል።
• ይህ ንጥረ ነገር ሰው ላይ ከመሞከሩ በፊት ሊያስከትል ስለሚችለው ጉዳት (serious harm) እንስሳት ላይ የሚሞከርበት ሂደት ነው። ሁለት አይነት መንገዶች አሉ። Good Laboratory Practice (GLP)ን በመከተል - In vitro (ቤተሙከራ ውስጥ በብርጭቆ) ወይም
- In vivo (ህይወት ባላቸው እንስሳት ላይ) ይሞከራል።
3) Clinical research: ከ 5-7 ዓመታት ይወስዳል።
ደህንነቱ የተረጋገጠለት ንጥረ ነገር የሰው ልጅ ላይ የሚሞከርበት ደረጃ ነው።
የተለያዩ ደረጃዎች አሉት።
PHASE 1:
ከ 20-80 ፈቃደኛ እና ጤነኛ ሰዎች ላይ የሞከራል
ብዙ ወራትን ይወስዳል
አላማው፡ ደህንነቱን (safety) እና መጠኑን (dosage) ለማወቅ ነው
PHASE 2
ከ100- 300 መድኃኒት የሚፈለግለት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ላይ ይሞከራል።
እስከ ሁለት ዓመታት ይወስዳል።
አላማው: የጎንዮሽ ጉዳቱን (side effect) እና ፍቱንነቱን (efficacy) ለማወቅ
PHASE 3፡
ከ 1000-3000 መድኃኒት የሚፈለግለት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ላይ ይሞከራል።
ከ 1-4 ዓመታት ይወስዳል።
አላማው፡ በቁጥር ብዙ ሰዎች ላይ ፍቱንነቱን እና ሌሎች አላስፈላጊ ጉዳቶችን ለማየት ነው።
እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ መድሃኒት ነው ለፈቃድ (ap¬proval) ወደ ተቆጣጣሪ እና ፈቃድ ሰጪ ክፍል (Regula¬tory authority, in our case it is EFDA, the former EFMHACA) የሚላከው። ይሄ ራሱን ችሎ ከ 1-2 ዓመታት ይወስዳል።
PHASE 4: post-marketing surveillance
ምንም እንኳን እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ መድኃኒት ብዙ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ተሞክሮ ደህንነቱ የተረጋገጠ ቢሆንም አሁንም ግን ስለ መድኃኒቱ በቂ እና ሙሉ መረጃ የሚኖረን መድኃኒቱ ገበያ ላይ ወጥቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለዓመታት ወስደውት ደህንነቱ እና ፍቱንነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
ይህን ያላሟላ መድኃኒት ከገበያ ላይ ተሰብስቦ ይወገዳል።
ይህን ያክል ስለ አዲስ መድኃኒት አመራረት ካወራሁ ስለ COVID-19 መድኃኒት ግኝት የተባለው ላይ ያሉኝ ጥያቄዎች
- መድኃኒቱ የትኛው ደረጃ ላይ እንደደረሰ በግልፅ አልነገሩንም
- ምርምሩን የጀመሩት “የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ነው” ብለዋል። ነገር ግን አይደለም እንኳን የዛን ጊዜ አሁንም እንኳን ስለበሽታው በቂ የሆነ መረጃ የለም እና ምንን መነሻ አድርገው ምርምሩን የጀመሩት?
- መድኃኒቱ የመከላከል አቅምን የሚጨምር (immu¬nity booster) ፡ መርዛማነት የሌለው (non-toxic) እና አዋጭነቱ የተረጋገጠ (feasible) ነው ብለዋል። ይህን ደሞ ማወቅ የሚቻለው STAGE 3 (clinical research) ላይ ነው። እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ለማለት ደሞ በጣም ይከብዳል። እና ነገሩ እንዴት ነው? ትንሽ ግራ አያጋባም?
በጨዋ ደንብ ሰከን ብለን እንወያይበት እስኪ።
አመሰግናለሁ።
ከሐኪሞች አስተያየት የምንረዳው ነገር መድኃኒት ብዙ ውጣ ውረድ ስላለው አሁን ለተጋረጠብን የኮሮና ወረርሽኝ መዘናጋት እንደሌለብን ነው። ሌላው ክርክር ሌላ ጊዜ ይደርሳል፤ አሁን የባለሙያዎችን ምክር እንስማ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012 ዋለልኝ አየለ