ኢትዮጵያና የሲኒማው ዓለም የተዋወቁት በእምዬ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነው። ይህም የዓለማችን የመጀመሪያው ፊልም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1895 ተጠናቆ በፓሪስ ከተማ ለእይታ ከቀረበ ሦስት ዓመታት በኋላ ነው። በኢትዮጵያ ፊልም ዙሪያ /A Brief overview of Ethiopian film History/ አጭር የዳሰሳ ጥናት የሠራው ክንድነህ ታመነ የተባለ ሰው ከዚህ ሌላ ተጨማሪ ሃሳብ አካቷል።
በጥናቱ ላይ እንደተጠቀሰው፤ አንዳንድ መዛግብት ላይ ኢትዮጵያ ከሲኒማው ዓለም ወይም ከፊልም የተዋወቀችበትን ዘመን ከዓለም በ26 ዓመታት ወዲህ ያዘገየዋል። ክንድነህ እንዳተተው ግን የተባለው ጊዜ የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት በኢትዮጵያ የተከፈተበት ነው። ታድያ ምንም እንኳ የመጀመሪያውን ሲኒማ ቤት ኢትዮጵያውያን «የሰይጣን ቤት» እያሉ ቢጠሩትና በቶሎ ተቀባይነት ያገኘ ባይሆንም፤ ከሌሎች አፍሪካ አገራት አንጻር ግን በጊዜው የኢትዮጵያ ሲኒማ እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነበር ሲል ጥናቱ ላይ ይጠቅሳል። ይህም በቅኝ ግዛት ካለመያዟ ጋር የተያያዘ ነው።
ሌሎች የአፍሪካ አገራት በገዢዎቻቸው ጫና የተቀበሉትን ኢትዮጵያ ወስዳ እንጂ ተጭኖባት አልነበረም ይላል አጥኝው። እንግዲህ በዚህ መሰረት፤ የኢትዮጵያ ፊልም ታሪክ ከአጼ ምኒልክ ዘመን ይጀምራል። ከዛም በኋላ በነበሩት ነገሥታትና መንግሥታትም ዘርፉ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፏል። ፖለቲከኞች ተጠቅመውበታል፣ ገዝተውታል፣ ሲፈልጉ አፍርሰው ዳግም ሠርተውታል። አሁንም ችግሮቹን ለመፍታትና ከሃሳብም ሆነ ፖለቲካ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ሃሳብ ያላቸውና ጥረት የሚያደርጉ አልጠፉም።
አሁን ያለንበትን ጊዜ ስንታዘብ፤ የአሜሪካው ሆሊውድ የምድሩን ጨርሶ ጠፈር ላይ ወጥቷል። የህንዱ ቦሊውድ ባህሉን አስተዋውቆ ሲያበቃ በሕዝቡ ተቃውሞ የሚደርስብትን የባህሉን ተቃራኒ ማሳየት ጀምሯል። ሁሉም ዝም ባለበት ሰዓት ትንሿም ድምጽ ትሰማለችና፤ በዚህ ጊዜ የአገራችን የፊልም ዘርፍ ቢጠነክር እንኳን በሙያቸው እርካታን ለሚያገኙት ባለሙያዎች ለአገርም ብዙ ትርፍ ማግኘት የሚቻልበት ጊዜ ላይ መሆናችን ግልጽ ነው።
ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት በብዛትም በውበትም የሚገኙባት አገር ለፊልም ጽሑፍ፣ ለመጽሐፍ ታሪክ፣ ለግጥም ሃሳብ የሚሆን ግብዓት ሊጠፋ አይችልም። ግብዓቱ እያለ በሌላው ላይ ጫና ፈጥሮ ትኩረት የሚስብ አዲስ ሥራ ማምጣት ላይ አሁንም ወደኋላ ይቀራል። የፊልሙን ዘርፍ ወደፊት እንዲራመድ ለማስቻል እምነት ከሚያዝባቸውና ተስፋ ከሚጣልባቸው መካከል ደግሞ የሙያ ማኅበራትን እናገኛለን።
የፊልም ሙያ ማኅበራት- በኢትዮጵያ
በአገራችን በፊልሙ ዘርፍ ከተቋቋሙ ማኅበራት መካከል በምሥረታ ቀዳሚው የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር ነው። ይህም በ1985ዓ.ም አካባቢ እንደተቋቋመ አንዳንድ ሰነዶች ይጠቁማሉ። እንደተመሠረተም አስቀድሞ ከነበረውና ከኢህአዴግ ኢትዮጵያን መያዝ በኋላ የፈረሰው የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን አባላት ተቀላቅለውታል።
ማኅበሩ በየትኛውም የስኬት ደረጃ ቢገኝ አልያም የሚነቀፍበት ብዙ እንከን ቢኖር እንኳ፤ የመጀመሪያው የፊልም ማኅበር በመሆን ለተከታዮቹ የከፈተው መንገድ ግን መኖሩ አይካድም። በየጊዜውም ያሳካቸው ሥራዎች ያሉ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ ከሚዘጋጁ የፊልም ፌስቲቫሎች ባሻገር የፓን አፍሪካን ፊልም ሠሪዎች ፌዴሬሽን አባል መሆን ችሏል።
ከዚህ ማኅበር በኋላ አላቲኖስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮድዩሰሮች ማኅበር ተቋቁሟል። በተለይ አላቲኖስ የፊልም ሠሪዎች ማኅበር የተለያዩ የፊልም ላይ ውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ስልጠናዎችን በማመቻቸትና ልምድ በማካፈል እንዲሁም በሌሎች በርካታ ሥራዎች ውስጥ ይሳተፋሉ። አሁን ላይ ምስጉን የሆኑ የፊልም ዳይሬክተሮችና አዘጋጆችም ከእነዚህ ማኅበራት ወጥተዋል።
በድምሩ እነዚህ ሦስት ማኅበራት በፊልሙ ዘርፍ አሉ ማለት ይቻላል። ታድያ እነዚህ ማኅበራት ብዙ ጊዜ በግል፤ ጥቂት ጊዜ በጋራ ለውጦችን ለማምጣት ጥረዋል። ያም ሆኖ በቅርብ ላሉ ባለሙያዎች ከሚታዩ መጠነኛ ልዩነቶች ባሻገር በአገር ደረጃ ግን እምብዛም ለውጥ አላስመዘገቡም። የማኅበራቱ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ምን ችግርስ ኖሮባቸው ነው? የሚሉ ጥያቄዎች አነሳን።
የማኅበራቱ እንቅስቃሴ
ባሳለፍነው ዓመት ማብቂያ አካባቢ «የፊልም ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎቹ» በሚል ዐብይ ርዕስ የውይይት መድረክ ተዘጋቶ ነበር። ይህም በኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል እና ቫምዳስ ሲኒማ በጋራ ያዘጋጁት ነው። በእለቱ ትኩረት አግኝተው ለውይይት ከቀረቡት ሃሳቦች መካከል አንዱ የፊልም ሙያ ማኅበራት እንቅስቃሴዎች ናቸው። ይህንንም በተመለከተ ተወዳጅነትን ያተረፉ ፊልሞችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ሄኖክ አየለ «በኢትዮጵያ የፊልም ሥራ ውስጥ የማኅበራት እንቅስቃሴ» በሚል ርዕስ አንድ ዳሰሳ አቅርቧል። ሄኖክ በመግቢያው የኢትዮጵያውያንን የኅብረት እንቅስቃሴ አንስቷል። እዚህ ላይ ይህችን ስንኝ ጠቀስ አደረገ፤
«አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፤
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል።» አብሮነትና የጋራ ሥራ ያውቃሉ በሚባሉ ሕዝቦች መካከል፤ እድርና እቁብን የመሰሉ ግዙፍ ተቋማዊ እንቅስቃሴዎች በሚከወኑባት አገር፤ አብሮነት እጅግ ጎድሎ የመታየቱን ነገር ሲጠቅስ ነው። በኢትዮጵያ የፊልም ሙያ ማኅበራት ነገርም ከዚህ መንቶ ግጥምና ከያዘው ሃሳብ ጋር ይገጥማል።
የማኅበራቱ ችግር ምንጭ ከሦስት ዋናዋና ነጥቦች የዘለለ አይደለም። እነዚህም የእውቀት፣ የገንዘብ እና የስነምግባር እጥረት ወይም ጉድለት ናቸው። በመቋቋሚያቸው በተሰጣቸው ትርጓሜ ማለትም «ለትርፍ ያልተቋቋሙ፣ የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ተቋማት ጋር ለመተባበር በአባላቱ ስምምነት የተመሠረቱ የሰዎች ስብስብ» ከሚለው ጋር ተመሳስለው አይገኙም።
የፊልም ሙያ ማኅበራት ለምን ይጠቅማሉ?
ከላይ ባልኳችሁ መድረክ ላይ የፊልም ባለሙያው ሄኖክ ባቀረበው ዳሰሳ መሰረት ማኅበራት በቀዳሚነት የጋራ ሀብቶች፣ እድሎችና መብቶችን በጋራ ለመጠቀም ያስችላሉ። ይህም ደግሞ አንዱ ባለሙያ ወይም ግለሰብ ለብቻው ከሚኖረው ኃይል ይልቅ ተመሳሳይ እሳቤና ዓላማ ካላቸው ጋር በአብሮነት ሠርቶ የሚኖረውን አቅምና ኃይል ያሳይበታል።
በአገራዊ ጉዳይ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚቻለውም በማህበር ሲደራጁ ነው። ከዚህም ባሻገር ሁሉም በሙያው ያለበትን ኃላፊነትና ግዴታ ለመወጣት ማስቻሉ ጥቅሙ ነው። ታድያ ግን የፊልም ሙያ ማኅበራትን የማይፈልጉ መኖራቸው በዳሰሳው ተካቷል። ለምን አይፈልጉም? በየጊዜው የሚፈጠረውን ግርግር ስለሚወዱትና በየግላቸው ጥቅም ለማግኘት ስለሚሹ።
«በዚህ ውስጥ የሚገኙት አንድም ፊልሞችን የሚሰርቁ ናቸው። ሲኒማ ቤቶችም የማይገባ ጥቅም ስለሚያስገኛቸው ይስማማቸዋል። ከዛ ባሻገር ከማኅበራት ጋር በተያያዘ ጥሩ ትዝታ የሌላቸውና የማኅበርን ጥቅምና ወሳኝነቱን ባለመረዳት ለብቻ የሚንቀሳቀሱ አሉ።» ይላል ሄኖክ። የማኅበራትን ወሳኝነት በቅድሚያ መረዳት ለሁሉም ባለሙያዎች እንደሚያስፈልግ ያነሳልም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር በኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ ላይ ተሳትፎ አድርጓል። ይህም ቢያነስ በመንግሥት ሙያው ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር ይልቁንም እንዲያግዘው ለማስቻል የመጀመሪያው እርምጃ ሆኖ ይቆጠራል።
ከዳሰሳው ሻገር ብለን ስንመለከት፤ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ «አንስቻለሁ» ያለውን «ቅድመ ግምገማ» እናስታውስ። ቢሮው ይህን ውሳኔ ሲወስን ምንም ዓይነት አማራጭና ሌላ መንገድ ያስቀመጠ አለመሆኑ የማኅበራቱን እንቅስቃሴ አስፈላጊነት ይነግረናል። ልክ እንደሌሎች አገራት፤ ማኅበራት ለፊልሞች ደረጃ መስጠቱን ወይም «ሬቲንግ» እንዲሠሩ ይጠበቃል።
እንደምናየው ከሆነ በትኩረት ሠርተው ተጠብበው ካሳዩት በላይ የይድረስ ጥደው በወራት ሁለት ሦስት ያደረሱት ያተርፋሉ። ታሪክን እናሳይ ብለው የተነሱት ሲከስሩ ከአውሮፓ ሃሳብ ሰርቀው፤ መንገድ ተውሰው የሚያሳዩት ያልደከሙበትን ዋጋ ይቀበላሉ። ይህ ያለጥርጥር የማኅበራት መዳከም ያመጣው ነው። የማኅበራት መጠናከር የተሻለ ባለሙያን ማውጣት ብቻ ሳይሆን የተመልካችንም ጣዕም ወርዶ መሥራት ይችላል።
ለባለሙያው እንዲሁም ለአገራችን የፊልም ዘርፍ ይህን ጥቅም መስጠት የሚችሉ ማኅበራት ለምን አቅም አጡ? ብለን ብንጠይቅ ደግሞ «ንቁ የአባላት ተሳትፎ ማጣት ማኅበራትን አዳክሟል።» ይላል ሄኖክ። አባላት ከሌሉና በሚገባ ካልተንቀሳቀሱ ማኅበራት አይታሰቡምና። ታድያ የማኅበራቱ ጥቅም ባለቀ ሰዓት የሚታያቸውና ሲዘራና ሲታጨድ ሳይገኙ ፍሬውን ለመብላት የሚታደሙም መኖራቸው ለብዙዎች ትዝብት ግልጽ ነው። ይህ ለምን ሆነ? ምንአልባት ብዙዎቹ ባለሙያዎች የማኅበርን ጥቅም አልተረዱትም ይሆናል።
እናብቃ! በግላቸው ተንቀሳቅሰው ለራሳቸው ለውጥ ያመጡ፤ አልፈውም የሲኒማውን ዓለም መነቅነቅ የቻሉ ባለሙያዎችን እናውቃለን። ለኢትዮጵያ የፊልም ችግር በቋሚነት መፍትሄ መስጠት የሚቻለው ግን በአንድና ሁለት አዳዲስ ሃሳብ በያዙ ፊልሞች አይደለም፤ ሥራውን ተከትለው ማደግ በሚችሉ ተከታዮች ነው። ሰባሪ የመጣ ቀን ለብቻው የተገኘ እንጨት ነውና የሚሰባበረው፤ ተሰባስቦ ኃይልን በማጠንከር፤ በፊልም ሙያ ማኅበራት አንድ እርምጃ አራምዶ የአገርን የፊልም ዘርፍ ወደ ከፍታው ማውጣት እንደሚገባ ማመን ይበጃል። ኢትዮጵያዊነትንና መሰባሰብን በፊልሞች ለማሳየት ከመሞከር በፊት ሰብሰብ ብሎ እንደ ኢትዮጵያዊ በጋራ መሥራትን አያሻም ትላላችሁ? ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
ሊድያ ተስፋዬ