የፊልሙ ርዕስ፡- ኮንታጅን
ፀሐፊ፡- ስኮት በርንስ
ዳይሬክተር፡- ስቴቨን ሶደርበርግ
የተሰራበት ዘመን፡- እ.አ.አ 2011
የፊልሙ ርዝማኔ፡- 1:46
ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በሆሊውድ አማካኝነት የተሰራ ምናባዊ የፈጠራ ውጤት ነው:: ‹‹ልብወለድ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው›› ቢባልም አንዳንዴ ደግሞ እንዲህ የገሃዱ ዓለም የልብወለድ ነፀብራቅ ይሆናል:: ልክ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ የኮንታጅን ፊልም ነፀብራቅ እንደሆነው ማለት ነው:: በእርግጥ ብዙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መነሻቸው ኪነ ጥበብ ነው:: ከአውሮፕላን በፊት በሰማይ የሚሄድ ግዑዝ አካል እንደሚኖር የኪነ ጥበብ ሰዎች መጻፋቸው ተደጋግሞ የተነገረ ነው:: በዚያው ልክ ዘመኑን እየተከተሉ ብዙ የውጭ ፊልሞች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኩራሉ::
ይህኛው ደግሞ ይለያል:: ከሳይንስ ፈጠራ ይልቅ ትንቢት ሁሉ ያለበት ይመስላል:: ከመሰረታዊ የሳይንስ ባህሪ ተነስቶ ወደፊት ሊሆን የሚችለውን መናገር ብቻ ቢሆን ኖሮ ብቃታቸውን ብቻ አድንቀን እናልፍ ነበር:: ግርምትን የሚፈጥረው ግን ከተፈጥሮ ሳይንስ ይልቅ ማህበራዊ ሕይወትንም ቀድሞ ማሳየቱ ነው:: እርግጥ ነው ማህበራዊ ሕይወትንም ወደፊት ምን ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል፤ አንዳንድ የማይገመቱ ነገሮች ሆነው ሲታይ ግን ምን አይነት ትዕንቢት እንደሆነ ያስገርማል:: ለማንኛውም ግርምት የሚፈጥሩትን ነገሮች ወደ ፊልሙ ይዘት ስንገባ እናወራቸዋለን::
ኮንታጅን ፊልም እንደ አዲስ እየታየ ነው:: ይህ ፊልም ብዙዎችን አስገርሟል፣ አስደንግጧል፣ ተስፋ ሰጥቷል፣ ግራ አጋብቷል… በአጠቃላይ ምስቅልቅል ስሜት እየፈጠረ ነው:: በዘመኑ ከነበረው በላይ አሁን ላይ ተመልካች እያገኘ ነው:: እንዲያውም በዘመኑ ከፍተኛ ትችት ቀርቦበታል:: ለእውነት ከመቅረብ ይልቅ ሳይንሳዊ ፈጠራው በጣም ተጋነነ ተብሎ ወቀሳ ደርሶበት ነበር::
ኮንታጅን ፊልም በዚህ ወቅት አጀንዳ የሆነበት ምክንያት ወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው:: በዚህ የጭንቅ ወቅት ዓለም ስለመዝናኛ የሚያወራበት ጊዜ አልነበረም፤ ዳሩ ግን ይሄ ፊልም ደግሞ ከመዝናኛ ይልቅ አሁን ያለውን የዓለም ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ መሳየት የቻለ አስገራሚ ፊልም ሆኗል:: ዓለም በዚህ ወቅት እንኳን ስለፊልም ሊያወራ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮችንም ረስቶ ባለበት ይሄኛው ፊልም ግን ራሱ ኮሮና ሆኖ መጣ:: በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተውን ነገር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሆነ:: ድንጋጤን ፈጠረ፤ ትንሽም ብትሆን የተስፋ ጭላንጭል ቢያሳይም አስደንጋጭነቱ ይበልጣል:: ምናባዊ ፈጠራ ነው ብለን እንዳናልፈው እስከአሁን የሆኑት ነገሮች ፊልሙ ላይ በሚታየው ልክ ነው::
የፊልሙ አስደንጋጭነት እዚህ ላይ ነው፤ መድኃኒት ካልተገኘለት ከ26 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በቫይረሱ ይሞታል:: ፊልሙ ሲጀማምር አካባቢ ደግሞ የተለያዩ አገራትን የህዝብ ብዛት ያሳያል:: መረጃው ከ9 ዓመታት በፊት መሆኑን ልብ እያልን:: ያለው የተስፋ ጭላንጭል ደግሞ ክትባት ይገኝለታል፤ ችግሩ ግን ክትባቱ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ተግባር ለመሸጋገር ችግር ይገጥመዋል:: ክትባቱን ለማግኘት ግርግርና ዘረፋ ይፈጸማል፤ በዚህም ሌላ የህይወትና የንብረት ጥፋት ይደርሳል::
ወደ ዋናው የፊልሙ ይዘት እንግባ::
አንዲት ከሚኒሶታ ሚኒያፖሊስ ከተማ የተነሳች ሴት ለሥራ ጉዳይ ቻይና ትሄዳለች:: ቻይና እንደሄደችም ከአንድ ምግብ ቤት የበላችው ምግብ ስለተመቻት ሼፉን አስጠርታ አድናቆቷል ትገልጻለች:: ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ተጨባብጠውና ተቃቅፈው ፎቶም ይነሳሉ:: በዚህ መጨባበጥ ነው ቫይረሱ የያዛት:: የቻይና ቆይታዋን ጨርሳ ቀጥታ ወደ ቤቷ አልሄድችም:: ከትዳር ጓደኛዋ ውጭ ካለው የወሲብ ጓደኛዋ ጋር ለመገናኘትም ወደ ችካጎ ትሄዳለች:: ሽርሽሯን ከጨረሰች በኋላም ወደቤቷ ሄደች:: ከዚያ በኋላ በፀና ታመመች:: ባሏ ወደ ሆስፒታል ቢወስዳትም መትረፍ አልቻለም:: ባሏን ጨምሮ ከዚያ በኋላ የነካቻቸውና የተነካኩት ሁሉ ይታመማሉ::
የቫይረሱ መነሻ ደግሞ እንዲህ ነው::
በግሬደር የሚቆረጡ ዛፎች እየተገነደሱ ይወድቃሉ:: ዛፎች ሲወድቁ ብዙ የሌሊት ወፎች ግርርር ብለው ይነሳሉ:: አንደኛዋ የሌሊት ወፍ ሙዝ የመሰለ ነገር ከአፏ ይወድቃል:: ይሄን ከአፏ የወደቀ ፍሬ አሳማው ይበላዋል:: ያ አሳማ ሲታረድ ደግሞ ሼፉ ይነካዋል:: ሼፉ እጁን ልብሱ ላይ ሲጠራርግ ሁሉ ይታያል:: ያንን አሳማ በነካ እጁ ነበር ሰላም ያላት:: እንግዲህ ቫይረሱ በዚህ አይነት ንክኪ ይተላለፋል::
የፊልሙ መቼት በዋናነት አሜሪካ እና ቻይና ሲሆን በተለይም ቻይና የቫይረሱ መነሻ ናት:: ይሄ ምናባዊ ፈጠራ አሁን ያለውን ገሃዳዊ የኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታ እያሳየን ነው:: የኮሮና ቫይረስ መነሻ ቻይና ነው:: እስከአሁን ባለው መረጃም የተጠቂዎች ቁጥር የሚበዛው አሜሪካ ውስጥ ሆኗል:: በእርግጥ ይሄ መረጃ በየዕለቱ ስለሚቀያየር ለጊዜው ማሳያ ሊሆን አይችልም::
ምናባዊ ፈጠራ የሆነው ፊልም በአሜሪካና በቻይና መካከል ፖለቲካዊ ፍጥጫ ያሳያል (ልብ በሉ እንግዲህ ይህ ሁሉ የተጻፈው ከ9 ዓመት በፊት ነው):: ቫይረሱ ሆን ተብሎ የተሰራጨ ስነ ሕይወታዊ ጦርነት እንደሆነ ይገልጻል:: በሚደረጉ የወንጀልም ሆነ የህክምና ምርምሮች በአይን የማይታይ ረቂቅ ቫይረስ ነው፤ ለሽብርና ለፖለቲካ ፍጆታ የተሰራጨ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ:: ይሄን ይዘን አሁን ያለውን ገሃዳዊ ሁኔታ ደግሞ እንየው፤ ይሄው አሜሪካና ቻይና እየተነታረኩ ነው:: ቻይና አሜሪካ ናት የፈጠረችው ትላለች፤ አሜሪካ ደግሞ የቻይና የአመጋገብ ሥርዓት ያስከተለው አደገኛ ቫይረስ ነው ትላለች::
ይሄ ፊልም ከፍተኛ ፖለቲካዊና ህክምናዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው:: ተመራማሪዎች ስለዚህ ቫይረስ ያለቀለት ጥናት አላቀረቡም:: የበሽታው ምልክቶችም ሆኑ የመከላከያ መንገዶች እየተቀያየሩ ነው:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምናልባት ይሄ ፊልም ተፅዕኖ እያሳደረባቸው እንዳይሆን እፈራለሁ:: የሚነገሩ ጥንቃቄዎችም ፊልሙ ላይ የሚታየው አይነት ነው:: ፊልሙ ላይ ብዙዎች የፊት መሸፈኛ (ማስክ)አድርገው ይታያሉ::
በፊልሙ ላይ ቫይረሱ ያለበት ሰው የነካውን ዕቃ የነካ ሁሉ ይታመማል:: በጉዞ ቦታዎች ሁሉ መበካከልና የቫይረሱ መሰራጨት ይታያል:: በዚህ ልብወለድ ፊልም ውስጥ ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፣ መስሪያ ቤቶች ሥራ ያቆማሉ፣ መዝናኛ ቤቶችና ህዝብ የሚበዛባቸው ቦታዎች ፀጥ ረጭ ይላሉ:: ይሄው በገሃዱ ዓለም ሁሉም እየሆኑ ነው:: በተለይም በአሜሪካ እና በአውሮፓ አገራት ፀጥ ረጭ ብለዋል:: በፊልሙ ላይ በሽታውን ለመከላከል የሚመከሩት ነገሮች አሁን እየሆነ የምናየው እጅን መታጠብና አካላዊ መራራቅ ነው::
የፊልሙ አስገራሚ ትንቢት ደግሞ ይሄኛው ነው:: በዚህ ምናባዊ ፈጠራ ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጥቁር ነው:: እነሆ በአሁኑ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ናቸው:: ምን አይነት ግጥምጥሞሽ እንደሆነ ግራ ያጋባል:: መቼም ነጮች ለጥቁሮች ይህን ያህል ቦታ የላቸውም:: እየሆነ የምናየው ነገርም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ ነጮች ናቸው:: እንኳን ከዘጠኝ ዓመት በፊት አሁንም ቢሆን ነጮች ያሉበት ነው:: ኢትዮጵያዊው ጥቁር የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲመረጡ ዜና የሆነው ጥቁር መሆናቸው ነበር::
ይሄ ፊልም እንዴት አሰበው? ሳይንሳዊ ባህሪውን በምርምር ያደረጉት ነው እንበል፤ እንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎችስ ምን ይባላሉ?
በፊልሙ ላይ የታዩት ነገሮች እነሆ በኮሮና ወረርሽኝ ላይ የምናያቸው ናቸው:: አሁን የቀረ ወደፊት የሚሆነው ነገር ነው:: ክትባቱ በአፍንጫ የሚወሰድ ነው:: :: በአንዳንድ ውጭ ሚዲያዎች እንዳየነውም የኮሮና ቫይረስን ለመለየት በአፍንጫ በኩል ምርመራዎች እየተደረጉ ነው:: እንዲያው ሳይንሳዊ ምርምሩም በአፍንጫ የሚወሰድ መድኃኒት ትክክል መሆኑን በእውኑ እያረጋገጠ ከሆነ ግን በብዙ ያስገርማል:: ቫይረሱ ሰው ሰራሽ ነው ብሎ ለመገመትም ያስገድዳል::
ፊልሙ ማህበራዊ አኗኗርን ያቃውሳል:: ከፍተኛ የፍርሃት ስነ ልቦና ይፈጥራል:: ተሰባስቦ ማየትን ይፈራሉ፤ ሰላምታና መነካካት ያስደነብራቸዋል:: ከበሽታው በላይ ጭንቀትና ፍርሃት ያንቀጠቅጣቸዋል:: በዚህም የተለመደው ማህበራዊ ህይወት ባህሪውን ይቀይራል::
ይሄን ነገር በሀሜት ደረጃ ከሚወራው ጋር ማነፃፀር እንችላለን:: ጥናታዊ መሰረት ባይኖረውም ሃይማኖትን የሚቃወሙ (በተለምዶ ሰይጣን አምላኪዎች የሚባሉት) የፈጠሩት ነው ይባላል:: ምክንያታቸው ደግሞ ሃይማኖትና ማህበራዊ ህይወትን ለማፍረስ ማለት ነው:: የሃይማኖት ዝግጅቶች በመሰባሰብ የሚደረጉ ናቸው፤ ከሃይማኖት ጋር የዳበሩ ባህሎችና ማህበራዊ ህይወትም እንደዚሁ ነው:: ይህ ወረርሽኝ ግን እነዚያን የሚያስቀር ነው:: እነሆ እንደምናየው የሃይማኖት ተቋማት ሁሉ መደበኛ ዝግጅቶቻቸውን አጥፈዋል:: ማህበራዊ ህይወት እየቀረ ነው:: ሰላምታና መተቃቀፍ ከቀረ ቆየ::
ይህ ሁኔታ እየተለመደ ሲሄድ መደበኛ ህይወት ይሆናል:: እስኪ እናስታውስ! ገና የቫይረሱ መግባት እንደተሰማና ‹‹አትጨባበጡ!›› ሲባል የነበረንና አሁን ያለንበት እኩል ነው? ገና እንደተጀመረ የቆየው ልማድ ይዞን ላለመጨባበጥ በጣም ተቸግረን ነበር:: አሁን ግን ለምደነዋል:: ማንም ሲገናኝ የሚሸማቀቅ የለም:: ለምን አይጨብጠኝም ብሎ የሚጠብቅም የለም:: አያድርገውና ይሄ ነገር ከአንድ ዓመት በላይ ቢቆይ እኮ አለመጨባበጥ ልማድ ይሆናል::
ፊልሙ እንደሚያሳየን ሥርጭቱ የሚዛመትባቸው ቦታዎች አሁን እየተከለከሉ ያሉት አይነቶች ናቸው:: የአየር ማረፊያ አካባቢ ያሉ የሰዎች ማረፊያዎች፣ ሆቴሎች፣ ሊፍት… የመሳሰሉት ናቸው:: በነገራችን ላይ ይሄ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ማሳያ ሊሆን አይችልም:: ምክንያቱም በአሜሪካ፣ አውሮፓና ቻይና ያሉ አገራት እነዚህ ነገሮች የቅንጦት ሳይሆን የየዕለት ክንውን የሚፈጸምባቸው ናቸው:: የኢትዮጵያን ማህበረሰብ አኗኗር ስለማያውቁት ሊያካትቱት አይችሉም:: ስለዚህ ለሊፍት የተጠቀሙትን ዘዴ ለሞፈርና ቀንበር ልናደርገው እንችላለን:: አንዱ የጨበጠውን እርፍ ወይም ሞፈር ሌላ ገበሬ ቢጨብጠው ይተላለፋል ማለት ነው::
ለማንኛውም ይሄ ፊልም ነው:: እኛ በገሃዱ ዓለም ያሉ የህክምና ባለሙያዎች የሚነግሩንን እንስማ:: በዚህ ፊልም መደናገጥም የዋህነት ነው:: ይህ ሳይንሳዊ የምናብ ፈጠራ ነው:: የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት በመጨባበጥ የሚተላለፍ አሁን የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ብቻ አይደለም:: ብዙ የቫይረስ አይነቶች በመጨባበጥ ይተላለፋሉ:: ፊልሙን ከዚያ ተነስተው ይሰሩታል:: ባለፈው እሁድ አንድ የህክምና ባለሙያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲናገሩ ነበር:: ጉንፋን በጣም ቀላል ስለሆነና ስለማናካብደው ነው እንጂ በመጨባበጥ ይተላለፋል::
አሁን የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ሰው ሰራሽም ይሁን የተፈጥሮ በሽታ ዞሮ ዞሮ ገዳይ ነው:: ለእኛ የሚያዋጣን መጠንቀቁ ነው:: አሜሪካም ትፍጠረው ቻይና ለእኛ የሚተርፈን ጦሱ ነው:: ተጠንቀቁ የተባልነውን እንጠንቀቅ:: መቆጣጠር የምንችልበት ደረጃ ላይ ነን:: በውጭ የምንሰማው አይነት አስከፊ ደረጃ ላይ አይደለንም:: ካልተጠነቀቅን ግን ባለን የኑሮ ሁኔታ ከእነርሱም የከፋ ሊሆን ይችላልና እንጠንቀቅ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
ዋለልኝ አየለ