ተወልደው ያደጉት ወንጂ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተና ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ወንጂ ከተማ በሚገኘው ትግል ለእድገት ትምህርት ቤት ነው የተማሩት።በወንጂ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።በ1983 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ህክምና ትምህርት ክፍል ገብተው ለሰባት ዓመታት የህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው የዶክትሬት ዲግሪቸውን አግኝተዋል።ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በደቡብ ክልል ዱራሜ፥ አላባ፥ ሃዋሳና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመዘዋወር በሙያቸው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል።
በመቀጠልም የደቡብ ህዝቦች የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ከአምሰት ዓመት በላይ ሰርተዋል።በቢሮው በአገለገሉበት ወቅት በተለይም ኤች ኤይቪ ኤድስ በወረርሽኝ መልክ ተስፋፍቶ ሰለነበር የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ የማስተማር ሰራ በስፋት አከናውነዋል።ይህንኑ በሽታ የመከላከሉን ስራ በአገራቸው ብቻ አልተወሰኑም።ወደ ደቡብ ሱዳን በመዝለቅም የሙያ ግዴታቸውን ለሶስት ዓመታት ሲወጡ ቆይተዋል።በዋናነትም ከአስገደዶ መድፈር ጋር ተያያዞ ሊመጣ ከሚችለው የኤች አይቪ ኤድስና የአባላዘር በሽታን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን የሰነ አዕምሮ ጉዳቶችን መከላከል ላይ የሚስሩ ባለሙያዎችን የማብቃትና የማሰልጠን ስራ ማከናወናቸው ይጠቀሳል።
ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም በሙያቸው ለተለየዩ ድርጅቶች የማማከር ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ። በተጨማሪም በኢትዮ ኤፍኤም 107.8 ላይ ‹‹ የልጆቻችን ኢትዮጵያ›› የተባለ በስልጡን ሰነምግባር ላይ የሚያተኩር ፕሮግራም በማዘጋጀት የማህበረሰቡን አመለካከት የመቅረፅ ስራ እየሰሩ ነው።በዚህ የሬድዮ ፕሮግራም በተለይም በአሁኑ ወቅት ትልቅ የአለም ሰጋት በሆነው በኮረና ቫይረስ ዙሪያ ህብርተሰቡ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረውና ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል የማስተማር ስራ በስፋት እየሰሩ ይገኛሉ።በዚሁ ወቅታዊ የኮረና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ዙሪያ ከዛሬው እንግዳችን ከዶክተር ኤርሲዶ ለንደቦ ጋር ቆይታ አድርገናል።እንደሚከተለው ይቀርባል። አዲስ ዘመን፡- ውይይታችንን ስለ ኮረና ቫይረስ ሳይንሳዊ ምንነት በማስታወስ ብንጀምር?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ያው በተደጋጋሚ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲገለፅ እንደነበረው ኮረና የሚለው ቃል ክራውን ከሚለው የእንግሊኛ ቃል የተወሰደ ነው።ይህም ማለት ከስያሜ እንደምንረዳው የቫይረሱ ቅርፅ ዘውድ የሚመስል በመሆኑ ከዚያ የተወሰደ ነው።በነገራችን ላይ በኮረና ስር የተለየዩ ቫይረሶች አሉ።ከዚያ ውስጥ አንዱ ኮቪድ 19 የምንለው ነው።ኮረና ቫይረስ ከሌላው የሚለየው ልክ እንደ ኤች አይቪ ኤድስ ዘረመሉ አር ኤን ኤ ቫይረስ አይነት መሆኑና የፕሮቲን ሽፋን ያለው መሆኑ ነው፡፡ይህ ቫይረስ የፕሮቲን ሽፋን ያለው መሆኑ ደግሞ በሙቀት ለማጥፋት የሚቻል መሆኑ እንደጥሩ ጎን ልንወስደው እንችላለን።ይህም ማለት ቫይረሱ የነካካቸውን ነገሮች በሙቅ ውሃ ብናጥባቸው ይጠፋል እንደማለት ነው።ቫይረሱ በዋነኝነት በመተንፈሻ አካላት በአፍጫ፥ በአፍና በአይን ይገባል።ከዚያ ትልቁ የሚያጠቃው የሰውነት አካል ሳንባ ነው።ይህም የሆነበት ምክንያት ዙፋኑ ላይ ካሉት ፕሮቲኖች ጋር መጣበቅ የሚችል የሳንባ ሌላ ክፍል ስላለ ነው።ለዚህም ነው የመተንፈስ ችግር የሚፈጥረው።በተጨማሪም ቫይረሱ ስንናገርና ስንተነፍስ እስከ አንድ ሜትር ተኩል ድረስ አየር ላይ ቆይቶ ይወድቃል። ነገር ግን ቫይረሱ የወደቀባቸው አካላት ላይ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ባህሪ አለው፡፡
የቫይረሱ የተፈጥሮ ታሪክ እንደወረርሽኝ ሲከሰት ምንም የህክምና አገልግሎት ባይሰጥ ምን ሊፈጠር ይችላል? ብለን ስንጠይቅ 80 በመቶ የሆነው ሰው ይድናል፤ 20 በመቶው ይታማመማል። ከዚያ ውስጥ ደግሞ አሁን ባለው መረጃ ከሶስት እስከ አራት በመቶ የሚሆነው ይሞታል።ይህ ቀላል ቁጥር አይደለም።ምክንያቱም ይህ ቫይረስ 100 ሰው አይደለም የሚይዘው ሚሊዮኖችን ነው።ለዚህ ደግሞ አሜሪካና ጣሊያን የደረሱበትን ሁኔታ ማየት ቀላል ነው። ስለዚህ እኛም ሰዎች እንደመሆናችን ወረርሽኙ ወደዛ ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።ስለዚህ በ100 ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያዙ ከሆነና 20 በመቶዎቹ በደንብ ታመው አልጋ የሚይዙ ከሆነ ያሉንን የጤና ተቋሟት በሙሉ በመሙላት ሌሎች በሽታዎች ፈፅሞ ማከም የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህም ከፍተኛ ሞትና ምስቅልቅል ሊፈጥር ይችላል። በሁለተኛው ደረጃ ከ100 ሺ ውስጥ አራትና ሶስት ሺ ሰዎች ሞት ማለት ትልቅ ጥፋትና የአገር ጉዳት ነው። ስለዚህ ጥቂት ሰው ነው ሊሞት የሚችለው ብለን የምንዘናጋበት ጉዳይ አይደለም።በጣም ኣሳሳቢና ገዳይ በሽታ ነው። በነገራችን ላይ 80 በመቶው ይድናል ተብሎ የሚነገረው ሰዎች በጣም ጭንቀት ውስጥ እንዳይገቡ
በማሰብ ነው። በእርግጥ የኢቮላን ያህል አስፈሪ በሽታ አይደለም።የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው።ከዚያ ጋር የሚወዳደር አይደለም።ነገር ግን ደግሞ የሚይዘው ሰው ብዛት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የህመሙ ዋና ዋና ምልክቶች የተለየዩ መረጃዎች ሲወጡ እንመለከታለን፤ በተለይ በቅርቡ ቫይረሱ የሆድ መታወክንና ተቅማጥም ሊያስከትል እንደሚችል ሰምተናል።ይህ ምን ያህል ተጨባጭነት አለው?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ልክ ነሽ ግን እስካሁን በተደጋጋሚ የሚነገሩት ምልክቶች ዋና ዋናዎቹ ብቻ ናቸው።ቫይረሱ በባህሪው ሁሉንም የሰውነት አካላት የማጥቃት አቅም ያለው ነው።ዋናው የመተንፈሻ አካላት ሲሆን ደረቅ ሳል፥ ከፍተኛ ራስምታት፤ ከዚያም ቀስ በቀስ የትንፋሽ እጥረት ያስከትላል።ነገር ግን እስካሁን ባሉት ሪፖርቶች እስከ 28 በመቶ የሚሆኑት ህሙማን የሆድ እቃ መረበሽ፥ ተቅማጥና ማስታወክ ያጋጣመቻው እንዳሉ እናያለን።ነገር ግን በእኛ አገር ተቅማጥና ተውከት የተለመደ በሆነበት ሁኔታ ተቅማጥ የያዘው ሁሉ በኮረና ቫይረስ ተይዞል ማለት አንችልም።በእኔ እምነት ግን አንድ ሰው ራሱን ለመጠርጠርና ወደ ጤና ተቋም ለመሄድ በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚታዩ ምልክቶች በቂ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከበሽታው አስከፊነት አኳያ እንደአገር ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራ በሚፈለገው ደረጃ ተሰርቷል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- እኔ ይህንን ጉዳይ በሁለት ጎኑ ነው የማየው። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ህይወት ባለቤት ከሆነ፤ የራሱ ህይወት የሚገደው ከሆነ ከወረርሽኙ መምጣት ጋር ተያይዞ ስለበሽታው ለማወቅ ይጥራል።በነገራችን ላይ በሽታው በአገራችን ውስጥ ሳይገኝም ብዙ ተወርቷል።አሁን ደግሞ ሁሉም መገናኛ ብዙሃን በሚባል ደረጃ ሌላ ጉዳዮችን ትተው ስለዚህ በሽታ እያወሩና ግንዛቤ እያስጨበጡ ነው የሚገኘው። ስለዚህ እኔ መስማት ለሚፈልግ ሰው የተሰጠው የእውቀት መረጃ ከበቂ በላይ ነው ብዬ ነው የማስበው።ሌሎች ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው አነስተኛ ነው ቢሉም እኔ አልስማማም።እኔ ላዝንላቸውና በቂ መረጃ አልደረሳቸውም ብዬ የማስብላቸው ሰዎች በገጠርና በሩቅ ስፍራ ያሉ፤ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ተደራሽ ያልሆኑ ዜጎች ነው።ለከተማው ሰው ግን የተሰራው የማስተማር ስራ እውነቱን ለመናገር በቂ ነው። ለእኔ የአስተማሪና የተናጋሪ እጥረት ሳይሆን ያለው የሰሚ እጥረት ነው ያለው። በዚህ ላይ መንግስትን መውቀስ ፍትሃዊ አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል መንግስት ስለበሽታው ባወራው ልክ ዝግጅት አላደረገም ብለው የሚያነሱ ሰዎችም አሉ?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ይሄ ጥያቄ በተጨባጭ የሚመለከተቻው አካላት ቢመልሱ የተሻለ ይመስለኛል። ነገር ግን እንደባለሙያ ከምመለከተው አንፃር ጉድለቶች ናቸው ብዬ የማስባቸው ነገሮች አሉ።ለምሳሌ ሰሞኑን ክልሎች በራቸውን እየዘጉና የህዝብ ትራንስፖርትን እያስቆሙ ይገኛሉ።ይህ ስራ በእኔ እምነት አሁን አልነበረም መሰራት የነበረበት።በተለይ አዲስ አበባ ላይ ቀደም ብሎ መሰራት ነበረበት።አሁንም የባስና የባቡር አገልግሎት በመሰጠት ላይ የሚገኘው። ይህም ተገቢ አይደለም። ይህንን ለማድረግ ደግሞ አስቀድሞ የአኮኖሚና የምግብ ዝግጅት ማድረግ ይገባል። ሰዎች እንደአቅማቸው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በየቀበሌው ለዚህ ስራ ኮሚቴዎችን የማደራጀት ስራ ሊሰራ ይገባል።ለምሳሌ የበሽታ መከላከል ኮሚቴ፥ የመረጃ ኮሚቴና የድጋፍ ኮሚቴ ማደረጀት ይኖርበታል። ይህ ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስራ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለነው አደጋ ላይ እንደመሆኑ ሁሉም ዘርፎች፤ ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች እዚህ ላይ ነው ማተኮር የሚገባቸው። ከዚያ አንፃር ምንአልባት በቂ አይደለም የሚል እምነት አለኝ።
በተጨማሪም ዝም ብሎ በተባራሪ ከምንሰማው በቂ የመከላከያ ግብዓት ለጤና ባለሙያዎች አለመኖሩን እገነዘባለሁ። እሱን እንግዲህ በሚመለከት መንግስት ከውጭ የማምጣትና እዚሁም የሚመረቱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን ገልጽዋል።እኛም ያሟላል ብለን እናምናለን። ደግሞም ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም።ምንአልባት በርከት ያለ ቁጥር ከሆነ የህሙማኑ መጠን ባለሙያውን የመጠበቅ ስራ በጣም ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው።በአጠቃላይ ግን ከመንግስት መዋቅር በበለጠ ዜጎች ላይ የማየው መዘናጋት በጣም ያሳስበኛል።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ይህንን ያህል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሰርቶ እያለና በመስራት ላይም እያለ የህብረተሰቡ መዘናጋት ከምን የመነጨ ይመስሎታል? ምንአልባት በቫይረሱ የሞተ ሰው ባለመኖሩ ይሆን?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ስላልሞተ ነው የሚለውንም ሃሳብ አስምሪበት። በእኛ አገር ወረርሽ ሲከሰት የመጀመሪያው አይደለም። ኤች አይቪ ሲከሰትም በተመሳሳይ መዘናጋት ይታይ ነበር።ሰዎች በብዛት እስከሚሞት ድርስ ብዙ መዘናጋት ነበር በህብረተሰቡ ዘንድ ይታይ የነበረው።ብዙ ሰዎች የሚገባውን አይነት ትኩረት እየሰጡ አልነበረም። ሰው መሞት ከጀመረ በኋላ ነው መንግስትም ሆነ ዜጎችም ትኩረት መስጠት የጀመሩት። እንዳልሽው ሰው ስላልሞተ የተፈጠረ መዘናጋት ሊሆን ይችላል።ሌላው የመዘናጋቱ ነገር የተፈጠረው ቫይረሱ የጠየቀው ጥያቄ ከእኛ የአኗኗር ዘይቢያችን በጣም ተቃራኒ የሆነውን መንገድ ነው። ለምሳሌ መቀራረብ፥ መተቃቀፍ፥ መጨባበጥ፥ ተሰብስቦ ማውጋት ቡና መጠጣት ሺ ዓመታትን ያስቆጠረ በጣም ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው። ይህንን ባህል እንድንቀይር ነው ቫይረሱ ተግዳሮት የደቀነብን።እናም እጅግ በለመድነውና በጠንካራው ባህላችን ስለመጣ ግራ ገብቶናል፤ ቶሎ ለመቀበልም አንገዳግዶናል።ደፍረን የምንነቃው ሰው ሲሞትብን ሊሆን ይችላል።ሌላው በእኛ አገር መረጃን እንዳለ የመቀበልና ወስዶ የመተግበር ችግር በስፋት አለብን። ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ደግሞ ይህንን አይነት በሽታ ሰው አይመልሰውም፤ አምላክ ነው የሚመለስው የሚል በጣም ስህተት የሆነ አለመካከት የሚያራምዱ አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ከተስፋ መቁረጥ የመነጨ ነው ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ይቅርታ አድርጊልኝና ይህ አስተሳሳብ ድንቁርና ያመጣው ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ድንቁርናቸውን በእምነት የሚሸፍኑ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የማይታየውን ለማመን የሚታየውን መካድ ድንቁርና ነው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች ይህንን ድንቁርናቸውን በእምነት ይሸፍናሉ።ጥንቃቄ ማድረግ ምንም እኮ ከእምነት ጋር ማያያዝ አያስፈልገውም።እጅን መታጠብ፤ ሳኒታይዘር መጠቀምና ከቤት አለውጣትና ቤት ሆኖ መፀለይ ካለማመን ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።ማድረግ የሚገባቸውን ሳያደርጉ በሌላው ማሳበብ ተቀባይነት የለውም።በኢትዮጵያ ታሪክ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ ቤተእምነቶቹ አመራሮች በወቅቱ ይህ አስተሳሰብ እንዲስተካከል መመሪያ እየሰጡ ባሉበት ከዚህ በተቃራኒው የሚሰብኩና የሚሰሩ ሰዎች ማየት ያሳፍራል።
ስለዚህ አሁን የሚቀረው ህግ ማስከበር ነው። ለምሳሌ የትግራይ ብሄራዊ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ላይ እስማማለሁ።በፌዴራል መንግስቱም ተመሳሳይ ነገር መፈፀም አለበት ብዬ አምናለው።ምክንያቱም የአንድ ሰው መዘናጋት ራሱ ላይ የሚያቆም ቢሆን ኖሮ ችግር የለውም። ይሄ ወረርሽኝ ነው። ስለዚህ የአንዳንድ ዜጎች መዘናጋትና ትኩረት ያለመስጠት ራሳቸውን ብቻ አይደለም የሚጎዳው። ሌላውንም ነው የሚጎዳው። ስለዚህ መንግስት ህግ ማስከበር ይገባዋል። ለተከታተይ ሳምንታት ሁሉም ቤቱ በተጨባጥጭ ተከቶ በራችንን ዘግተን መርምረን ቫይረሱ ሊኖርበት የሚችል ሰው
መለየት መቻል አለብን። ይህን ማድረግ ከቻልን ባጠረ ጊዜ ወረርሽኙን መቆጠጣር እንችላለን።ስለዚህ ህግ ማስከበሩ ስራ በጣም ጥብቅ ሊሆን ይገባል።ከዚህ አንፃር ክልሎች ያደረጉት እርምጃ በጣም ትክክል ነው።ይህም ሲባል የህዝብ ትራንስፖርት ሲዘጋ መሰረታዊ እቃዎችን የመዘዋዋሩን ተግባር አብረን ግን ማገት አይገባንም። በነገራችን ላይ የህዝብ ትራንስፖርትን መዝጋት ከተቻለ በተዘዋዋሪ ህዝቡ ሳይወድ በግዱ ቤቱ እንዲቀመጥ ያስገድደዋል።አዲስ አበባ ላይ ብዙ ሊሰራ ይገባል። በሌላ በኩል ግር ግር ባለበት ቦታ ሄዶ እባካችሁ ተራራቁ የሚባለው ነገር መፍትሄ ነው ብዬ አላምንም።ከዚያ ይልቅ ሰዎች ቤታቸው ቁጭ እንዲሉ የሚያስገድድ መፍትሄ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ረገድ እንደ ህንድ ያሉ አገራት እየወሰዱ ያሉት እርምጃ በመልካምነት የሚነሳ ነው፤ ይህ ተሞክሮ ወደ እኛ አገር መምጣት የማይችልበት ምክንያት አለ ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ልክ ነሽ ለእኔም እንደ አገር ህንድ ትልቅ ምሳሌ ናት። ምክንያቱም የድህነት ሁኔታውም ማህበራዊ ህይወታቸውም ከእኛ ጋር ይመሳሰላል።ህንድ የእኛን 10 እጥፍ ህዝብ ነው ያላት።ስለዚህ በጣም ትልቅና አስተማሪ የሆነ እርምጃ ነው የወሰዱት።ህንዶች ይህንን ባያደርጉና በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ከታመመባቸው በጣም ትልቅ ጥፋት ነው የሚያደርስባቸው።ለምሳሌ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ አንድ በመቶ እንኳ ቢታመምባቸው 13 ሚሊዮን ህዝብ ታመመባቸው ማለት ነው።ይህ ማለት የጤና ስርዓታቸው ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ነው የሚሆነው።ሞቱንም ሆነ ኢኮኖሚውን አይቋቋሙትም።ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ከእኛ ጋር የማይወዳደር ትልቅ ኢኮኖሚ ቢኖራትም ዘግታ ወረርሽኙን ለማስቆም የሄደችበት ርቀት አስገራሚ ነው።ከቻይናም የምንማረው ነገር አለ።ወረርሽኙ የተከሰተባት ውሃን ግዛት ውስጥ ያለውን 50 ሚሊየን ህዝብ ነው እንዳይነቀሳቀስ ያገዱት።በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ 2 ነጥብ 38 ቢሊዮን ህዝብ ቤቱ ለመቀመጥ ተገዷል።ስለዚህ እኛ ቢያንስ ቢያንስ አዲስ አበባ ላይ ቀድመን ማድረግ እንዳለብን ይሰማኛል።አሁንም ቢሆን ከቀረ የዘገየ ስለሚሻል ሁሉንም የአዲስ አበባ በሮች የመዝጋት ጉዳይ በአፋጣኝ ሊፈፀም ይገባል።
አዲስ አበባ፡- የከተሞችንና የክልሎችን በር መዝጋቱም ሆነ የህዝብ ትራንስፖርት ሙሉ ለሙሉ ማቆሙ በተለይ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ህይወት ለሚመራው ህዝብ አስቸጋሪ ነው፤ በርሃብ እንዲሞት ማስገደድም ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ይህ ምንአልባት ጥሩ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሰዎች ለምን መልሱን መስማት እንደማይፈልጉ አይገባኝም እንጂ በተደጋገሚ መልሱ ተነግሯል።በር ይዘጋ ሲባል አብረውት የሚመጡ የሚሰሩ ስራዎች አሉ።ከሚሰሩት ስራዎች አንደኛው የቀን ተቀን እንቅሳቀሴ ባያደርጉ መኖር ለሚያዳግታቸው ሰዎች የድጋፍ ስታራቴጂ መቀየስ አለበት።ይህም ሲባል ለሶስት ሳምንት የሚሆን ምግብና አንዳንድ መሰረታዊ ሸቀጦችን መስጠት ማለት ነው።ይህ ተግባር አንድ ላይ ከወረርሽኝ መከላከሉ ጋር አብሮ መታቀድ አለበት።በር የሚዘጋው አካል ይህንን አመቻችቶ ነው መዝጋት ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ከዚህ አኳያ በተለይ የከተማ አስተዳደሩ ዝገጁነት አለው ተብሎ ይታመናል?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ዝግጁነት ሳይሆን የፍላጎት ጉዳይ ነው የሚመስለኝ።በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ ብዙ ማካባድ አይገባንም።በየቀበሌው ለእነዚህ ሰዎች ድጋፍ መስጠት የሚችል አቅምና ጉልበት አለ።አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 330 ሺ ተማሪዎችን ሲመግብ አልነበረም እንዴ? እሱ ስርዓት አሁን የምንላቸውን ሰዎች አይመግብም? ስለዚህ የማሰብ፥ የማቀድ፥ የመፈፀም ጉዳይ ነው እንጂ የአቅም ጉዳይ አይደለም።በየሰፈሩ እኮ ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን መመገብ የሚችሉ በርካታ ሰዎችም አሉ።ደግሞም እየተሰበሰበ ያለውና መንግስት የመደበው ገንዘብ እዚህ ስራ ላይ ይውላል ብዬ አምናለሁ።ያሉትን የመንግስት ተቋማት በማደራጅት በአንዲት መመሪያ ስር አድርጎ የማንቀሰቅስ ተግባር ነው።ሌላው ከሌሎች አገራት ተሞክሮ ልንወስድ ይግባል።ስለዚህ ለእኔ ይህ ምክንያት የሚባለውን ላለመስማት ከፊት የሚደረደር ምክንያት ነው።በነገራችን ላይ ጦርነት ውስጥ ብንሆን ይህንን አይነት ጥያቄ ለመጠየቅ አንዳዳም ነበር።ሊሆን የሚገባው ጉዳይ እነዚህን ሰዎች እንዴት እናግዛቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ነው።ይሁንና እነዚህ ሰዎች ስላሉ በፍፁም በር መዘጋት የለበትም የሚል ክርክር ሳይንሳዊም አይደለም፤ ተቀባይነትም የለውም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የመንግስት አብዛኛው ትኩረት መከላከሉ ላይ መሆኑ ከዚያ ይልቅም አደጋው የከፋ ከሆነ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከወዲሁ በአፋጣኝ ማምረትና ማስመጣት አለመቻሉ አያሰጋዎትም?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- እንደተባለው መንግስት በእኛ አገር ለምሳሌ የአልኮል ፋብሪካዎች መጦችን ማምረታቸውን ትተው የሳኒተሪ ምርቶችን እንዲያመርቱ አቅጣጫ ማስተላለፉ በጣም ጥሩ ነገር ነው።ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችም ማስክ ማምረት የጀመሩ አሉ።ይህም የሚበረታተ ነው።በሌላ በኩል ግን ሌላው እንደስህተት የማየው መንግስት ቁጥጥር ውስጥ መግባቱን ነው።አንዳንድ ቁሳቁሶችን ዋጋ ጨምሩ ብሎ ፋርማሲዎችን የመዝጋት ስራ ውስጥ ፖሊስ መግባቱ ለእኔ አሳፋሪ ነው።ምርቱን መጨመር ማገዝና ስህትት የሚሰሩትን ማስጠንቀቅ እንጂ ፋርማሲ መዝጋት መፍትሄ አይሆንም።ይህ ትክክል ያልሆነ አካሄድ ነው የሚመስለኝ። እንዳልሽው እነ አሜሪካ የመኪና አምራቾች የመተንፈሻ ማሳሪያዎች እንዲያመርቱ እንዳረጉት ሁሉ የእኛም ፋብሪካዎች ማስክ ሳኒታይዘርና ሌሎች የህክምና ግብዓቶችን የሚመረቱበትን መንገድ ቶሎ ቶሎ መሳብ
ይገባል። በነገራችን ላይ ሰዎች ይህንን ወረርሽኝ በመጥፎ ጎኑ ብቻ ማየት የለባቸውም፤ ችግሩ በራሱ ስራ እንድንፈጥር ምክንያት እንደሚሆንም ማሰብ ይገባናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለበሽታው እየተሰጠ ካለው ግንዛቤ አኳያ በበሽታው የተያዘንና የተጠ ረጠረን ሰው የማግለል ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደሚስተዋል እንሰማለን፤ ይህም ሰዎች ራሳቸውን ቢጠረጥሩ እንኳ የመገለል ስሜቱ ይደርስብኛል በሚል ስጋት በሽታው እስከሚጥላቸው ድርስ የሚደበቁበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ይጠቀሳል።እነዚህን ሰዎች ምን ይመክራሉ?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- በወረርሽ ስራ ውስጥ ሁልጊዜ በጥንቃቄና በፍርሃት መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቁ ላይ ነው ትልቅ ችግር የሚሆነው።ሰዎች እንዳይዘናጉ በትክክል እንዲጠነቀቁና ጉዳዩን በት ኩረት እንዲወስዱት ይፈለጋል። ይህንን ጥንቃቄ ደግሞ በእውቀትና በዲሲፒሊን ካላደረጉት በፍርሃትና በመሸማቀቅ ከወሰዱት ወደ መደናበር እና ወደ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።በነገራችን ላይ ኤድስ ላይም የታየው ነገር ይሄ ነው።ስለዚህ ይህንን ሚዛን መጠበቅ ነው።ይህም የሚቻለው በእውቀት ነው።እኛ አገር ያለው ችግር ሰዎች በእውቀት አለመንቀሳቀሳቸው ነው።ከምትናገሪው ነገሮች ውስጥ በእውቀት ሰምቶ ከመተግበር ይልቅ ችግር የለም ብሎ ይክዳል ወይ ደግሞ ከሚገባው በላይ መፍራትን ይመርጣል።ሁለቱም ትክክል አይደለም።ከስሜት ወጥተሽ ሚዛናዊው መንገድ ጠብቀሽ ነው መሄድ ያለብሽ።በጣም መፍራት ተገቢ አይደለም።ይህንንም የምንልበት ምክንያት ይህ በሽታ ኢቮላ አይደለም።ግን ደግሞ ቀላል በሽታ አይደለም።መዘናጋት አይገባንም።ስለዚህ ሰዎች ሰከን ብለው ከስሜት ወጥተው ተረጋግተው ማሳብና መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው የጤና ስርዓት ላይ ካለመተማመን እንዲሁም ለይቶ ማቆያውን በሚመለከት የጠራ ግንዛቤ የሌላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚመጣባቸውን እንግልት በመፍራት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ የማይፈልጉበት ሁኔታ ይኖራል።ይህስ ችግር በምን መልኩ ሊፈታ ይግባል ይላሉ?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- እንዳልሽው ለይቶ ማቆያውን የሰዎች አያያዝን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ሊሰራ ይገባል፡፡በተገቢው መንገድ በቴሌቪዥን አያያዙ ምን እንደሚመስል ማሳየትና ማስረዳት ያስፈልጋል።ነገር ግን የቤት ለይቶ ማቆያ ዘዴ መኖሩ ሊዘነጋ አይገባም።በመጀመሪያ ራሳቸውን የጠረጠሩ ሰዎች በቤታቸው ራሳቸውን ማግለል ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ይቅርታ ዶክተር ላቋርጦትና እንደሚያውቁት የእኛ ኑሮ በአንድ ቤት ውስጥ አራትና አምስት እንዲያውም ከዚያ በላይ ሆነን ነው የምኖረው ይህ የሚሉት ራስን የማግለል ነገር በእኛ የአኗኗር ሁኔታ የሚቻል ነው?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- መሞት ካልፈለግሽ ይቻላል፤ እያልኩሽ ያለሁት እኮ ይሄ የኑሮ ሁኔታችን አይፈቅድም እየተባለ የሚሳበበው ነገር ነው መቆም ያለበት።አቅሙ ከሌለሽ ሁለተኛውን አማራጭ የግድ መጠቀም አለብሽ። ለቤተሰብሽ የምትጨነቂ ከሆነ በፍጥነት ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከሉ መሄድ ነው የሚገባሽ።አለዚያ ሁለቱንም ትተሽ እንዴት ሊሆን ይችላል።እኔ ራሴን ማግለል የሚያስችል አቅምም ምቹ ሁኔታ ሊኖረኝ ይችላል።ነገር ግን የምመርጠው ራሴንም ሆነ ቤተሰቤን ለመጠበቅ ወደ ለይቶ ማቆያው መሄዱ ነው።ስለዚህ ሰዎች ስለኳራንታይን ወይም ለይቶ ማቆያው ሲያስቡ ለቤተሰባቸው ማሰብ ይገባቸዋል።ምክንያቱም አንድ ሰው ተይዞ እንደተራ ጉፋን ታሞ ሊድን ይችላል።ግን እናቱን ወይም አባቱን ለሞት ሊዳርግ ይችላል።ስለዚህ በሽታው ይዞናል ብለን በትክክል ከተጠራጠርን ወደ ጤና ተቋም ሄደን ማረጋገጥ ይገባናል።ምክንያቱም በአንድ ሰው ምክንያት 10 ሺ ሰው ሊያዝ ይችላል።ያ አንድ ሰው ላለመሆን ዜጎች መስራት አለባቸው።አንድ ሰው የአዕምሮ ህመም ከሌለበት በስተቀር የዚህ አይነት ተራ ፍርሃት ላይ የተመሰረተ ስህተት ሰርቶ ለሺዎች መሞት ምክንያት መሆን የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡
በነገራችን ላይ በህግ መጠየቅም ሊመጣ እንደሚችል ዜጎች ማወቅ ይግባቸዋል። ይሄ ሁሉ መረጃ ባለበት የጉዞ ታሪካቸውንና አጋጣሚዎቻቸውን እያወቁ ጥንቃቄ ሳያደርጉ በእነሱ ምክንያት ሰዎች ከተያዙ በህግ ይጠየቃሉ።ይህንን ደግሞ በሳይንስ ማረጋገጥ ይቻላል።አይከብድም።ስለዚህ የህግ ተጠያቂነትም ሊከተል እንደሚችል ዜጎች ማወቅ አለባቸው። ሚዲያዎችም ይህንን ጉዳይ ማሳወቅ ይገባቸዋል። ዜጎች እያወቁ፥ በግዴለሽነት ወይም ራሳቸው በፈጠሩት ሃሰተኛ እውቀት ተሸብበው ለሌላው ሞት ምክንያት ከሆኑ በህግ መጠየቅ እንደሚመጣ ማወቅ አለባቸው። እንዳውም እኮ ዜጎች መንግስት ይህንን እና ያንን ያድርግልን ከማለት ይልቅ ራሳቸው ፈልገው ነው ማውቅና መጠንቀቅ የሚገባቸው።ደግሞ ልነግርሽና አንቺም በቀጥታ እንድታስተላልፊልኝ የምፈልገው ጉዳይ የእያንዳንዱ ሰው ህይወት የራሱ ነው፤ የመንግስት አይደለም።ስለዚህ መንግስት ይህንንና ያንን ያድርግልኝ ከማለታችን እኩል እኛ ምን አደረግን ብንል እያንዳንዳችን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።ይህ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው፤ ልክ ጦርነት ውስጥ እንዳለን ልናስብ ይገባል።ግን አጭር ጊዜ ነው እናልፈዋለን።አሁን የምንሰራቸው አብዛኞቹ ስህተቶች ግን ለዓመታት የማንከፍለው እዳ ሊጭኑብን ይችላሉ።ስለዚህ መፍትሄዎችን ነው ማሰብ የሚገባን።እንዴት እንደማንችል ሳይሆን እንዴት እንደምንችል ነው ማሰብ የሚገባን።አንዳንዱ ሰው በር ይዘጋ ሲባል «የመንገድ ተዳዳሪዎች ምን ይበላሉ?» እያለ እሪ ይላል፤ ሁላችንም መንገድ ተዳደሪዎች የሚበሉትን ምግብ ማመቻቸት አንችልም? በየቀበሌው ብንበትናቸው እነሱን መመገብ አንችልም? ቶሎ ያለመፈፀማችን ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል።
ሌላው ያልተረጋገጡ ሳይንሶች የማይሰሩ ነገሮችን በማህበራዊ ሚዲያ አንዳንድ ጊዜ በዋና ዋና ሚዲያዎች የሚያሰራጩ ሰዎች ወረርሽኙን የመከለካሉን ስራ እየሸረሸሩ ስለሆነ ቢጠነቀቁ ጥሩ ነው።ምርምር ካላቸው ባሉበት ተደብቀው ይስሩና መፍትሄ ሲሆን ይዘው ይውጡ።አለበለዚያ መፍትሄ መሆኑን ያልተረጋገጠ ነገር አየር ላይ ማውጣት ከማዘናጋት የበለጠ ምንም ጥቅም የለውም።ይህንን የምልሽ ተስፋ ሰጪ መድሃኒት አግኝተናል ያሉትን የመንግስትን ሰዎች ጨምሮ ነው።ይሄ የማይጠቅምና ጊዜውን ያልጠበቀ ወሬ ነው።የመከላከሉን ስራ የሚያዘናጋና ሀይል የሚበታትን ስልሆነ ሁለተኛ እንዲህ አይነቱ ነገር ሊደገም አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? መድሃኒትና መፍትሄ ማምጣት የሚችሉ
ኢትዮጵያውያኖች የሉም እያሉ ነው?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- እውነቱን ከጠየቅሽኝ አዎ፤ ዘይትና ስኳር በአግባቡ ማምረት ያልቻለ አገር ብድግ ብሎ ድንገት የባህል መድሃኒቶቼን አሰባስቤ መድሃኒት ሰራሁኝ ቢለኝ ለእኔ ተራ ፖለቲካ ነው የሚሆንብኝ።በነገራችን ላይ ይህንን ሀሳቤን ሳትሸራርፊ እንድትፅፊው ነው የምፈልገው።አሁን ከእንደዚህ አይነት ተራ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት ነው ያለብን። ይልቁንም መከላከሉ ላይ ነው ማተኮር ያለብን። እስቲ በመጀመሪያ መንግስት ስኳር በአግባቡ ያምርት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቢገኝስ ግን?
ዶክተር ኤርሶዶ፡- ቢገኝስ ብሎ ጫወታ የለማ፤ ሰዎች ሊሞቱ ነው፤ በመጀመሪያ ደረጃ በሳይንስ መድሃኒት የሚሰራው በጣም ሰፊ የሆነ የቤተ መኩራ ስራ ተሰርቶ የዓመታት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በርካታ ዓመታት ፈጅቶባቸው ነው የሚሰራው።ስለዚህ ባንፎጋገር ጥሩ ነው።ደግሞም ከስድስት ወር በኋላ ያ መድሃኒት የት ደረሰ? ብዬ እጠይቅሻለው።እስከዚያው ግን እጃችን መታጠብ፥ መራራቅ ቫይታሚን ሲ መብላት ላይ እናተኩር።ወደፊትም ግን ሌላ ፉገራ መምጣት የለበትም።ይሄ ማለት የኢትዮጵያን መናቅ አይደለም።እስከዛሬ ያልታየው አቅም ኮረና ሲመጣ ነው እንዴ የሚነሳው።ይሄ ፖለቲካ ነው ተዪው።ከመሬት የሚነሳ ነገር የለም።ከተመሰረተ ኢንዱስትሪ ነው ሁሉም ነገር የሚመጣው።የምንችለው ስራ እዚህ እያለ የማንችለውን ወሬ በማምጣት ህዝብ ማዘናጋት ስህተት ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ አረጋገጥኩ እያለ በየቀኑ በሚያወጣው መረጃ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው አንዳንድ ሰዎች ይገልፃሉ፤ አንዳንዶቹም ቁጥሩ ከዚህም በላይ የላቀ እንደሆነ ይጠረጥራሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመመርመር አቅማችን አነስተኛ ስለሆነ እንጂ የተያዘው ሰው ቁጥር የላቀ እንደሆነ የሚናገሩ አካላት አሉ፤ እነዚህ ጉዳዮች እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- በመጨረሻ ያነሳሽው ነገር ትክክል ነው።የምታውቂያቸው ኬዞች መጠን ባለሽ የመመርመር አቅም ሊወሰን የሚችልበት ሁኔታ አለ።ስለዚህ ይህንን ጉዳይ በተናጠል አንስቶ ማብራራት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስራ ነው የሚሆነው።እንደተባለው ብዙ ብንመረምር ብዙ ልናገኝ እንችላለን።ግን ለመመርመር መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ።ለምሳሌ ምንም ምልክት ያላሳዩ ሰዎች ልንመረምር አንችልም።አሁን በትክክል መመርመር ሲገባቸው ምልክት ያሳዩ ሰዎች ተመርምረዋል ወይ ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው።ግን ያለው አቅም ውስንንት እንዳለው እሙን ነው፡፡
በሌላ በኩል ግን መንግስት ቁጥሩን እየደበቀ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም በመደበቁ የሚያገኘው ጥቅም አለ ብዩ አላምንም።ለመንግስት መረጃን መደበቅ ማለት እሳትን በጋቢ ለመደበቅ መጣር ማለት ነው።እሳትን በጋቢ ብትደብቂው ለተወሰነ ደቂቃ ሊቆይ ይችላል ግን እሳቱ ጋቢውን በልቶ መውጣቱ አይቀርም።ስለዚህ መንግስት እንደዚህ አይነት ነገር ይሰራል ብዬ አላስብም።ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ናቸው።በተለይ ጤና ጥበቃ አካባቢ ያሉ ብዙዎቹ ወጣቶች ሳይንቲስቶችና ሐኪሞች ናቸው።ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነም እረዳለሁ።ስለዚህ የሚደብቁበት ምክንያት አይታየኝም።ግን ከመመርመር አቅም ጋር የተገናኘ የቁጥር ማነስ ሊኖር ይችላል የሚለው ጉዳይ አሳማኝ ጥያቄ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሌላ አገራት ከሚጠረጠሩ ሰዎች ወይም ምልክት ከታየባቸው ሰዎች ውጭ ምንም አይነት ህመም ሳይኖራቸው ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን፤ በእኛ አገርም በቅርቡ በመጀመሪያ ቫይረሱ ተገኝቶባት የነበረ በኋላ ላይ ግን በተደረገላት ተደጋጋሚ ምርምራ ነፃ የተባለች ወጣት ጉዳይ የቫይረሱን ውስብስብ ባህሪያት ሊያመላክት የሚችል ይሆን?
ዶክተር፡- በጠቀሺያት ወጣት ጉዳይ ላይ መረጃው የለኝም።በሌላ በኩል ግን አንድ ቫይረሱ ያለበት ሰው ከቀናት በኋላ ሲመረመር ነፃ ከሆነ ድኗል ማለት ነው።ምክንያቱም በሽታው የሚመረምረው ቫይረሱን በመሆኑ ነው። ይህም ሲባል በአሁኑ ሰዓት በቀጥታ የምንመረምረው ቫይረሱን ነው ልክ እንደወባ ማለት ነው። በሌላ መንገድ የሚደረግ ምርመራ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ በሽታው ከሚያሳያቸው ምልክቶች አንፃር የሚደረግ ምርመራ አለ።ስለዚህ ኮረና የተያዘ ሰው ነፃ ሊሆንበት የሚችልበት እድል ሊኖር ይችላል።እኔ ግን እዚህ ጋር የሚያሰጋኝና አንቺም ለአንባቢዎች ማስረፅ ይገባሻል የምለው ጉዳይ ሰዎች በጣም አልፎ አልፎ ሊከሰት በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ነው።ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ነገሮችን ማስጮህ የሚፈልጉ ሰዎች ዋናውን ነገር በመካድ ስራን ለመሸሸ የሚሹ ናቸው።ለምንድን ነው አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ የምንጠለጠለው? በኤች አይቪ ላይ ተመሳሳይ ነገር ነበር።90 በመቶ ኤች አይቪ የሚተላለፈው በወሲብ ሆኖ እያለ ሰዎች ሌሎች ጥቃቅን የመተላለፊያ መንገዶች ላይ ትኩረት አድርገው ማውራት ይፈልጉ ነበር።አሁንም ሴራ ትንተና ላይ ሰዎች ጊዜ እንዳያጠፉ እናንተ ማስተማር ይገባችኋል።አሁን ያልሻት ወጣት ጉዳይ ምርመራው በትክክል እንደዚያ ሊሆን ይችላል፤ ወይም የማህበራዊ ሚዲያው የፈጠራ ሪፖርትም እንዳይሆን እሰጋለሁ።አሁን የሰዎችን ትኩረት የሚበታትን ነገር ማምጣት ጥሩ አይደለም።ትኩረታችን ከመከላከሉ ላይ የሚነቅል ነገር ጥሩ አይደለም።ለወሬ ስለሚመች ብዙ ሰዎች እንደዚህ አይነቱን ነገር ይወዳሉ።ሌላኛው ግን ተግባር ስለሚጠይቅ አይመርጡትም።ስለዚህ የቡና ወሬ ቫይረሱን አያቆመውም፤ ስለዚህ ዜጎች ወደ እውነተኛው ነገር ላይ ማተኮር ይገባቸዋል።አሁንም ቢሆን ርቀታችንን እንጠብቅ፥ እጃችን እንታጠብ፥ ምልክቶቹ ካሉብን ቶሎ ሪፖርት እናድርግና ራሳችንን እናግልል።ይሄ ብቻ ነው መፍትሄው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ቫይረሱን የመመ ርመር ስራ በመንግስት ነው እየተከናወነ ያለው፤ መንግስት ቶሎ ለግሉ ተቋም ካላከፋፈለ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል ብለው የሚሰጉ ሰዎች አሉ፤ በዚህ ረገድ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- እንደሚመስለኝ ግን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለግል ጤና ተቋማት ብሄራዊ ማህበር ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል።ከእነሱ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም መረጃው አለኝ።በማህበራቸው በኩል ተደራጅተው እየሰሩ ነው።በነገራችን ላይ ከመንግስት ባልተናነሰ መልኩ ተስፋዎቻችን እነሱ ናቸው።ስለዚህ መቶ በመቶ መንግስት እንሱን እያሳተፈ አይደለም የሚለው ትክክል አይደለም።ግን በቂ ድጋፍ እየተሰጠን አይደለም እያሉ ነው።ይህም ማለት ዝግጅት እያደረጉ ነው።የጤና ባለሙያዎቻቸውን አሰልጥነዋል፤ የመከለካያ ግብዓቶችን እያሟሉ ነው፤ የሚጠረጠሩ ኬዞችን እየለዩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር እየሰሩ ነው።ወደፊት የምርመራ ቴክኖሎጂው እየረከሰ ሲሄድ ሁሉም ጋር ምርመራው ይኖራል ብዬ አስባለው።
እንዳውም ያነሳሽው ጥያቄ ጥሩ ነው።ምክንያቱም እስካሁን ባለው ሁኔታ ቡዙ ኬዞች ከግሉ የጤና ተቋም ነው ወደ መንግስት የሄዱት። ከዱባይ የመጣ አንድ ግለሰብ ጤና ጥበቃ የሚሄድበት አጋጣሚ ጠባብ ነው።ስለዚህ የግሉ ተቋም እየሰራ ነው እየተባበረም ነው። ግን ከዚህ በላይ መደገፍም አለበት።ጊዜው የአደጋ ስጋት በመሆኑ በቀጣይ ሁኔታውን አመቻችቶ ልክ እንደመንግስት ተቋማት ሁሉ ወደ ግሉም ሪፈር ማድርግ ይጠበቅበታል።የመንግስት ተቋማት የሚደረግላቸው የሚገባ ድጋፍ ሁሉ ሊደረግላቸው ይገባል።ለምሳሌ የመመሪያ መሳሪያዎች እኩል ማሰራጨት ይገባል።በተለይ ደግሞ የጤና ባለሙያዎች የመከላከያ መሳሪያዎች እኩል ሊሰጥ ይገባል።ለዚህ ደግሞ አሁን እየሰሩ መሆኑን አውቃለው፡፡እነሱ ጋር ያለውን ጉልበት በፍፁም መርሳት የለብንም ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ።
በቅርቡ እንዳውም እንደሰማሁት አንድ የግሉ ሆስፒታል ያለው ሐኪም ከቱርክ ለፅኑ ህሙ ማን የሚሆን 10 የመተንፈሻ መሳሪያ በእርዳታ አስመ ጥቷል። ይህም ማለት ብዙ ህሙማንን ህይወት ሊታደግ የሚችል ነው። በነገራችን ላይ የመተንፈሻ መሳሪያ በተመለከተ በአለም ላይ ከፍተኛ እጥረት አለ። በአገራችን ያለው የመተንፈሻ ማሳሪያ 300 አይሞላም። አሁን እንግዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከታመሙብን ምን እንደምንሆን ማሳቡ ከባድ አይሆንም፡፡ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ ይህንን አቅማችንን ገንብተን መውጣት አለብን። እንደአገርም እንደዜጋም ብልጥ መሆን አለብን። ከዚህ ወረርሽኝ ስንወጣ በትምህርት፥ በሃሳብ ፥ ድንገተኛ አደጋዎችን የመቋቋም ልምዳችንን አዳብረን ስርዓቱንም ገንብተን የምርምር አቅም ገንብተን መውጣት አለብን። ከዚህ ወረርሽኝ ስንወጣ ተሸንፈን መውጣት የለብንም። ለዚህ ደግሞ ከሚጠበቅብንም በላይ መስራት ይጠበቃል። አንዳንዱ ሰው በጣም አበዛችሁት ይላል።ግን ለእኔ ማብዛት አይደለም።እንዳውም ከሚገባን በታች ሰርተን ብዙ ሰው ከሚሞትብን ከሚገባን በላይ ሰርተን ሰው ብናተርፍ ተጠቃሚዎች ነን።
አዲስ ዘመን፡- በሌሎች አገራት እንደተያው ሁሉየባለሙያ እጥረት እንደስጋት ሊታይ አይችልም?
ዶክተር ኤርሲዶ፡- ለዚህ እኮ ነው መከላከል በጣም አስፈላጊ የሚሆነው። ስንከላከል ሰዎችን እንዳይታመሙና ወረርሸኙ እንዳይሰፋ ማድረግ አንዱ ትልቁ ውጤት ነው። ሁለተኛው የመከላከል ውጤት የጤናውን ዘርፍ ከጥፋት የመታደግ እርምጃ ነው።ምክንያቱም በሽታው የሚከላከሉትም ሆነ ከህሙማኑ ጋር በቀጥታ የሚገናኙት የጤና ባለሙያዎች ናቸው።ስለዚህ እነሱን ካልጠበቅናቸውና ካልተከላከልናቸው ከወረርሽኙ ስንወጣ ቁጥራቸው የላቀ የጤና ባለሙያዎችን አጥተን ልንወጣ እንችላለን።ይሄ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል።የጣሊያን ሪፖርት የሚያሳየው አንድ በመቶ የሚሆነው ህይወቱን ያጣው የጤና ባለሙያው ነው፤ የስፔን ይብሳል 15 በመቶ የሚሆነው የጤና ባለሙያ ነው የሞተው። እኛ ካለችን የጤና ባለሙያዎች ላይ 15 በመቶውን ማጣት ማለት ለኢትዮጵያ ትልቅ ሞት ነው። ስለዚህ ዘግተንም ሆነ እንከላከል እያልን የምንጮኸው የጤና ሴክተሩን ከጥፋት ለመታደግ ከማሰብ ነው። ይህ ሊታወቅ ይገባል።ስለዚህ ባልተከላከልን ቁጥር የጤና ሴክተራችንንና ባለሙያዎቻችን ላይ እየፈረድን ነው።እንኳን እኛ የሰጠለጠኑት አገራትም ከአቅማቸው በላይ ሆኗል።ስለዚህ እኛ የማይመስል እርምጃ መውሰድም ቢሆን ግዳጃችን ነው።ከዚህ በሽታ ተሸንፈን ወጣን ማለት የጤና ስርዓታችንን ወደኋላ አምስትና አስር ዓመት ጎተትነው ማለት ነው።ይህንን መፍቀድ የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- የተለየዩ ባለሀብቶችና ግለሰቦች በሽታውን ለመከላከል በበጎ ፍቃድ እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል።ነገር ግን ካለው ሰፊ ህዝብና አቅም አኳያ እየተሰራ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ኢርሲዶ፡- ይህ ተግባር ገና እየጀመረ ያለ ነው፤ ወደፊት ከዚህ በተሻለ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብዬ ነው የማስበው።ምክንያቱም እንደሌላ ጉዳይ ለተወሰነ በተወሰነ ሰው ብቻ የሚፈፀምና የሚቆም አይደለም ዘላቂነት ያለውና በሁሉም ሊደረግ የሚደረግ ድጋፍ ነው። ገና ጅምር በመሆኑ ለመገምገም አስቸጋሪ ነው።ግን ቅስቀሳው መጠናቀር ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ኤርሲዶ፡- እኔም አመሰግናለሁ። አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012 ማህሌት አብዱል