ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት አቅም እንዳላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ምሽት ለካፍ ፣ለፊፋ ፕሬዚዳንቶች እና ለካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከፍተኛ አመራሮች በታላቁ ቤተ-መንግሥት የእራት ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ በይፋ ጠይቀዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ትልቁን አህጉራዊ የእግር ኳስ መድረክ የማዘጋጀት አቅም አላት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እያስተናገደች ከምትገኘው 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጉባዔ አስቀድሞ የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔን እና የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከፍተኛ አመራሮችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፣ በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታንም በጋራ መጎብኘታቸውን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ይህ ጠቃሚ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን ለማገዝ በሚገባ መዘጋጀቷንም ተናግረዋል።
የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበው፣ የኢትዮጵያውያን ባህል፣ እሴትና እንግዳ ተቀባይነት “ኢትዮጵያ ቤታችን እንደሆነች እንዲሰማን አድርጎናል” በማለት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ካፍ ከኮሚቴው ጋር እንደሚመክርበት ገልጸዋል።
የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም “የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የኛም ሀገር ነች” ሲሉ ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለሁለቱም ፕሬዚዳንቶች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ማሊያን በስጦታ አበርክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ 2029 የሚል ፊርማቸውን ያሳረፉበትን ኳስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አበርክተዋል።
በተመሳሳይ እለት ቀን ላይ በአዲስ አበባ ስቴድየም በተካሄደ የወዳጅነት ጨዋታ መርሃግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሳላዲን ሰዒድ፣ አዳነ ግርማና ሌሎችም የቀድሞ የዋልያዎቹ ኮከቦች ስብስብ ከቀድሞ የተለያዩ ሀገራት የአፍሪካ ኮከቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል። የካሜሮን ኮኮብ ተጫዋች ሳሙኤል ኢቶ፣ የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪ ሞትሴፔ፣ የቀድሞው ካሜሩናዊ ኮከብና የአሁኑ የሀገሩ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ኢቶ፣ ናይጄሪያዊው የቀድሞ ኮከብ ጄይጄይ ኦካቻና ሌሎችም የወዳጅነት ጨዋታው ተካፋይ ሆነዋል።
ይህንን በተመለከተ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ 46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲሁም ጉባዔውን በማስመልከት የተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ያነቃቃ እንዲሁም የኢትዮጵያን ገፅታ የገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ አያይዘውም፣ 46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅትን እንዲሁም የኢትዮጵያን የ2029 አፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት ፍላጎትን እንዳላት ገልጸው መንግሥትም በሀገሪቷ የሚገኙ ግንባታቸው የተጀመሩ ስታዲየሞችን የማጠናቀቅ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
“የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ የማጠናቅ ልምድ ያለን በመሆኑ በግንባታ ላይ ያሉ ስታዲየሞችን የማጠናቀቅ ብቃትም ተነሳሽነትም አለን” ያሉት ሚኒስትሯ፣ አብዛኞቹ ስታዲየሞች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው፤ የአፍሪካ የእግር ኳስ የበላይ አካል (ካፍ) ይሁንታውን የሚሰጥ ከሆነ ከሚኖረው 5 ዓመት አስቀድሞ ስታዲየሞቹን የማጠናቀቅ ሥራ እንደሚሠራ አሳውቀዋል። ለሥራዎቹ ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት እና ብቃትም እንዳለ አስረድተዋል።
ከስቴዲየሞቹ ባሻገርም ተተኪ ስፖርተኞች የሚወጡባቸው ትንንሽ ሜዳዎች (Mini stadium) ታሳቢ እንደሚደረጉ እና ውድድርን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የመሠረተ ልማቶች ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴም ካፍ ትናንት ጠቅላላ ጉባዔውን ሲጀምር በመድኩ ተገኝተው ካፍ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያጸድቅ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ዐሻራ እንዳላትና እ.አ.አ በ1957 ካፍ ሲመሠረትም መሥራች ከነበሩ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን በማስታወስ፣ የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም መድረክ የሚገባውን ቦታ እንዲያገኝ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
‹‹ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እግር ኳስ ወዳዶች ያሉባት ሀገር ናት›› ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ያላትን ታሪካዊ ድርሻ ከግምት በማስገባት በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫውን ተጠቅማ የአፍሪካን እግር ኳስ ለማሳደግና በስፖርቱ ሀገር ለመገንባት እንደምትሠራም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ስታዲየሞች እየገነባችና ያሉትንም ማሻሻያ እያደረገች እንደምትገኝም አመልክተዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም