የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ሃኪዬንዳ ሂቺሌማ በዳኝነት ሥራቸው ላይ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ፈጽመዋል ያሏቸውን የሀገሪቱን ሦስት ከፍተኛ ዳኞች ከሥራ አባረሩ። በፕሬዚዳንቱ የተሰናበቱት የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ከስምንት ዓመት በፊት በተካሄደው እና የአሁኑ ፕሬዚዳንት በተሸነፉበት ምርጫ ላይ ያቀረቡትን ቅሬታ ውድቅ አድርገውት ነበር።
በተጨማሪም ዳኞቹ አሸናፊው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ለሁለት የምርጫ ዘመን በሥልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ ለሦስተኛ ዙር እንዲወዳደሩ በተፈቀደበት አወዛጋቢ ውሳኔ ውስጥም ተሳትፈው ነበር። ዳኞቹ በፕሬዚዳንቱ ከመባረራቸው በፊት እገዳ ተጥሎባቸው የነበረ ሲሆን፣ ይኸው እገዳ እንዲነሳላቸው ለዳኞች ጉባዔ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ዳኞቹ ከሥራ የተባረሩት የሀገሪቱ የፍትህ ቅሬታዎችን የሚመለከተው ኮሚሽን “በአስቸኳይ እንዲሰናበቱ” ባቀረበው ሃሳብ መሠረት መሆኑን ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አመልክቷል። መግለጫው ጨምሮም “በዛምቢያ ሕገ መንግሥት መሠረት ዳኞችን የማሰናበት ሥልጣን ለፕሬዚዳንቱ የተሰጠ በመሆኑ” ውሳኔው መተላለፉን ገልጿል። በፕሬዚዳንቱ ከዳኝነት ሥራቸው የተሰናበቱት ሦስቱ የዛምቢያ ከፍተኛ ዳኞች በውሳኔው ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።
የፍትህ ቅሬታዎችን የሚመለከተው ኮሚሽን ሦስቱ ዳኞች በተሰጣቸው ኃላፊነት አማካኝነት ተገቢ ያልሆኑ ከባድ ጥፋቶችን ፈጽመዋል በሚል በአንድ ግለሰብ የቀረበባቸውን ክስ ሲመርምር ቆይቷል። ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ኮሚሽኑ ዳኞቹ ከስምንት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ላይ ያሳለፉት ውሳኔ ተገቢ አልነበረም በሚል በአንድ ጠበቃ የቀረበለትን ክስ ውድቅ አድርጎት ነበረ።
ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ ለማስተናገድ እየተዘጋጀች ባለችው ዛምቢያ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሂቺሌማ እና ቀድሞው
ፕሬዚዳንት ሉንጉ እንደሚፎካከሩ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ውጥረት እየጨመረ መሆኑ ይነገራል። የፕሬዚዳንቱ ውሳኔን በተመለከተ በሀገሪቱ ዜጎች መካከል የተደበላለቀ አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ውሳኔው ሕጋዊ ነው ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ እና ደጋፊዎቻቸው ለእራሳቸው በሚጠቅም መልኩ ርምጃ ወስደዋል ሲሉ የሀገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ዜጎች ተችተዋል። ላውራ ሚቲ የተባሉ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ እንዳሉት “በ2016 (እአአ) የተካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ዳኞቹ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ አሳልፈዋል። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ የበቀል የሚመስል ውሳኔ መስጠታቸው በጣሙን አሳሳቢ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጠበቃ የሆኑት ማኬቢ ዙሉ ርምጃውን “ሕገወጥ” በማለት “ሥራ አስፈጻሚው በፍትህ አካሉ ነጻነት ላይ ጣልቃ ለመግባት ያለመ ነው” ሲሉ ከሰው “የትኛውም ዳኛ ሕግ የመተርጎም ሥራውን በማከናወኑ ሊቀጣ አይገባም” ብለዋል።
በዛምቢያ ሕገ መንግሥት መሠረት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሁሉም ዳኞች በሀገሪቱ የሕግ አገልግሎት ኮሚሽን ተመርጠው በፕሬዚዳንቱ ሚሾሙ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤትም ተቀባይነት ማግኘት አለባቸው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም