ቢሾፍቱ:- አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ እንደ ሀገር የተያዘውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ያግዛል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ትናንት ለተጠሪ ተቋማት እና ለክልል ግብርና ኃላፊዎች ሲያስተዋውቅ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከ20 ዓመት በፊት የወጣና አሁን ከሚሠሩ የግብርናው ዘርፍ ሥራዎች ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም።ይህን መነሻ በማድረግም አዲስ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል።
አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲም እንደ ሀገር የተያዘውን እቅድ ከግብ ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፤ፖሊሲውን የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ፖሊሲው ውስጥ ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችን አውቆ እንዲተገብር ያደርገዋል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ፖሊሲው አሁን የግብርናው ዘርፍ ያለበትን ደረጃ ብቻ የሚያይ ሳይሆን ኢትዮጵያ ወደፊት ልትደርስበት ካሰበችው ቦታ የሚያደርስ ነው።በፖሊሲው ዙሪያም ግንዛቤ ተፈጥሮ ቶሎ ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል።
ሚኒስትሩ፤ በፖሊሲው ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ የግብርና ፋይናንስ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ያለውን የፋይናንስ ሥርዓት መጠቀም እንደተጠበቀ ሆኖ የግብርና ባንክ ማቋቋም የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመቻች ፖሊሲ መሆኑን ተናግረዋል።
የመሬትና ተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተ የመሬት ሀብት አሲዞ ብድር ማግኘት እንደሚቻል በፖሊስው መቀመጡን የጠቆሙት ግርማ ( ዶ/ር)፤ ለዚህ የሚሆን ተጨማሪ መመሪያና ደንብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የግብርናው ዘርፍ ገጠሩን ህብረተሰብ ለማሻገር ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፤ ፖሊሲው የግብርናና ገጠር ልማት የተባለው ለዚህም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ፖሊሲውን የማስተዋወቅ ሥራው በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እስከ ዞን እና ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር የሚሠራ መሆኑን አመልክተው፤ የማስተዋወቅ ሥራውንም ሁሉም በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚኒስትሩ በመድረኩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ እንደገለፁት፤ ከግብርና የወጪ ንግድ በሩብ ዓመቱ 796 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ከቡና የወጪ ንግድ ብቻ 519 ሚሊዮን ዶላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል ።
የሌማት ትሩፋት ንቅናቄው ባለፉት አራት ዓመታት ሲተገበር የነበረበት አካሄድን በማሻሻል በዘንድሮ ሩብ ዓመት 20 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ማሰራጨት ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሥራው ሲጀመር በዓመት ይሰራጭ የነበረው የአንድ ቀን ጫጩት 26 ሚሊዮን ብቻ ነበር ብለዋል። በዚህ ዓመትም 150 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ለማሰራጨት መታቀዱን ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ የያዘችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማሳካትና የኑሮ ውድነት ለማቃለል ዘንድሮ ምርትን በብዛትና በጥራት ወደ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በግብዓት አቅርቦት ረገድ የተሻለ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ያለፈው ዓመት ተሞክሮ በመውሰድ የማዳበሪያ ግዢው ቅድሚያ እንዲፈጸም እየተደረገና ማዳበሪያ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ2017 የምርት ዘመን 24 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን የገለፁት ሚኒስትሩ ፤የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግዱ እንዲቀንስ ማድረጉን ተናግረዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም