– ለሁለት አሸናፊዎች 20 ሚሊዮን ብር ሽልማት ይበረከታል
አዲስ አበባ፡- የምርጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ሥራዎች ሽልማትና የእውቅና መርሀ-ግብር በሥራቸው ለሌሎች አርዓያ የሆኑ ግለሰቦችን ለሚያበረታታት እንደሚያግዝ ተመላከተ። ለሁለት አሸናፈዎች በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚበረከት ተጠቁሟል።
የምርጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ሥራዎች ሽልማትና እውቅና መርሀ-ግብር ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ታውቋል። የመርሀ-ግብሩ አዘጋጅ የአንቴክስ ጨርቃጨርቅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፕሬዚዳንት ሚስተር አንጉስ ቺን እንዳስታወቁት፤ ድርጅታቸው ለሌሎች አርዓያ የሚሆኑ ግለሰቦችንና ተቋማትን ለመሸለም አቅዷል።
ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ላደረጉ እና በሕዝቡ መካከል ሰላማዊ አብሮነትን ለማጎልበት ለሚተጉ እንዲሁም በሥራቸውም ውጤታማ ሆነው ለሌሎች አርዓያ መሆን ለቻሉ ግለሰቦችና እና ድርጅቶች የማበረታቻ ዕውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
ሽልማቱ በሁለት ዘርፎች የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢኮኖሚ ሽልማት ዘርፍ ከትንሽ ተነስቶ በራሱ ጥረት የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለ፣ ለብዙዎች የሥራ ዕድል የከፈተ፣ ሕዝብና ሀገርን ለመጥቀም የሚሠራና ካፈራው ሀብት ላይ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ኢትዮጵያዊ ዕጩ ሆኖ መቅረብ እንደሚችል አስታውቀዋል።
በተጨማሪ የሰላም ሽልማት ዘርፍ ደግሞ በአኗኗሩ ሰላምን ከፍ የሚያደርግ፣ ዋጋ ከፍሎ በህብረተሰብ መካከል እርቅን ለማውረድ የሠራ፣ ይቅርታን እየኖረ ይቅርታን የሰበከ፣ የፆታ አኩልነትን ያበሰረና ፆታዊ ጥቃትን የሚፀየፍ የእጩ ዝርዝር ውስጥ መካከት እንደሚችል ጠቁመዋል።
የሽልማት መርሃ-ግብሩ ታህሳሰ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት የስብሰባ አዳራሽ ከፍተኛ የመንግሥት አካላትና የክብር እንግዶች በተገኙበት እንደሚካሄድ አመላክተዋል። ለሁለት አሸናፊዎች ለእያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር ሽልማትና የእውቅና ዋንጫ እንደሚበረከትላቸውም ገልጸዋል።
በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ራሳቸው ወይም ጠቋሚዎች ከጥቅምት 11 ቀን ጀምሮ ለቀጣይ 15 ቀናት በቴሌግራም ቻናል @Biwprize ወይም በኢሜይል አድራሻ biwsprize@gmail.com መመዝገብና ጥቆማ መስጠት የሚቻል መሆኑ አስታውቀዋል።
አንቴክሰ ጨርቃጨርቅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የተለያዩ አላባሳትን አምርቶ ለውጭ ገበያ እያቀረበ ሲሆን፤ ለአራት ሺህ 500 ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ኩባንያ መሆኑ ተጠቁሟል።
ድርጅቱ በቀጣይም 10 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም በህብረተሰቡ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠራ ተመላክቷል። የምርጥ ተፅእኖ ፈጣሪ ሥራዎች የሽልማት መርሀ-ግብርም በየዓመቱ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም