የአፍሪካ እግር ኳስ አባት

የአንዳንዶች ስኬት ከመቃብር በላይ ከፍ ብሎ መታየቱ ብቻ ሳይሆን የትናንት ሥራቸውን በዛሬ መነፅር እንኳን ስንመዝነው እና በተመሳሳይ የሙያ መስክ ከሚገኙ የዛሬዎቹ ባለሙያዎቻችን ጋር ስናስተያየው ገዝፎ ይሰማናል። ሆኖም በሰሩት ሥራ ልክ የእነዚህ ቀደምቶቻችንን ስም ከፍ አድርገን ቀጣዩን ትውልድ ለማነሳሳት ስንጠቀምበት አንታይም።

የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) 46ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለተቋሙ ምስረታ ጉልህ ድርሻ ባበረከተችው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ እያካሄደ ይገኛል። እኛም ይህንኑ መነሻ በማድረግ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን በስኬት በመምራት የላቀ አበርክቶ የነበራቸውን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ዛሬ እናስታውሳለን።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ 1928 ላይ ተመስርቶ የመጀመሪያውን ጨዋታ አራራት ከተባለው የአርመን ኮሚኒቲ ቡድን ጋር ለማድረግ ቀጠሮ ቢይዝም አንድ ተጫዋች ጎሎት ነበር። የቡድኑ አባላት በቦታው ያልተገኘውን ጓደኛቸውን ቦታ እንዴት መሸፈን እንዳለባቸው ግራ በተጋቡበት ወቅት ታድያ በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ግቢ የቄስ ትምህርት ሲማር የሚያውቁት አንድ ታዳጊ በመንገድ ሲያልፍ ያገኙት እና ቆሎ ሊገዙለት ቃል ገብተው እንዲጫወትላቸው ያግባቡታል። እሱም በሀሳቡ ተስማምቶ በጨዋታው ተሰለፈ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን 2-0 ሲያሸንፍም አንድ ጎል አስቆጠረ።

በዚያ ጨዋታ የጀመረው የታዳጊው እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቁርኝትም ለ23 ዓመታት ዘለቀ። እግር ኳስን በዚህ መልክ የጀመረው ያ ታዳጊ ከዓመታት በኋላ ከሀገር አልፎ በአህጉር እና በዓለም እግር ኳስ ላይ ታላቅ ተፅዕኖን ያሳረፉት ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ።

ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ከአባታቸው ከነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሙላቷ ገ/ሥላሴ መስከረም 01 ቀን 1914 በጅማ ከተማ ነበር የተወለዱት። እንደማንኛውም የዘመኑ ልጆች በቄስ ትምህርት ቤት አልፈው ከ6-14 ዓመት ዕድሜያቸው ዘመናዊ የፈረንሳይኛ ትምህርት በአሊያንስ፣ በዳግማዊ ምንሊክ እና በተፈሪ መኮንን ት/ቤቶች ተከታትለዋል። ዕድሜያቸው 14 በሆነበት ጊዜ ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሩ በኢጣሊያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመዘዋወር ለሀገር ተወላጆች የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቀዋል።

በአራራቱ ጨዋታ መነሻነትም ከ45 ዓመታት በላይ በስፖርቱ ውስጥ አሳልፈዋል። በ23 ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታቸው ዝነኛ ተጫዋች ከመሆናቸው ባለፈ ቡድኑን በአምበልነት እና በአሰልጣኝነትም አገልግለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ1940 ከተቋቋመ በኋላም በ15 ጨዋታዎች ሃገራቸውን ወክለው ተጫውተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆንም በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ አድርገውታል።

ከመጫወት እና ማሰልጠን ባለፈውም ኳስን በመዳኘት፣ የኳስ ዳኞችን በማሰልጠን፣ አንዳንዴም በሬዲዮ ኳስ በማስተላለፍ፣ የእግር ኳስ ክለቦችና ፌዴሬሽኖችን በማደራጀት፣ የአሁኑን አዲስ አበባ ስታድየምን ጨምሮ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በማስገንባት ታላቅ አሻራ አኑረዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የስፖርት ጉባኤዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፣ የስፖርት ሕጎች እና ደንቦችን ወደ አማርኛ በመተርጎም፣ በምክትል ሚኒስትርነት የኢትዮጵያ ስፖርት መሪ በመሆን፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በስኬት በመምራት እንዲሁም በፊፋ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥም በአባልነት በመካተት ዕድሜ ዘመናቸውን በእግር ኳስ ውስጥ ኖረዋል። እነዚህ ነገሮች በአንድ ሰው ዕድሜ ይፈፀማሉ ብሎ ማሰብ ቢከብድም ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ግን አሳክተውት አልፈዋል።

የጣልያንም አገዛዝ ካበቃ በኋላ አቶ ይድነቃቸው በፍጥነት በእግር ኳሱ ማህበረሰብ ውስጥ ስመጥር ተጫዋች፣ ዳኛ እና አስተዳደር በመሆን በነበራቸው የተለየ የማስተባበር ክህሎት፣ የፖለቲካ አረዳድ ኳስን የሚጫወቱበት መንገድ እና የመምራት ችሎታ ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ በእኩዮቻቸው ዘንድ የተለየ ከበሬታን አስገኝቶላቸዋል።

ገና በ22 ዓመታቸውም ተጫዋች ሆነው ሳለ ነበር የማስታወቂያ ሚኒስቴር በነበሩት ከክቡር አቶ ዓምደሚካኤል ደሳለኝ በተደረገላቸው ድጋፍ የስፖርት ፅ/ቤት ያቋቋሙት። በወቅቱ ፅ/ቤቱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራውን ማከናወን ቢያዳግተውም ከአራት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ተጠናክሮ ስራውን እንዲጀምር አደረጉ።

በ1944 ደግሞ ነገሮች እየተስተካከሉ ሄደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተመሰረተ። ይድነቃቸውም ዋና ፀሀፊ ሆነው በመመረጥ የሙሉ ጊዜ ስራቸው ሆነ። በዚህም የመተዳደሪያ ደንቦችን ወደ አማርኛ በመመለስ ተቋሙን ያጠናከሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በማስጀመር ረገድ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

እግር ኳስ በሀገር ውስጥ እንዲተዋወቅ እና መስመር እንዲይዝ ከማገዛቸው ባለፈ የታላቁ ሰው አህጉራዊ ተፅዕኖም መታየት ጀመረ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ1949 ካርቱም ላይ በሱዳን፣ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ አባልነት ሲመሰረት የተቋሙን መተዳደሪያ ደንብ በመቅረፅ ረገድ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆንም አገልግለዋል። በዚሁ ዓመት የተጀመረውን የአህጉሪቱን ውድድርም ሀገራችን ከአምስት ዓመታት በኋላ አስተናግዳ ባለድል እንድትሆን በአሰልጣኝነት ታላቅ ታሪክን ፅፈዋል።

በአስተዳደሩ ረገድ በካፍ ውስጥ የነበራቸው ተፅዕኖ ከሚገለፅባቸው ነጥቦች አንዱ በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት በመቃወም ሀገሪቷ በአህጉራዊው ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እና ከካፍ እንድትገለል ጫና በማሳደራቸው ነው። የታላቁ ሰው የፀና አቋምም ካፍ ሀሳባቸውን ተቀብሎ በ1951 ሀገሪቷን በማገድ በአስከፊው ሥርዓት ላይ ውሳኔ ያስተላለፈ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ተቋም ሆኗል። በወቅቱ አፓርታይድ በፊፋም ሆነ በዓለም ዓቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ተቀባይነት ነበረው። እነዚህ ትልቅ የስፖርት ተቋማትም የካፍን ውሳኔ “ፖለቲካንና ስፖርትን የሚቀላቅል” በሚል አጣጥለውት ነበር።

በ1956 በካይሮ 23 የአፍሪካ አባል ፌዴሬሽኖች በተሳተፉበት ጉባዔ ይድነቃቸው ተሰማ የካፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ። ይድነቃቸው በዚህ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት ካከናወኗቸው ነገሮች ግንባር ቀደሙ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና መጀመር ሲሆን 1957 ላይ በጃፓን ቶክዮ በተደረገው የፊፋ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ጋና በህብረት አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ከአባልነት እንድትታገድ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄውም ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀባይነት አግኝቶ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ ውጪ እንድትሆን ተደረገ።

በተመሳሳይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው ርሆዴሺያ (የአሁኗ ዚምባቡዌ) ከፊፋ እንድትወገድ ይድነቃቸው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በ1962 በሜክሲኮ የተደረገው የፊፋ ጉባዔ ላይም ከተፈሪ በንቲ ጋር በጋራ የህግ መዝገብ በማዘጋጀት እና መዝገቡ ለአባል ሃገራት እንዲቀርብ በማድረግ ርሆዴሺያ ከፊፋ እንድታገድ አድርገዋል።

በ1950ዎቹ መጨረሻ 30 አባል ሃገራት የነበሩት ካፍ በዓለም ዋንጫው ግን ግማሽ ኮታ ብቻ ነበረው። የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ እና የእስያ ዋንጫ አሸናፊ እርስበርስ ተጫውተው ከሁለቱ ያሸነፈው ቡድን ብቻ ዓለም ዋንጫውን ይቀላቀል ነበር። የማጣሪያ ሂደቱ ርዝመት፣ ከፍተኛ ወጪ እና የማለፍ የተመናመነ ተስፋ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በማጣሪያው እንዳይሳተፉ አደረጋቸው።

የፊፋ አመራሮችም ይህንን ተጠቅመው የአፍሪካ ሃገራት ያላቸውን ድምፅ ብዛት ለመቀነስ ተንቀሳቀሱ፤ “በሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ወይም የኦሊምፒክ ማጣሪያዎች ላይ ያልተሳተፈ ፌዴሬሽን በፊፋ ስብሰባዎች ላይ የመምረጥ መብት የለውም” የሚል ሃሳብ ያለው ሕግም ማርቀቅ ጀመሩ። በዚህ ወቅት ነበር ይድነቃቸው ተሰማ እና የአፍሪካ እግር ኳስ መሪዎች በጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ድጋፍ ራሳቸውን ከ1959ኙ የእንግሊዝ ዓለም ዋንጫ ያገለሉት፤ በቀጣይ የዓለም ዋንጫዎችም ለአፍሪካ አንድ ሙሉ ኮታ ካልተሰጣት በቀር እንደማይሳተፉ ገለፁ።

ፊፋ በመጀመሪያ የአፍሪካ ፌዴሬሽኖች ይህንን በማድረጋቸው እያንዳንዳቸው 5000 ፍራንክ ቅጣት እንዲከፍሉ ትእዛዝ ቢያስተላልፍም በመጨረሻ በጉዳዩ በመስማማት ለአፍሪካ አንድ የዓለም ዋንጫ ኮታ መደበ። ሞሮኮም በ1963ቱ የዓለም ዋንጫ በመሳተፍ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሃገር ሆነች።

በ1965ቱ የያውንዴ ጠቅላላ ጉባዔ ይድነቃቸው የሱዳኑን ዶ/ር አብዱልሃሊም መሃመድ 15 ለ 12 በሆነ የድምፅ ብልጫ በማሸነፍ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት የእግር ኳስ ሰው ከአማርኛ በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ጣልያንኛን በጥሩ ሁኔታ መናገር መቻላቸው ተፅዕኗቸው በአህጉራዊ ደረጃ ከፍ እንዲል አስተዋፅዖ ነበረው ማለት ይቻላል።

በካፍ ፕሬዚዳንትነት በሰሩባቸው 15 ዓመታት የፈጠሯቸው ለውጦች በብዙዎች አስተሳሰብ እስካሁን ካየናቸው የአፍሪካ እግር ኳስ መሪዎች ሁሉ የበለጠ ስኬታማ አድርጓቸዋል። በይድነቃቸው የካፍ አመራር ስር በርካታ ፈር ቀዳጅ ስራዎች ተከናውነዋል። የመጀመሪያው የአፍሪካ የወጣቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ የዋንጫ አሸናፊ ክለቦች ውድድር (የአሁኑ የኮንፌዴሬሽኖች ዋንጫ) በይድነቃቸው ጠንሳሽነት የተጀመሩ ውድድሮች ናቸው።

የካፍ ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ በ1974ቱ የሊቢያ የአፍሪካ ዋንጫ የቴሌቪዥን እና ስርጭት መብት ታይቶ በማይታወቅ ትርፍ ለመሸጥ ተችሏል። ይድነቃቸው የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም ያለውን ስፍራ ለማሳደግም በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል። ለዚህ ዓላማቸው ቁልፍ መሳሪያ አድርገው የተጠቀሙት ደግሞ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ኮንፌዴሬሽኖች መሃል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነበር። በብራዚል የነፃነት ድል ማክበሪያ ውድድር ላይ ከአፍሪካ ሃገራት የተውጣጣ ቡድን እንዲሳተፍ ማድረጋቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።

ብራዚላዊው ጆ ሃቫላንጅ እንግሊዛዊውን ስታንሊ ሮውስ በማሸነፍ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሲሆን የይድነቃቸው ሚና ቀላል አልነበረም። በተለይ ቀጣዩን የፊፋ ምርጫ እንደመሳሪያ በመጠቀም አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ አዘጋጅታው ከነበረ ዓለም ዓቀፍ የእግር ኳስ ውድድር ብራዚል ራሷን እንድታገል ያደረጉበት ሂደት የሚረሳ አይደለም።

በ1971 አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ያላት ኮታ እንዲጨምር ጥያቄዋን አቀረበች። ጥያቄውም በአብዛኛው የፊፋ አባላት ተቀባይነት በማግኘቱ ከ1974ቱ የዓለም ዋንጫ ጀምሮ የአፍሪካ ኮታ ወደ 2 እንዲያድግ ተፈቅዷል፡፡ ከዚህ በኋላ የነበሩትን ጭማሪዎች ይድነቃቸው ለማየት ባይታደሉም በሃቫላንጅ የሥልጣን ዘመን የአፍሪካ ኮታ 1986 ዓለም ዋንጫ ከ24 ተሳታፊዎች ወደ ሦስት በ1990 ከ32 ተካፋዮች ወደ አምስት ከፍ ብሏል።

ይድነቃቸው ከ1965 ጀምሮ አራተኛው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በመሆን ለአራት የስልጣን ዘመናት ማለትም ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በፕሬዚዳንትነት አሳልፈዋል። በዚህ የሥልጣን ዘመናቸው ለአፍሪካ እግር ኳስ የተለያዩ ስራዎችን ሰርተዋል።

የትንባሆና የአልኮል ማስታወቂያዎች በአፍሪካ ስታድየሞች እንዳይሰቀሉ ማድረጋቸው፣ እንደ ድርጅት አፓርታይድን መቃወማቸው፣ በ1968 በአዲስ አበባ በተጀመረው የሥልጠና ፕሮጀክት በሁሉም የአፍሪካ ዞኖች በማስቀጠል በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ዳኞች፣ አሠልጣኞች፣ የእግር ኳስ አስተዳደር፣ ሕክምና ወዘተ ባለሙያዎች እንዲፈሩ ማገዛቸው፣ የአፍሪካ ዳኞች እና ባለሙያዎች የዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጋቸው፣ አፍሪካ በራሷ ሀኪሞች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች ራሷን እንድትችል ማድረጋቸው ይድነቃቸው ለአፍሪካ እግር ኳስ ከሰሯቸው ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።

ታላቁ የእግር ኳስ ሰው ለእግር ኳስ በተሰጠው ዕድሜያቸው በዘርፈ ብዙ ሙያዎች በትጋት ሲያገለግሉ ቆይተው ነሀሴ 13 በ1979 ዓ.ም ነበር በካንሰር ሕመም ምክንያት በ 65 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

እኛም በዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የስፖርት ሰው የአፍሪካ እግር ኳስ አባት በመባል የሚታወቁትን ክቡር ይድነቃቸው ተሰማን ላበረከቱት መልካም አሻራ አመሰገንን። ሰላም! ለዚህ ፅሑፍ በምንጭነት የተለያዩ ድህረገጾችን ተጠቅመናል።

ክብረአብ በላቸው

 

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You