ብሊንከን ከጋዛው ጦርነት ወዲህ 11ኛ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን እያካሄዱ ነው

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል ገቡ፡፡ ሚኒስትሩ ለአንድ ሳምንት በሚዘልቀው የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው ወደ ዮርዳኖስና ኳታርም ያቀናሉ፡፡ ሚኒስትሩ ቴል አቪቭ የገቡት ሄዝቦላህ ወደ ማዕከላዊ እስራኤል በርካታ ሮኬቶችን ከተኮሰ ከሰአታት በኋላ ነው።

ብሊንከን የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ 11ኛ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው ሲሆን፥ በእስራኤል ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁና ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት ጋር ይመክራሉ። እስራኤል በጋዛ እና በሊባኖስ በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉ ቡድኖች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እያደረሰች በምትገኝበት ወቅት የጀመሩት ጉብኝትም የተቋረጠውን የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር ማስጀመር ያለመ መሆኑን ተዘግቧል።

10 ጊዜ በእስራኤልና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በመጓዝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥረት ያደረጉት ብሊንከን 11ኛው ጉዟቸውም የተሳካ ውጤት ይታይበታል ተብሎ አይጠበቅም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተደጋጋሚና ያልተሳካ ጉዞም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውድቀት ማሳያ ተደርጎ ሲነሳ ቆይቷል።

ከእስራኤል ባሻገር በዮርዳኖስ እና ኳታር ቆይታ የሚያደርጉት ዲፕሎማት በአሁኑ ጉዟቸው ግን ተጨባጭ ውጤት ያመጡ ዘንድ ይጠበቃል። ከሁለት ሳምንት በኋላ ከሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አስቀድሞ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተደረሰ ለዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ፈታኝ እንደሚሆን ነው ተንታኞች የሚያነሱት።

የጋዛውን ጦርነት ማስቆም ሳትችል በሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር ውጊያ መጀመሩ የኔታንያሁ አስተዳደር ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወታደራዊ ድጋፍ ከፈቀደለት የባይደን መንግሥት ጋር ተደጋጋሚ ቅሬታ ውስጥ ገብቷል፡፡በቅርቡም እስራኤል በጋዛ ሠብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ የምታደርገውን እገዳ በ30 ቀናት ውስጥ ካላቆመች ወታደራዊ ድጋፉ ሊቋረጥ እንደሚችል ብሊንከንና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊዩድ ኦስቲን በደብዳቤ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው ሲል አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You