አይንና ጆሮ የራቃቸው ዘራፊዎች
ምሽት ሦስት ሰዓት ገደማ ከአፍንጮ በር ወደ 70 ደረጃ በሚወስደው መንገድ ስልክ እያናገርኩ ስሄድ ማንነታቸውን በውልብታ እንኳን የማላውቃቸው ቁጥራቸው አራት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሌቦች ጭንብል ለብሰው ጨለማን ተገን አድርገው በቡጢ ተቀባበሉኝ::ጨኸት ባሰማ በአካባቢው የደረሰልኝ አልነበረም::በኋላ እንዳልጮኅ አፌን አፈኑኝ::ዘራፊዎቹ ድንገተኛ ያልሆኑ፤ ይልቁንም መውጫና መግቢያ ሰዓቴን አጢነው ይከታተሉኝ እንደነበር ድርጊታቸው ያስታውቃል::ስልኬንና ገንዘቤን ከቀሙኝ በኋላ ተሸክመው መኪና ውስጥ ሊያስገቡኝ ሲሉ ከርቀት የሚመጣ መኪና ድምጽ ስሰማ ታግዬ ከእጃቸው አመለጥኩ:: ተከትለውኝ ወደ መንደር ውስጥ ስገባ እየሮጡ ተመልሰው በሚከታተሉኝ የላዳ ታክሲ ሄዱ::ነገሩ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ሆነና እኔ በፈጣሪ አጋዥነት ከተረፍኩ በኋላ የአካባቢው ሰው አስፓልቱን ሞላው::በወቅቱ 40 ደረጃ አጠገብ የተሰራውን ህንጻ ሲጠብቅ የነበረው የጥበቃ ሰራተኛ እንኳን ጩኸቴን እየሰማ ነበር ዝም ያለው::ነገሩ ከበረደ በኋላ ነው መጥቶ በላዳ መሄዳቸውን ለተሰበሰበው መንደርተኞች የተናገረው::እዚህ ላይ ለጥንቃቄ ያህል እርስዎም ይህንን ቢያስተውሉ መልካም ነው::አምሽቶ ለብቻ አለመንቀሳቀስ፣ አንድን መንገድ ብቻ አለማዘውተር፣ ቢቻል ምሽት ላይ በተለይ ጨለማ ቦታ ላይ ስልክ እያናገሩ አለመሄድ….፡፡
በአካባቢው ፖሊስ ፍለጋ ብንሰማራም ከአፍንጮ በር ጀምሮ ራስ መኮንን ድልድይን አካሎ እስከ መቶ ደረጃ ጋዝ ማደያው ድረስ አንድ ፖሊስ የለም::የኋላ የኋላ ግን ጋዝ ማደያውን አልፈን ሁለት የፖሊስ አባላትን አገኘን::(ወንድና ሴት) የተመደቡበት ቦታ ጥቃቱ የደረሰበት ቦታ አካባቢ አይደለም::ሌሎች ጋር ደውለው ሲጠይቁም በአካባቢው የተመደበ የፖሊስ አባል የለም:: የጃን ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ ተቀብለን ደወልን::…ጉዳዩን በትክክል ስልኩን ላነሳችው የፖሊስ ባልደረባ አስረዳሁ:: ‹‹እንዴት በእዚህ ስፍራ ፖሊስ አይመደብም›› ብዬ ቅሬታዬንም አቀረብኩ:: አንደኛ በአካባቢው 70 ደረጃ፣ 40 ደረጃ እና 100 ደረጃ የሚባሉ ስፍራዎች ጨለማ ናቸው:: በሌላ በኩል በዚህ ስፍራ ብዙ የግድያና የዘረፋ ወንጀሎች ተፈጽመዋል::አካባቢውን ፖሊስ በአይነ ቁራኛ እንዲከታተል ብዙ ጥቆማ ተሰጥቷል::አንድ የቀጣና ፖሊስ ‹‹ስቴሽን›› ቢከፈትም ቢሮው ቀንም ሆነ ማታ ዝግ ነው::ይሄንን መነሻ አድርጌ ስናገር፤ ‹‹አንተ ስላልከን አይደለም የምንመድበው…የፖሊስ አባላት ቁጥር ያንሰናል…አባል የለንም…›› በማለት መለሰችልኝ::‹‹አመሰግናለሁ›› ብዬ ጠዋት ለጣቢያው መርማሪና አዛዥ ቃሌን በሙሉ ሰጥቻለሁ::የሆነው ሆኖ እኔ ተርፌያለሁ:: የተፈጸመብኝ ወንጀል ከዝርፊያ በላይ በመሆኑ በጸጥታ አካላት ክትትል እየተደረገበት ነው።
እውን ከእነዚህ ጋር ኢትዮጵያዊ ተብሎ መቆጠር አይከብድም? ኢትዮጵያዊነት በወረቀት ላይ ብቻ ሆነ ማለት ነው? ምንም አይነት የሕግ አካል የለም በሚያስብል ደረጃ በጠራራ ፀሀይ ሳይቀር እየገፈፉን ነው::
በዚህ ወር ብቻ ስንት ነገር እንደታዘብኩ፤ 70 ደረጃ ብቅ በሉ የዝርፊያ ቡፌ ታነሳላችሁ::ሌቦቹ መቼ በመሸልን ነው የሚሉት::ገና አንድ ሰዓት ነው ወደ ስራ የሚገቡት::በዚህ ስፍራ እንደ ልብ መግባት መውጣት ከብዷል::እያረዱ እየወጉ በመኪና እየጫኑ… ስንቱን ለህልፈት ዳርገዋል::ልብ ይስጣቸው ተብሎ የሚታለፈውስ እስከ መቼ ነው? ግን ለገንዘብ ብለው የሰው ህይወት ሲያጠፉ እጃቸው እንዴት ይጨክናል? ጎበዝ ምን እየጠበቅን እንደሆን አይገባኝም::
ይሄ ጉዳይ እንዲሁ በቀላሉ የምናየው ወይንም እንደ አንዳንዶች የሚቀለድበት ጉዳይ አይደለም:: በኋላ እንደነ ደቡብ አፍሪካ በቀን ሰዎች እርስ በእርስ ሲተናነቁና ሲዘረፉ እያየን በዝምታ እንዳላየ የምንሆንበት ጊዜ ላለመምጣቱ እርግጠኞች መሆን አይቻልም:: ስለዚህ በየአካባቢያችንም ይሁን በሌላ ስፍራ እንዲህ ያለ እኩይ ተግባር ስናይ ዝም ከማለት ደህነኛ ሰዎችን በማስተባበር ልንከላከል ይገባል:: (የፖሊስን ነገር ሆድ ይፍጀው)
በአሁን ሰዓት በተለይ ምሽት ላይ ፖሊስ ከሌባ ያስጥለኛል ብሎ በልበሙሉነት መናገር አይቻልም::ማን ሌባ ማን ፖሊስ እንደሆነ ለመለየት እየተቸገርን ነው::አንዳንድ ሰፈሮች ውስጥማ ‹‹ዛሬ እገሌ የሚባል ፖሊስ ተረኛ ነው›› ከተባለ፤ ሌቦቹ ‹‹በቃ ሽቀላ አለ ማለት ነው›› ይላሉ:: ያው ሥራው በህቡዕ ቢሆንም የሚካፈሉት ግን በጋራ ነው::አንድ ንብረቱ የተወሰደበት ሰው እንዲህ አይነት ሥራ ውስጥ ወደ ገባው ፖሊስ አቅንቶ ‹‹ሪፖርት›› ሲያደርግ ምን ያህል ብር እንደተወሰደበት፣ ምን ያህል ግራም ወርቅ እንደጠፋበት፣ ምን አይነት ስልክ እንደተወሰደበት በሚገባ ይመዘግባል:: የሚገርመው ታዲያ የውሸት ምዝገባው ንብረቱን ለማስመለስ ሳይሆን ንብረቱን ከወሰዱት ሌቦች ጋር ሲካፈል እንዳያጭበረብሩት ነው::
በአንዳንድ አካባቢዎች ደግም የቡድን ፀብ አስመስለው በቡድን ሆነው (ግማሹ ተባራሪ ግማሹ ደግሞ አባራሪ) ድንጋይ እና ስለት ይዘው ልክ እንደ አውሎ ንፋስ አንድ ሰፈር ላይ ይከሰታሉ:: ከዛ ሰፈሩ ላይ የቆሙ መኪኖች መስታወታቸው ተሰብሮ ይሰረቃሉ:: ሱቆች መስኮት ላይ የሚቀመጡት እንደ ሃይላንድና የለስላሳ ሳጥኖች ይሰረቃሉ:: መንገዱ ላይ ያሉ ሰዎች ተፈንክተው ወይም ተደብድበው ንብረታቸውን ይዘረፋሉ:: በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉ የሚሆነው በቅፅበት ውስጥ ነው:: (ልክ እንደ አውሎ ንፉስ ማለት ነው) እየተሯሯጡ ሰፈሩን አካለው ዘርፈው የት እንደሚገቡ አይታወቅም:: ለመጀመርያ ጊዜ እንደዚህ ሲያደርጉ አስተውዬ የእውነት የቡድን ፀብ መስሎኝ ነበር:: ነገሩን በተደጋጋሚ ሳስተውል ነው የሌብነት ዘዴ መሆኑን የገባኝ::
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ፖሊስ የት ነው? የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጉዳዩን ችላ ባይሉትና ህዝቡ ላይ የከፋ በደል እንዳይደርስ ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነው::ካልሆነም ህዝቡ አካባቢውን ተደራጅቶ መጠበቅ አለበት::
በአለም አቀፍ ደረጃ አንዳንድ ሀገራት በየሕገ መንግስታቸው እውቅና በመስጠት በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የሚያከብሩት መብት አለ::የእኩልነት መብት::ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው::የእኩልነት መርህን ያልተከተለ የክስ አቀራረብ ሂደት፤ ወጥነትና ተገማችነት የጎደለው የቅጣት አጣጣል ስርአት አጠቃላይ የአንድ ሀገር የወንጀል ፍትህ ስርአትን የሚያናውጥና የህጎች አላማን የሚያናጋ ነው::በግልፅ ተለይቶ የታወቀ የሕግ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ማንኛውም አጥፊ በፈፀመው የወንጀል ተግባር ልክ በሕግ መሰረት ይከሰሳል፤ ተመጣጣኝ ቅጣት ይጣልበታል::
ተመሳሳይ ጥፋት የፈፀሙ ሰዎች ተመሳሳይ ክስ ሊቀርብባቸው ይገባል:: ከጥፋተኝነት ውሳኔ በኋላ ታሳቢ የሚደረጉ ግላዊ ሁኔታዎችንና የሚቀርቡ የቅጣት ማቅልያዎችን እንደተጠበቁ ሆኖው ለተመሳሳይ የወንጀል ክስ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል:: በፍርድ ቤት የሚቀርቡ ክሶች ተፈፀመ ከተባለው የወንጀል ተግባር የሚጣጣም መሆኑን ወይም የተጋነነ ልዩነት አለመኖሩን ዳኞች ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል::ስለሆነም ፍርድ ቤቶች የማስረጃ ምዘናን ብቻ ሳይሆን የህጋዊነትና የእኩልነት መርህንም በአግባቡ እየተፈጸሙና ስራ ላይ እየዋሉ ስለመሆናቸው የመመርመር ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነት አለባቸው:: በተለይ ደግሞ ለህብረተሰቡ አንገብጋቢ እየሆኑ የመጡ የዝርፊያ ወንጀሎችን በተመለከተ አፋጣኝ ፍትህ ሊሠጥ ይገባል::ሌብነትም ስራ ነው ብሎ የተሰማራው ተባባሪ አካልም በጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል::የዘገየ ፍርድ ደግሞ የዘራፊዎችን ጉልበት በማጠናከር ለተጨማሪ የዝርፊያ ወንጀሎች ይዳርጋል::
ህጉ ምን ይናገራል?
የውንብድና ወንጀል ተፈፅሟል የሚባለው ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ የሌላ ሰው ንብረትን ለመውሰድ በተጎጂው ላይ ቀጥተኛ የሆነ የኃይል ተግባር ወይም ከባድ የሆነ የማንገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ የፈፀመ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው እንዳይከላከል ያደረገ እንደሆነ ነው በማለት የወንጀል ህጉ ይደነግጋል::
በሰው አካል ላይ በቀጥታ ማናቸውም አይነት የኃይል ተግባር ተጠቅሞ ንብረት መውሰድ ውንብድና ነው::በተጎጂው አካል ላይ ቀጥተኛ ኃይል ሳይጠቀም ንብረቱን ብቻ ለመቀማት፣ ለመመንተፍ ወይም ለመንጠቅ ኃይል የተጠቀመ እንደሆነ ግን ወንጀሉ ውንብድና መሆኑን ቀርቶ አስገድዶ መጠቀም ይሆናል::በወንጀል ህጉ አንቀፅ 713 ስር ‹‹ከውንብድና ውጪ ያለው ኃይል›› እየተባለ ያለውም ይህን ነው::በውንብድና ወንጀል ላይ የሚያስፈልገው የኃይል መጠን ንብረትን ለመውሰድ በተበዳይ ላይ የሚጠቀመው ኃይል አለ፤ በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ላይ የሚያስፈልገው ኃይል ግን ንብረቱን በቀጥታ ቀምቶ በመውሰድ ላይ ብቻ የተገደበና የተበዳይ አካልን የማይጎዳ ሀይል ነው፡፡
ለውንብድና ወንጀል የሚያስፈልገው ኃይልና ለአስገድዶ መጠቀም ወንጀል የሚያስፈልገው ኃይል ወይም ጉልበት በዚሁ መልኩ እየለያየን ከልተጠቀምንበት ህጎቹ በሚፈለጉበት አግባብ ስራ ላይ ማዋል አይቻልም::በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ላይ ኃይልን መጠቀም የሚቻለው ንብረቱን በሚወሰድበት ጊዜ ብቻ ነው:: በውንብድና ወንጀል ላይ ግን ኃይል መጠቀም የሚቻለው ንብረቱን በሚወሰድበት ጊዜም ንብረቱን ከተወሰደ በኋላም ሊሆን ይችላል::ይህ የሚያሳየው ደግሞ በአስገድዶ መጠቀም ወንጀል ላይ ኃይል የሚያስፈልገው ንብረቱን ለመቀማት ብቻ መሆኑና፤ ለውንብድና ወንጀል የሚያስፈልገው ኃይል ደግሞ በሰው አካል ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም ጉዳት ለማድረስ ከባድ የማንገላታት ተግባርና ከባድ ዛቻን መጠቀምን ጭምር መሆኑን ግልፅ ነው::
በመሆኑም የጽጥታ አካላት፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤያነ ህግ፣ የደኅንነት ኃይሎች ይህንን በመገንዘብ ከየመንደሩ ጀምሮ እስከ አገር የሚፈጸሙትን መሰል ድርጊቶች የመከላከል ሥራ ትኩረትን ይሻል:: ህግ ማስከበሩ የሚጀምረው ደግሞ ዜጎች ሲዘረፉ በቸልተኝነት የሚያልፉና ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው የሚተባበሩትን የጸጥታ አካላት በማደን ነው::
እንግዲህ ስርቆት፣ በማስገደድ መጠቀምና የወንብድና ወንጀሎች የሚመሳሰሉበት ምክንያት ሁሉም ከተጎጂው መልካም ፈቃድና ፍላጎት ውጪ በንብረት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ሲሆኑ የሚፈጸሙበት መንገድ ግን የተለያየና የየራሳቸውን ባህርይና የአፈፃፀም ዘዴ የሚጠቀሙ ናቸው::
ምናልባትም ዘርፈን እንበለጽጋለን የሚሉ ካሉም ድኅነትን ማምለጫ ብቸኛው አማራጭ መሥራት ብቻ መሆኑን ማስገንዘብ ይገባል::
በየሠፈሩ ተሰግስገው ማጅራት የሚመቱትና የሰውን ንብረት የሚዘርፉትን እንዲሁም ነገሩን ችላ ብለው የሚያልፉትን አካላት መንግሥት አደብ ሊያስገዛልን ይገባል:: እንደኔ እምነት ያለን ምርጫ ሁለት ነው::አንድም ህይወታችንን ሳናጣ የንብረት ዝርፊያው እንዲቀጥል መፍቀድ፤ ሁለት መንግስት እነዚህን ዘራፊዎች አደብ እንዲያሲዝልን መጎትጎት:: የሌብነት ድሩን ለመበጠስ ግን ሁለተኛው አማራጭ ተግባራዊ እንዲሆን እመኛለሁ::የተደራጀ ሌብነትን ለማጥፋት ባህላችንና አስተሳሰባችንን በለወጠና ችግሩን በሚያሳይ ልክ በጋራ መስራቱ ያዋጣል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
አዲሱ ገረመው