ሰዎች በተፈጥሮአቸው ስነ-ተፈጥሮአዊ (ስነ-ህይወታዊ) እንዲሁም ማህበራዊ (ሶሻል)ናቸው። ከዚህም የተነሳ በተፈጥሮ እንዲሁም በማህበራዊ ከባቢያቸው የሚከሰቱ የተለያዩ ክስተቶች ለጤናማነታቸውም ሆነ ጤና ለማጣታቸው መንስኤ የሚሆኑበት አጋጣሚዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ይህም ማለት በራሳቸው (በውስጥ በተፈጥሮ አካላዊ በሆነ ማንነታቸው) እንዲሁም በውጭ (በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ በሆኑ ሁኔታዎች) በሚከሰቱ አዎንታዊና አሉታዊ ክስተቶች ሰዎች ጤንነታቸው ሊጠበቅ ወይም ጤንነታቸው ሊጎዳ ይችላል።
ጤንነት አካላዊና ስነ-ልቦናዊ (ስነ-አእምሯአዊ፣ ስነ-ባህርያዊ) ጤንነትን የሚያካትት ነው። ማለትም አካላችን በተለያዩ በሽታ አምጪ ህዋሳትና በተለያዩ ምክንያቶችም እንደሚታመም አእምሮአችንም (ስነ-ልቦናችን ወይም ባህርያችን) በተለያዩ ምክንያቶች ይታመማል። ለአእምሮ ጤና መታወክ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። አንዳንዶች ተፈጥሮአዊ (ስነ-ህይወታዊ) ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ናቸው። ለአእምሮ ጤና እክል መንስኤ የሚሆኑ ነገሮች ብዙ እንደመሆናቸው መፍትሄ የሚሆኑ ነገሮች ከብዙ አቅጣጫ ይገኛሉ። ከዚህ በማስከተል ለአእምሮ ጤና መታወክ መፍትሔ ከሚሆኑ ነገሮች አንዱን እንመለከታለን።
ማህበራዊነት (ሶሻል ስፖርት)፡- ሰዎች በተለያዩ የአእምሮ ጤና እክሎች ሲጠቁ እንደ መከላከያ እንዲሁም እንደ መፍትሄ የሚያገለግል ነገር ነው። ለመሆኑ ማህበራዊነት ምንድን ነው? በዚህ ጹሑፍ ማህበራዊነት አብሮነትን፣ በጋራ መደጋገፍን፣ እንዲሁም መረዳዳትን የሚገልጽ ቃል ነው። በአንዳንድ ጹሑፎች ማህበራዊ መደጋገፍ በሰፊው ሲተረጉም የመረዳዳት ግንኙነቶች መኖርን እና
የእነዚህን ግንኝነቶች ጥራት ለመግለጽ ነው (ሌቪ 1983)። በተመሳሳይ መልኩ ሌላ ጸሐፊ ማህበራዊ መደጋገፍን ሲተረጉም ማህበራዊ ድጋፍ ሰዎች እርስ በርሳቸው ያላቸው የመተጋገዝ መስተጋብር ሆኖ በውስጡ የስነ-ልቦና ድጋፍን፣ በሚያስፈልግ ቁሳዊ በሆነ ነገር መደጋገፍን፣ የመረጃና የማበረታታት ድጋፍን የሚያካትት ነው ይላል (ሃዉስ 1981)። በተጨማሪም በሌሎች መጻሓፍት እይታ ማህበራዊ ድጋፍ ሰፋ ያለ ሃሳብ የያዘ ሀረግ ሲሆን አንድ ግለሰብ በተጨባጭ ያገኘውን ድጋፍ (መረጃዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ ወይም ቁሳዊ) እንዲሁም ድጋፉ የተገኘባቸውን ምንጮች (ጓደኛ፣ ቤተሰብ፣ እንግዳ እንዲሁም ሌሎችን) የሚገልጽ ነው ይሉታል (ሄትዝማን እና ካፓላን 1988)።
በአጭሩ ማህበራዊነትን (የሰዎች እርስ በርሳቸው መደጋገፍ) ከላይ በተገለጸው መልኩ የምንረዳ ከሆነ ከዚህ በመቀጠል በሰዎች አእምሮአዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ስነ-ባህርያዊ ጤንነት ላይ ያለውን አዎንታዊ አስተዋጾ እንመለከታለን።
ከሞላ ጎደል ሁሉም ሰው በሚገባ እንደሚገነዘበው ማንኛችንም ብንሆን በተለያየ ወቅት በልዩ ልዩ የሕይወት ጫናና ውጥረት ውስጥ እንገባለን። ይህ የሕይወት ጫናና ውጥረት ምንጩ ከብዙ የሕይወትና የኑሮ አቅጣጫ ይሆናል። ለምሳሌ በሥራ መደራረብና ጫና የሚፈጠር ውጥረት ይኖራል፤ እንዲሁም በቤተሰብና በጓደኛ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ምክንያት የሚፈጠር ውጥረት ይኖራል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ ከኑሮ ጫና ማለትም ከገንዘብ እጦት ወይም እጥረት የተነሳ የሚፈጠር ውጥረት ይኖራል፤ እንዲሁም ከጤና ማጣትም (በተለይ ከአካላዊ ጤና ማጣት ለምሳሌ ካንሰር፣ ኤች አይ ቪ፣ የስኳር ህመም፣ እንዲሁም ሌሎች የዕድሜ ልክ ህመሞች) ጋር ተያይዞ የሚከሰት ውጥረት ይኖራል። በተጨማሪም ለልዩ ልዩ አደጋዎች በመጋለጣችን ምክንያት የሚከሰትም ውጥረት አለ። ከዚህ ባለፈም የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት በምናጣበት ጊዜም የሐዘኑ ጫና የሚፈጥርብን ውጥረት ይኖራል። በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች በሕይወታችን ውጥረት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የአእምሮ ጤና እክሎች ለምሳሌ፡- ጭንቀት፣ ድባቴ፣ ፍርሃት፣ መረበሽ፣ ስጋት፣ ራስን የመጥላት ስሜት፣ ራስን ለማጥፋት መፈለግ፣ ሌሎችም እዚህ ያልተዘረዘሩ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።
እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩ የተለያዩ የጤና እክሎች በሚያጋጥሙን ጊዜ መፍትሔ መፈለግ የግድ ይሆናል።
ከእነዚህ ከመፍትሔ አቅጣጫዎች አንደኛው ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ማህበራዊነት ነው። ማህበራዊነት ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች ህይወታችን ከአቅም በላይ ወደ ሆነ ውጥረት እንዳይገባና ወደ ውጥረት ውስጥ እንኳን ብንገባ በውጥረቱ ምክንያት የሚመጣው ጉዳት አነስተኛ እንዲሆን እንደሚያግዝ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ማህበራዊነት ይህንን ሚና የሚጫወተው በምን መልኩ ነው የሚለውን ለመፈተሽ በተደረጉ ጥናቶች እንደታየው የማህበራዊነት (መደጋገፍ) መኖር በቀጥታ ጫናው እንዲወገድ በማድረግ (ለምሳሌ በሥራ አካባቢ የሚፈጠር ጫና ከሆነ የሠራተኞች መደጋገፍ የሥራ ጫና እንዳይፈጠር በማድረግ)፣ የጫናው ተጽእኖ እንዲቀንስ በማድረግ፣ ወይም ጫናውን በመገደብ፣ ወይም ከጫናው በመከለል በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ውጥረቶችንና የአእምሮ ጤና እክሎችን ይከላከልልናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ ጥናቶችን በማቀናጀትና በመፈተሽ በተደረገ ምርምር ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚመጣን ውጥረት በጋራ መደጋገፍ በቀጥታ ጫናውን በመቀነስ ለጤናማነት አስተዋጾኦ እንደሚያደርግ እንጂ ጫናው ከተከሰተ በኋላ ማህበራዊ ድጋፍን የመሻትና የማሰባሰብ ሁኔታ እምብዛም እንዳልሆነ ጥናቱ ያሳያል (ቪስዊስቫራን፣
ሳንቼዝ እና ፊሸር 1999)። በእርግጥ ከሥራና ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ የሚመጣው ጥረት መነሻ የሚሆነው አንድ ነገር ሳይሆን ብዙ ነው። ለምሳሌ በሥራ ላይ ያለ የሚና ግጭት፣ ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው ሰዓት እጥረት፣ በሥራ ላይ ያለ ሚና ግልጽ ያለመሆን፣ በሥራና በቤት ባሉ ሚናዎች መካከል ግጭት መኖር፣ በቤት ያሉ ቤተሰቦች አብሮ ጊዜ ማሳለፍን መፈለግ፣ በቤት ውስጥ ባሉ ኃላፊነቶችና ሚናዎች ላይ ግልጽነት መታጣትና የመሳሰሉ ናቸው። እንዲህም ሆኖ በእነዚህ ሁኔታዎች የሚመጣ ጫናና ውጥረት በሥራ ሥፍራና በቤት ውስጥ ማህበራዊ መደጋገፍ ካለ ጫናውና ውጥረቱ ይቀነሳል ወይም ይወገዳል (ካርሊሰን እና ፔሬዊ 1999)።
ከላይ ያየናቸው ጥናቶች በአብዛኛው የቆዩ ጥናቶች ቢሆኑም የቅርብ ጊዜ ጥናቶችንም የሚያመለክቱት ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮችን ነው። ለምሳሌ በዩኒቨረሲቲ ተማሪዎች ላይ
በ2015 በቱርክ አገር በተደረገ ጥናት ከወላጆቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እንዲሁም ከመምህራኖቻቸው ማህበራዊ ድጋፍ ያገኙ ተማሪዎች የስነ-ልቦና ጤንነታቸው መልካም እንደነበረ ጥናቱ አሳይቷል (ማልኮች እና ያልችን 2015)።
በአጠቃላይ በዚህ አጭር ጹሑፍ በጥልቀት ሁሉንም ሀሳቦች መዳሰስ ባይቻልም ማህበራዊነትን ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በእኛ አገር ሁኔታ ይህ የማህበረሰቡ እሴት ለአእምሮ ጤና ያለው ፋይዳ እጅግ ጉልህ መሆኑን በጥቂቱ ለማሳየት ይህች ጹሑፍ ተዘጋጅታለች። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ሰዎች በዕድር፣ በማህበር እና በሌሎችም በጋራ መደጋገፎች ብዙ ችግሮቻቸውን በጋራ ሲወጡ እንደነበረ ይታወቃል። ይህ አብሮነትና አንድነት አሁንም ለወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የዚህ ጹሑፍ አዘጋጅ በጽኑ ያምናል። መልካም የአእምሮአዊ፣ አካላዊና ማህበራዊ ጤንነት ለኢትዮጵያዊን በሙሉ!!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ሞገስ አየለ (ዶ/ር)