“ባንዳዊነት” ብለን ርእስ ስናበጅ የቁጣ ወይም ለወቀሳ ሽንጥን ገትሮና ወገብን አስሮ የመነሳት ጉዳይ ሊመስል ይችል ይሆናል፤ ግን አይደለም። “ባንዳዊነት” ስንል የተለየ ነገር ማለት ሳይሆን ልክ “ኢትዮጵያዊነት”፣ “ጥሮሳዊነት”፣ “መንፈሳዊነት”፣ “አፍሪካዊነት” እንደምንለው ሁሉ የባንዳን ማንነትና ምንነት መግለፃችን ነው።
ሌላው የ”ባንዳዊነት” መገለጫው ተቃራኒው ሲሆን እሱም “ኢትዮጵያዊነት” የሚለው ነው። “ኢትዮጵያዊነት” ማለት ደግሞ ብዙዎቻችን የምንስማማበት ብያኔ ቢኖር “ዜግነት”፣ “ብሄራዊነት”፣ “ብሄራዊ ፍቅር”፣ “ሰዋዊነት”፣ “ሀይማኖታዊነት”፣ “ህዝባዊነት”፣ “አገር ወዳድነት”፣ “አስታራቂነት”፣ “አብሮነት”፣ ወዘተ ማለት ነው። በመሆኑም የ”ባንዳዊነት” ተቃራኒ መገለጫው “ኢትዮጵያዊነት” ነው ስንል ምክንያታዊ ሆነን ነው ማለት ነውና እንቀጥል።
በመሰረቱ የ”ባንዳ”ን ተግባርና መገለጫውን ከላይ ባየነው መልኩ እንግለፀው እንጂ ተግባሩ “ዲያቢሎሳዊነት”፣ “ይሁዳዊነት (ወይም፣ ክርስቶስን ለ30 ዲናር የሸጠው የሥርቆቱ ይሁዳ)”፣ “አሪዮሳዊነት” ላለመሆኑ በምንም መንገድ መከራከርና “ባንዳ”ን ከሀጢያቱ ነፃ ማውጣት አይቻልም።
ከላይ “ባንዳ”ን፣ “ባንዳዊነት”ን እና “ባንዳዊያን”ን በተመለከተ ዳር ዳሩን የዞርነውን እዚህ ጋር እራሱ ግዝፈት ነስቶ እናገኘዋለን። በየትኛውም መንገድ ለህግ አለመገዛትና በወገንና አገር ላይ ወንጀል መፈፀም ተግባሩ “ባንዳነት”፤ እይታውም “ባንዳዊነት” ነው። ለህግም ሆነ ለደንብና ስርአት አለመታመን “ባንዳነት” ነው፤ በ”ኢትዮጵያዊነት”ና “ብሄራዊነት” አለማመንና ለሱም አለመታተር የ”ባንዳነት” ተግባርና “ባንዳዊነት” ነው። ለአገር ፍቅር ደንታ ማጣት፣ ለወገን ተማኝ ሆኖ አለመገኘትና በእሱ ሞት መሸቀል፣ የማንነት ተንጠፍጥፎ ማለቅ በክህደት ስር ተመድቦ በህግ መቀጣትን ብቻ
ሳይሆን የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ፖለቲካዊ ወዘተ ቀውስ ያመጣልና ተግባሩና ርእዮቱ በ”ባንዳነት”፣ “ባንዳዊነት”ና “ባንዳዊ ቀመር” ቀማሪነት ተመዝግቦ ለታሪክ መተላለፍንም የግድ ይላል።
ምንም እንኳን በመንግስት፤ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ንግድ ቢሮ “ነጋዴው ህብረተሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ በያገባኛል፤ በእኔነት እና ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ሀገራዊ ስሜት ከሸማቹ፣ ከነዋሪው ህዝብና ከመንግስት ጋር በጋራና በአንድነት በመቆም ማንኛውም ለንግድ የሚውል እቃ፣ ሸቀጥ፣ መሰረታዊ የፍጆታ እቃ፣ ምርትና አገልግሎት ላይ በምንም አይነት መልኩ እና ሁኔታ ዋጋ ሳይጨምር፣ የጥራት ደረጃ ሳያጓድል የሚዛንና የመስፈርያ መሳሪያዎችን ሳያስተጓጉል፣ ባእድ ነገር ሳይቀላቅል፣ ምርት ሳይደብቅ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣም” በተደጋጋሚ ቢጠየቅም፤ “በዚህ ተግባር የተገኘ ማንኛውም ነጋዴ ላይ ቢሮው በህግ መሰረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የንግድ ስራ ፈቃዱን የሚያግድ ወይም የሚሰርዝ ወይም የንግድ ድርጅቱን የሚያሽግ ተግባር እያከናወነ ነው፡፡
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንም ነጋዴው ላይ አግባብ ባለው ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት የሚያስቀጣና ንብረቱም በህግ መሰረት በመንግስት የሚወረስ መሆኑን” ቢገልፅም ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ ሆነና ሰሚ ጠፋ። ጠፋና፣ ባለፈው ማክሰኞ እለት ማታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከሰባት ሺህ በላይ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን፤ ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ ጉዳያቸው የከፋ በመሆኑ ለፍርድ የቀረቡ መሆናቸውን፤ ይህ ህገ-ወጥና ዘራፊ ነጋዴዎችን የመቆጣጠሩ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በቲቪ መስኮታችን መጥተው በምሬት ሹክ አሉን። “ባንዳ”፣ “ባንዳነት”ና “ባንዳዊነት” በህግ ፊት ሲታዩ ይህንን ይመስላሉ።
ለወትሮው 25 ብር የነበረን አንድ ኪሎ ሎሚን 150፤ 70 ብር የነበረን ነጭ ሽንኩርት ከ250 እስከ 300 ድረስ መቸብቸብ ኮሮና ወለድ ባንዳነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊባል፤ ምንስ ስም ሊሰጠው ይችላል።?
ከሶስት ቀን በፊት የኮሮና መምጣት የአፍሪካን ኢኮኖሚ ከመጉዳትም አልፎ ገና ካሁኑ 29 ቢሊዮን ዶላር ገቢን አሳጥቷታል እየተባለ ገበያን ከማረጋጋትና ከአገርና ህዝብ ጎን መቆም ሲገባ ባንዳ ሆኖ መገኘት በእውነት ፀጋዬ እንዳለው “ሸቃይነት” ነው፤ “ባንዳዊነት”።
ይህ የተሳሳተ፣ በኢ-ታማኝነት ላይ የተመሰረተ ባንዳዊ የቢዝነስ ስሌት ያለበት ሁኔታ ይህ ብቻ አይደለም። በመዲናችን በአንድ ቀን ያልተጠበቀ አሰሳ ብቻ የመንግስትን ውሳኔ የጣሱና በህዝብ በህይወት የመኖርና አለመኖር ህልውና ላይ የዘመቱ 767 ህገ-ወጥ ባንዳዊያን ላይ እርምጃ ተወስዷል። ይሁን እንጂ የባንዳው ቡድን በዚህ አልቆመም። ለዚህ ማረጋገጫችን ደግሞ አቶ አቤ የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከፊት ለፊት ተሰልፈው ጓንትና የፊት መሸፈኛ ማስክ ሲጠብቁ በጓሮ በር ወደ ውጭ ሲወጣ በማየታቸው ወዲያውኑ ለሬዲዮ ጣቢያዎች (ኤፍኤም) ደውለው በእልህ “እባካችሁ አንድ በሉን” ማለታቸውና ባለፈው ሰኞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ መስተዳድር በኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ ክስተት በመጠቀም በሰው ልጅ ህይወት ላይ ሊያተርፉ ሲንቀሳቀሱ በያዛቸው 271 ህገ-ወጥ ባንዳ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን መግለፁ ናቸው። እንዘርዝር ካልን ቦታም ጊዜም የለምና ለ”ባንዳ”፣ “ባንዳነት” እና “ባንዳዊነት” ተግባር ማሳያነት ይህንን ያህል ካልን በቂ ነው።
ለነገሩ ኢትዮጵያ እኮ በታሪኳ ባንዳ አጥታ አታውቅም። በየጊዜው ያጋጠሙንን እንቅፋቶች አስመልክቶ ታሪክ ላገላበጠ “ባንዳ”ን፣ “ባንዳነት”ንና “ባንዳዊነት”ን በየፈርጃቸው ያገኛቸዋል። በጣሊያን ወረራ ወቅት ስንትና ስንት ጊዜ የአርበኞችን ድል ያኮላሹት ባንዶች ናቸው፤ ለጠላት መደምሰሻ የታጠቁትን መሳሪያ ወደ ወገናቸው ያዞሩ ባንዶቹ እንጂ ሌሎች አልነበሩም። ከፋሺስት ለምትጣልላቸው ፍርፋሪ ብለው ማንነትን፣ የአገርና የወገን ፍቅርን ከውስጣቸው ጥንፍፍ አድርገው ለጠላት ያደሩት፣ የወገን ፍቅር ይሉ ታሪክን እንደ ኮፍያ አውልቀው የጣሉት ባንዶች እንጂ አርበኞች አይደሉም። ይህ የያኔው ሲሆን ባንዶች በሀይለ ሥላሴም፤ በደርግም (የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነትን ጨምሮ) ነበሩ (“የእናት ጡት ነካሾች” ማለት “ባንዶች” ማለት አይደለም ካልተባለ በስተቀር) ተከስተዋል።
ለነገሩ በዘመነ ደርግ ባንዶች በጦር ሜዳና ፖለቲካው ቅጥር ግቢ ብቻ አይደለም የነበሩት፤ በገበያው አውድም ነበሩ። ያዩ፣ የነበሩ እንደሚነግሩን መንግስቱ ሃይለማርያም “ባንዳ”፣ “ባንዳነት”ና “ባንዳዊነት”ን በመጠየፍ በኩል የሚያክላቸው የለም። በጉዳዩ ላይ ያጫወቱኝ አንድ አዛውንት እንዳሉት ባንዳ ገና ብቅ ሲል “ባማያዳግም እርምጃ” (እሳቸው ያሉኝ ሌላ ነበር) ይቀጨዋል። (በነገራችን ላይ አሁንም የአሁኑ አይነት የገበያ ባንዳና ባንዳዊ ተግባር ሲያጋጥም መንግስት የመንጌን አይነት እርምጃ አለመውሰዱ አገሪቱን ጎድቷታል፤ የገበያ ስድነትንም አበረታቷል፣ በነፃ ገበያ ስም ህዝብን እያዘረፈ ነው ወዘተ የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።)
ባጠቃላይ በዚህ ህይወት በሰኮንዶች በሚያልፍበት፣ የሰው ልጅ እንደ ቅጠል እየረገፈ ባለበት፣ ነገ ተረኛው ማን እንደሆነ እንኳን በማይታወቅበት፣ የአለምም ሆነ የአገራት ህልውና የመቀጠል አለመቀጠል ሁኔታ ገደል አፋፍ ላይ ባለበት፤ የተማረው፣ ባለሀብቱ፣ አርቲስቱ፣ ሰራተኛው፣ በተለይ የህክምና ባለሙያዎች በጥቅሉ ሁሉም እስከሚችለው ጥግ ድረስ እየተረባረበ ባለበት በዚህ ቀውጢና ፈታኝ ወቅት በገበያው አካባቢና ንግዱ ዘርፍ እንዲህ አይነት ባንዳዊ ስሌት አየሩን ሲቆጣጠረው በእውነት ያሳዝናል፣ ያስተዛዝባል፣ ያቀያይማል፣ ያቆራርጣልና ቢታሰብበት መልካም ነው። የመጣውን መአት ፈጣሪ ይመልሰው። አሜን!!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ግርማ መንግሥቴ