አበው ሲተርቱ «ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል» ይላሉ፤ እውነትነቱንም ያየ ያውቀዋል። መናገርና መጠየቅ እየተገባ ነገርን በዝምታ ማለፍ ዋጋ እንደሚያስከፍልም አባባሉ በትክክል ያሳያል። ከሰሞኑ ኦዲቲ ሴንትራል የተባለው ድረገጽ ያስነበበው ዜናም፤ «ካለመናገር እደጅ ይታደራል» በሚል እንዲሻሻል የሚያደርግ ነው።
የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታው፣ የህይወት መስመሩ አሊያም እንደ ሃሳቡ ለመኖር ባህር ሊሻገርና ረጅም መንገድም ሊያቋርጥ ግድ ይለዋል። ዣንግ ዳሚንግ የተሰኘው የ18ዓመት ማሌዢያዊ ወጣትም እንጀራ ፍለጋ ከወር በፊት ነው ወደ ሲንጋፖር ያቀናው። ኑሮውንም በአንድ ደሴት ላይ ከሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ ከጓደኛው ጋር ያደርጋል። ከዕለታት በአንዱ ቀንም ባልንጀራው ምሳውን መቢያ ይሆነው ዘንድ 37ዶላር ትቶለት ወደ ሥራው ይሄዳል። ወጣቱም በአካባቢው ባለ አንድ ምግብ ቤት ምሳውን ተመግቦ ወደ ቤቱ ሊመለስ ይነሳል።
እንዳሰበው ግን አልሆነም፤ ዣንግ ዳሚንግ የመጣበትን መንገድ በደንብ አላስተዋለና ምልክትም አልያዘ ኖሮ መመለሻው ግራ ይሆንበታል። ወዲህ ቢል ወዲያ ቢቃኝም የሚያስታውሰውን ነገር ማግኘት አልቻለም። መጥፎው ነገር ደግሞ ቶሎ እንደሚመለስ አስቦ በመውጣቱ የእጅ ስልኩን፣ ፓስፖርቱን፣ የመኖሪያ ፈቃዱንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አለመያዙ ነበርና ከጓደኛው መገናኘት አልቻለም። ያለው የመጨረሻ አማራጭም ሰዎችን አቅጣጫ መጠየቅ አሊያም ስልክ ተውሶ ለጓደኛው መደወል ቢሆንም ግን ያንን አላደረገም። ጠላቱ ደግሞ የገዛ አይናፋርነቱ ነበርና ለ10ቀናት ቤቱን ሳያገኝ ከደጅ ውሎ አደረ።
ለቀናት ምሽቱን በገበያ ማዕከላትና ሬስቶራንቶች በሚገኙ መጸዳጃ ቤቶች ተኝቶ ሲያሳልፍ፣ ቀን ቀን ቤቱን ፍለጋ በከተማዋ ሲዘዋወርና በጠፋበት ዕለት ከምሳው በተረፈው ገንዘብም ርካሽ ምግቦችን እየገዛ ሲመገብ ቆየ። እንደ ዕድል ሆኖም በመጨረሻ በቴሌቪዥን በተሰራጨው የአፋልጉኝ ማስታወቂያ የተመለከቱት ነዋሪዎች እርሱ መሆኑን ሊያውቁ ቻሉ። ዣንግ ዳሚንግ ከጠፋ ከአንድ ቀን በኋላ እንደወጣ አለመመለሱን ያረጋገጠው ጓደኛው አፋልጉኝ አስነግሮ ነበርና ከቀናት በኋላ በዓይነስጋ ሊገናኙ ችለዋል።
ወጣቱ የተገኘው ከመኖሪያው ስድስት ኪሎ ሜትሮችን ርቆ ሲሆን፤ በድጋሚ ላለመጥፋቱ ማረጋገጫ ባለማግኘቱም በአውቶቡስ ለሁለት ሰዓታት ተጉዞ ወደ ሃገሩ ለመመለስ ወስኖም ነበር። ከተገኘ በኋም ለመገናኛ ብዙሃን ሁኔታውን አስረድቶ ነበር፤ «ምሳዬን የበላሁት ብዙም ካልራቀ ቦታ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ጓደኛዬ ቤት የሚወስደኝን መንገድ ማግኘት አልቻልኩም። ሁሉም ቤቶች ተመሳሳይ በመሆናቸው በጣም ግራ ተጋብቼ ነበር፤ ማስታወስም አልቻልኩም» ብሏል። ዕርዳታ ያልጠየቀበትን ምክንያትም «በከፍተኛ ደረጃ አፍር ስለነበር ሲንጋፖሪያዊያንን አቅጣጫ ለመጠየቅም ሆነ ስልክ ለመዋስ አልደፈርኩም። የፖሊስ ጣቢያም ማግኘት አልቻልኩም» ሲል ነበር ያብራራው።
ከጠፋ በኋላ ስለነበረው ቆይታም «ለ24ሰዓታት እንቅልፍ አልያዘኝም ነበር፤ ከሁለት ቀናት በኋላም ተርቤና ተጠምቼ ስለነበር ለመለመን ተገደድኩ። እንዲያም ሆኖ ሁሉንም ሰው ለመጠየቅ ስላልደፈርኩ፤ በሁለት ቀናት ከስድስትና ሰባት ሰዎች አንድና ሁለት ዶላር ብቻ ነበር ያገኘሁት» በማለት ገልጿል። ገንዘቡ ከውሃ ያለፈ የሚገዛለት ነገር ባለመኖሩም ቀናቱን በከፍተኛ ችግር ሊያሳልፍ መቻሉንም መረዳት ይቻላል።
ዜናው በመገናኛ ብዙሃን ከተላለፈ በኋላም በሲንጋፖርና ማሌዢያ መነጋገሪያ ሊሆን ችሏልኝ። አይናፋርነቱ በአንዳንዶች ዘንድ ኀዘኔታ ሲቸረው፤ በሌሎች ደግሞ «አቅጣጫ ለመጠየቅ አፍሮ ለልመና ያላፈረ» የሚል መብጠልጠል ደርሶበታል። የተቀሩት በበኩላቸው «አቅጣጫ መጠየቅ የፈራ እንዴት ሥራ ሊያፈላልግ ይችላል?» ሲሉም ጠይቀዋል። ታዲያ እኛ እንዳልነው «ካለመናገር ደጅ ይታደራል» ማለትስ ይኸው አይደል?
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
ብርሃን ፈይሳ