አንዱ «ነይ ግቢልኝ» እያለ ዘፍኖ ሲያበቃ፤ ሌላኛው «ነይ እንመቻች» እያለ ይቀጥላል። አንደኛው ዘፋኝ ሊል የፈለገው ሳይገባኝ ደግሞ ሌላኛው ተተክቶ ይበልጥ ግራ ሲያጋባኝና «ነውርን ማወቅ ነውር ሆነ እንዴ» ሲያሰኘኝ ቆየ። ያሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የዕረፍትም አልነበር፤ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ መሰናዶዎችን ስመለከት ነበር። እናላችሁ አንዱን ጣቢያ ተጠይፌ ወደሌላኛው ስሸጋገር በየመሰናዶው ማብቂያ ከሚታዩት ሙዚቃዎች ትዝብት ብቻ ነበር ያተረፍኩት።
ከታዘብኳቸው መካከል አንዱን ልንገራችሁማ፤ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች መካከል በአንዱ የተዘፈነ የባህል ሙዚቃ ነው። ነገር ግን ዘፋኙና የባህል ጭፈራውን የሚያሳዩት ተወዛዋዦች ሙሉ ለሙሉ ዘመናዊ አለባበስ የሚስተዋልባቸው ናቸው። የሚዘፈንላት ቆንጆ ወጣት ደግሞ በተራቆተ ልብሷ አንዴ መንገድ ላይ ስትሄድ ሌላ ጊዜ እየዘፈነላት ስትሽኮረመም ትታያለች።
የእኔን ቀልብ በተለይ የሳበው ግን ወጣቷ አብዛኛውን ጊዜ በምስሉ ላይ የምትታየው ከጀርባዋ መሆኑ ነው። የወቅቱን ሙዚቃዎቻችንን ከመታዘባችን እንመለስበታለን፤ በቅድሚያ ግን ስለ መዚቃ ጥቂት እንበል።
«ልዩ ዉበት ያለውና የሰውን ልቦና ሰርስሮ ሊገባ የሚችል ኃይል ያለው» ይሉታል አዋቂዎች ሙዚቃን ሲገልጹት። እውነት ነው፤ መግቢያው ከጆሮ ይሁን እንጂ የሙዚቃ ማረፊያው ግን ከልብ ላይ ነው። ስሜትን፣ ቀልብንና ሃሳብን ጠቅልሎ ከመግዛቱም በላይ ጭንቀትንና ችግርን ሁሉ የማባረር ምትሐታዊ አቅምም አለው።
ደስታን ወደ በለጠ ሃሴት የሚያሻግር፣ የተሰበረ ልብን የሚጠግን፣ የተጎዳ ስሜትን የሚያክም፣ ለኀዘንተኛ መጽናኛ የሚሆን፣ ልብን እያሞቀ ፍቅርን የሚያጎለምስ (ከዚህም በላይ ሊባልለት ይችላል) ነው፤ ሙዚቃ። የህክምና ሰዎችም ቢሆኑ ህመምን በማስረሳትና ተስፋን በማለምለም ሙዚቃ እንደ አንድ መድሃኒት የሚያገለግል መሆኑን መስክረዋል።
እስኪ ልጠይቃችሁ፤ በህይወታችሁ ትልቅ ቦታ በምትሰጡት አንዳች አጋጣሚ ያደመጣችሁት ሙዚቃ፣ እጅግ የምትወዱት ሰው የጋበዛችሁ ዘፈን፣ በተከፋችሁበትና ባዘናችሁበት ወቅት ያጽናናችሁ ድምፅ ወይም በሌላ አጋጣሚ በነበራችሁበት አካባቢ ከነፋስ ጋር የነፈሰ ሙዚቃ ከልቦናችሁ ይጠፋል? ድጋሚ ስትሰሙትስ በትዝታ ወደኋላ ተጉዛችሁ አታውቁም?
ብዙዎች «ይህ ሙዚቃ ሲወጣ እዚህ ቦታ ነበርኩ፣ ዕድሜዬ እንዲህ ነበር፣ አፍቅሬ ስንንከራተት አደምጠው ነበር፣ ከሃገሬ ስወጣ እየሰማሁት ነበር፣…» እና ሌላም ሌላም ሲሉ ይደመጣሉ። እህሳ እንዳይዘነጋ ያደረገው ሙዚቃ ከሰው ልጅ ልቦና ጋር ያለው ኃያል ቁርኝት አይደል?
አሁንም ሌላ ጥያቄ ላስከትል፤ በቅርቡ እየወጡ ካሉት ሙዚቃዎች የትኛው ትዝታ ዘርቶባችሁ አለፈ? አንዳንድ ሰዎች «ከኳኳታ ያለፈ የትኛው ዘፈን ኖሮ ትዝታ ያጭራል?» ብለው ጥያቄዬን በጥያቄ መልሰውልኛል። ሁሉንም በአንድ ጠቅልሎ መፈረጁ አግባብ ባይሆንም ይህንን ስሜት ምን አመጣው የሚለውን ግን መፈተሽ አስፈላጊ ይሆናል። እኔም ከብዙ በጥቂቱ የታዘብኳቸውን ላጋራችሁ።
«ወርቃማው ዘመን» እየተባለ በሚጠራው ወቅት (የሙዚቃው ጣዕምና ምርጫ እንደ አድማጩ ቢወሰንም) የተሠሩ ሙዚቃዎች ግን አሁንም ድረስ ተደማጭነታቸው አልቀነሰም ሊባል ይችላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየወጡ ያሉትስ? እውነት ለመናገር ከጥቂቶቹ በቀር አብዛኛዎቹ ከወራትና ከአንድ ወቅት ያላለፈ አጭር ዕድሜ ነው ያላቸው።
እርግጥ ነው የሙዚቃ ባለሙያዎች እዚህ ላይ ትንታኔ ቢሰጡበት የተሻለ ይሆን ነበር። ነገር ግን አድማጭም ስሜቱን መሰንዘር ይችላልና እንደ አድማጭ የታዘብኩት ከክፋት አይቆጠርብኝ (ለዘፋኞቹ ነው)። ከወቅቱ ሙዚቃዎች ይዘት እንነሳ፤ የሚበዙት ትኩረታቸውን ያደረጉት በተቃራኒ ጾታ የፍቅር ግንኙነቶች ላይ ነው። ይህ አዲስ ነገር ባይሆንም ፍቅርን የሚመለከቱበት መንገድም ቢሆን የተንሸዋረረ ሊባል የሚችል ነው። ምክንያቱም ያፈቀሩትን ሰው ከማደስም አልፈው ሌላ ዓይነት ስሜትን የሚያነሳሱ እንዲሁም ለሌላ ትርጓሜም የተጋለጡ ናቸው። እኔ ይህንን ታዝቤያለሁ እናንተስ ይህንን አላስተዋላችሁም?
በፊት በፊት በአማርኛ ፊልሞች ላይ ይታይ የነበረው ተመሳሳይ ርዕስ መያዝ በዘፈኖቹም ላይ ይታይ ጀምሯል። ታስታውሱ እንደሆን የአንድ ወቅት ፊልሞች «የ…ልጅ» ያበዙ ነበር፤ አንድን ሃሳብ ይዞ መዝፈን እየተለመደ ነው። እንዲያውም በቅርቡ ዘፈኖቻችን የማር ወቅት ላይ ነበሩ፤ ማርን ተንተርሰው የተዘፈኑ በርካታ ዘፈኖችን ለማሳያነት ማንሳትም እንችላለን። ሌላም አለላችሁ ደግሞ (እነዚህ ዘፈኖች ለሌላ ትርጓሜ ተጋላጭ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ) «ነይ ማታ ማታ»፣ «ላግኝሽ ማታ ማታ»፣ «ወደ ማታ»፣ «ምነው ወደ ማታ»፣ «ነይ እንመቻች»፣ «ነይ ግቢልኝ»፣ … የሚሉ የጅምላ ዘፈኖች።
የአውሮፓዊያኑን ባህል እንዳለ መውረስ ያመጣው ጣጣ ደግሞ በእነርሱ ስልት ከመዝፈንና አኳዃናቸውን ከመውረስ አልፎ አማርኛውንም ማበላሸቱን ተያይዘውታል። በርካታ ሚሊዮን ህዝብ ሊመለከታቸው እንደሚችል በመዘንጋት የሚጠቀሟቸው ቃላት ግራ የሚያጋባና ከዘፈንም የማይጠበቁ ይሆናሉ። እስኪ አስቡት «ባላየ ባልሰማ» የሚል ርዕስ ያለው ዘፈን ምን ሊያስተላልፍ ይችላል? ልቧ መሃላ እንዳለው ለመግለጽ «ልቤ ማላ» የምትል ዘፋኝስ ምን ትባል ይሆን?
ለማጣቀሻነት የማይውሉና ከግጥማቸውም አንዳች ቁምነገር ማግኘት በማይቻልበት መልኩ የሚሠሩም ናቸው። በብዛት ከሚታዩት ዘፋኞች መካከል ታዳጊነታቸው የሚያሳብቅባቸውም ይገኛሉ፤ ታዲያ እነዚህ የመዝፈን ፍላጎት ብቻ ያላቸው ልጆች ሙዚቃ ሊወደድ ቀርቶ ሊያዝና ሊደመጥ የሚችል ግጥምም ሃሳብም ያልያዙ ናቸው። የቀደመው ዘመን ዘፋኞችን በማሳያነት ብናነሳ ከዘፈኖቻቸው የሚወጡ ሃሳቦች ነገሮችን የመግለጽ አቅም ያላቸው ናቸው።
የአለባበሳቸው ነገርማ አይነሳ፤ ሁሉም ባይባሉም ጥቂቶቹ ግን ለየትኛውም ሰው ምሳሌ መሆን የማይችሉና አሳፋሪም ናቸው። ለዘመናዊ ዘፈን የግድ የባህል ልብስ ይለበስ ባይባልም ቅሉ ቢያንስ ራሳቸውን ባያራቁቱና ልቅነቱንም ባያበዙት መልካም ነው። የሚመለከታቸውና የሚከተላቸው አድናቂ ነገሮችን ማገናዘብ የሚችል አዋቂ ብቻም ሳይሆን ምንም የማያውቁ ሕፃናት መሆናቸውን ማሰብም ተገቢ ይሆናል።
ከላይ የተዘረዘሩት ዓይነት ነገሮች በኢትዮ ጵያዊያን ዘፈኖች ላይ መታየታቸውን ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። በሙዚቀኞቹ ዘንድም ተመራጭ መሆናቸውን በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል። ሙዚቃን ያስወደዱት ሙዚቀኞች መልሰው ሙዚቃን እንድንጠላ እንዳያደርጉንም ሊያስቡበት ይገባል። ምስጉንና ለባህል እና ለኪነጥበብ በማሳያነት የሚነሱ መልካም ሙዚቃዎች እንዳሉ ሁሉ፤ አርዓያነት የጎደላቸውን ደግሞ እንዳይተላለፉ ማድረግ የቴሌቢዥን ጣቢያዎች ኃላፊነት ሊሆንም ይገባዋል ባይ ነኝ። እኔ ይህንን ታዝቤያለሁ በጎደለው እናንተ ሙሉ፤ የትውልድ ኃላፊነት ግን የሁላችንም ነውና አንዘናጋ።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
ብርሃን ፈይሳ