ኢትዮጵያውያን በየዘመናችን የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠሙን ተግዳሮቶቹን ወደ ትውልድ የተጋድሎ ታሪክ እየለወጥን የብዙ አኩሪ ታሪክ ባለቤት የሆንን ህዝቦች ነን ። የአኩሪ ታሪክ ባለቤት የመሆናችን እውነታ በየዘመኑ አንገቱን አቅንቶ በኩራት የሚራመድ ትውልድ ባለቤት እንድንሆን አድርጎናል ።
በየዘመኑ በህይወት ኖረው ያለፉ አባቶቻችን፣አያቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን በሰሯቸው ታላላቅ ገድሎች ኢትዮጵያዊነት የኩራት፤ ኢትዮጵያዊነት የጥንካሬ፤ኢትዮጵያዊነት የአልበገሬነት ብሎም ኢትዮጵያዊነት የሞራል ልእልና ምንጭ ሆኗል። ይህም በብዙ የታሪክ ጸሐፊያንና የታሪክ መዛግብት ሰፍሮ የሚገኝ እውነታ ነው።
በየዘመኑ የሚከተለን ታሪክ ሰሪነት ለአለንበትና ዛሬም በልዩ ታሪካዊ ወቅት ላይ እንድንገኝ አድርጎናል። በአንድ በኩል የዘመናት ጸጸት በወለደው መንፈስ «እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን» በሚል ሀገራዊ መነሳሳት እየገነባን ነው ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ታሪካዊ ጠርዝ ላይ የደረስንበት፤ ለፍጻሜው ከመቼውም በላይ የህዝባችንን ሁለንተናዊ የሞራልና የቁስ ድጋፍ በሚፈልግበት የመጨረሻው መጀመሪያ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።
በግንባታው ዙሪያ በየወቅቱ ከውስጥም ከውጪም መልካቸውን እየቀየሩ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብረን በአሸናፊነት ለመውጣት የሞራል ልእልናችንን የምናድስበት ወቅት ነው። በጀመርነው «የይቻላል መንፈስ»ሀገራዊ የብልጽግና ጉዟችንን አስፍተንና በአዲስ የአሸናፊነት ዝማሬ አጅበን ለመጓዝ የአዲስ ታሪክ መባቻ ላይ ነን። ለዚህም እንደቀደመው ሁሉ የግድቡ ፍጻሜ እንዲያምር በታሪክ ተወዳሽ ትውልድ ሆኖ የታሪክ ሰሪነት የትውልዶችን ቅብብል ለማስቀጠል ስንጀምረው ያሳየነውን የይቻላል መንፈስና ግንባታውን ለመጨረስ የሚያስችለንን ህብረታችን በሁሉም መልኩ በማደስ ለፍጻሜው ህብረ ዜማ ራሳችንን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል።
ይህ እውነታ በአንድ በኩል እንደቀደመው ዘመን ትውልዱ እንደቃሉ የጀመረውን በድል በማጠናቀቅ የታሪክ ባለቤት የሚያደርገው ነው፤ከዚህም በላይ ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ አቅም የሚሆን የሞራል ልእልና መፍጠር የሚያስችለን የተሻለ አጋጣሚም ጭምር ነው። በተመሳሳይ መልኩ ዓለምን በሞት ስጋት የሞላው ፤የሰውን ልጅ ታሪካዊ ዋጋ እያስከፈለ ያለውን የኮሮና ቫይረስ በሀገር ደረጃ የፈጠረብንን ስጋት ያለ ብዙ ዋጋ ለመቀልበስ በሚያስችል ሌላ ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን። ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ የመግባቱን ዜና ተከትሎ ችግሩ ህዝባችንን እና ሀገራችን የከፋ ዋጋ እንዳያስከፍል ከፍተኛ ርብርቦሽ እየተደረገ ነው።
ችግሩን ባልከፋ ዋጋ ለመሻገር እያደረግነው ያለው ጥረት የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊነት ጥረት የሚጠይቅ፤ ብልጽግናን ተስፋ አድርገን ከጀመርነው የብልጽግና ጉዞ አንድም ዜጋ እንዳይጎድል ከራስ ጋር ቃል መግባትን የሚጠይቅ ነው። ራሴን በመጠበቅ ወገኔን አተርፋለሁ በሚል ለኛ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ባልሆነ ማህበራዊ እሴት ሰራዊት ሆነን የምንሰለፍበት በዚህም ወገንን በማትረፍ አዲስ ታሪክ የምንሰራበት ወቅት ላይ ነን ።
በሽታው የጀመርነው አዲስ የብልጽግና ታሪክ የመስራት ጉዞ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ ከፊታችን የቆመ ነው። ይህን ተግዳሮት በአሸናፊነት ለመወጣት እንደ ሀገር የሚጠበቅብን እጅን ደጋግሞ ከመታጠብ ራስን ከማቀብ የሚበልጥ አለመሆኑ ደግሞ ትውልዱ ይህንን ታሪካዊ ወቅት ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ የተሻለ እድል የሚፈጥርለት ይሆናል።
ሁላችንም በሽታውን ለመከላከልና ሊያደርስ የሚችለውን ሰብአዊ ጥፋት ለመቀልበስ ራሳችንን በመጠበቅ ለወገናችን ተስፋ መሆን ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ ከራሳችን ጋር ቃል ልንገባ ለቃላችን ደግሞ ታማኝ ልንሆን ይገባል። በዚህም ራሳችንን ከበሽታ እየጠበቅን የታላቁ ህዳሴ ግድባችንን ለፍጻሜ በማድረስ ዛሬም እንደትናንቱ የአዲስ ታሪክ ባለቤት እንሆናለን!።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012