ስለ ይርጋ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
“ይርጋ” የሚለው ቃል ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል። “ይርጋ አግዶታል”፤ “በይርጋ ቀሪ ሆኗል”፤ “የይርጋ ጊዜው አልፎበታል” ወዘተ… ሲባል እንሰማለን።
ለፍትሐብሔርም ሆነ ለወንጀል ጉዳዮች የይርጋ ጊዜ ይቀመጣል። በፍትሐብሔር ሕጉ በውል፣ ከውል ውጭ፣ በንብረት፣ በውርስ፣ በሽያጭና በመሰል ጉዳዮች የይርጋ ጊዜዎች ተቀምጠዋል። በንግድ ሕጉም የተለያዩ የይርጋ ደንቦችን እናገኛለን። በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ እና በሌሎችም አዋጆች ይርጋ ደንጋጊ አንቀጾች አሉ። የወንጀል ይርጋ ዝርዝር ደንቦች ደግሞ በወንጀል ሕጉ እና የወንጀል ድንጋጌን በሚያካትቱ አዋጆች ውስጥ ተቀምጠዋል።
ጠቅለል ባለ አገላለጽ የይርጋ ደንብ የአንድ ሰው የመብት ጥያቄ በጊዜ ማለፍ ቀሪ የሚሆንበትን፤ በአንጻሩ ደግሞ በጊዜው ማለፍ ምክንያት ሌላኛው ወገን የመብቶች ባለቤት የሚሆንበትን የሕግ መርሆ የሚያሳይ ነው።
በይርጋ መርህ መሰረት የአንድ ንብረት ባለቤት ያልሆነ ሰው ያንን ንብረት በይዞታው ሥር አቆይቶ ሕግ በሚጠይቀው አግባብ የተጠቀመ መሆኑ ከታወቀ ባለቤት ሊሆን የሚችልበት ነው። በዚሁ መነሻ የይርጋ ደንብ አንድም የባለዕዳውን ግዴታ የሚያስቀር ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ መብት ላልነበረው ሰው መብትም የሚሰጥ ነው።
የባለዕዳን ግዴታ የሚያስቀር ይርጋ የተደነገገው በግዴታ ሕጎች ውስጥ ነው። የባለዕዳ ግዴታ ደግሞ ከውል ወይም ከውል ውጭ ሊመነጭ ይችላል። በሁለቱም ግዴታዎች የይርጋ ዘመኑ ርዝማኔ የተለያየ ቢሆንም ቅሉ ይርጋው ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ በግዴታው ውስጥ ባለገንዘብ (ባለመብት) የሆነውን ሰው መብት ያስቀራል። ምክንያቱም ባለገንዘቡ በሕጉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ባለዕዳውን ጠይቆ መብቱን ሳያስከብር ጊዜው ካለፈ መብቱን ያጣል። ለዳተኛ ሰው ሕግ ከጎኑ አይቆምምና። ባለዕዳው ደግሞ የጊዜውን ማለፍ ተከትሎ በባለገንዘቡ ከመጠየቅ ይድናል፤ ግዴታውም ቀሪ ይሆንለታል።
ሕጉ የጊዜውን ገደብ ያስቀመጠበትም መሰረታዊ ምክንያት በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ባለገንዘቡ መብቱን ካልጠየቀ ከዚያ በኋላ የመጠየቅ ፍላጎቱ እየተዳከመ ይሄዳል የሚል ግምት በመውሰድ ስለመሆኑ የሕግ ልሂቃን ያስረዳሉ። በተጨማሪም ቀን አልፎ ቀን በተተካ ቁጥር የማስረጃዎች መገኘትና አስተማማኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ስለሚገባ የመብት መጠየቂያ ጊዜን ገድቦ ማስቀመጡ አስፈላጊ ነው።
ከባለዕዳውም አንጻር ቢሆን ዕድሜ ልኩን አበዳሪውን ወይም ባለገንዘቡን ባየ ቁጥር መንገድ እያሳበረ መሄድ ስለሌለበትና ይህ ስጋቱም የሆነ ጊዜ ላይ ሊቋጭለት ስለሚገባ ነው ሕጉ የይርጋ ገደብ ያስቀመጠው።
ያልነበረ መብትን የሚያስገኘው የይርጋ ደንብ ደግሞ አንድን ጠያቂ ያጣ ንብረት ለረዥም ጊዜ በይዞታው ሥር ያደረገ ሰው በሕግ የተቀመጡ ግዴታዎችን እያሟላ ሲጠቀምበት ከቆየ በኋላ በሕግ የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ሲጠናቀቅ የንብረቱ ባለቤት የሚሆንበት ነው።
ሕጉ አንድ ሰው አንድን ጠያቂ የሌለው ንብረት ለረዥም ጊዜ በይዞታው ሥር አቆይቶ ሲጠቀምበት በመቆየቱ ምክንያት “የንብረቱ ባለቤት ነኝ” የሚል ስሜትን እንደሚያሰርጽበት ግምት በመውሰድ ነው የባለቤትነት መብትን እንዲጎናጸፍ የፈቀደለት።
በዚህም መነሻ በሕጉ የተቀመጠው ጊዜ ካለፈ በኋላ አንድ ሌላ ሰው “የንብረቱ ባለቤት እኔ ነኝኮ” ብሎ ከበቂ የባለቤትነት ማስረጃዎች ጋርም ቢመጣ እንኳ ሕጉ “ካንተ ይልቅ ከንብረቱ ጋር የአካልም የሥሜትም ተዛምዶ አድርጎ ለዓመታት በእጁ ያቆየው እሱ ስለሆነ ላንተ ሳይሆን ለእሱ ነው የሚገባው” በማለት የንብረቱን ባለቤትነት በይዞታው ሥር ላቆየው ሰው ያስተላልፍለታል።
የፍትሐብሔር መብትና ግዴታን ከሚመለከቱት የይርጋ ድንጋጌዎች በተጨማሪ በወንጀል ጉዳዮችም የወንጀል ሕጉ ዝርዝር የይርጋ ደንቦችን አካቷል። የወንጀል ይርጋ ዋነኛ ዓላማው በሕጉ የተቀመጠው ጊዜ በማለፉ ምክንያት ተጠርጣሪውን በወንጀል ከመከሰስ ወይም የተፈረደበትን ሰው ከተወሰነበት የእስራት ወይም የገንዘብ ቅጣት ወይም የንብረት መወረስ የሚያድን ነው።
የወንጀል ክስ የማቅረቢያ ጊዜ (በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው) እንዲሁም የወንጀል ቅጣትን የማስፈጸሚያ የይርጋ ጊዜ በ997ቱ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 211 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ላይ በዝርዝር ሰፍረው እናነባቸዋለን።
በፍትሐብሔር ጉዳዮች የይርጋ ክርክር በባለጉዳዮች ካልተነሳ በስተቀር ዳኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ሊያነሱት አይችሉም። ምክንያቱም የአንዱን ወገን የሙግት ደካማነት በመደገፍ ሌላኛውን ወገን እንዳይጎዱና የተከራካሪዎችን በሕጉ ፊት በእኩልነት የመዳኘት መብትን እንዳይጥሱ ለማድረግ ስለመሆኑ የተለያዩ የሕግ ልሂቃን ያስረዳሉ። ለዚህም የ1949ኙን የወንጀል ሕግ ያረቀቁትና በሕጉ ላይ “An Introduction to Ethiopian Penal Law” በሚል ሰፊ የማብራሪያ መጽሐፍ የጻፉትን ፊሊፕ ግራቨንን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል።
በወንጀል ጉዳዮች ግን የይርጋን ጥያቄ ተከሳሽ ባያነሳውም ዓቃቤ ሕግም ሆነ ዳኞች ነገሩን መርምረው በይርጋ ከታገደ በራሳቸው አነሳሽነት ይርጋን በማንሳት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
በምርመራ ላይ የሚገኝ ጉዳይ የይርጋ ጥያቄ ካለበት ዓቃቤ ሕጉ መዝገቡን መዝጋት ይገባዋል። ያለአግባብም ክስ ተመስርቶ ከሆነም ዓቃቤ ሕጉ ጉዳዩን ማቋረጥ አለበት። ዳኞችም ቢሆኑ በይርጋ የታገደ ጉዳይ ከቀረበላቸው መዝገቡን መዝጋት አለባቸው።
የወንጀል ክስ አቀራረብ በጥቂቱ
ምርመራ እንዲደረግ የወንጀል ክስ የሚቀርበው በሁለት ዓይነት መልኩ ነው – በግል አቤቱታ አቅራቢነት (upon complaint) እና በወንጀል ክስ አቅራቢነት (upon an accusation)።
የወንጀል ክስ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚመሰረተው ቀላል ቅጣት የሚያስከትሉ ሆነው የወንጀል ሕጉ ራሱ “በግል አቤቱታ የወንጀል ክስ ይቀርብባቸዋል” በሚል ለደነገጋቸው ወንጀሎች ነው። ስድብና ማዋረድ፣ ቀላል ዛቻ፣ ስም ማጥፋትና መሰል ወንጀሎች በግል አቤቱታ ክስ የሚቀርብባቸው ናቸው።
በግል አቤቱታ ክስ የሚመሰረትባቸው ወንጀሎች ከተበዳዮች አንጻር ሲታዩ የሚያስከትሉት ጉዳት መጠነኛ ነው። ወንጀሎቹ በተበዳዮቹ በአካላቸው፣ በግል ነጻነታቸው፣ በክብራቸውና በግል ንብረታቸው ላይ የሚፈጸሙ መጠነኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው።
በመሆኑም በእንዲህ ዓይነት ወንጀሎች ተበዳዮቹ ወይም ሕጋዊ ወኪሎቻቸው አቤቱታ ካላቀረቡ መንግስት በራሱ አነሳሽነት የወንጀል ምርመራ ቢያደርግና ክስም ቢመሰርት ከሚገኘው የፍትህ ፍሬ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።
ለዚህም ነው ሁሉም በግል አቤቱታ የሚቀርቡ ወንጀሎች ተጠርጣሪው ይቅርታ ከጠየቀና ተበዳዩም በጄ ካለ የክስ ዶሴ መክፈት ሳያስፈልግ በእርቅ እንዲያልቁ የሚደረገው።
የወንጀል ክስ የሚቀርብበት ሁለተኛው መንገድ በዓቃቤ ሕግ በኩል ነው(የወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚባለው ማለት ነው)። በመርህ ደረጃ በሕጉ በተለየ ሁኔታ (በግል አቤቱታ ክስ ይቀርባል በሚል) በግልጽ ካልተደነገገ በስተቀር በማናቸውም ጉዳይ ላይ ፍርድ እንዲሰጥና ቅጣት እንዲወሰን ለማድረግ የወንጀል ክስ የሚቀርበው በዓቃቤ ሕግ በኩል ነው።
የክስ ይርጋ
በወንጀል ሕጉ የክስ ይርጋ የሚባለው የወንጀል ክስ ለማቅረቢያ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ ነው። የክስ ይርጋ የግል አቤቱታ ለማቅረብም ሆነ በመንግስት/በዓቃቤ ሕግ ክስ ለመመስረት የተቀመጠ ነው።
በዚሁ መሰረት የግል አቤቱታ መቅረብ ያለበት ተበዳዩ የወንጀሉን ድርጊት ወይም የወንጀል አድራጊውን ማንነት ካወቀበት ቀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም ሕጉ “ፍጹም የሆነ የይርጋ ዘመን” በሚል የይርጋ ዘመኑን እስከ ሶስት ዓመት ከፍ በማድረግ በወንጀል ክስ የማቅረቢያ ጊዜውን ይበልጥ ለማርዘም ሞክሯል።
በዚሁ መነሻ ተበዳዩ የግል አቤቱታውን ማቅረብ ያልቻለው ለማቅረብ በማያስችል ጉልህ ምክንያት ካልሆነ በቀር ይርጋው ካለፈ የግል አቤቱታ ለማቅረብ እንዳልፈለገ ነው ሕጉ የሚቆጥረው። የግል አቤቱታውንም ለመቀበል አይቻልም።
በወንጀል ክስ አቅራቢነት መደበኛ ክስ የማቅረቢያ ጊዜን በተመለከተ ደግሞ ሕጉ በየወንጀሎቹ የቅጣት ጊዜ በመከፋፈል የይርጋውን ዘመን አስቀምጧል።
በዚሁ መሰረት የሞት ፍርድ ወይም የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በ25 ዓመት ውስጥ ክስ ካልተመሰረተ ጉዳዩ በይርጋ ይታገዳል። ከ10 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ በ20 ዓመት፤ ከ5 እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ በ15 ዓመት እንዲሁም ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በ10 ዓመት ውስጥ ክስ ማቅረብ የግድ ነው።
ከዚህም ሌላ ከአንድ ዓመት በላይ በቀላል እስራት ለሚያስቀጣ አምስት ዓመት እንዲሁም እስከ አንድ ዓመት በቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ ብቻ ለሚያስቀጣ ወንጀል ሶስት ዓመት የይርጋ ጊዜ ተቀምጦለታል።
ሕጉ “ፍጹም የሆነ የይርጋ ዘመን” በሚልም ከላይ በየቅጣቶቹ የተቀመጡት የይርጋ ጊዜያት በእጥፍ ጊዜ ካለፉ የወንጀል ክስ ማቅረብ እንደማይቻል ደንግጓል። ለምሳሌ መደበኛ የይርጋ ዘመኑ አስር ዓመት ለሆነ ወንጀል ፍጹም ይርጋው ሃያ ዓመት ይሆናል።
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ቁልፍ ጉዳይ የወንጀል ሕጉ ክስ የማቅረቢያ የይርጋ ዘመን ቢደነግግም የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በበኩሉ በይርጋ የማይታገዱ ወንጀሎችን አስቀምጧል።
በዚሁም መሰረት ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለምአቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የአገሪቱ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተለዩትን የሰው ዘር ማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት ርምጃ መውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር ወይም ኢ-ሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም።
የክስ ይርጋ ዘመን አቆጣጠር
በወንጀል ክስ አቅራቢነት የይርጋ ዘመን የሚታሰበው የቅጣት ማክበጃ ወይም ማቅለያ ምክንያቶች ከግምት ውስጥ ሳይገቡ ለየወንጀሎቹ በሕጉ የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መሰረት በማድረግ ነው። ለምሳሌ አንድ ወንጀል ከ7-12 ዓመት የሚያስቀጣ ቢሆን የይርጋ ዘመኑ የሚሰላው በከፍተኛው ቅጣት ማለትም በ12 ዓመት ነው። እናም የይርጋ ዘመኑ 20 ዓመት ይሆናል ማለት ነው።
ከዚህ ሌላ የተፈጸመው ወንጀል በተለዋጭ ወይም በተደራራቢ ተፈጻሚነት በሚኖራቸው ቅጣቶች የሚያስቀጣ ሲሆን የይርጋ ዘመኑ የሚታሰበው ከሁሉም ከባድ ለሆነው ወንጀል የተደነገገውን ከፍተኛውን ቅጣት መሰረት በማድረግ ስለመሆኑም ሕጉ ይገልጻል።
ከላይ እንደተመለከትነው በግል አቤቱታ ለሚቀርቡ ወንጀሎች የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው ተበዳዩ የወንጀሉን ድርጊት ወይም የወንጀል አድራጊውን ማንነት ካወቀበት ቀን ጀምሮ ነው። በወንጀል ክስ አቅራቢነት ለሚያስቀጡ ወንጀሎች ደግሞ በመርህ ደረጃ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው ጥፋተኛው የወንጀሉን ድርጊት ከፈጸመበት ቀን አንስቶ ነው።
ይሁንና የወንጀሉ ድርጊት እየተደጋገመ ተፈጽሞ እንደሆነ (ለምሳሌ አስገድዶ መድፈሩ ተደጋግሞ ከሆነ) ይርጋው መቆጠር የሚጀምረው የመጨረሻው የወንጀል ድርጊት ከተፈጸመበት ቀን አንስቶ ነው። የወንጀል ድርጊቱ ለረዥም ጊዜ ሲፈጸም የቆየ እንደሆነ ደግሞ ይርጋው መቆጠር የሚጀምረው የወንጀሉ ድርጊት ካቆመበት ቀን ጀምሮ ነው።
አቶ ኃይሉ ወልዴ በወንድማቸው አቶ ሰይፉ ወልዴ ሥም የተዘጋጀ የትምህርት ማስረጃ በመጠቀም እና በፍርድ ቤትም ስማቸውን ወደ ሰይፉ ወልዴ በማስለወጥ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ተቀጥረው ለ25 ዓመታት አገልግለዋል። የኋላ ኋላ ድርጊታቸው ተደርሶበት ለእርሳቸው አገልግሎት ባልተዘጋጀ ሀሰተኛ ሰነድ ተጠቅመዋል በሚል በ2005 ዓ.ም. ክስ ይመሰረትባቸዋል።
እሳቸውም የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው ድርጊቱ ከተፈጸመበት 1977 ዓ.ም. ጀምሮ ስለሆነ የተቀመጠው የአምስት ዓመት የይርጋ ጊዜ መጠናቀቁን፤ በወንድማቸው የትምህርት ማስረጃ ለሥራ ቢመዘገቡም የመግቢያ ፈተናውን ተፈትነው ያለፉት ራሳቸው መሆናቸውን እንዲሁም በሥራው ላይ ለረዥም ጊዜ የቆዩት አየር መንገዱ በሰጣቸው የስልጠና ዕውቀት እንጂ ባቀረቡት የትምህርት ማስረጃ አለመሆኑን ጠቅሰው ሞገቱ።
ዓቃቤ ሕግም የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው የወንጀል ድርጊቱ ከቆመበት ከሕዳር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ እንጂ ድርጊቱ መፈጸም ከጀመረበት ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ አይደለም በማለት ተከራክሯል።
በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ክርክሩ ከተደረገ በኋላ ግለሰቡ በሌላ ሰው የትምህርት ማስረጃ ተጠቅመው በመቀጠራቸውና ስልጠና አግኝተው በሥራ በመሰማራታቸው በሃሰተኛው ሰነድ ተገልግለው ጥቅምና መሻሻልን ማግኘታቸው እንዲሁም የሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎቹ አገልግሎትም እስከመጨረሻው ድረስ አለመቋረጡ ተጠቅሶ፤ የወንጀሉ ድርጊት ለረዥም ጊዜ ሲፈጸም የቆየ ከሆነ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው ድርጊቱ ካቆመበት ቀን ጀምሮ በመሆኑ ጉዳዩ በይርጋ ሊታገድ እንደማይገባው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቶበታል።
የክስ ይርጋ ዘመን መቋረጥ
ሕጉ የይርጋ ዘመን አቆጣጠርን ከማስቀመጡም በተጨማሪ የይርጋ ዘመን የሚቋረጥበትንም ሁኔታ ደንግጓል። ይኸውም ከወንጀሉ ወይም ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ብርበራ እንዲደረግ፣ መጥሪያ እንዲሰጥ ወይም ክስ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ከተላለፈ ወይም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከተከናወነ ወይም ውሳኔ ከተሰጠ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ይቋረጣል።
በእነዚህ ምክንያቶች የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ከተቋረጠ በኋላ ክስ የማይቀርብ ከሆነ ግን የይርጋ ዘመኑ በተቋረጠ ቁጥር እንደገና እንደአዲስ መቆጠር ይጀምራል ማለት ነው።
ለምሳሌ አስር ዓመት የክስ ማቅረቢያ ጊዜ የተቀመጠለት ወንጀል በተፈጸመ በስድስት ዓመቱ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ከተላለፈ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ይቋረጣል። የምርመራ ትዕዛዙ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ደግሞ እንደገና እንደአዲስ የይርጋ ዘመኑ “አንድ ቀን” ተብሎ መቆጠር ይጀምራል። ከዚያም በአስር ዓመት ውስጥ የወንጀል ክስ ካልቀረበ ጉዳዩ በይርጋ ይታገዳል ማለት ነው።
ይሁንና የምርመራ ትዕዛዙ ተሰጥቶ ምርመራውም ተጀምሮ ክስ ሳይመሰረት ለምሳሌ ሰባት ዓመት ከቆየ በኋላ ለተጠርጣሪው መጥሪያ ከተላከለት የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ይቋረጣል፤ እንደገናም እንደአዲስ መጥሪያው ከተላከበት ቀን ጀምሮ መቆጠር ይጀምራል።
ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ በፌዴራል ሰበር ችሎት እልባት ያገኘ አንድን ጉዳይ በወፍ በረር አስቃኝቻችሁ ጽሑፌን ልቋጭ።
የትግራይ ክልል ዓቃቤ ሕግ በስምንት የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ላይ በ29/04/1997 ዓ.ም. በተደረገ የመኪና ግዥ ጨረታ የሥራ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል በ11/12/2002 ዓ.ም. ክስ ይመሰርትባቸዋል። የተከሰሱበት አንቀጽም እስከ አምስት ዓመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ነው። የይርጋ ዘመኑ ደግሞ አምስት ዓመት ነው።
ተከሳሾችም ወንጀሉ ተፈጸመ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ክስ እስከቀረበበት ድረስ ያለው ጊዜ ሲቆጠር እንዲሁም ቃላቸውን እንዲሰጡ ፖሊስ መጥሪያ እስከላከላቸው 27/05/2002 ዓ.ም. ድረስ ያለውም ጊዜ ሲቆጠር ከአምስት ዓመት በላይ መሆኑን በመጥቀስ የይርጋ ክርክር አንስተው በመሟገታቸው ጉዳዩ እስከ ፌዴራሉ ሰበር ደርሷል።
ይሁንና በፍጻሜው ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ ማድረግ የጀመረው በ14/04/2001 ዓ.ም. መሆኑ በመረጋገጡ ይኸው የፖሊስ ምርመራ ደግሞ የይርጋው ዘመን ከማለፉ አስቀድሞ የይርጋውን መቆጠር ያቋረጠው በመሆኑና ይርጋውም እንደገና እንደአዲስ መቆጠር በመጀመሩ ጉዳዩ በይርጋ እንደማይታገድ ሊወሰን ችሏል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
በገብረክርስቶስ