ለማስታወስ፤
ቅሬታ አቅራቢ አቶ በዛብህ ታምሩ ወደ ዝግጅት ክፍላችን ለመምጣት መሰረታዊ ምክንያት ሆኖኛል ብለው የነበረው የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያስቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት በትክክለኛው የስራ ሂደት ላይ ባለመሆኑ ሂደቱ እንዲስተካከል ችግሩን ለማጋለጥ ነበር፡፡ዝግጅት ክፍሉም መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም ይህንኑ አቤቱታ ማቅረቡ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ ላለፉት ዓመታት የሚሰራቸው ስራዎች በአጠቃላይ የተቋሙን ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማ ለማሳካት በሚያስችለው መንገድ አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢው አቤት ብለው ነበር። የሚጠበቅበትን ኃላፊነቶች ለማሳካት ከመትጋት ይልቅም በገጽታ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጓል የሚል ትዝብት መያዛቸውንም ዘግበን ነበር።
ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ተግባሩን ባለመስራቱ አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን ከፍተኛ የስነ ምግባር ብልሽት ገንኖ እንዲታይ ምክንያት መሆኑን እና በየተቋማት ከፍተኛ የስነ ምግባር ብልሽት እንዲፈጠር ማድረጉንም ማመልከታቸው ይታወሳል።
በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ክፍተት የተፈጠረው ኮሚሽኑ ተልዕኮውን በትክክል መወጣት ባለመቻሉ የመጣ መሆኑን ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ ባሳለፋቸው የትግበራ ዓመታት ኃላፊነቱን ባግባቡ ቢወጣ ኖሮ የሥነ ምግባር መጓደል ዛሬ ገንኖ ሊታይ እና መነጋገሪያ ሊሆን አይችልም ነበር ሲሉም በቁጭት መናገራቸውን ዘግበነው ነበር።
የምርመራ ዘርፍ በተቋሙ በነበረበት ወቅትም (አሁን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተጠቃሏል) የሙስና ወንጀል በሚደረግበት ወቅት አንዳንድ የኮሚሽኑ ሰራተኞች የሆኑ በሙስና የተጠረጠረን ግለሰብ እንዳይከሰስ በዋስ ለማስወጣት ጫና የመፍጠር አዝማሚያ ታይቶባቸዋል።እንዲህ አይነት ግለሰቦችን ተጠያቂ ማድረግ ሲገባቸው በተቃራኒው ተሹመው ኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ መኖራቸውንም በመጠቆም ተግባሩ ትክክል አለመሆኑን በማንሳት ይወቅሱና፤ እንደዚህ አይነት ሰዎች ከኮሚሽኑ መወገድና ህጋዊ ርምጃ ሊወሰድባቸው ሲገባ፤ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ግን የስራ ሂደት ኃላፊ ሆኖ መሾማቸውን ኮንነው እንደነበርም አይዘነጋም።ዛሬ ደግሞ ኮሚሽኑ ለቀረበበት ቅሬታ ምላሽ ሰጥቷል።እነሆ፡-
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም በፍረዱኝ አምዱ የኮሚሽኑ ባልደረባ የሆኑት አቶ በዛብህ ታምሩ በኮሚሽኑ አመራርና አሰራር ላይ ያቀረቡትን አቤቱታ ይዞ መውጣቱ ይታወሳል።በመሠረቱ አቶ በዛብህ ለጋዜጣው ያቀረቡት አቤቱታ በተደጋጋሚ በኮሚሽኑ የግምገማ መድረኮች ያነሷቸውና መልስ የተሰጠባቸው፣ ከግል ፍላጎትና ጥላቻ የተነሱ ተጨባጭነት የሌላቸውና አማራጭ ሃሳብ እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ተጠይቀው ማቅረብ ያልቻሉባቸው ቢሆኑም አንባቢያንን የሚያሳስቱ በመሆናቸው አንባቢንና ህብረተሰቡ እውነታውን እንዲያውቅ ባቀረቧቸው የአቤቱታ ጭብጦች ላይ በማተኮር ለአንባብያን መረጃና ማብራሪያ እንደሚ ከተለው እናቀርባለን፡፡
አቶ በዛብህ ኮሚሽኑ በከፍተኛ ደረጃ በሥነ-ምግባር ጥሰት እና በሙስና ችግር የተዘፈቀ፣ አመራሩና ሠራተኞቹ የሥነ ምግባር ግድፈትና የሙስና ችግር ያለባቸው፣ ተቋሙ ተጠያቂ የማድረግ አሰራር የሌለው እና እርምጃ የማይወስድ ነው በማለት ከእውነታ የራቀ ስም ማጥፋት እና ተራ ውንጀላ አቅርበዋል።
ኮሚሽኑ ከተገልጋዮች እና ከውስጥ ሠራተኞች በሰራተኞች እና በሥራ መሪዎች ላይ የሚቀርቡ የሙስና እና የሥነ-ምግባር ግድፈት ቅሬታ እና ጥቆማዎችን ተቀብሎ የሚያስተናግድበት እና ውሳኔ የሚሰጥበት የተጠናከረ አሰራር ያለው ተቋም ነው።ኮሚሽኑ አቶ በዛብህ እንደሚሉት የሥነ-ምግባር ግድፈት እና የሙስና ተግባር የፈጸሙ ሠራተኞችን የማይጠይቅ ሳይሆን በዘረጋቸው የጥቆማና የቅሬታ መቀበያ አሰራሮች የቀረቡለትን ጥቆማዎች ተቀብሎ በማጣራት የተወሰነ የኮሚሽኑ ሠራተኞችን ለህግ በማቅረብ አስቀጥቷል።የተለያዩ የሥነ ምግባር ግድፈት የፈጸሙ ሠራተኞችንም ከሥራ አሰናብቷል፤ የአስተዳደር እርምጃም ወስዷል።
በዚህ በኩል በርካታ ስራዎችን ለመስራቱ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።ለዚህም ማሳያ ቅሬታ አቅራቢው አቶ በዛብህን ጨምሮ በኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ በቀረበ ጥቆማ መነሻነት በዚህ በኩል በርካታ ስራዎችን ለመስራቱ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።ለእዚህም ማሳያ ቅሬታ አቅራቢው አቶ በዛብህን ጨምሮ በኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ በቀረበ ጥቆማ መነሻነት የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሉ አጣርቶ ውሳኔ የሰጠባቸው 108 ጉዳዮችን ማየት ይቻላል።ብዙ እርቀት ሳንሄድ አቶ በዛብህ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስልጠና እንዲሰጡ በተላኩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የኮሚሽኑን መመሪያ በመጣስ ከኮሚሽኑ አበል ወስደው አስገድደው አላግባብ ከሦስት ዩኒቨርሲቲዎች 17000 ብር (አስራ ሰባት ሺ) በድጋሚ መቀበላቸው ለኮሚሽኑ የሥነምግባር መከታተያ ክፍል በቀረበ ጥቆማ ማጣራት ተደርጎበት ጥፋተኝነታቸው በመረጋገጡ እና ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ በመጠየቃቸው ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ቅሬታ አቅራቢውን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው።አቶ በዛብህ ያነሱት ወቀሳ የፈጸሙት የሥነ ምግባር ግድፈት በመርሳት ነው? ወይስ የሳቸው ተግባር ግድፈት ባለመሆኑ?
ከዚህ በተጨማሪ ‹‹የውሸት ንግግር አይደገምም›› እንደሚባለው ቅሬታ አቅራቢው ያነሱት ወቀሳ በመርሳት በአቤቱታቸው ያነሱት ከምርመራ እና ዓቃቤ ህግ እንዲሁም ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች እና ጥቆማዎችን የኮሚሽኑ አመራር በወሰደው እርምጃ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ባለሙያዎች በመመደብ እንዲጣራ ማድረጉ ሌላው ማሳያ ነው፡፡
አቶ በዛብህ በእዚህ የማጣራት ሥራ እርምጃ አልተወሰደም የሚል ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸዋል። በመሰረቱ እርምጃ ለመውሰድ በግልጽ እና በማያሻማ ሁኔታ የቀረቡ ጥቆማዎች በማስረጃ መረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በዚህ በኩል አቤቱታ አቅራቢው እንደገለፁት በኮሚቴው የማጣራት ሥራ አቃቤ ህጉ ተከሳሾችን በዋስ እንዲለቀቁ ማድረጉ ጥቅም ተቀብሎ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንዳልሆነ ኮሚቴው የገለጸ በመሆኑና፤ ዓቃቤ ህጉ በተሰጠው ነፃነት መሰረት ጉዳዩን አገናዝቦ የዋስትና መብት እንዲከበር ተገቢ ነው ያሉትን ውሳኔ የሰጡበት ሁኔታ መኖሩን ስለሚያሳይ፤ እንዲሁም ለተጠርጣሪ አማላጅ ሆነዋል በሚለው ጉዳይ ቅሬታ አቅራቢው እንደገለጹት ምስክሮች ቀርበው የተባለው ግለሰብ ጉዳያቸውን እንዲያስፈፅምላቸው ሳይሆን ቅሬታቸውን ለማቅረብ እንደመጡ የመሰከሩበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ አብዛኞቹን ችግሮች በአሰራር ማሻሻያ እንዲፈቱ ተደርጓል።
ኮሚሽኑ ያጣራቸው ጥቆማዎች በኮሚሽኑ ብቻ እንዳይታጠር ለማድረግም ህዝቡ እና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግልፅ እና የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው በወቅቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እንዲላክ ተደርጓል። በጉዳዩ ላይ በሠራተኞችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት መተማመን የተፈጠረበት ጉዳይ ነው።ቅሬታ አቅራቢው ዛሬ እንደ አዲስ የኮሚሽኑ ሠራተኞችና አመራሮች በሙስና እና በሥነምግባር ችግሮች ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው ብሎ ለማሳያነት ማንሳት ለጸረሙስና ትግሉ ከመቆርቆር የመነጨ ነው ለማለት ያስቸግራል።
እጅግ ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ ብዙ መስዋእትነት የከፈሉ የሙስና ወንጀል መርማሪዎችና አቃቤ ህጎችን ስምና ክብር የሚነካ በመሆኑና ህብረተሰቡ በጸረሙስና ትግሉ ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽር በመሆኑ አቶ በዛብህ አለኝ የሚሏቸውን ማስረጃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማቅረብ ማረጋገጥና ተጠያቂ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።የሰሚ ሰሚ የሙስና ወንጀል ተፈጽሟል አውቀለሁ ማለት ከተጠያቂነት እንደማያድን ኮሚሽኑ መግለጽ ይወዳል።
ከዚህ በተረፈ ማንኛውም ዜጋ የቀረበውን ጥቆማና ተጣርቶ ውሳኔ የተሰጠበትን ሪፖርት ማየት ከፈለገ በማንኛውም ጊዜ ማየት እንደሚችል እየገለጽን አሁንም ያልተጣሩ ጉዳዮች አሉ የሚባሉ ከሆነም ኮሚሽኑ በማንኛውም ጊዜ ለማጣራት ዝግጁ መሆኑን እናረጋግጣለን።
ቅሬታ አቅራቢው ‹‹ኮሚሽኑ ላለፉት 19 ዓመታት የሰጣቸው የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች ኮሚሽኑ ከቆመለት ዓላማ እና ተልእኮ ጋር የተቃረነ አካሄድን የተከተለና የሙስናን አስከፊነት በማስገንዘብ ሰልጣኞች ሙስናን በመታገል ድርሻቸውን እንዲወጡ በሚያስችል ሁኔታ የተቃኙና የተተገበሩ አይደለም፤ የሥልጠና ሞጁሎችም የሙስና ጽንሰ-ሃሳብ፣ የሥነምግባር ጽንሰ ሃሳብ እና የሙስና ወንጀል ህጎች ላይ ብቻ የታጠሩ ናቸው›› በሚል አንስተዋል።ለዚህም ማሳያ ኮሚሽኑ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በመልካም ሥነ-ምግባር፣ በሙስና ጽንሰ ሃሳብ እና በሙስና ወንጀል ህጎች ዙሪያ አጠቃላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መስጠቱን እንደ ችግር ለማሳየት ሞክረዋል፡።
በመሠረቱ አቶ በዛብህ በሥልጠና ሥራ ላይ ያነሱት ትችት በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ፣ አሳሳች እና ከእውነታው የራቀ ሃሳብ ነው።እንደሚታወቀው ከኮሚሽኑ ዓላማዎች መካከል አንዱ የሥነምግባርና የጸረሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ መፍጠር ነው።ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር በቅድሚያ በመልካም ሥነምግባርና በሙስና አስከፊነት ዙሪያ አጠቃላይና መሠረታዊ የሥነምግባርና የጸረሙስና ትምህርትና ስልጠና ለሁሉም ህብረተሰብ በመስጠት በመልካም ሥነምግባር አስፈላጊነት፣ በሙስና አስከፊነትና ሙስናን ለመዋጋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚያስፈልግ በሙስና መከላከል ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።ሙስናን በመከላከል ውጤታማ የሆኑ አገራት ይህን ዓላማ ለማሳካት አጠቃላይ እና ሁሉን አቀፍ መሰረታዊ የሥነምግባር ትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራም በመቅረጽ ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ይሰጣሉ።
አጠቃላይ እና ሁሉን አቀፍ መሰረታዊ የሥነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርት እና ሥልጠና በማዘጋጀት ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ይመክራሉ፤ በጸረሙስና ትግሉ ውጤታማ የሆኑ አገራት ልምድም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።ኮሚሽኑም በመልካም ሥነምግባር፣ በሙስና እና በሙስና ወንጀል ህጎች ዙሪያ አጠቃላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መስጠቱ ሙስናን የሚዋጋ ህብረተሰብ ለመፍጠር መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።ይህ ሥልጠና ላለፉት ዓመታት የተሰጠ ሲሆን አሁን የሚሰጥበት ሁኔታ ግን ለሥልጠናው አዲስ ለሆኑና ሥራ ለሚጀምሩ የስራ ሥነ ምግባር ይሰጣል።
አቶ በዛብህ እንደሚሉት ሳይሆን የኮሚሽኑ የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ትምህርትና ሥልጠና ስለመልካም ሥነምግባርና ሙስና አስከፊነት ግንዛቤ ከመፍጠር በዘለለ በጥናት በተለዩ በአገራችን ልማትና እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በሚያስከትሉ እና ለሙስና ይበልጥ በተጋለጡ ሴክተሮች ማለትም (በመሬት
አስተዳደር፣ በፋይናንስ፤ ግብርና ታክስ አስተዳደር፣ በኮንስትራክሽንና ትላልቅ ግዢና ሽያጭ እና በፍትህ አካላት)፤ እንዲሁም በህፃናትና ወጣቶች ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ያተኮሩ ሴክተር ተኮር ስልጠናዎችም ይሰጣሉ።
ለዚህም አቶ በዛብህ እንደሚሉት በሦስት ሞጁሎች (የሙስና ጽንሰ ሃሳብ፣ የሥነምግባር ጽንሰ ሃሳብና የሙስና ወንጀል ህጎች) ላይ ብቻ የታጠረ ሳይሆን ለየሴክተሩ ሰባት መሠረታዊ የማስተማሪያና ማሰልጠኛ ሞጁሎች አዘጋጅቶ ለሴክተሮቹ የሥራ ኃላፊዎችንና ሠራተኞች፣ ለሲቪክና የሙያ ማህበራት አባላት እና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
በቅርቡም በወጣቶችና በህጻናት ሥነምግባር ግንባታ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሥነምግባራዊ አመራርና በሀብት ምዝገባ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅቶ ወደሥራ አስገብቷል። ይህን ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ ያዘጋጃቸውን ሞጁሎች መመልከትና የሰልጣኞችን ፕሮፋይል በማየት እና ሰልጣኞቹን በመጠየቅ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
እንግዲህ ኮሚሽኑ አጠቃላይና መሠረታዊ የሆነ የሥነምግባርና የጸረ ሙስና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እና ሥልጠና መስጠቱ፣ በህብረተሰቡ ልማትና እድገት እንቅፋት በሆኑ እና ይበልጥ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በተጋለጡ መስኮች እና በነገ አገር ተረካቢ ህጻናትና ወጣቶች ሥነምግባር ላይ መመስረቱ እንዴት ከተልእኮው በተቃረነ መንገድ እየተጓዘ ነው ያሰኛል።አቶ በዛብህ በኮሚሽኑ በዚህ የሥራ ክፍል እየሰሩ ይህንን መደበቃቸው ለምን ይሆን?
በተለያዩ ጊዜያት በኮሚሽኑ እና በውጪ አካላት በኮሚሽኑ ትምህርትና ስልጠና ላይ የተደረጉ ጥናቶች ሳይሆን አቶ በዛብህ እንደሚሉት፤ ዓላማውን የሳተና ሙስናን ለመዋጋት የማያግዝ እንዳልሆነ አሳይቷል፤ ይልቁንም ከኮሚሽኑ ሥራዎች የተሻሉና ተቀባይነት ያላቸው እንደሆነ ነው።ይህ ማለት በኮሚሽኑ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ፍጹምና ከችግርና ድክመት የጸዳና የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ ነበሩ ማለት አይደለም። ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት የትምህርትና ሥልጠና ድክመትና ችግሮች የአቀራረብ የሳቢነት፣ የተደራሽነት፣ የተከታታይነትና የአሰልጣኞች የልምድና ተጨባጭ የማድረግ ችግር እንጂ ከኮሚሽኑ ተልእኮ አንጻር ያልተቃኘና ሙስናን ለመዋጋት የማያግዙ መሆናቸውን የሚያሳዩ አይደሉም።ይህንን ለማረጋገጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከሊማንጃሮ በተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅትና በኮሚሽኑ የተካሄዱ ጥናቶችን መመልከት ይቻላል።
ቅሬታ አቅራቢው ሥልጠናው ለተለያዩ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች ከሥነምግባርና ከሙስና ችግሮች አንጻር የተቃኘ ሥልጠና ማዘጋጀትና መስጠት ቢቻል ያሉት ተገቢ ቢሆንም አዲስ ሃሳብ ማቅረባቸው ግን አይደለም።እርሳቸው በሥራው ላይ እያሉ የቅርብ ሩቅ ሆነው ማየት አለመቻላቸው ከቅንነት አለመነሳታቻው እንጂ ሥራው በዚህ መልክ እየተሰራ ነው።
የትምህርትና ሥልጠና ሥራ ከፍተኛ ሀብት፣ በርካታ የሰው ኃይልና ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ነው።በመሆኑም ኮሚሽኑ አገሪቱ ውስጥ ላሉ ተቋማት እና የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ለእያንዳንዱ በተናጠል ሥልጠና የማዘጋጀት አቅም ስለሌለው ባለው ውስን ሃብት ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል አሰራር ቀይሶ እየተገበረ ይገኛል፡፡
በዚህ በኩል የኮሚሽኑ የፊት ለፊት ሥልጠና የሥራ ክፍል የተቋማትን የስልጠና ፍላጎትና ጥያቄ በመቀበል አሰልጣኞች በተለያዩ አግባብ የተቋሙን የሥነምግባር እና የሙስና ችግሮች በመለየት ለተቋሙ የሚስማማ ስልጠና የሚሰጥበት አቅጣጫ ተቀይሶ እየተሰራበት ነው። አቶ በዛብህ ይህን አያውቁም ማለት ያስቸግራል። ምናልባት ይህ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ መልክ ራሳቸው መስራት አልቻሉ ይሆናል እንጂ።
በሌላ በኩል አቤቱታ አቅራቢው ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ባለማከናወኑ በየተቋሙ እና በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚታዩ ለኢሥነምግባራዊ ድርጊቶች፣ ለአገልግሎት አሰጣጥ እና ለሙስና ችግሮች ማደግ ኮሚሽኑ ተልእኮውን በአግባቡ ባለመወጣቱ ብቻ የመጣ እንደሆነ በድፍረት ገልጸዋል። በመሰረቱ አስተያየት ሰጪው የጸረ ሙስና ተቋም ሠራተኛ ሆነው የሥነምግባርና የጸረሙስና ችግሮች በአንድ ተቋም ጥረት ብቻ የሚፈታ ችግር አለመሆኑን መገንዘብ አለመቻላቸው በእጅጉ ያሳዝናል።
ይህን በተመለከተ አንባቢያን መገንዘብ ያለባቸው ለሙስናና ሥነምግባር ችግሮች መከሰት በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ምክንያቶች መኖራቸውን ነው።ይህንንም በሥነምግባርና በሙስና ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች ያሳያሉ። ችግሩን ለማቃለልም የተለያዩ አካላትን ተሳትፎ እና በሁሉም አቅጣጫዎች ሰፊ እና ሥርነቀል የሆኑ የአሰራር ማሻሻያዎች እንዲሁም የመፍትሄ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል።ከእነዚህ መካከል የሥነምግባርና የጸረሙስና ኮሚሽን ተግባር አንዱ ነው እንጂ ብቸኛው አይደለም።ለዚህ ነው በአገራችንና በተለያዩ ዓለማት በርካታ ሴክተሮችን የሚመለከቱ የማሻሻያ ፕሮግራሞችና የለውጥ መሳሪያዎች የሚዘረጉት እና ተግባራዊ የሚደረጉት።በአገራችንም የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራምን መመልከት ተገቢ ነው።በመሆኑም በአገራችን የሥነ ምግባርና የሙስና ችግሮች መስፋትም ሆነ መቀነስ በኮሚሽኑ ጥንካሬ እና ድክመት ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም።
ለአብነት እ.ኤ.አ በ2020 በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ግምገማ አገራችን ኢትዮጵያ በሙስና ከነበረችበት ከ114ኛ ደረጃ ወደ 96ኛ እንዲሁም ከ33 ከመቶ ወደ 37 በመቶ መሻሻሉን ያሳያል፤ ይህ ሊሆን የቻለው የኮሚሽኑ የፀረ ሙስና ትግል እንቅስቃሴ ታክሎበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።ይህ ረጅም አመት በጸረሙስና አሰልጣኝነት ሰራሁ ከሚል ሰው ይሰወራል ብለን አናምንም፡፡
አቶ በዛብህ በኮሚሽኑ ላይ ቅሬታ በማቅረባቸው በጂኤጂ ውጤት እያላቸው ከነበሩበት ደረጃ 14 ወደ ደረጃ 11 ዝቅ መደረጋቸውን ገልጸዋል።ይህንን በተመለከት እውነታው ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም በወጣው በነጥብ የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ዘዴ የመንግሥት ሠራተኞች የድልድል አፈፃፀም መመሪያ መሠረት ማንኛውም ሠራተኛ እስከ ሁለት የሥራ መደቦች ተመዝግቦ መወዳደር እንደሚችል ይገልጻል፣ ሠራተኛው በዕጩነት በተመዘገበባቸው ሁለት የሥራ መደቦች ላይ ተወዳድሮ ካልተመረጠ የድልድል ኰሚቴው በሌሎች አቻ ወይም ዝቅ ባሉ ደረጃዎች ላይ አወዳድሮ ይመድበዋል ይላል።በመመሪያው በተቀመጡ መሥፈርቶች መሰረት የሁሉም የኮሚሽኑ ሠራተኞች ውጤት በግልጽ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ እንዲመለከቱት ተደርጓል።
ቅሬታ አቅራቢው በመስፈርቱ መሰረት ያገኙት አጠቃላይ ውጤት 89.885 በመቶ ሲሆን በድልድል መመሪያው መሰረት ሁለት የስራ መደቦች ላይ ማለትም የመጀመሪያ ምርጫቸውን የስነ ምግባር አውታሮች ማስተባበሪያ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር መደብን፣ ሁለተኛው ምርጫቸው ደግሞ የስልጠና ማእከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሥራ መደብ በማድረግ ተወዳድረዋል።በውድድሩም ለሥነ ምግባር አውታሮች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር መደብ በአጠቃላይ ውጤታቸው 93.007 በመቶ ውጤት ያላቸው ተወዳዳሪ አንደኛ በመሆን ዳይሬክተር ሲሆኑ ለሥልጠና ማእከል ዳይሬክተር የሥራ መደብ ከተወዳደሩት መካከል ደግሞ በአጠቃላይ ውጤታቸው 92.902 በመቶ ያገኙ ተወዳዳሪ ዳይሬክተር ሆነዋል።ቅሬታ አቅራቢው በሁለቱም ምርጫቸው ከተወዳዳሪዎች ያነሰ ነጥብ በማምጣታቸው እድሉን አላገኙም፡፡
ሠራተኛው በዕጩነት በተመዘገበባቸው ሁለት የሥራ መደቦች ላይ ተወዳድሮ ካልተመረጠ የድልድል ኰሚቴው በሌሎች አቻ ወይም ዝቅ ባሉ ደረጃዎች ላይ አወዳድሮ ይመድበዋል በሚለው መሰረት የትምህርት እና ስልጠና ባለሙያ IV ደረጃ XII የተመደቡ ሲሆን በራሳቸው ፍላጎት የፊት ለፊት የሥነ ምግባር ትምህርት ባለሙያ III ደረጃ XI እንዲመደቡ በጠየቁት መሰረት የተመደቡ መሆናቸውን አንባቢ ሊገነዘብ ይገባል።
የፌደራል የሥነምግባርና የጸረሙስና ኮሚሽን የሰራተኞች ቅጥር እና እድገት የሚፈጽመው በኮሚሽኑ የአስተዳደር ደንብ ላይ የተቀመጡ የትምህርትና የሥራ ልምድ መሥፈርቶችን መሠረት በማድረግ ነው።መስፈርቱን ያሟሉ ተመዝጋቢዎች በውጪ አካልም ፈተናም ይሰጣል።ሆኖም ግን ቅሬታ አቅራቢው ሁለት ጊዜ በቡድን መሪነት እና የስልጠና ባለሙያ IV ደረጃ XIII በወጣው የደረጃ እድገት ማስታወቂያ መሰረት ለመወዳደር ከተመዘገቡ በኋላ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው ፈተና ላይ ተገኝተው ፈተናውን እንዲወስዱ በማስታወቂያ ተገልጾላቸውና ተነግሯቸው ፈተናውን ሳይወስዱ የቀሩ ናቸው።እንግዲህ አቶ በዛብህ ኮሚሽኑን እና የኮሚሽን አመራር የሚወነጅሉትና ሥም የሚያጠፉበት ምክንያት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ስልጣን ለማግኘት ወይም የኃላፊነት ቦታ ለመቀመጥ ካላቸው ፍላጎት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
አቤቱታ አቅራቢው በኮሚሽኑ የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ሰራተኞች እንደሚለቁ እና ነባር ሰራተኞች በአሁኑ ጊዜ እንደሌሉ በመረጃ ያልተደገፈ ሃሳብ አቅርበዋል። በኮሚሽኑ የሰራተኞች መልቀቅ ወይም ፍልሰት መጠን ከ2005 – 2012 ዓ.ም በአማካይ 11 በመቶ ነው።ይህ ባይሆን ይመረጣል።ነገር ግን አብዛኛቹ የኮሚሽኑ ሠራተኛ ወደ ሌላ መስሪያ ቤት ወይም የግላቸውን ስራ ለመስራት የወጡት የተሻለ ደመወዝ ወይም ገቢ አግኝተው እንደሆነ አሁን በሚሰሩበት መስሪያ ቤት ወይም በተሰማሩበት የግል ሥራ ላይ ማረጋገጥ ይቻላል።ነባር ሠራተኞች የቀሩት ጥቂት ናቸው የሚለውን በተመለከተ ኮሚሽኑ አሁን ባለው መረጃ መሰረት በኮሚሽኑ ቆይታ ከ5 – 17 ዓመት የቆዩ ሰራተኞች መጠን 44.44 በመቶ ሲሆን ከ3 እና 4 ዓመት በላይ የቆዩ 26.36 በመቶ ሲሆን በጥቅሉ ከ3 ዓመት በላይ ቆይታ ያላቸው ናቸው፡፡
የኮሚሽኑ አመራር የለውጡ ተፃራሪ፣ በሙስና የተዘፈቀና የቀድሞ ሥርዓት አገልጋይ ሆኖ የተመደበ ነው በማለት አቤቱታ አቅራቢው ላቀረቡት ተራ ውንጀላ እና ስም ማጥፋት ኮሚሽኑ ጉዳዩን በማስተዋልና በጥንቃቄ ተመልክቶታል፡፡
የኮሚሽኑ አመራር እጅግ በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ የሚደረገውን የፀረ-ሙስና ትግል እንደ ሃገር በማስተባበር እና በመምራት ቀላል የማይባሉ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ የራሱን ድርሻ ያበረከተና ሚናውን የተወጣ አሁንም በአዲስ የለውጥ መንፈስ ኃላፊነቱን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት ጊዜውን ጉልበቱን እና ዕውቀቱን ሣይቆጥብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ አመራር ነው፡፡
በተለይ ከለውጡ ወዲህ በፀረ-ሙስና ትግሉ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት በመለየት እና የዕቅድ አካል በማድረግ የአመራሩ ቁልፍ የርብርብ ማዕከል ሆነው እንዲተገበሩ ደፋ ቀና በሚባልበት በአሁኑ ወቅት አመራሩ የለውጥ ተፃራሪ ነው ብሎ መፈረጅ ዕውነታን ማገናዘብ ከሚችል ባለሙያ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለን አናምንም።
በተለይ ‹‹የኮሚሽኑ ቢሮ ወደ ካሣንችስ የተዛወረው አመራሩ ከችግሮቹ ለመሸሽና ሰራተኞችን ለመበተን ነው›› ያሉት ውንጀላ አቤቱታ አቅራቢውን ግምት ውስጥ የሚጥል አስተያየት ሲሆን ስለ ኮሚሽኑ ዝውውር ሁኔታ መላው ሠራተኛ የሚያውቀው በመሆኑ ፍርዱን በዋናነት ለተቋሙ ሠራተኞች እንተዋለን።
በመጨረሻም ቅሬታ አቅራቢው ከጭፍን ጭፍን ትችትና ፍረጃ ወጥተው አማራጭ ሃሳብ እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ በአመራሩ እና በሥራ ክፍል ኃላፊዎቻቸው ሲጠየቁ በተለያዩ ምክንያቶች ሃሳብ ማቅረብ ያልቻሉ መሆናቸውን መግለጽ እንወዳለን።በመሠረቱ አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከሰጠ በጉዳይ ሌላ አማራጭ እንዳለው ይታመናል።ለእዚህም ማሳያ በማሰልጠኛ ሞጁሎች ላይ በሰጡት አስተያየት መሰረት ሞጁሉን እንዲያስተካክሉ ሲጠየቁ ‹‹አስተያየት በመስጠቴ ሥራ (አስተካክል) ተባልኩ›› ብለው ለቅርብ አለቃቸው፣ በግልባጭ ለኮሚሽነር ጽ/ቤት የጸፉትን ማመልከቻ ማየት ይቻላል፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና የሥራ ኃላፊያቸውን በመጠየቅም ማረጋገጥ ይቻላል።
የኮሚሽኑ አመራር ሙስናና ብልሹ አሠራር ለሀገራችን ዕድገትና ብልፅግና ማነቆ እንዳይሆን ትግሉን በማስተባበር ረገድ የሚቻለውን ሁሉ በቅንነት እያደረገ የሚገኝ፣ ራሱን ከሙስና እና ብልሹ አሰራር በመጠበቅ በዚህ ውስጥ የሚገኙ ኃይሎችን በፅናት የሚታገል፣ ከተግባር እየተማረና ራሱን እያበቃ አጠቃላይ የፀረ-ሙስና ትግሉ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ አመራር ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ በእጥረትና በድክመት የሚታዩበትን ማንኛውንም ነገሮች ከየትኛውም አቅጣጫ ሂስ ቢቀርብበትም ለመማር እና ለመሻሻል ሁሌም በለውጥ ጎዳና ለመራመድ ፍላጐቱም ሆነ ብቃቱ ያለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።አቶ በዛብህ አለኝ የሚሉትን ማስረጃና አማራጮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያቀርቡ፤ይህን ማድረግ ካልቻሉ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማሳሰብ ኮሚሽኑ ይወዳል፡፡
የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን አዋጅ
የተሻሻለው የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ቁጥር 433/1997 ማቋቋሚያ አዋጅ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦች ሙስናና ብልሹ አሠራር የአንድን አገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት የሚገታ ተግባር መሆኑን የተገነዘቡ በመሆናቸው፤ አገሪቱ የተያያዘችውን የእድገት ጎዳናና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማፋጠንና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በቁጥጥር ሥር ማዋል አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት መሆኑን ደንግጓል።
ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን ለመሸከም የማይፈልግ እና ይህንኑ በብቃት ለመዋጋት ዝግጁ የሆነ ሕብረተሰብ መፍጠር በማስፈለጉ፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመመርመር፣ ለመክሰስ ለመቆጣጠርና ለመከላከል መልካም ሥነ ምግባር በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ በማድረግ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በብቃት መዋጋት እንዲቻል፣ የኮሚሽኑን አሰራር እና እንቅስቃሴ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሆዎችን በሚገልጽ መልኩ ማዕቀፉን ማዘጋጀት ማስፈለጉም ለአዋጁ መሻሻል እንደምክንያት ተቀምጧል።
እንዲሁም ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ በሚያስችለው መልኩ ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻልም አስፈልጓል።በመሆኑም የኮሚሸኑን ስልጣንና ተግባር ከኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ጋር በማጣጣም እና በሌሎችም ግልጽነት በሚያንሳቸው አንዳንድ የአዋጁ ድንጋጌዎች ማሻሻያ መደረጉን ያትታል።
ስለኮሚሽኑ የአሰራር ነጻነት በሚደነግገው የአዋጁ ክፍል እንዳመለከተውም፤ ኮሚሽኑ በሚመረምራቸው ወይም ክስ በሚመሰርትባቸው ወይም ክስ በመሰረ ተባቸው ጉዳዮች ላይ ከማንኛውም ሰው ወይም አካል ጣልቃ ገብነትና አመራር ነፃ መሆኑም ተደንግጓል።
አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ስለ ሙስና ጎጂነት የህዝቡ ንቃተ ህሊና እንዲጎለብት በማስተማር እና መልካም ሥነ-ምግባር በሕዝብ አገልግሎት እና በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ በማድረግ ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን መዋጋት ኮሚሽኑ ከተጣሉበት ኃላፊነቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት የነቃና ሙስናን ሊሸከም የማይችል ሕብረተሰብ እንዲፈጠር ጥረት ማድረግና አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሙስና ወንጀልን እና ብልሹ አሠራርን መከላከልም ኮሚሽኑ ዓላማው አድርጓል።
የኮሚሽኑ ሰራተኛ በማንኛውም አጋጣሚ የበላይ ኃላፊዎችን በአግባቡ የመጠየቅ፣ ስህተት ሲያይ የመጠቆም በውይይት ችግሮችን የመፍታት እንዲሁም የስልጣን ተዋረድን ጠብቆ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችልም በማሻሻያ አዋጁ ተቀምጧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
ዘላለም ግዛው