የኢሚግሬሽን ዜግነት ጉዳዮች አገልግሎት ከ 1930 ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ እንደዋለ መረጃዎች ያመለክታሉ ። አገልግሎቱ በሀገሪቱ የረጅም ዓመታት እድሜ ቢኖረውም እስከ አሁን ሊሻገራቸው ያልቻላቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ከወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር ተጣምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ፣ ጥምረቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የተሻለ እድል ይፈጥርለታል ተብሎ ይታመናል ።
እኛም የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማልን በተቋሙ ሥራዎች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የዛሬው የተጠየቅ አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ይባል የነበረው ተቋም ወሳኝ ኩነትንም እንዲይዝ ተደርጎ በአዲስ መልክ ተደራጅቷል፤ በዚህ መልኩ መደራጀቱ ፋይዳው ምንድን ነው ?
አቶ ሙጂብ፦ ኢሚግሬሽን ለረጅም ዓመታት በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የነበረ አንድ የሥራ ሂደት ነበር ። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ግን ከወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር ተዋህዶ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በሚል በአዲስ መልክ በህግ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ነባሩን የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መስሪያ ቤት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን አዋህዶ ወደ ሥራ ከመግባቱ አንጻር ወሳኝ ኩነት ምንድን ነው የሚለው ላይ እንደ ተቋም የግንዛቤ ሥራዎችን እየሰራን ነው ። ኢሚግሬሽን ደግሞ ነባር እንደመሆኑ አዲስ ሆኖ ወደ እርሱ የመጣውን ወሳኝ ኩነት በአሰራሩ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖረውና ተናብበው እንዲሰሩ የሚያስችል አሰራሮችን እየፈጠርን ነው ። አዲስ ተቋም መገንባት ላይ ነን ። ይህ ደግሞ በራሱ ትልቅ ውጣ ውረድ አለው ።
አዲስ ዘመን፦ እነዚህን ተቋማት ማዋሃድ ለምን አስፈለገ ?
አቶ ሙጂብ፦ ሥራቸው የሚተሳሰርበት ነገር አለ፤ ሁለቱም ህጋዊ የማንነት መታወቂያ መስጠት ነው ሥራቸው ። ለምሳሌ ህጋዊ መታወቂያ ሲባል የሚጀምረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አገላለጽ ከልደት ሰርተፍኬት ነው፤ ወሳኝ ኩነት ይህንን ይሰራል ፤ይህ የምስክር ወረቀት የማይታደስ ወይም የማይቀየር ሆኖ እድሜ ልክ ያገለግላል። 18 ዓመት የሞላው ወጣት ብሔራዊ መታወቂያ ይፈልጋል ፣ ያወጣል ። በነገራችን ላይ አዲሱ ብሔራዊ መታወቂያም የሚሰራው እዚሁ መስሪያ ቤት ነው አሁን ላይ ሰላም ሚኒስቴር የሄደው ፕሮጀክቱ እስከሚያልቅ ድረስ ብቻ ነው።
ከዚህ በመቀጠል ሰውየው ከአንድ አገር ወደሌላ ሊጓዝ ይችላል በዚህ ጊዜ ደግሞ የፓስፖርት ጥያቄ ያቀርባል ፤ ፓስፖርት ይሰራለታል ። በዚህ መሰረት ሥራዎቹ ማንነትን የሚገልጽ ህጋዊ መታወቂያን ከመስጠት ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለዚህ መተሳሰራቸው ይጠቅማል የብዙ አገሮች ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች የተለያዩ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ ሚናው የጎላ ነው፤ ይህ በእኛ አገር እንዴት ይታያል ?
አቶ ሙጂብ ፦ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት በኢትዮጵያ አዲስ ነው ። እ.ኤ.አ. በአዋጅ 760/2012 ወጥቶ ለሶስት ዓመት ሳይተገበር ቆይቶ እ.ኤ.አ. በ 2016 ነው መተግበር የጀመረው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ አገልግሎቱን ከዛ በፊት አትሰጥም ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ በ 1960 ዓ.ም. ወጥቶ የነበረው አዋጅ ላይ ዜጎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ
ማድረግ እንዳለባቸው ይዘረዝራል ነገር ግን ያው አዋጅ ሌላ ማስፈጸሚያ እስከሚወጣለት ድረስ አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን ይከለክል ነበር። በዚሁ ምክንያት አዋጁ ከወጣ በኋላ ለ 50 ዓመት አገልግሎቱን ሳይሰጥ ቆይቷል ። ይህ ማለት ግን ሥራዎቹ አይሰሩም ማለት አይደለም ። ሥራዎቹ በማዘጋጃ ቤቶች በኩል ይሰሩ ነበር ። ሥራው ግን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ መሰራት የጀመረው እ.ኤ.አ. በ 2016 ተግባራዊ በሆነው አዋጅ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሁንስ እንደ አገር ወሳኝ ኩነትን ተግባራዊ እያደረግን ነው ለማለት ይቻላል?
አቶ ሙጂብ፦ አሁን ላይ ከህጻናት መብት ጋር እየተያያዘ ፣ የልማትም አጀንዳ እየሆነ ፣ ከሚሊኒየሙ ልማት ግቦች መካከል 10 ወይም 12ቱ ከወሳኝ ኩነት ጋር የሚገናኙ በመሆናቸው አገልግሎቱ ዓለም አቀፍ ትኩረት እያገኘ መጥቷል። ስለ ህጻናት፣ ስለ ሴቶች መብት እንዲሁም የህጻናት ጉልበት ብዝበዛንና ያለእድሜ ጋብቻን ለመከላከል የምናስብ ከሆነ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ያስፈልጋል።
አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም የዓለም ባንክ በየጊዜው በሚያወጣው ሪፖርት መሰረት ብዙ ዜጎች ህጋዊ ማንነታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ (ዶክመንት) የላቸውም። ወደ አፍሪካ ስንመጣ ደግሞ ከ 5 መቶ እስከ 7 መቶ ሚሊዮን የሚጠጉት ይህ ማስረጃ የላቸውም። ይህ ማለት ደግሞ በመንግሥት ዶክመንት ውስጥ አልተመዘገቡም ማለት ነው።
በእኛም አገር ችግሩ ተመሳሳይና ያለንበት ደረጃም በጣም ኋል ቀር በመሆኑ የዚህን ግንዛቤ ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከዚህ አንጻር መሻሻሎች እየታዩ ነው ። አገልግሎቱንም ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር ማስተሳሰር ጀምረናል፤ ለምሳሌ አንድ ህጻን ልጅ ትምህርት ቤት ሊመዘገብ ሲሄድ የልደት ካርዱን እንዲያቀርብ መደረጉ ከትምህርት ስርዓቱ ጋር እንዲተሳሰር እያደረገው ነው። ከፓስፖርት ጋርም እንዲያያዝ ሆኗል፤ በዚህ የሚፈለገውን ያህል ግንዛቤ ማሳደግ ባይቻልም ለውጦች ግን አሉ።
አዲስ ዘመን፦ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንደ ዓለምም ብዙ እየተሰራበት ያለ ገና ለውጥ ያላመጣ እንደሆነ ገልጸዋልና፤ እንደ አፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ የት ላይ ናት ማለት ይቻላል?
አቶ ሙጂብ፦ ከአፍሪካ አሁን ላይ የፈረሱትን አገሮች እንበልጣቸው ይሆናል እንጂ ብዙዎቹ በወሳኝ ኩነት አገልግሎት ይበልጡናል። ለምሳሌ ግብጽን ብንወስድ መቶ በመቶ ዜጎቻቸውን ይመዘግባሉ ፤ ያውቋቸዋል። በእኛ አገር ካለው የግንዛቤ እጥረት ከጉዳዩም አዲስነት ጋር በተያያዘ የኩነት ምዝገባ 12 በመቶ ነው ። የሞትን ካየነው ደግሞ 7 በመቶ አካባቢ ነው። እዚህ ላይ ግን አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች መቶ በመቶ ምዝገባውን አሳክተዋል ስንል ያላቸው የህዝብ ቁጥር 1 ሚሊዮን፣ 7 መቶ ሺና እዛው ገደማ በመሆኑ ነው፤ እኛ ደግሞ 110 ሚሊዮን ህዝብ አለን ፤ ይህ ደግሞ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ትልቅ ቁጥር ነው፤ ይህም ቢሆን ግን እኛ በዚህ ደረጃ አለመመዝገባችን አፍሪካ በዓለም ላይ ሊኖራት የሚገባውን ደረጃ ሁሉ ይዞት ወርዷል።
የአፍሪካ ህብረትም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአፍሪካን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ደረጃ ማሻሻል ከተፈለገ ኢትዮጵያ ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለው በትኩረት እየሰሩ ሲሆን ፣ መንግሥትም ይህንን ተገንዝቦ የምዝገባ ሥራውን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በተሻለ መልኩ ለማከናወን ምን ታስቧል ? እንዴትስ ለማሳደግ ታስቧል?
አቶ ሙጅብ ፦ የ 2030 የልማት ግብ የሞትን
ምዝገባ አሁን ካለበት 7 ከመቶ 180 በመቶ ፤ የልደት ምዝገባን ደግሞ ከ12 ከመቶ ወደ መቶ በመቶ ማድረስ አቅደናል። ከዚህ አንጻር ብዙ ሥራ ይቀረናል። ከሞት ጋር በተያያዘ አንዱ የሚፈለገው ሞቱን መመዝገቡ ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ የሞቱ ምክንያት ያስፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ መረጃዎች የሚያሳዩት ብዙ የመሞት ምክንያቶች የሚፈጸሙት በቤት ውስጥ ነው ፤ ይህ ደግሞ ምክንያቱን ለማወቅ ያዳግታል።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለአገራችን አዲስ ነው፤ የግንዛቤ ደረጃውም ቀስ በቀስ መሻሻል እያሳየ ነው። ግን በሚፈለገው ደረጃ ላይ አይደለም። ምዝገባው የልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝና በጣም አስፈላጊ ሥራ ነው። ዘመናዊ የመንግሥት ስርዓት ለመገንባት፣ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለስታትስቲክስ እና ለህግም በጣም የሚያስፈልግ ነው። ከዚህ አንፃር በቂ ሀብት በማሰባሰብ እና በስልጠና በመታገዝ በጉዳዩ ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ሥራውን ማሳደግ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን ፦ በወሳኝ ኩነት ምዝገባቸው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የደረሱ አገራት መረጃውን ህዝባቸው ለማወቅ ከመጠቀም ሌላ ለምን አገልግሎት ይጠቀሙበታል?
አቶ ሙጂብ ፦ ብዙ አገሮች የህዝብ ቆጠራቸውን በወሳኝ ኩነት ላይ መስርተውታል፤ የህዝብ ቆጠራ አያደርጉም። ሲወለድ ይመዘገባል፣ ሲሞት ይቀነሳል። ከዚህ አንጻር በየጊዜው ያለውን ለውጥ ከወሳኝ ኩነት ይወሰዳል።
ሌላው ደግሞ ለስታትስቲክስ ይጠቅማል፤ በዚህም የተወለደ፣ የሞተ ፣ያገባ ፣የፈታ እና ጉዲፈቻ የወሰደ ሁሉም ይመዘገባል ። ይህ ለስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት ይሰጥና ተጠናክሮ መረጃ ሆኖ ይወጣል። ስለዚህ ብዙ አገሮች የህዝብ ቆጠራ ሥራቸውን ወሳኝ ኩነት ላይ እንዲመሰረት አድርገዋል።
አዲስ ዘመን ፦በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ሥራችንስ የት ላይ ነን?
አቶ ሙጂብ ፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መስሪያ ቤት ለዜጎች ፓስፖርት ይሰጣል ፣ የጠረፍ ቁጥጥር ሥራ ይሰራል ፣ የቪዛ አገልግሎት እና የዜግነት አገልግሎትም ይሰጣል። ከፓስፖርት አገልግሎት አንጻር ፓስፖርት እኛ አገር አይታተምም። በግዥ ታትሞ የሚመጣው ከውጭ ነው። ከዚህ አንጻር ደግሞ ብዙ ገዝተን በመጋዘን ማስቀመጥ አለብን፤ እሱንም እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን ፦ወደኋላ ልመልስዎና ከጥቂት ወራት በፊት ከፍተኛ የሆነ የፓስፖርት እጥረት ተከስቶ መጉላላቶችም ነበሩ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ሙጂብ፦ ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም የካቲት ወር ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ፓስፖርት ሳይገዛ ቆይቷል ። ከምክንያቶቹ መካከልም አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነበር።ሌላው ደግሞ ፓስፖርቱን አምርቶ የሚሰጠው ኩባንያ የፓስፖርቱ ዲዛይን ፓተንት ባለቤት መሆኑ ነው። 2008 ዓ.ም ላይ አስተዳደሩ ፓስፖርቱን ሌሎች እንዲሰሩት ፈልጎ ጨረታ አውጥቶ ወደ ግዢ ከተሄደ በኋላ አካሄዱ ችግር አለው በሚል ጸረ ሙስና አገደው፤ በኋላ ደግሞ ፈቀደ። በዚህ መሀል ደግሞ ፓስፖርቱን ይሰራ የነበረው ኩባንያ የፓተንት ጥያቄ በማንሳቱ ህትመቱ ቆመ ። ይህም ሆኖ ግን በወቅቱ ግዢ አልተፈጸመም እንጂ ሥራው ይሰራል ፤ ፓስፖርትም ለጠያቂዎች ይሰጥ ነበር።
በመጋዘን ተይዞ የነበረው ፓስፖርት ቁጥርም ከቀን ቀን እየቀነሰ ሄደ፤ 2011 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ፈቀደ፤ ከኩባንያው ጋር 1 ሚሊዮን ፓስፖርት ለመግዛት ውል ገባን ፤ በዚያ መሰረት እየተሰራ ባለበት ጊዜ ኩባንያው የወረቀት እጥረት ገጠመኝ በማለቱ እጥረት ተከሰተ። ይህንን ችግር ለማለፍ ተቋሙ ለተገልጋዮች ረጅም ቀጠሮን እየሰጠ መስራቱን ቀጥሎ ነበር።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ሁኔታ ግን አገልግሎት አሰጣጥ ጥራታችሁ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ አድርሷል?
አቶ ሙጂብ፦ በጣም ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ሰዎች በረጅም ቀጠሮ መሰጠታቸው ቅሬታን ከመፍጠሩም በላይ ቀጠሯችንን እናሳጥራለን በማለትም ወደ ደላላና ጉቦ ወደ መስጠት የሄዱም ብዙዎች ነበሩ። ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን በቂ ፓስፖርት በመያዛችን 75 ቀን ይሰጥ የነበረውን ቀጠሮ ወደ 30 ቀናት አውርደነዋል። ይህ ደግሞ የብዙ አገሮች ልምድ ነው።
ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ 10 ሳምንት፣ ዚምባብዌ ሦስት ወር፣ አሜሪካ ከ ስድስት እስከ ስምንት ሳምንት፣ ጀርመን ከ አራት እስከ ስድስት ሳምንት፣ ቻይና 15 የስራ ቀናት፣ እንግሊዝ ሦስት ሳምንት ይጠይቃሉ። እዚህ ላይ ከዝምባብዌ በቀር ሁሉም አገሮች ፓስፖርት አምራቾች ናቸው ።
እኛ ደግሞ ፓስፖርት አናመርትም ። ትራንስፖርት እና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚጠበቅ ወረፋ አለ ከዚህ አንጻር 30 ቀናት መፍጀቱ ጥሩ የሚባል መሻሻል ነው። በሌላ በኩል ግን ከ 30 ቀናት በታች ፓስፖርት ማግኘት አለብኝ የሚል ሰው ካለ ደግሞ በአስቸኳይ ሂሳብ ከፍሎ መስተናገድ የሚችልበት እድልም አለ።
አዲስ ዘመን ፦ በቅርቡ በቪዛ አሰጣጥ ላይ የተሻሻሉ አሰራሮችን መንደፋችሁን ስትገልጹ ነበርና ስለ እሱ ትንሽ ይንገሩኝ?
አቶ ሙጂብ፦ ቪዛ ከፍተኛ የሆነ መሻሻል ያሳየንበት ሥራ ነው፤ በተለይም ከአየር መንገዱ ጋር በጋራ እየሰራን ባለነው ሥራ አማካይነት አገልግሎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ መሻሻልን እያሳየ ነው። የአፍሪካ ልማት ባንክ የቪዛ አቅላይ አገራት በማለት በሚያወጣው ማውጫ ላይ በፊት 50ኛ ደረጃ ላይ ነበርን አሁን ግን ወደ 18ኛ ደረጃ ወርደናል። ለዚህ መሻሻል ዋናው ምክንያት ከሆኑት መካከል ሁሉም አፍሪካ አገራት ዜጎች አየር ማረፊያ ላይ ሲደርሱ ቪዛን ማግኘት ይችላሉ፤ ሌላው ኦን ላይን (ኢ)ቪዛን መጀመራችን ሰዎች ባሉበት ሆነው ቪዛን ለማግኘት ቢያመለክቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚችሉበት እድል ተመቻችቷል።
ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ 2019 ላይ ከ 169 ሺ በላይ ሰው በኦን ላይን ቪዛ ተጠቅሞ ወደ አገር ገብቶ እንዲወጣ ተደርጓል። አሁንም የበለጠ አገልግሎቱን ተደራሽና ፈጣን ለማድረግ ከአየር መንገድ ጋር እንዲሁም ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር ሆነን በመስራት ላይ ነን ። እንደ እቅድ በቅርቡ እንተገብረዋለን ብለን የያዝነው እስከ 500 ሺ ሰው በኦን ላይን ቪዛ ወደ አገር ለማስገባት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ከቪዛ ነጻ ( ስቶፕ ኦቨር ቪዛ) በመጠቀም አንድ ሰው ወደ አገር ገብቶ ለቀናት ያህል ቆይቶ እንዲወጣ ለማድረግ አስበናል። እንደዚህ ያለው ቀልጣፋ የቪዛ አገልግሎት ደግሞ ቱሪዝሙን ያሳድገዋል፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢንም ከፍ ያደርጋል በሌላ በኩልም ለአየር መንገዱ ገበያ ይፈጥርለታል።
አዲስ ዘመን፦ የድንበር ቁጥጥሩስ ምን መልክ አለው?
አቶ ሙጂብ፦ የድንበር ቁጥጥሩ ላይ አገሪቱ በምትዋሰንበት ከደቡብ ሱዳን በስተቀር በሁሉም ቦታዎች ላይ የኢሚግሬሽን ቁጥጥር ይደረጋል። ገቢ ወጪው ቪዛ ያለው መሆኑ ይጣራል። በዚህ ዓመትም ለውጡን ተከትሎ ከኢትዮ- ኤርትራ ጋር ባለን የሰላም ግንኙነት አራት ኬላዎችን (ቡሬ፣ ዛላምበሳ፣ ራማና ሁመራ ኬላዎችን) ጨምረናል። ሌላው በአየር ማረፊያዎች የምናደርገው መንገደኞችን የመቆጣጠር ሥራ ነው። በዚህም መንገደኛው ትክክለኛ ፓስፖርት እና ቪዛ ያለው መሆኑን እናረጋግጣለን ፤ ይህም ለ24 ሰዓት የሚሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአየር ማረፊያ ላይ በሚደረጉ ቁጥጥሮች ዙሪያ ሙስናዎች ይበዛሉ የሚል ቅሬታ አለ ? ለሙስና የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ላይ ቁጥጥር ታደርጋላችሁን ?
አቶ ሙጂብ፦ አዎ አንዳንድ ከሙስና ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ይሰማሉ። ይህንን ለማስተካከል እየሰራን ነው ። በዚህ ዓመት ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለይም ወደ አረብ አገራት የሚሄዱ እህቶች ስልጠና መውሰድ አለባቸው ብሎ ህግ ከማውጣቱ ጋር በተያያዘ ስልጠናውን ያልወሰዱ ሰዎች ከሠራተኞች ጋር የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር የማለፍ ሁኔታ እንዳለ መረጃ ነበረን፤ በተጨባጭ ተከስቶ የተገኘም አለ። ሌላው ህጋዊ ባልሆነ ፓስፖርት የማለፍም ችግሮች አሉ፤ በዚህ ሁኔታ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን ልየታ አድርገናል፤ በቅርቡም 12 ሠራተኞችን ከሥራና ከደመወዝ አግደን ለተቋሙ ዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዲቀርቡ አድርገናል እንደ ሁኔታውም እያየን በወንጀል የሚጠየቁበትም ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
ቁጥጥሩ በዚህ ያበቃል ማለት አይደለም ከደላሎች ጋር ተመሳጥረው አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር የሚፈጥሩትን የማጣራት ሥራው ይቀጥላል። በዚህ ረገድም ጥሩ መሻሻሎች እናመጣለን ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ችግር በህገ ወጥ ስደተኞች ቁጥጥር ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ምን ሊሆን ይችላል?
አቶ ሙጂብ፦ የህገ ወጥ ስደተኞች ጉዳይ በተለየ መልኩ የሚታይ ነው። ሁሉም ኢሚግሬሽን በሚቆጣጠረው ኬላ ይወጣሉ ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች የምትዋሰንባቸው ስፍራዎች ሰፊ ናቸው። በእግር ሊቋረጡ የሚችሉ ሜዳዎች ናቸው። እነዚህን ቦታዎች በሙሉ በፖሊስ (በወታደር) ማስጠበቅ አይቻልም። ስለዚህ የድንበር አካባቢ ባህርይን ማየት ያስፈልጋል። በአየር መንገድ የሚሄደውን ህገ ወጥ ስደት ብናይ ግን ብዙዎቹ ህጋዊና ቪዛ ያላቸው ናቸው ጥቂቶቹ ናቸው ቪዛ የማይኖራቸው።
አዲስ ዘመን፦ ቪዛ ካላቸው ህገ ወጥ የሚያሰኛቸው ምንድን ነው?
አቶ ሙጂብ፦ ህገ ወጥ የሚያሰኛቸው ስልጠና አለመውሰዳቸው ነው። ይህ ስልጠና ከተጀመረ በኋላ እንኳን ሳይሰለጥኑ ከአገር ለመውጣት ወደ አየር ማረፊያ የሄዱ ከ 7ሺ 500 በላይ ተመልሰዋል። ጥቂቶች ደግሞ ከላይ በተገለጸው የስነ ምግባር ጥሰት አልፈው ሄደው ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ወቅታዊ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ስጋት አንጻር ያለው ቅድመ ዝግጅት ምን ይመስላል?
አቶ ሙጂብ፦ እስከ አሁን እንደ ኤጀንሲ ጤና ሚኒስቴር በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት ሥራዎች ሲከናወኑ ነበር። ለምሳሌ በዋናው መስሪያ ቤት ስለ በሽታው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ለውጭም ለውስጥም በሚሆን መልኩ እንሰጣለን ። በሌላ በኩልም ተራ በሚጠብቁ ሰዎች መካከል በቂ ርቀት እንዲኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ።ንጽህና ከመጠበቅ አንጻርም በጀት በመመደብ የመታጠቢያ እቃዎችን በማዘጋጀት አገልግሎት ፈላጊዎች እንዲጠቀሙበት የማድረግ ሥራም እየተከናወነ ነው።
አሁን ደግሞ ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ የፓስፖርት አገልግሎት በከፊል እንዲቋረጥ ሆኗል። በዚህም መደበኛ ፓስፖርቶችን አዲስም እድሳትም አገልግሎት አይሰጥም ። ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልልም ተግባራዊ እየሆነ ነው ። ሆኖም ለአስቸኳይ ሥራ ከሀገር ለሚወጡ፣ ከሀገር ውጭ ህክምና ለሚወስዱ ፣ በውጭ አገር ነዋሪ ለሆኑ እና መንግሥት ለአስቸኳይ ሥራ የሚልካቸው ዜጎች በአስቸኳይ የፓስፖርት አገልግሎት እንዲስተናገዱ ይደረጋል።
ከዚህ በፊት ፓስፖርት ለመውሰድ የተመዘገቡ ሰዎች ፓስፖርታቸው ሲደርስም በፖስታ ቤት በኩል አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይሆናል። ከቪዛ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መብረር ካቆመባቸው አገሮች የሚመጣን የቪዛ ጥያቄ የማናስተናግድ መሆኑን ገልጸናል። ስለዚህ ኢ ቪዛ ፣ ኦን ላይንና ኦን አራይቫል ቪዛ አየር መንገዱ ከሚበርባቸው አገራት ለሚመጡ ጥያቄዎች ብቻ ነው የምናስተናግደው ማለት ነው።
ሌላው ለውጭ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የምንሰጠው የመውጪያ ቪዛ አገልግሎት ይቀጥላል ። በቪዛ ሆነ የመኖሪያ ፍቃድ አግኝተው አገር ውስጥ ያሉ የውጭ ሀገር ዜጎችን በተመለከተም ቪዛዬ ይራዘምልኝ፤ የመኖሪያ ፍቃዴ ይታደስልኝ የሚሉ ጥያቄዎቻቸውን ላልተወሰነ ጊዜ የማናስተናግድ በመሆኑ ሰዎቹ ባሉበት ተረጋግተው እንዲቀመጡ ወስነናል ። ኤጀንሲው ይህንን ውሳኔ ካስተላለፈበት ቀን ጀምሮ ምንም ዓይነት ቅጣት አይጣልባቸውም ።
የአየር መንገድ አገልግሎቱ መንገደኛ እስካለ ድረስ ይቀጥላል፤ የጠረፍ አካባቢዎችም ስለተዘጉ እንቅስቃሴ አይኖሩም፤ ለማንኛውም አስቸኳይ አገልግሎት ግን ቢሮዎቹ ክፍት ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን ፦ለነበረን ቆይት አመሰግንለሁ።
አቶ ሙጂብ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
እፀገነት አክሊሉ