አንድ የሥራ ባልደረባዬ በፌስቡክ ገጹ የለጠፈውን ምስልና ከስሩ የሰፈረውን የፎቶ መግለጫ ሳነብ በምስሉ ላይ የሚታየው ወታደር ስለተሸከማት አህያ የሰፈረው ሃሳብ በእውነት ገላጭ በመሆኑ ለዛሬው የርዕሰ አንቀጽ ጽሁፍ መነሻ ሆነኝ።
ጽሁፉ ‹‹ ይህ ወታደር ይህቺን አህያ የተሸከመው አህያ መሸከም ወድዶ አይደለም፤ አካባቢው በተቀበሩ ፈንጂዎች የተሞላ በመሆኑ ምክንያት እንጂ። አህያዋ ነጻ ሆና ብትንቀሳቀስ እርስዋ ረግጣ በምታፈነዳው ፈንጂ አማካይነት የበርካታ ወታደሮች ህይወት ያልፋል። ልክ እንደዚሁ በአሁኑ ሰዓት ዓለም በኮሮና ቫይረስ ተወርራለች፤ አህያዋ ተረማምዳበት ፈንጂ አፈንድታ ለወታደሮቹ ሞት መንስዔ እንዳትሆን በወታደሩ ጀርባ ታዝላ እንደታገተችው ሁሉ በቫይረሱ ንጹሃን እንዳይበከሉ መታገድ ያለበት መታገድ ይኖርበታል›› ይላል።
እውነት ነው! ዓለም በኮሮና ቫይረስ ስርጭት በምትታመስበት በዚህ ወቅት መታቀብ ያለበት ካልታቀበ፣ መታገት ያለበት ካልታገተ ጤነኛውንም የቫይረሱ ተጠቂንም መለየት ስለማይቻል ተያይዞ ማለቅ የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል።
የኮሮና ቫይረስ ሁሉን ነገር በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን ከሚሉት ኃያላን አገራት ቁጥጥር ውጭ ሆኖ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ሲነጠቁ በአይናቸው እያዩ ምጽአቱ ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል እስከማለት መድረሳቸውን እያደመጥን ነግ በእኔ ብለን ትምህርት በመውሰድ ለመጠንቀቅ ቸልተኛነትን ማሳየታችን የሚያስገርምም የሚያሳዝንም ነው።
በአገራችን ይህንን መሰሉ እልቂት እንዳይከተል ዜጎች ሊያደርጉት የሚገባውን ጥንቃቄ አስመልክቶ በጤና ሚኒስቴር ፣ በባለሙያዎችና ከፍ ሲልም በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካይነት የተላለፈው መልዕክት ዜጎች ከንክኪ እንዲቆጠቡ፣እጆቻቸውን በሳሙና እንዲታጠቡ፣አንዳቸው ከአንዳቸው ሁለት የአዋቂ እርምጃ እንዲራራቁ፣በእምነት ሥፍራዎች የሚኖረው መቀራረብ ጥንቃቄ እንዲደረግበት፤ መጠጥና ጭፈራ ቤቶች እንዲሁም ጫትና ሺሻ ቤቶች የቫይረሱን ስርጭት ሊያባብስ ከሚችል ድርጊት እንዲታቀቡ፣ በሥራ ቦታዎች የሰዎች መቀራረብ እንዳይኖር ከጥቂት ሠራተኞች በስተቀር በቤታቸው ሆነው ስራቸውን የሚያከናውኑበት ሁኔታ እንዲመቻች ማሳሰቢያም ልመናም ቢቀርብም በህብረተሰቡ ዘንድ ሰሚ ያገኘ አይመስልም።
ለዚህ ወቀሳ አሳማኝ መረጃ ለማቅረብ ከተማችንን በቀንና በማታ መቃኘት ይበቃል። ከሥራ ቦታ ተገልለህ ራስህን በቤትህ ወስነህ ከቫይረሱ ስርጭት ራስህን ጠብቅ የተባለው ሰው ማሳሰቢያውን እንደ ፈቃድ ቆጥሮት በየመሸታ ቤቱ መለኪያና የቢራ ጠርሙስ ጨብጦ ይታያል። በታክሲና በአውቶቡስ ተራዎች መጓጓዣ ለመሳፈር ሲጋፋ ይስተዋላል። የተለመደ የእለት ተእለት ተግባሩን ለማከናወን በመርካቶ፣በፒያሳ፣ በሳሪስና በመገናኛ አውራ ጎዳናዎች እርስ በርሱ እየተጋፋ ይጓዛል።
የመንግስትን ማሳሰቢያም ሆነ የባለሙያዎችን ምክር ባለመስማታችን በሽታውን መቆጣጠር ይችላሉ የሚባሉት የሰለጠኑ አገራት ከደረሰባቸው የባሰ እልቂት እንዲደርስ ምጽአት የሚጠሩትን በልመናና በማሳሰቢያ ብቻ መስመር ማስያዝ ስለማይቻል ጠንካራ ህግን የማስከበር ርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ያለው የመጨረሻ አማራጭ ይሀው ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012