አዲስ አበባ:- በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ወደ ድርድር ከመገባቱ በፊት ቅድሚያ የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ቀይ መስመሮች ሊሰመሩ እንደሚገባ ተገለጸ።
በውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር በድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ውሃዎች ዙሪያ በአማካሪነት የሚሰሩት ኢንጅነር ተፈራ በየነ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ በማንኛውም መልኩ ኢትዮጵያ በፍትሃዊነት የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚያግዳት ውይም የሚከለክላት
አንዳች ስምምነት እንደሌለ ጠቁመው፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ለማስገባት የሚሰሩ ሴራዎች ስላሉ፤ ከአሁን በኋላ ወደ ድርድር ሲገባ የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ቀይ መስመሮች ቅድሚያ መሰመር አለባቸው።
ግብጽ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅን አስታካ የውሃ ክፍፍልን በውል በማሰር የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነትን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ለማስገባት ቁማር እየተጫወተች እንደነበር ባለፉት ጊዚያት ሶስቱ ዋነኛ የተፋሰሱ አገራት ባደረጉት ድርድሮች በግልጽ ታይቷል ያሉት ኢንጅነሩ፤ ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ አቅርባው የነበረው አንዱ ሃሳብ ግድቡ ውሃ የሚሞላው በሰባት ዓመት እንዲሆን፤ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንድትለቅና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ በዋናነት ውሃ እንዲለቅ የሚጠይቅ እንደነበር ተናግረዋል።
ኢንጂነሩ ይህ ማለት ወደ ግብጽ የሚሄደው ውሃ ከጎደለ ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ያጠራቀመችውን ውሃ እንድትለቅ ስለሚያስገድድ፤ የግብጾችን የቅኝ ግዛት ዘመን የውሃ ተጠቃሚነታቸውን ሲያረጋግጥ፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት የሚነፍግና በምታካሂዳቸው ልማቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ መደረጉን ገልጸዋል።
ግብጽ ይህ አልሳካላት ሲል በተዘዋዋሪ የውሃ ድርሻዬ ብላ የምታምንበትን ለማረጋገጥ፤ የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ህዳሴ ግድቡ በዋናነት ሥራው ውሃ መልቀቅ ይሆናል የሚለውን ተንኮላዊ በጥበብ በተሞላበት ሁኔታ በድርቅ ወቅት የአባይ የውሃ ፍሰት ከ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ማነስ እንደሌለበትና ተፈጥሯዊ ፍሰቱ መጠበቅ እንዳለበት መጠየቋን ኢንጂነሩ አስረድተዋል።
አቶ ተፈራ ይህ የግብጽ ጥያቄ ከአባይ ታሪካዊ የውሃ ፍሰት አኳያ አነጻጽረው ሲገልጹ በኢትዮጵያ በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ሳቢያ የአባይ የውሃ ፍሰት 29 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የደረሰበት ሁኔታ ነበር። ግብጽ በዚህ የድርቅ ወቅት የግድቧን የውሃ ፍሰት በአግባቡ ያስተዳደረችበት ሁኔታ እያለ፤ ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታ
40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መልቀቅ አለባት ማለቷ እንደ 1997 ዓ.ም አይነት ድርቅ በአገሪቱ ቢከሰት ከየት አምጥታ ነው ኢትዮጵያ ውሃ የምትለቀው? ይላሉ።
ይህ ማለት አንተ እየተጠማህና እየተራብህ፣ በጨለማ ተዳፍነህና ፕሮጀክቶችህን ዘግተህ የተባለውን ውሃ ከየትም ተበድረህ ቢሆን አምጣ ማለት ነው። በጥቅሉ ከተባለው ውሃ በታች ከሆነ ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ ውሃ እየቀነሰችም ቢሆን ለመክፈልና ለመስጠት በፊርማዬ አረጋግጣለሁ ብላ ትፈርም ማለት እንደሆነ ኢንጅነሩ ይናገራሉ።
ይህ ጥያቄ ግብጽ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በዓመት እንድታገኝ የሚያስገድድ ነው ያሉት ኢንጅነሩ፤ የግብጽ ምኞት የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ሰብብ አድርጋ የቅኝ ግዛት የውሃ ክፍፍልን የማስረገጥ አላማ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ይሄን ዓይነት ስምምነት እንደማታደርግ በግልጽ አስረድታለች። ነገርግን ግብጽ በተለያዩ ጊዜ በተደረጉ የግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ድርድሮች ላይ ታሪካዊ የውሃ ተጠቃሚነቷን ስላላሳካች ከተፋሰሱ አገራት ጋር ሲደረግ የነበረውን ድርድር አፍርሳ ሌላ ሶስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ማድረጓን ተናግረዋል።
ኢንጂነሩ በአሜሪካና ዓለም ባንክ አደራዳሪ ሆነው በዋሽንግተን በተደረገው ድርድር ግብጾች የኢትዮጵያን ተባባሪነትና ቅንነት ወደ ጎን በመተው የግድቡን የውሃ ሙሌትና አተገባበር በማስታከክ የአባይን ውሃ ክፍፍል ስምምነት በማድረግ ታሪካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠል ሴራውን እንደገፉበት ጠቁመው፤ አሜሪካም ለግብጽ ባደላ መልኩ ያዘጋጀችውን ሰነድ በጥድፊያ ኢትዮጵያ እንድትፈረም ዛቻና ማስፈራሪያ አድርጋለች ብለዋል።
እንደ ኢንጂነሩ ማብራሪያ በአሜሪካ በኩል የተደረገው ነገር በጥድፊያና በማጭበርበር ግብጽ ታሪካዊ የምትለውን የውሃ ድርሻ ማስጠበቅ ስለሆነ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚሰሩ ሴራዎች የኢትዮጵያ የአሁኑና የመጪው ትውልድ ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዳይገባ፤ ከአሁን በኋላ ወደ ድርድር ሲገባ ቀድሞ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ቀይ መስመሮቹ ሊሰመሩ ይገባል። ተደራዳሪዎች ቀይ መስመሮቹን ጠብቀው የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባቸዋል፤ ቀይ መስመሮቹን እንዳይጣሱም ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ቀይ መስመሮቹም እንደ አገር ይፋ ሊደረጉ ይገባል ብለዋል ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
ሶሎሞን በየነ