አዲስ አበባ፡- የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ አንዱ መፍትሄ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለው ቸልተኝነት ዋጋ እንዳያስከፍል ስጋት ማሳደሩ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል መንግሥትና መገናኛ ብዙኃን እየለፉ ቢሆንም፤ በከተማዋ አሁንም ማህበራዊ ርቀትን የማይጠብቁና በቸልተኝነት የሚያልፉ ሰዎች መኖራቸው ይታያል፤ ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ይቻል ዘንድ የሚደረገውን ርብርብ ወደ ኋላ የሚጎትትና ስጋት የሚፈጥር ነው፡፡
የመዲናዋ ነዋሪ አቶ መርከቡ አህመድ እንደተናገሩት፤ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ባለሙያዎች የቫይረሱን ስርጭትና የመከላከያ መንገዶች በተመለከተ በየጊዜው ግንዛቤ ቢሰጡም፤ ህዝቡ ‹‹በቫይረሱ ምን ያህል ሰው ተያዘ›› የሚለውን ከማዳመጥ ውጭ በተለይ ማኅበራዊ ርቀትን ከመጠበቅ አኳያ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ህይወት ከተቀጠፈ በኋላ መጸጸት ስለማይቻል ህዝቡ የመንግሥትን መመሪያ በማክበር
ለሌላው ህይወት መጨነቅ ይኖርበታል፡፡
ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አቶ ሂርጳ ዳዲ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ የተለያዩ አካላት በትኩረት መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ሲያስተላልፉ እንደቆዩና አሁንም ሙሉ ጊዜያቸውን ግንዛቤ በመስጠት ላይ እያሳለፉ መሆኑን ጠቁመው፤ በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ የሆነ ግብረ መልስ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ መመሪያዎችን ንቆ በመተው ይልቁንም የተለመደውን ማህበራዊ ቅርርብ በማጉላት የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ኃላፊነትን የዘነጋ እንቅስቃሴ በዚሁ ከቀጠለ ዋጋ እንደሚያስከፍልም አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ያለው ማህበራዊ ህይወት ‹‹ማህበራዊ ርቀትን›› ለመተግበር አዳጋች መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ምሥራቅ አንዳርጌ፤ የበሽታው ተጽእኖ ከዚህ የከበደ በመሆኑ ህዝቡ ቫይረሱን ለመከላከል ሲባል የግድ የጤና ሚኒስቴር መመሪያዎችን መተግበር እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ስጋቱ የሁሉም ህብረተሰብ እንደሆነው ኃላፊነት መውሰዱም የሁሉም መሆን እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በመዲናዋ አንዳንድ ሱቆችና የንግድ ሥፍራዎች ላይ በርካታ ዜጎች ተጠጋግተው እየተገበያዩ መሆኑን በመጠቆም፤ ይህ አካላዊ ርቀትን ያልጠበቀ እንቅስቃሴ መዘናጋትን የሚፈጥርና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አደጋች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም፤ በተለይም በሰዎች መካከል ያለውን ርቀት ስለ መጠበቅ አስፈላጊነትና የእጅ ንፅህናን ያለመዘናጋት የመጠበቅን ጠቃሚነት አስገንዝበዋል። መንግሥት ይህንን ለማስተግበር የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ሥራ ላይ ማዋሉን በማውሳት፤ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሂደቶች በቀጣይ ይከናወናሉ ብለዋል፡፡ በመንግሥት በኩል የሚተላለፉ መመሪያዎችን የማስተግበሩ ሂደትም በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና ሌሎች ሚኒስትሮች ትላንት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የኮሮና ቫይረስን ህብረተሰቡ እንዴት መከላከል እንደሚገባው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ አከናውነዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
አዲሱ ገረመው