የዛሬ ሳምንት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የገና በዓል መከበሩ ይታወሳል፡፡ በዓሉ የክርስቶስ የልደት በዓል በመሆኑ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው በዓል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በድምቀት ለማክበር ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መሰረት ከዶሮ እስከ በሬ፣ ከቅንጥብጣቢ እስከ ቅርጫ ሥጋ፣ ወዘተ ሁሉም እንደአቅሙ ለመዋል የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡
ይህ አንድም እያንዳንዱ ሰው ለእምነቱ ካለው ቀናኢነት በሌላም በኩል ለዘመናት የቆየ ባህላዊ ሁነት ነውና አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን አቅምን ማወቅና በዓላትን በአቅም ልክ ማሳለፍ የሚለው ደግሞ ደጋግሞ ሊታሰበብት ይገባል፡፡ ለዛሬም ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ አንድ ጎረቤቴ ያጋጠመው ገጠመኝ ነው፡፡
ጊዜው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፤ የገና በዓል ዋዜማ፡፡ ጎረቤቴ ለበዓል በግ ለመግዛት ፈልጎ ወደ አዲሱ ገበያ ይሄዳል፡፡ ይህ ጎረቤቴ በግል ሥራ የሚተዳደርና መካከለኛ ገቢ ያለው በመሆኑ ወጪውም በአቅሙ ልክ ነው፡፡ በዕለቱም በግ ለመግዛት ያሰበው በወቅቱ ገበያ እስከ ሁለት ሺህ ብር የሚገዛው መካከለኛ በግ ነበር፡፡
ታዲያ በጉን ለመግዛት ዞር ዞር እያለ አንድ የበግ ነጋዴ ጋር ሲደርስ የሚፈልገውን የበግ ዓይነት ይመለከታል፡፡ ያየውንም በግ ለመግዛት ድርድር ይጀምራል፡፡ ነጋዴውም በጉን በመጀመርያ ጥሪ ሁለት ሺህ ብር መሆኑን ይነግረዋል፡፡ ገዢም ይከራከራል፡፡ በክርክር ሂደቱም ሻጩ የመጨረሻ ዋጋው 1,800 ብር መሆኑን ተናግሮ ከዚህ እንደማይቀንስ ይገልጽለታል፡፡ ገዢም በጉን ስለወደደው ትንሽ እንዲቀንስለት ለማግባባት እየሞከረ እያለ አንድ መኪና እነሱ ካሉበት ጥቂት ራቅ ብሎ ሲቆምና የነጋዴውም ትኩረት ወደዚያው ሲሄድ ይመለከታል፡፡ ከዚህች ደቂቃ ጀምሮም ነጋዴው ይህንን የቀደመውን ገዢ ጎረቤቴን ፊት ነሳው፡፡
ሁለት ሰዎችም ከመኪናው ወርደው በቀጥታ ወደ እነሱ አመሩ፡፡ ከነጋዴው ጋርም ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ በቀጥታ በግ ለመግዛት እንደሚፈልጉ ተናግረው በአጋጣሚ ይህ ጎረቤቴ ለመግዛት ሲደራደርበት የነበረውን በግ ጠቆሙ፡፡ ነጋዴውም ወዲያው በጉን ወደፊት ጎትቶ ካመጣ በኋላ ፊታቸው በማቅረብ ውሰዱ ይላቸዋል፡፡ ስንት ነው ይሉታል፡፡ እሱም ሦስት ሺህ አምስት መቶ ብር መሆኑን ይነግራቸዋል፡፡ እነሱም ብዙም ሳይጨቃጨቁ አልተወደደም? ብለው የጠየቀውን ገንዘብ ከፍለው መኪናቸው ላይ እንዲጭነው ያዙታል፡፡
በዚህ ወቅት ጎረቤቴ ግራ ይገባዋል፡፡ በአንድ በኩል ምንም ቢሆን አንድ በግ ሲገዛ እንዴት ያለምንም ክርክር ሊገዙ ቻሉ? በሌላ በኩል ደግሞ ነጋዴውስ ለምንድነው በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር በላይ የጨመረባቸው? የሚለው ሆዱን በላው፡፡ ከዚያ በኋላ ይህንን ጉዳይ ማወቅ አለብኝ በማለት ማጣራቱን ይቀጥላል፡፡ ቆየት ብሎ የተረዳው ታዲያ ሰዎቹ የአንድ ክፍለ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ሰዎቹ በዕለቱ ብቻ ሳይሆን ቋሚ የበግ ደንበኛ መሆናቸውንም ይረዳል፡፡
እንግዲህ ተመልከቱ፤ እነዚህ ሰዎች የመንግሥት ተቀጣሪዎች ናቸው፡፡ በየጊዜው በግ የሚገዙበት የገቢ ምንጭ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ነገር ግን ገንዘቡን ለፍተው ያመጡት ባለመሆኑ ዋጋ እንዲያጣ አድርገውታል፡፡ የኑሮ ጫናና ውድነትም እያስከተሉ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ በየቦታው መኖራቸው ሐቅ ነው፡፡ ያልለፉበት ገንዘብ ሲወጣ አይቆጭም፤ አያንገበግብም፡፡ ለዚህ ነው «የሌባ ገንዘብ አይበረክትም» የሚባለው፡፡ የእኔነት ስሜት ስለማይኖረው ለማጥፋትም ጭንቀት የለበትም፡፡
አገራችን በድህነት ውስጥ የምትገኝ አገር ናት፡፡ አሁን አሁን የአገራችን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ800 ዶላር በላይ መድረሱ ሲነገር ብንሰማም ይህ ግን ወደ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የወረደ ባለመሆኑ የኑሮ ልዩነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ አንዳንዱ ምናልባትም ተቀምጦ ቢበላው እንኳ ለአንድ ክፍለ ዘመን የሚሆን በሚሊየኖች እና በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ሲያንቀሳቅስና በእያንዳንዱ ልጁና ዘመዱ ስም ቤት፣ መኪናና ልዩ ልዩ ሀብቶችን ሲያከማች አብዛኛው ደግሞ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት የተራራ ያህል ከብዶት ሲባዝን ይውላል፡፡
አንዳንዱ በየዕለቱ ለጫትና ለመጠጥ እንዲሁም ለዝሙት የሚያወጣው ገንዘብ ለሌላው የአንድ ዓመት ጠቅላላ ገቢው ሊሆን ይችላል፡፡ ከፊሉ ለልጁ ደብተር መግዣ አጥቶ እና ቁርስ የሚመግበው ቸግሮት ከትምህርት ቤት ሲያስቀረው ሌላው ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች አይመጥኑኝም በሚል ሰበብ ብዙ ሺ ዶላሮችን እየከፈለ ወደ ውጭ ልኮ ያስተምራል፡፡ አንዱ ማታ የሚበላው እራት አጥቶ ሲቸገር ከፊሉ ደግሞ ሌሊቱን ሙሉ ዳንስ ቤት ውስኪ ሲጎነጭና ሲተፋ ያድራል፡፡ የአገራችን አኗኗር ልዩነት እንዲህ የትየለሌ ነው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ደግሞ ሌብነትና አልጠግብ ባይነት ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ እየተሳከረና እየተበላሸ፣ የዜጎ ቻችንም ስነምግባር ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና ከ«እኛነት» ይልቅ «እኔነት» እያየለ መጥቶ ሌብነትና ዘረፋ በመስፋፋቱ የድሆችንና የሀብታሞችን ልዩነት እያሰፋው መጥቷል፡፡ ካለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ወዲህ በአገራችን የነበረው ስርዓት በተከተለው የኢኮኖሚ ስርዓት ያየናቸው በርካታ ኢኮኖሚያዊ እመርታዎች በአግባቡ ባለመያዛቸው ሆዳምነት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ በርግጥ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በተለይ የማህበራዊ ትስስራችን መላላት ግን ዋነኛው ነው፡፡
«ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» በሚል ብሂል ያደገው ማህበረሰባችን ለሌብነትና ለጉቦ ነውርነት ቦታ ያልሰጠ መሆኑ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሌብነትን በአራዶች ቋንቋ «ቢዝነስ» የሚል ሽፋን እየሰጡ እከሌ ቢዝነስ ሠርቶ አደገ፤ እከሌ ተለወጠ፤ ወዘተ የሚሉ አስተሳሰቦች እየጎሉ በመምጣታቸው ለችግሩ መስፋፋት አንዱ መንስኤ ሊሆን ችሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር አንዳንድ ወላጆች የእከሌ ልጅ በአቋራጭ ሄዶ ባለሀብት ሆነ፤ እሱ/እሷ ወንድ ናት፣ በአጭር ጊዜ የራሷን ቢዝነስ ሠርታ ተለወጠች፣ ወዘተ የሚሉ አስተሳሰቦች ሠርቶ በራስ ላብ ከመለወጥ ይልቅ በአቋራጭ የሚከብሩ ሰዎችን የሚያበረታታበት ባህል እንዲዳብር አድርጓል፡፡ በትምህርት ቤትም ቢሆን ተመሳሳይ ነው፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ይህንን ያህል ተማሪዎች አስፈትነው ከፍተኛ ውጤት አመጡ በሚል በሚነገር ማስታወቂያ የሚመስል አነጋገር እየተጠለፉ ኩረጃን የሚያበረታቱበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ኩረጃን በይፋ ያበረታታሉ፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች የሌብነት መንፈስ በሰዎች ውስጥ በተለይ በታዳጊዎች ውስጥ እንዲሰርፅ በመደረጉ የሌብነት አስተሳሰብ በሂደት ስር እየሰደደ ሌባ እንዲበዛ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሌላም በኩል በአገራችን በድንገት ባለሀብት የሚሆኑ፣ አንድ ሰሞን ከአካባቢያቸው ጠፍተው ሲመለሱ የሕንፃ ባለቤት የሚሆኑ፣ ውድ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን የሚነዱና በውድ ቦታዎች ሲዝናኑ የሚታዩ ሰዎችም የሚፈጠሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሲገኙም ከየት አመጣኸው? መነሻህ ምንድነው? የሚል አካል የለም፡፡ ይህ ደግሞ ሌብነት እንዲስፋፋ ትልቅ ምክንያት ሆኗል፡፡
በተለይ አየር በአየር በሚባል አዲስ የአሠራር ስርዓት በድንገት ባለሀብት ሲሆኑ የሚታዩ በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ ሆኖም ሀብታችሁ ከምንድነው የሚላቸውም የለም፡፡ ለስሙ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ተቋም በሐቅ ከመሥራት ይልቅ የፖለቲካው ጠባቂ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ አንድ ሰሞን ያፈነገጡ ፖለቲከኞችን ለመያዝ ሲፈለግ ሙስናን አስወግዳለሁ እያለ ያቅራራል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ደብዛው ይጠፋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የፖለቲካ ሥራ ብቻ ሲሠራ ኖሮ አሁን ላይ ደርሷል፡፡
ይህ ተቋም ስሙ እንደሚያመለክተው ከሙስናው በተጨማሪ ስነምግባርንም የማስፈን ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ ለውጥ አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ ምናልባት አልፎ አልፎ በቴሌቪዥን ብቅ እያለ ከሚያስነግረው ማስታወቂያ የዘለለ ምን ለውጥ አመጣ ተብሎ ቢታይ ውጤቱ የዜሮ ብዜት ነው፡፡
ሲለው ደግሞ ወደ መንግሥት ሠራተኞች ብቅ ብሎ ሀብት አስመዝግቡ ሲል ይሰማል፡፡ ነገር ግን ይህ የተመዘገበ ሀብት ምን ላይ ደረሰ? የማን ሀብት ምን ላይ ነው? የሚል ጥያቄ ሲቀርብም አይታወቅም፡፡ ከዚህ በዘለለ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች ሀብትና ንብረት ምንድነው? የሚለውን ለመናገር አቅም ያለው አይመስልም፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ትላልቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞቻችን የሀብት መጠን ምን ያህል ነው? ማንም አያውቅም፡፡ አንድ ጉዳይ ሲፈለግ ብቻ አንድ በፖለቲካ የሚፈለግ ሰውና ሌሎች እዚህ ግባ የማይባሉ ሰዎችን ሰብስቦ አንድ ሰሞን የሚዲያ የትኩረት አቅጣጫ መቀየሪያ ሲያደርግ ይሰማል፡፡ ይህ ግን ማንንም አይጠቅምም፡፡
ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞችና ባለስልጣናት በሙስና ተጠርጥረው ሲታሰሩ ሁላችንም ተከታትለናል፡፡ በወቅቱ ከታሰሩት ውስጥ በትክክልም በወንጀል ተጠርጥረውና ማስረጃ ተገኝቶባቸው የተያዙ እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ ነገር ግን ጥቂቶቹ የአብዛኞቹ ማሟሟቂያ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አይጠየቁ የሚል አቋም ባይኖረኝም አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንደሚባለው አብዛኞቹ ለሚዲያ ፍጆታ ከመዋል በዘለለ ትልቅ አቅም የነበራቸውና የፀረ ሙስና ትግሉን ለመታገል ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ ለማለት አያስደፍርም፡፡
በሌላም በኩል አንዱ ሰርቆ ሀብታም ሲሆንና በዚህ ድርጊቱም እንደፈለገ በማህበረሰቡ ውስጥ ሲኖር የሚያስቆመው አይታይም፡፡ በዚህ የተነሳ አንዳንዱ ሰርቆ አንገቱን ቀና አድርጎ ሲሄድ ይታያል፡፡ በዚህ የተነሳ ሌላውም ሌብነትን ከመጠየፍ ይልቅ እንደእርሱ «ቢዝነስ ለመሥራት» ይነሳሳል፡፡ ምክንያም በአዲሱ ቋንቋ «ቢዝነስ መሥራት» /ሌብነት የተከበረበት ጊዜ ነውና፡፡
በሌብነት በተገኘ ሀብትም ሆነ በላብ በተገኘ ገንዘብ ከልክ በላይ የመኖር ዝንባሌዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደራሳቸው ሳይሆን እንደጎረቤታቸው ለመኖር በሚያደርጉት ጥረትና ፍላጎት ላልተገባ ወጪና ላልተገባ ድርጊትም እስከመጋለጥ ይደርሳሉ፡፡ ለምሳሌ በበዓል ሰሞን ጎረቤቴ በግ የሚገዛ ከሆነ እኔም የግድ በግ መግዛት አለብኝ፣ ወይም ጎረቤቴ የቤቱን እቃ የሚቀይር ከሆነ እኔም እሱ ያደረገውን ማድረግ አለብኝ በሚል ከአቅም በላይ የሚደረግ ጥረት ላልተገባ ወጪና ብሎም እዳ በመጨረሻም ወዳልተፈለገ የሌብነት ተግባር እስከመዳረግ ሊደርስ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከዚህ አንጻር የሠርግ ወጪን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንድ ሰው ከአቅሙ በላይ ተበድሮ ሠርግ ካበላ ከጥቂት ወራት በኋላ እዳውን መሸከም ሲያቅተው ወደ መነጫነጭ ይሄዳል፡፡ ለአንዳንዶችም የፍች መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡
በአጠቃላይ አቅምን ያላገናዘበ የአኗኗር ዘይቤ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ያለውን መልካም እሴቶች በአግባቡ በመጠቀም እንዲህ ዓይነት ሌብነት፣ ከአቅም በላይ ለመኖር የሚደረጉ ሁኔታዎች፣ ወዘተ መከላከል ቢችል አገራችን ያላት ሀብት ለእያንዳንዳችን በቂ ነው፡፡ የከፋ ድህነትም ላይኖር ይችላል፡፡
የጥንታዊ ግሪክ ስልጣኔ ከሚታወቅባቸው መልካም ጎኖቹ መካከል መካከለኛ ህይወት የሚል እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ በዚህ የመካከለኛ ህይወት/moderate life/ አስተሳሰብ አንዱ ሰው ከሚበላው፣ ከሚለብሰውና ከሚኖርበት ሁኔታ ጭምር ከልክ በላይ መሆን እንደሌለበት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በአገራችን የነበረውን ሁኔታ ስንመለከት ግን ከዚህ የተለየ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡
እንግዲህ በሳምንቱ መጨረሻ በክርስትና እምነት ተከታዮች የጥምቀት በዓል ይከበራል፡፡ በዚህ የበዓል ወቅትም የእምነቱ ተከታዮች ሁሉ በዓሉን በአቅማችን ልክ ልናከብረው ይገባል፡፡ «ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ» በሚል የቆየ ብሂል ያለንን ሁሉ አውጥተን የምናወድምበት ሊሆን አይገባም፡፡ ከዚህ ይልቅ ስለበዓላት ስናስብ ነገን የተሻለ ለማድረግ ሁል ጊዜ በልካችን መኖርን መርሐችን ልናደርግ ይገባል፡፡ ገንዘብ «የተረ ፈንም» ካለን አላግባብ ዋጋን ከምናንር ከተቸገሩ ሰዎች ጋር ተካፍሎ መብላት የተሻለ ነውና ይታሰብበት፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
ውቤ ከልደታ