የግብርና ምርቶችን በዘመናዊ መንገድ በማቀነባበር ለሃገር ውስጥና ለውጪ ሃገር ተጠቃሚዎች ለማቅረብ ታስበው በአራት ክልሎች እየተገነቡ ካሉት ፓርኮች አንዱ የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። የፓርኩ ግንባታ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ አዳሚ ቱሉ ወረዳ ቡልቡላ ከተማ በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም፣በልዩ ልዩ ምክንያቶች ግንባታው ለተወሰኑ ወራቶች ዘግይቷል።
የግብአት አቅርቦትና ማምረቻ ቦታዎችን በጊዜ ያለማግኘት ችግር፣ የኮንትራት ጊዜና የስራ ብዛት አለመመጣጠንና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለግንባታው መዘግየት ከግንባታው ተቋራጭ በኩል የሚቀርቡ ምክንያቶች ናቸው። ለኮንትራቱ ከተሰጠው አጭር የጊዜ ገደብ አኳያ በፓርኩ የተከናወኑ የግንባታ ስራዎች በርካታ በመሆናቸውና ስራዎቹን ለማጠናቀቅ ከጫፍ በመድረሳቸው ግንባታው ያን ያህል ዘግይቷል ማለት አይቻልም። ለዚህም የፓርኩ ስራ ተቋራጭ ፕሮጀክት ማናጀሮች ማረጋገጫ ምክንያታቸውን ይሰጣሉ።
የፓርኩ የምእራፍ አንድና ሁለት ፕሮጀክቶች ማናጀር አቶ ደበበ ኩብራኤል እንደሚገልፁት፤ የፓርኩ ግንባታ በ272 ሄክታር መሬት ላይ በተለያዩ ምእራፎች ተከፋፍሎ እየተከናወነ ይገኛል። የመጀመሪያው ምእራፍ የፓርኩ ግንባታ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም ነው የተጀመረው፤ ስምንት ልዩ ልዩ ህንፃዎችን ያጠቃልላል። የተማከለ የገበያ አገልግሎት መስጫን፣ የማሰልጠኛ፣ የአስተዳደር፣ ኢንፎርሜሽን መስጫ ማእከላትን፣ የህፃናት ማቆያና 7 ሺ 500 ካሬ ሜትር የሚሸፍኑ ሶስት የተለያዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ሼዶችን በማካተት በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታው ተጠናቆ ባለቤቱ ተረክቧል።
እንደ አቶ ደበበ ገለፃ፤ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ከመሆኑ አኳያ ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ፈጥሯል፤ አካባቢውንም ከኮንስትራክሽን ስራ አስተዋውቋል። የቴክኖሎጂ ሽግግሮችንም ያደረገ ትልቅ የግንባታ ምእራፍ ሲሆን፣ በተለይ ከአካባቢው ላይ የተነሱ ሰዎችን በማደራጀት አሸዋ፣ ጠጠርና የተለያዩ የግንባታ ግብአቶችን እንዲያቀርቡ በማድረግ ከ30 በላይ የሚሆኑ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት የስራ እድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ሶስተኛው ምእራፍ የፓርኩ ግንባታ የተጀመረው በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ነው። ለግንባታው የተቀመጠው የጊዜ ገደብ አስር ወራት ብቻ ነው፤ በዲዛይን ለውጦች ምክንያት ግንባታው ተጓትቶ ቢቆይም፣ በመጪው ግንቦት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎም ይገመታል። ይህ ምእራፍ 70 የሚሆኑ የህንፃ ግንባታዎችን ያካትታል። ከእነዚህም 68 ያህሉ በፓርኩ ለሚሰሩ 300 አባወራዎች መኖሪያ የሚሆኑ ህንፃዎች ናቸው፤ ሁለቱ ለክሊኒክና የእሳት አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ብርጌድ የሚያገለግሉ ናቸው።
የፓርኩ 7 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር አጥር በብሎኬት ተገንብቶ ተጠናቋል። የሚቀሩት ስራዎች የአደገኛ አጥር ገጠማና የኳርትዝ ቀለም ቅብ ብቻ ናቸው። ለፕሮጀክቱም በአጠቃላይ 601 ሚሊዮን ብር ተይዟል።
እንደ አቶ ደበበ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈፃፀም በፋይናንስ ደረጃ 71 ከመቶ በፊዚካል ስራ ደግሞ 76 ከመቶ ደርሷል። ፕሮጀክቱ አሁን ባለበት ደረጃ 682 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥሯል። ከእነዚህ ውስጥም 26 ለሚሆኑና በግንባታ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ለሚሰሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት የስራ እድል ተፈጥሯል። በተመሳሳይ 26 ለሚሆኑ የኮንስትራክሽን እቃ አቅራቢ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት የስራ እድል ተፈጥሯል። 7 ጫኝና አውራጅ፣ 4 ሻይ ቡና የሚሰሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትም ተደራጅተው የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል።
በመጀመሪያዎቹ የግንባታ ሂደቶች የግንባታ እቃ አቅራቢዎች በተለይም ድንጋይና ሴሌክት ማቴሪያል አቅራቢዎች እጥረት ፕሮጀክቱን በመጠኑ እንዳዘገዩት አቶ ደበበ ጠቅሰው፣በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተፈትቶ ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአካባቢው ላይ በወቅቱ የነበሩ አለመረጋጋቶችም ለፕሮጀክቱ መዘግየት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ይህ ችግር ተፈቶ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያትም አንዳንድ የግንባታ እቃዎችን ከውጭ ሀገር ማስገባት ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ በተወሰነ መልኩ ለመጓተት ተዳርጓል።
የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማናጀር አቶ መርጋ ወላቡ እንደሚሉት፤ ከፓርኩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሁለተኛው ምእራፍ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሲሆን፣ ይህም በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም ነው የተጀመረው። ይህም 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ፣ ሳኒተሪ፣ የኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦት፣ የትራንስፎርመር ሀውስና ለሼዶች ግንባታ
ቦታዎችን የማስተካከል ስራዎችን ያጠቃልላል።
ለአስፓልት መንገድ ግንባታ ኮንትራት የተያዘው ገንዘብ 463 ሚሊዮን፣ ለሳኒተሪ ስራ 168 ሚሊዮን፣ለኤሌክትሪክ ስራ 350 ሚሊዮን፣ ለሼድ ግንባታዎች ቦታዎችን ለማስተካከል 380 ሚሊዮን ብር ነው። አጠቃላይ የፕሮጀክቱ የኮንትራት መጠን 1 ቢሊዮን 5 ሺ 586 ብር ይጠጋል። በዲዛይን ለውጥና በተጨማሪ ስራዎች ምክንያት የፕሮጀክቱ ወጪ ወደ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አካባቢ ደርሷል።
ከዚህ ፕሮጀክት ውስጥ አብዛኛዎቹ ስራዎች መገባደዳቸውን አቶ መርጋ አመልክተው፣የመንገድ ስራው የሰብ ቤዝ ስራ ተጠናቆ ወደ አስፓልት ስራ ተደርሷል ይላሉ። የሳኒተሪ ስራዎችን 83 በመቶ ያህሉ ተጠናቀዋል። የኤሌክትሪክ ስራዎች 50 በመቶ እንዲሁም የፓወር ሀውስ ስራ 25 በመቶ ያህሉ ተገባዷል። ለሼዶች ግንባታ ቦታዎችን የማስተካከል ስራውም 99 በመቶ ተጠናቋል። በጥቅሉም የፕሮጀክቱ አፈፃፀም 87 ከመቶ ደርሷል በማለት ያብራራሉ።
በዚህ የፕሮጀክት ሂደት በጊዜያዊነትና በቋሚነት 800 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፤ ፕሮጀክቱ እየተጠናቀቀ በመምጣቱ ከ150 እስከ 200 የሚጠጉ የቀን ሰራተኞች በስራ ላይ ይገኛሉ። 69 የሚሆኑ መሐንዲሶችና የሳይት ጥበቃዎችም ስራቸውን እያከናወኑ ነው።
ፕሮጀክቱ ሲጀመር ስራው ለአካባቢው ህብረተሰብ አዲስ ከመሆኑ አኳያ ተቀባይነቱ ላይ መጠነኛ ችግሮች ነበሩ ያሉት አቶ መርጋ፣ በወቅቱ ከቦታው ላይ የተነሳው ገበሬ ከፍተኛ ጥቅም ይጠበቅ ስለነበረ እነሱን መልሶ የማቋቋምና ስራ የመስጠቱ ተግባር አስቸጋሪ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ መርጋ ማብራሪያ፤ ለሼዶች ግንባታ ቦታ ለማስተካከል ከሳይቱ የሚወጣውን አፈር የማራገፊያ የቦታም አንዱ ችግር ነበር። ይሁንና ከወረዳዎቹ አመራሮች ጋር በመወያየት ለማህበረሰቡም ግንዛቤ በማስጨበጥ ችግሮችን መፍታት ተችሏል።
ከዲዛይን ውጪ ያሉ ተጨማሪ ስራዎች መኖር፣ ከውጭ ሀገር የሚመጡ እቃዎች መዘግየትና የውጪ ምንዛሬ እጥረት ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ ምክንያት ቢሆኑም፣የዚህ ምእራፍ አብዛኛዎቹ ስራዎች እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
አስናቀ ፀጋዬ