ኢትዮጵያ ከግብርናው ዘርፍ በመቀጠል ከፍተኛ በጀት የምትመድበው ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ነው። ዘርፉም በምላሹ በመሰረተ ልማት ፣በቤቶች ልማት እና በመሳሰሉት በሚያከናውናቸው ተግባሮች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፤ ከፍተኛ የስራ እድል በመፍጠርም ይታወቃል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በልማቱ በኩል ተጠቃሽ አስተዋጽኦ እያበረከተ ቢሆንም፣ በግዥ ላይ በሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣በሙስና፣በአቅም ውስንነትና በመሳሰሉት የተነሳ የሚጠበቅበትን እያከናወነ እንዳልሆነ ይገለጻል። መንግስትም የዘርፉ ባለሙያዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አምኃ ስሜም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንጻሩ የግዥና የመሳሰሉት ችግሮች ዘርፉን ቀፍድደው እንደያዙት ይናገራሉ። በግልና በመንግስት በሚሰሩ የኮንስትራክሽን ስራዎች ዘርፍ ባሉት ተግዳሮቶችና በመፍትሄያቸው እንዲሁም በውጭ ተቋራጮችና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከኢንጂነሩ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል ። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- –በቅድሚያ ማህበራችሁ ምን ያህል አባላት አሉት ?
ኢንጂነር አምኃ፡- አንድ ሺ750 ኩባንያዎች ወይም አባላት አሉት። የኩባንያው ባለቤቶች ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ዘጠኝ የሚገኙ ናቸው። በማህበራችን ውስጥ የሚመዘገቡት የድርጅት ባለቤቶች ብቻ ናቸው።
አዲስ ዘመን ፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለሀገሪቱ ስላለው ፋይዳ ቢያብራሩልኝ ?
ኢንጂነር አምኃ ስሜ፡- ኢንዱስትሪው ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት በየትኛውም አለም እስከ 9 ነጥብ 5 በመቶ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከኢኮኖሚው ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚያበረክተው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ነው። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለምም እንደዚሁ ነው።
ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የስራ እድል ለቀን ሰራተኞች፤ ለባለሙያዎች፤ ለአቅራቢዎች ይፈጥራል። በሆቴልም መስክ ብትወስደው ለሰራተኛው ምግብ በማቅረብ በርካቶች ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት ፣ከከተማ ግንባታ አንጻር መሰረተ ልማቱ እየተሻሻለና እያደገ የሚሄድበት ዘርፍ ነው።
በሀገራችን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የስራ እድል በመፍጠር ፣ለኢኮኖሚው እድገት የተሻለ ግብአት በመሆኑ ከግብርናው ቀጥሎ ይታያል።
አዲስ ዘመን፡- -በሀገሪቱ የጨረታ ህግ እያለ የኮንስትራክሽን ስራዎች ያለ ጨረታ ለተቋራጮች የሚሰጡበት ሁኔታ እንደነበር ይገለጻል፤ ጨረታ ወጣ የተባለ ጊዜም ሙያተኛ ያልሆኑ ሰዎች እንዲሳተፉበት ይደረግ ነበር ይባላል። ይህ ሁሉ የሚሆነው በባለስልጣኖች ጣልቃ ገብነት ወይንስ በሌላ ምክንያት?ዛሬስ ችግሩ ተቀርፎ ይሆን ?
ኢንጂነር አምኃ፡- እንደ አሰራር ሕጎች ይወጣሉ። ሕጎቹ ግልጽነትና የሙያውን ደንብ የጠበቁ አይደሉም። የሚተገብረው አካልም ችግር አለበት፤ ለጨረታዎች የማያስፈልጉ መመዘኛዎች ከሕጉና ከስርአቱ ውጭ ይቀመጥላቸዋል። የሚወድቁበት ሁኔታ አለ።
የስራ ተቋራጭ ፈቃድ እንዲሁም የባለሙያ ምዝገባ የቤቶች እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር በሚጠይቀው መመዘኛ መሰረት ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 9 ይሰጣል። ደረጃዎቹ የየራሳቸው ካፒታል የተቀመጠላቸው ናቸው። አንዳንድ ጊዜ በጨረታው የተቀመጡት መመዘኛዎች የደረጃ አራት ሆነው ለደረጃ አንድ የሚሆኑ ስራዎች ይወጣሉ። ጨረታዎቹ በአብዛኛው በሰው ልክ ተሰፍቶ እንደ ፈለገ ወይ አሰሪው መስሪያቤት ከራሱ የጥቅም ፍላጎት በመነሳት የሚፈጽማቸው ናቸው።
በመሰረቱ የጨረታ አይነቶችና የጨረታ ሂደቶች የሚካሄዱባቸው አግባቦች በርካታ ናቸው። በብሔራዊና በአለምአቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ሕጎችና አሰራሮች ፣ ግልጽ ጨረታዎች የሚካሄዱባቸው ማንኛውም ሰው የሚሳተፍባቸው የጨረታ ሂደቶች አሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቁርጥ ዋጋ ተብሎ በተወሰነ የሚደረጉ የጨረታ ሂደቶችን እናያለን። በአጭሩ ተመዝግበው የተወሰኑ የስራ ተጫራቾች ብቻ ተጋብዘው በእነሱ መካከል የሚደረጉ ውድድሮች አሉ። በድርድር የሚሰጡ ጨረታዎችም አሉ።
መስሪያ ቤቶች ለሚፈለገው መመዘኛና ስራ ሊመጥኑ ይችላሉ፤ ያስፈልጉኛል የሚሏቸውን ተቋራጮች መርጠው የሚያወዳድሩበትና የሚሰጡበት አግባብም ሊኖር ይችላል። በዚህ መልኩ ሲካሄድ ሂደቱ ምን ያህል ጤናማ ነው የሚለውን የሚወስነው አሰራሩ ነው። በእኛ ሀገር እነዚህን የመሳሰሉ ስራዎች ሲሰሩ ግልጽነት የጎደላቸውና ጤናማ ያልሆኑ ነገሮች ይስተዋላሉ። ይህ አይነቱ አሰራር በዚህ ኢንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም ይስተዋላሉ።
አዲስ ዘመን፡- –የግዥ ስርአቱን ችግሮች ለመፍታት ተሞክሮ ያወቃልን ?
ኢንጂነር አምኃ፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በተመለከተ የሚወጡት ጨረታዎች ወይንም አጠቃላይ የግዢ ስርአቶችን በተመለከተ የተደረጉ ጥናቶች መሞዳሞድ (ሙስና) የተደረገባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩ ያሳያሉ። ጨረታዎች እንዲወጡ ሲደረግ ከሕግ አግባብ ውጭ በሚፈልገው ሰው ልክ ተሰፍተው የሚዘጋጁ በመሆናቸው
በርካታ ተጫራቾችን እንደልብ የማያሳትፉ ግልጽነት የጎደላቸው፤ ተገቢ ያልሆኑ መመዘኛዎች የተቀመጡባቸው በመሆናቸው የግልጽነት ችግሩ ውስብስብና የገዘፈ ነው። ችግሩም ከዚሁ ይጀምራል።
የዶክመንት ዝግጅትና ዲዛይንን የመሳሰሉትን የያዙ ሰነዶች ሌሎች ተግዳሮቶች ናቸው። እነዚህ መሰረታዊ ተግዳሮቶች እስካልተቀረፉ ድረስ አንዱ በሌላው ላይ እየተደረበ ፕሮጀክቶቹን አጠናቆ ከማስረከብ ይልቅ የአብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ዋጋ በሁለት እና ሶስት እጥፍ እየተጨመረ ጨረታ የሚቀርብባቸው ሁኔታዎች ናቸው የሚታዩት። ይህ ትልቅ ሀገራዊ ኪሳራ ያስከትላል።
ችግሮቹን በመሰረታዊነት ለመፍታት የግልጽነትና
ተጠያቂነት መርህ መስፈን አለበት። ሁሉም ሰው በሕጉ መሰረት በግልጽነት መርህ ጨረታ የሚሳተፍባቸው፤ ሙያዊ ብቃቱ፤ አቅሙና የስራ ልምዱ፤ ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትና አድልዎ በአግባቡ የሚመዘንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ለችግሩ መፍቻ ብቸኛ ቁልፍ ነው።
ችግሮቹን አንጥሮ ለማውጣት ከፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንና ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ጥናቶች አካሂደናል። ይህን ተከትሎም በግዢ ስርአቱ ላይ የተወሰኑ ማስተካከያዎች ተደርገዋል። ማስተካከያዎቹ በስራ ላይ እንዲውሉ የእኛን ድርጅት ጨምሮ ለ122 የመንግስት መስሪያ ቤቶች መመሪያዎቹ ተግባራዊ እንዲደረጉ ተላልፈው ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የኮንስትራክሽን ዘርፉ በተወሰኑ ቡድኖች ተይዟል በሚል በስፋት ይገለጻል። ባለስልጣናትም የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለፈለጉት ተቋራጭ ይሰጣሉ ይባላል፤ እነዚህንስ እንዴት ይመለከቷቸዋል ?
ኢንጂነር አምኃ፡- በቅርቡ ባካሄድነው ስብሰባ አንዱ የተነሳው ጉዳይም ይሄው ነው። ተቆጣጣሪው ባለስልጣን ደረስኩባቸው ያላቸው በርካታ ነገሮችም አሉ። እንደተባለው 12፤ 20 የሚባሉ ነገሮች አሉ። ይህም ማለት 12 ሕንጻ 12 መንገድ ስራ በያዙ ግለሰቦች የሚንቀሳቀስ በሞኖፖሊ የተያዘ ነው ይባላል።
አንድ እንግሊዛዊት ለሶስተኛ ዲግሪ ጥናት ስትሰራ ተመሳሳይ ጥያቄ አንስታልናለች። በእርግጠኝነት በየመስሪያ ቤቱ የሙስና መገለጫ ባህሪዎችን እናያለን። ለሚሰጡት አገልግሎት እንዲከፈላቸው የሚፈልጉ ሞልተዋል። ይህም ከጥበቃ ይጀምራል። ጸሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ችግሩ አለም አቀፍ ተቋማት ድረስ ይሰማል። እነሱም አጥንተው መረጃዎችን አግኝተዋል።
በዚህ የተነሳም በርካታ ተቋራጮች ከስራው እየለቀቁ፤ ሀገር ጥለውም እየሄዱ ናቸው። አሁን በስራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ ከውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጡ ጋር ተያይዞ ከመጣው ግሽበት ጋር ተዳምሮ ችግሩን መሸከም ተስኗቸዋል፤ ድርጅታቸውን እየዘጉ ያሉበትና ፕሮጀክቶችን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። አቅም አላቸው ተብለው የሚታሰቡት ሳይቀሩ ተቸግረዋል።
አዲስ ዘመን:-መፍትሄው ምንድነው ብለው ያስባሉ ?
ኢንጂነር አምኃ፡- አሰራሩ በሀገር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉ እውነት ነው። ለመፍትሄው እነኚህን እንደ ትምህርት ወስደን ክፍተቶቻችንን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መግባት የሚያስችሉን ሁኔታዎችስ ምንድናቸው የሚሉትን መፈተሽ ያስፈልጋል። ሕጎቹን የመተግበሩ ስራ በሚመለከተው ባለሙያና አካል መመራት ይኖርበታል።
በዚህ ላይ ከአንድ አመት በፊት የተቋቋመ የጋራ መድረክ አለን። ዝግጅቶች ስናደርግ ቆይተን ባለፈው የካቲት አዳማ ላይ ከቤቶች ልማት እና ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤ ከኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ጋር ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ምክክር አርገናል። ስራዎቻችንና ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች ለይተን በምን አይነት መልኩ መቀጠል አለብን በሚል መክረናል፤ የኮንስትራክሽን ምዝገባም ሆነ የግዥ ስርአቱን በተመለከተ ጽሁፎች ቀርበው ተወያይተናል። ደምቦቹ በሚገባ እንዲዳብሩ እንዲሁም መካተት የሚገባቸው እንዲካተቱ ለማድረግ ተነጋግረናል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ስራ ተቋራጮች ማህበር፤ የአማካሪዎች ማህበር፤ የአርክቴክቶች ማህበር፤ የኤሌክትሮ መካኒኮች ማህበር ሆነን ያለፉትን ችግሮች ከማንሳት ይልቅ የወደፊቱ ላይ በማተኮር ተወያይተናል፤ አሰራሩ ምን መሆን አለበት የሚለውን አይተን የተጠናከረ ሰነድ አዘጋጅተን ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚጸድቅበትን ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመወሰን ከኮንስትራክሽን ተቆጣጣሪዎች ባለስልጣን ጋር ቀጠሮ ይዘናል። ለኢንዱስትሪው ችግር ፈቺ ሰነድ በማቅረብ ረገድ ከዚህ በኋላ እንዲኬድበት የተፈለገው አቅጣጫ ባለቤት ያገኘ ስለሆነ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተቀራርበን እየሰራን እንገኛለን።
ኩባንያዎች በሀገራችን የኮንስትራክሽን ስራ በስፋት መሰማራታቸውን እንዴት ያዩታል?
ኢንጂነር አምኃ፡- በሀገራችን ከሚንቀሳቀሱት የውጭ ተቋራጮች በርካታዎቹ የየሀገራቸው መንግስት ድርጅቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ እኛ እንደ ኢትዮጵያ ስራ ተቋራጮች ማህበር ከቻይና ኢንተርናሽናል ኮንስትራክሽን ማህበር ጋር የምንሰራበት የትብብርና የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመናል። በሀገራቸው የማህበሩ ፕሬዚዳንት በቀጥታ የሚሾመው በቻይና መንግስት ነው። እንደ እኛ ሲቪክ ሶሳይቲ ሆኖ በማህበር አባላት የተመረጠ ወይንም የሚሰራ ድርጅት አይደለም። የውጭ ኩባንያዎች ወደ ሀገራችን ሲገቡ መንግስታቸው በፋይናንስ ሎጀስቲክ ሙሉ ድጋፍ ያደርግላቸዋል። በዚህም የተነሳ የተሟላ አቅም ስላላቸው በቀጥታ ወደ ስራው ይገባሉ።
እንደኛ ሀገር በደከመ አቅም አንድ ኮንትራክተር ሁሉንም ስራ የሚሸከምበት ሁኔታ እነሱ ዘንድ የለም። የሀገራችን ኢኮኖሚ የሚከብደው ነገር ስላለ እነሱ ከውጭ ሲመጡ የፋይናንስ አቅማቸው ግዙፍ ስለሆነ ለመደራደርም ሆነ በግራንትና በተለያየ መልክ ቀርበው ፈጥነው ወደስራ የመግባት ሰፊ እድል አላቸው።
ሁለተኛው የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አቅማቸው ጥሩ ነው። እኛን አንዱ ትልቁ እየጎዳን ያለው የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ባህል፣ አሰራር፣ ልምድና እውቀታችን በጣም ደካማ መሆኑ ነው። በዚህ የተነሳ ወደስራው እንገባለን እንጂ እንዴት እንወጣለን የሚለውን የመገመት ድክመት አለብን።
ከኩባንያዎቻችን አብዛኞቹ በፕሮፌሽናሎች (ሙያተኞች) አይታገዙም። ወደ ስራው ማንኛውም ባለሀብት ይገባል። ከስራው ሲወጣም ያ ባለሀብት የሚያስበው ገንዘብ ብቻ ነው። ገንዘቡን ወደራሱ የንግድ ስራዎች ይለውጠዋል፤ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱን አየር ላይ ጥሎት ይሄዳል ማለት ነው። ይህም ተያያዥነቱ እስከላይኛው የመንግስት አካል ድረስ ይዘልቃል። ፕሮጀክቱን አሸንፎ የራሱን ድርሻ ወስዶ የሚሰጠውን ድርሻ ከመስጠት የዘለለ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የኮንስትራክሽን ዘርፉን አቅም እንዴት ማሳደግ ይቻላል ?
ኢንጂነር አምኃ፡- የአቅም ግንባታ በተለያዩ መንገዶች መፍጠር ያስፈልጋል። የአቅም ግንባታ የሰዎችን አመለካከት ከመለወጥ ይጀምራል። ሰዎች በሙያዊ ስነምግባር ላይ ተመስርተው ለሚሰሩት ስራ መልሰው ዴሊቨር ማድረግ እንዲችሉ እውቀት ያስፈልጋቸዋል። እውቀቱን ማግኘት እንዲችሉ ከትምህርት አለምም ይሁን ከልምድ ያገኙትን ደምረው ወደስራ መግባት የሚችሉበትን አቅም ለመፍጠር እንደ ማህበር ስልጠናዎችን እንሰጣለን።
ለአብነትም ከጀርመኑ ቢጂቪ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በስልጠና ላይ ላለፉት 7 አመታት ያህል አብረን ሰርተናል። በየአመቱ በተለይ በክረምት ወቅት በኩባንያ ማኔጅመንትና በተለያዩ ርእሶች ላይ ስልጠናዎች እያዘጋጀን የኩባንያ ባለቤቶችንና ሰራተኞችን አቅም ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የመንግስት ጥገኛ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከመንግስት ጋር የአቅም ግንባታ ስራዎች በጋራ የሚሰራበትን መንገድ በመፈለግ ረገድ ባለፉት 2 አመታት በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እቅዶች ተዘጋጅተው ነበር። በዚህ መሰረት የተወሰኑ የሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን አብቅቶ እንዴት አድርጎ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ ይቻላል?እንዴትስ ይብቁ ?ይፈጠሩ ? የሚለው እቅድ ከወጣ በኋላ ሚኒስቴሩ ያቀደውን ስራ ሳይጨርስ እንደገና ማዋቀር በሚል ፈርሶ ወደ ከተማ ልማት ገብቷል። የያዝነው ስራም ባለህበት ሂድ ሆኗል ማለት ነው።
እኔ ስመለከተው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ልክ ኢትዮጵያና ግብጽ የሚያደርጉትን የጥቅም ግጭት ይመስላል። ኢንዱስትሪው በቅቶና ተስፈንጥሮ እንዲሄድ በማይፈለግበት ደረጃና አይነት ታስሮ ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል።
አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ንረቱ አላሰራ ብሏል። ማሽነሪዎችን ማንቀሳቀስ አልተቻለም፤ የታክስ ችግር አለ። በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቶች እየቆሙ ናቸው የሚል መረጃ አለ። ይህን እንዴት ያዩታል ?
ኢንጂነር አምኃ፡- ግልጽ ነው። የዋጋ ንረቱ በአንዳንድ ጥናቶች ለምሳሌ ከአስራ አንድ አመት በፊት ወደ ደረጃ አንድ የተቋራጮች ማህበር የተቀላቀለው የደረጃ አንድ ስራ ተቋራጮች ማህበር በግሽበቱ ላይ ጥናት ባካሄደበት ወቅት ብረት እስከ 62 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይቶ ነበር። የሳኒተሪ እቃዎችና ሌሎችም እንዲሁ ዋጋቸው አሻቅቦ ነበር። በወቅቱ በ100 ብር እፈጽመዋለሁ በሚል የተያዘ ፕሮጀክት ወደ 50 ብር ዝቅ ያለበት ሁኔታ ስለነበረ 50 ብር ላይ ሲደርስ መቶ ብር ስለማይሞላ ስራው የግድ ይቆማል ማለት ነው። በውጭ ምንዛሬ የሚመጡ ግብአቶች ካጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ በተገቢው መልኩ እየቀረቡ አልነበረም።
ገበያውን ለማረጋጋት መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ስለሌሉ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሽባ ሆኗል። የኮንስትራክሽን ዘርፉ መሽመድመድ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው እንዳለ እንዲተኛ አርጎታል። ሆቴሎች፣ አቅራቢዎች ፣ላኪዎች፤ ሰራተኛው ሁሉም ከዚሁ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ሲወድቅ አብረው ነው የወደቁት።
አዲስ ዘመን፡- ይህንንስ እንዴት መፍታት ይቻላል ይላሉ?
ኢንጂነር አምኃ፡- ይህን ችግር በሩቅ መመልከት ሀገራዊ ጉዳቱ ትልቅ ነው። መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል። በእርግጥ የሀገር ሰላም ይቀድማል። ከሰላሙ ቀጥሎ ኢኮኖሚው ማደግ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ በስፋት በመስራት ስራ መፍጠር ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ካልቻልን ነገ የሚበላው ያጣ ሕብረተሰብ ለመኖር ሲል አንዱ ሌላውን ይበላል። ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።
ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ኢንዱስትሪውን ተቆጣጥረውት ነበር፤ ከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለት ተፈጽሞ ነበር የሚለው አንድ ጉዳይ ነው። ኢንዱስትሪው ግን በግለሰቦች እይታና ሚዛን መታየት የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቶችን በማዘግየት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ አድርገው ያራዝሙታል ይባላል። ጠ/ሚ/ሩ በአንድ ወቅት ሲናገሩ የኛ ተቋራጮች የስራ እድሉ ለቻይናውያን ተሰጠ ትላላችሁ። ለእናንተ ሲሰጣችሁ 5 እና 6 ዘመናዊ መኪኖችን እየገዛችሁ ከመንጎማለል ውጪ ውጤታማ ስራ ስትሰሩ አትታዩም ሲሉ ተደምጠዋል። ይህንንስ እንዴት ይመለከቱታል?
ኢንጂነር አምኃ፡- ይህን ጉዳይ በሁለት ከፍዬ አየዋለሁ። የአንድ ኮንስትራክሽን ግብአት ባለቤት፣ አማካሪና ኮንትራክተር ናቸው። ፕሮጀክት የሶስቱ ድምር ውጤት ነው። አንድን ፕሮጀክት በፕሮጀክትነቱ በሚፈለገው ጊዜ በጀትና ጥራት ማስረከብ የሚቻልባቸው ነገሮች በእነዚህ ላይ ይመሰረታሉ።
በኮንትራክተሩ በኩል ችግሮች እንዳሉ ሁሉ በባለቤትና በአማካሪውም በኩል ችግሮች አሉ። አማካሪ ስንል የአንድን ፕሮጀክት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን ሂደት የሚመለከተው ነው። ስራው ከዲዛይን ይጀምራል። ጥራት ያለው ዲዛይንና ቢል ኦፍ ኳንቲቲ ከተሰራ ተቋራጩ በእነዚህ መሰረት የሚያቀርባቸው ዋጋዎችና የሚወስዳቸው ኃላፊነቶች በሕጉ መሰረት በተደራጀ ሰነድ ውስጥ ከገቡ ስራዎቹን በሚፈለገው መልኩ ማጠናቀቅ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ሳይንስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሯቸውና ውጤታማ በሆኑባቸው ልምድ በወሰዱባቸው ፕሮጀክቶች ላይ በርካታ ነገሮችን ያዩ ይመስለኛል። ከ17 ሀገሮች የተውጣጡ መሐንዲሶችና አማካሪዎች በተሳፉበት ፕሮጀክት ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ ነግረውናል። 80 በመቶው የተሳካ ቢሆንም 20 በመቶው ክፍተት ነበረበት።
በእኛ ሀገር ባለሙያዎች የተፈቱ የውጪዎቹ ባለሙያዎች ያላዩአቸው ችግሮች ነበሩ። ከእዚህም የውጪዎቹ ልምድ የቀሰሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይ አንድ ለአረንጓዴ ስፍራ እየተዘጋጀ በነበረ ቦታ ላይ የፈሰሰ አፈር ዝናብ ሲጥል እየታጠበ አስቸግሮ ነበር። ለእዚህ ችግር የሀገራችን ባለሙያዎች ችግር ፈቺ መፍትሄ አፍልቀዋል። ቀርበህ ባየኸው ቁጥር ችግሮቹን በርቀት ከምትናገረው ይልቅ የችግሮቹ አካል የመፍትሄውም አካል ሆነህ የምትመጣባቸው ሁኔታዎች አሉ።
እንደሚታወቀው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከግብርናው ቀጥሎ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የሚመደብለት ትልቅ የስራ እድል የሚፈጥር ዘርፍ ነው። በዘርፉ የሚፈጠሩት ትንሽም ይሁኑ ትልቅ ችግሮች ሌላው አለም ላይ የሌሉ አይደሉም። እጅግ በሰለጠኑት ሀገራትም
የባሱ ችግሮች ያጋጥማሉ። እኛ ግን ለወሬውም ለትችቱም ለተለያዩ ነገሮችም ተጋላጭ ነን።
አዲስ ዘመን፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ማህበራችሁ ምን ሚና አለው? እንደ ዜጋም እንደ ባለሙያም ለግድቡ ምን አስተዋጽኦ አርጋችኋል?
ኢንጂነር አምኃ፡- ግንባታው እንደ ተጀመረ አካባቢ በተካሄደ ቴሌቶን ግንባር ቀደም ተሳትፎ አድርገናል። አባላቱም በርካታ ድጋፎችን አድርገዋል። ግንባታውን በባለቤትነት የሚመራው መንግስት ነው። ሳሊኒ የሲቪል ስራውን ይሰራል፤ በፊት ሜቴክ የተወሰኑ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች ሰርቷል። በዚህ ረገድ የማህበራችን ሚና የለም ማለት ይቻላል።
አሁን መንግስት አዲስ ጨረታ አውጥቶ የአሜሪካና የሌሎች ሀገሮች ኩባንያዎች ገብተው እየሰሩ ናቸው። እኛ በተለይ ኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ላይ በየጊዜው እየሄድን እንጎበኛለን። በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ላይ እንሳተፋለን።
አሁንም እንዴት እናድርግ በሚለው ላይ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አስተባባሪ ምክር ቤት አባል እንደመሆናችን መጠን በጉዳዩ ላይ የሚኖረን አስተያየት አለ። ስራው እንዲቀጥል በመዋጮ ረገድ ምን እናድርግ ከሚሉት ጋር አብረን እንመክራለን።
ከዚህ በተረፈ ፕሮጀክቱን የውጪ ሰዎች ቢሰሩትም የራሳችን ጉዳይ ነው ። ከውጭ የሚገኘው የእውቀትና የልምድ ሽግግር ለዜጎቻችን በሚጠቅም መልኩ እየሰራን፤ መንግስትንም እያገዝን፤ እኛም ዜጎች ተጠቃሚ የምንሆንባቸው ሰፊ ሁኔታዎች ነበሩ። ሆኖም ግን በሩ ዝግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተዘጋው በር እንዴት ይከፈት ትላላችሁ?
ኢንጂነር አምኃ፡- በሩ ለዜጎች ቢከፈት ጥሩ ነው። በሀገራችን በርካታ ባለሙያዎችና ማሽነሪዎች አሉ። እነዚህ የሀገር ሀብት ናቸው። ማሽነሪዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ
በሚገቡበት ጊዜ በራሱ ሌላ አለም ላይ አንድ ኮንትራክተር ፈቃድ ለማውጣት ፕሮፌሽናሊ የሚፈለጉበትን መስፈርቶች ስትመለከት እኛ ዘንድ የሚጠየቁት ማሽነሪዎች፣ ካፒታሎች ፣ ወዘተ ለእኔ አስፈላጊ አይደሉም። ምክንያቱም የደረጃ አንድ ስራ ተቋራጭ እስከ 350 ሚሊዮን ብር ይሰራል ከተባለ ከዚያ በላይ ይሰራል ተብሎ ይገመታል። 350 ሚሊዮን ካልን ለዚህ የሚያስፈልገው የሰው ኃይልና ማሽነሪ ነው የሚጠየቀው። እነዚህ ነገሮች አንድ ፕሮጀክት ካሸነፈ በኋላ አበቁ ማለት ነው። ሌላ ፕሮጀክት ቢያሸንፍ ሌላ ማሽነሪ አይገዛም። ደረጃ አንድ ለሚባለው አበቃ ማለት ነው›። እዚሁ ሀገር ውስጥ ካለው ተከራይቶ ነው የሚሰራው። ስለዚህ መስፈርቶቹ አሳታፊ በሆኑት ነገሮች ላይ ልክ አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡- በእዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግራችሁ ታውቃላችሁ?
ኢንጂነር አምኃ፡- አዎ። በሌላ ሀገር ያንን ስራ በተመለከተ የሚቀርቡልህ ፈተናዎች አሉ። እነዚያን ካሸነፍክ ያንን ፕሮጀክት አንተ መምራት ትችላለህ። በተረፈ ማኔጅ ታደርጋለህ፤ ቀሪውን ለሰብ ኮንትራክተር/ከፊል ተቋራጭ/ ትሰጣለህ። ለምሳሌ አንድን ሰብ ኮንትራክተር ይህን ቆፍርልኝ ብትለው ሌይአውቱን ከሰራህለት ማሽኖቹን ዶዘሮቹን አስገብቶ ቆፍሮልህ ይወጣል። ኮንክሪት አምራች ድርጅቱንም እንደዚያው ታስገባለህ። የውጪዎቹ እንዲህ እያደረጉ ይሰራሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ አብዛኛው ያንተ ስራ ፕሮጀክቱን መምራት ይሆናል። ቻይናዎች መጡ ሌሎችም መጡ የፕሮጀክት መምራት አቅማቸው ካልሆነ በስተቀር የሚጠቀሙት የሀገር ውስጥ ተቋራጩንና የሀገር ውስጥ ግብአትን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከውጭ ተቋራጮች ጋር የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለወይ?
ኢንጂነር አምኃ፡- የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደቱን በተመለከተ ወደ መንግስት ስንጮህ ቆይተናል። አሁንም እየጮህን ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ውሳኔ አላገኘም። የውጭ ኩባንያዎች መግባታቸው መልካም እድል ነው። ይህን አጋጣሚ እኛ መጠቀም እንድንችል ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው ብለን በተደጋጋሚ ጠይቀናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን።
ኢንጂነር አምኃ ስሜ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
ወንድወሰን መኮንን