
የኮተቤ አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ ላምሮት ጋሻው በአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት በፀሐፊነት ያገለግላሉ። መንግሥት በከተሞች አካባቢ የሚታየውን የህዝብ መጨናነቅ በመቀነስ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሰዎች ላልተወሰነ ጊዜ በቤታቸው ተወስነው እንዲቆዩ ያስተላለፈውን ትእዛዝ በመስማት እቤት መዋል ከጀመሩ ሳምንት ሆኗቸዋል። ትእዛዙ ተገቢ መሆኑንም ተናግረው፤ የቫይረሱን ስርጭት መከላከል እስከሚቻል ድረስ ሁሉም ሰው ትእዛዙን በማክበር በቤቱ ተወስኖ እንዲቆይም ይመክራሉ።
በቤት ውስጥ መቆይቱ ብቻውን ምንም ትርጉም የለውም የሚሉት ወይዘሮ ላምሮት፤ ቫይረሱን የመከላከሉ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ህብረተሰቡ በቤት ውስጥም በየእለቱ በተለይ የእጅ ንፅህናውን ሲጠብቅ ጭምር መሆኑን ያመለክታሉ። አንዳንድ ሰዎች ግን መንግሥት ያስተላለፈውን ትእዛዝ ወደጎን በመተው በቸልተኝነት ከቤታቸው ወጣ ገባ እንደሚሉ ጠቅሰው፤ ትእዛዙን መተላለፍ ጉዳቱ ለእነርሱም ለሌላውም ነው ይላሉ። ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በትእግስት በቤታቸው መቆየት እንዳለባቸው ነው ያስረዱት።
አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ከቤት እንደሚወጡ የሚናገሩት ወይዘሮ ላምሮት፤ወደ ውጭ ሲወጡና በተለይ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ እጃቸውን በሳሙና እንደሚታጠቡና በሳይኒታይዘር እንደሚያፀዱም ያብራራሉ። በተመሳሳይ ሌሎች ሰዎችም አስገዳጅ ሁኔታዎች ተፈጥረው ከቤት ውጪ ለመውጣት ፍላጎቱ ቢኖራቸው ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ እንደሚገባቸውም ያሳስባሉ። ሁሉም ይህንኑ ተግባር ቢፈፅም በአጭር ጊዜ ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት በመቀነስ ባለበት እንዲቆም ማድረግ እንደሚቻልም ያመለክታሉ።
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት መምህር አቶ በላይነህ ቦጋለ፣ ከሰሞኑ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት መጨናነቅን በመቀነስና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለማስቆም ሰዎች በቤታቸው ተወስነው እንዲቆዩ ያስተላለፈው ትእዛዝ ተገቢ መሆኑን ይገልፃሉ። ይህንኑ ተከትሎ እርሳቸውም በቤታቸው ተወስነው የሚጠበቅባቸውን ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ይናገራሉ።አንዳንድ ዝንጉና ቸልተኛ ሰዎችን ይህንን ትእዛዝ አክብረው ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ያስረዳሉ።
ራስን በቤት ብቻ በመወሰን ከኮሮና ቫይረስ ማምለጥ እንደማይቻል የሚናገሩት አቶ በላይነህ፣ በቤት ውስጥም የአብዛኛው ሰው አኗኗር በጥግግት በመሆኑ በተለይ ከእርስ በእርስ ንክኪ በመራቅ፣ እጆችን ሁሌም በሳሙና እና ሳኒታይዘር በማፅዳት ብሎም የበሽታው ምልክቶች ከታየባቸውም በጥንቃቄ በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እንደሚገባቸውም ያመለክታሉ።
የሥራ ሁኔታቸው ወደ ውጭ ለመውጣት የሚያስገድዳቸው ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውንም አቶ በላይነህ ጠቁመው፤ ከቤት ውጪ
በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ በተለይ በህክምና ባለሙያዎች እየተላለፉ ያሉ ምክሮችን በመከተል ራሳቸውንና ሌሎችንም ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ያሳስባሉ። ራሳቸውን በቤታቸው ለማቆየት የወሰኑ ሰዎችም ለሸመታና ለአንዳንድ ጉዳዮች ወደ ውጪ ሲወጡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና ወደ ቤታቸውም ሲመለሱ እጆቻቸውን በሳሙና በደምብ መታጠብና በሳኒታይዘር ማፅዳት እንዳለባቸውም ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ጤና ደምብ የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ፈይሳ ረጋሳ እንደሚሉት፤ የኮሮና ቫይረስ በአብዛኛው የሚተላለፈው በንክኪ ነው። በመሆኑም ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅና በተለይ ደግሞ ራስን በቤት ውስጥ ወስኖ ማቆየት ከቫይረሱ ራስን ለመከላከል ይረዳል። ይህም በጊዜ ሂደት የቫይረሱን ስርጭት ለማስቆም ያግዛል።
እንደ ዶክተር ፈይሳ ገለፃ፣ ራስን በቤት ውስጥ ወስኖ ማቆየት አንዱና ዋነኛው የቫይረሱ መከላከያ መንገድ በመሆኑ በመላው ዓለም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። በኢትዮጵያም መንግሥት ተማሪዎችና የመንግሥት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ለተወሰነ ጊዜ በቤታቸው ተወስነው እንዲቆዩ መመሪያ አውጥቷል። ይሁንና ህብረተሰቡ ይህን የመንግሥት መመሪያ ሰምቶ ተግባራዊ እያደረገ አይደለም።
‹‹በቻይና የቫይረሱን ስርጭት ማቆም የተቻለው ህብረተሰቡ ለተወሰነ ጊዜ በቤቱ ተወስኖ እንዲቆይ በመደረጉና ይህንኑ ትእዛዝ ተከትሎ በጥብቅ ዲሲፕሊን ተግባራዊ በማድረጉ ነው።›› የሚሉት ዶክተር ፈይሳ፣ ይህ የመከላከል ስልት ጠቃሚ በመሆኑ በኢትዮጵያም ህብረተሰቡ የመንግሥትን መመሪያ በመስማት ቫይረሱ ትልቅ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት አክብሮ ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚገባ ይናገራሉ። መንግሥትም ቫይረሱ ይበልጥ ከመስፋፋቱ በፊት መመሪያውን ለማስከበር ህጋዊ እርምጃዎችን አሁኑኑ መውሰድ እንደሚጠበቅበትም ነው ያስረዱት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
አስናቀ ፀጋዬ