አዲስ አበባ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በሚካሄድበት ስፍራ የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር በግድቡ ቦታ ላይ የቫይረሱ መመርመሪያ እንዲኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።ፕሮጀክቱ በሚካሄድበት ስፍራ መገኘት ያለባቸው ሰዎች ካሉም ምርመራ ተደርጎ እንዲገቡ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ፤የፕሮጀክቱ ሠራተኞችን ከኮረና ቫይረስ ስርጭት ለመታደግ እየተሰራ ሲሆን፣በቫይረሱ የሚጠረጠር ሠራተኛ ከተገኘም ማቆያ ለማዘጋጀት ከመንግሥት አካላት ውይይት እየተደረገ ነው።በግንባታው ላይ ለተሰማሩ ለሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገር ለመጡ ሠራተኞች ሲባል በሚካሄደው ጥንቃቄ በፕሮጀክቱ ቦታ የሚሄድ ማንም ሰው ጤንነቱ ይረጋገጣል።
በፕሮጀክቱ ሥፍራ የህክምና ባለሙያዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ኢንጅነሩ፣ በዋናነት የሚፈለጉት ግን በወረርሽኙ ዙሪያ ሰልጥነው እንክብካቤ የሚያደርጉ እና ምርመራ አድርገው መቆጣጠር የሚችሉ ባለሙያዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።ለእዚህም ከጤና
ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው ሲሉ ተናግረዋል። በወረርሽኙ የሚጠረጠር ሰው ካለ በክሊኒኩ የሚቆይበት ቦታ እንዲዘጋጅ የመመርመሪያ ኪቶችም እንዲኖሩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ የኮረና ቫይረስ ተፅዕኖን ለመግታትና ለተወሰነ ጊዜ ወደ ህዳሴው ግድብ የሚደረጉ ሠፊ ጉብኝቶች እንዲቆሙ መደረጉንም አስታውቀዋል። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሰዎች በፕሮጀክቱ ቦታ መገኘት ያለባቸው ከሆነም ምርመራ ተደርጎ እንደሚገቡ ተናግረዋል።ከፕሮጀክቱ ወደ አካባቢው ከተሞች በሚደረጉ ምልልሶች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ