•ለአንድ ዛፍ 960 ሺህ ብር
•ለአንድ ካሬ ሜትር መሬት 40 ሺህ ብር ተጠይቋል
አዲስ አበባ፡- በተጋነነ የካሳ ክፍያ ተመን እየተፈተነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። ለአንድ ዛፍ ካሳ እስከ 960 ሺህ ብር፤ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ደግሞ እስከ 40 ሺህ ብር እየተጠየቀ መሆኑን ጠቁሟል።
የባለስልጣኑ የመንገድ ወሰን ማስከበር ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ አየለ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ ተጨባጭነት የሌለው እጅግ በጣም የተጋነነ ዋጋ እየተጠየቀ ነው።
በቅርቡ በአፋር ክልል ከአንድ የቴምር ዛፍ በዓመት ስምንት ኩንታል ቴምር ይመረታል በሚል የአንድ ኩንታል ቴምር ዋጋ በስምንት ሺ ብር ተባዝቶ በአንድ ዓመት የአንዱ ዛፍ ዋጋ 64 ሺህ ብር መሆኑ እንደተገለጸለት ለአብነት ጠቅሰው፣በአዲሱ አዋጅ መሰረት የአንዱ ዛፍ ዋጋ በ15 ዓመት ተባዝቶ ሲሰላ ለአንድ ዛፍ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት እንደቀረበለት አመልክተዋል።
‹‹ለመንገድ ልማቱ 100 ዛፍ የሚነሳ ከሆነ ለዛፍ ብቻ ብዙ ሚሊዮኖችን ካሳ ለመክፈል እንገደዳለን።›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የተጋነነ የካሳ ክፍያ ተመኑ ምድር ላይ ተሰምቶ የማያውቅ ምርታማነት እየተጠቀሰ እንደሚጠየቅ ጭምር አብራርተዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ቴምር አምራች አገር አይደለችም። ከፍተኛ ቴምር አምራች የሚባሉት እስራኤል እና ሳውድ አረቢያ እንኳ ከአንድ ዛፍ የሚያገኙት በዓመት 180 ኪሎ ግራም ብቻ ነው›› ያሉት አቶ ደረጄ፤ ያለአግባብ ሰዎችን ለመጥቀም በሚል የግብርና ምርታማነትን መጨመር እና ዋጋውን ማጋነን በተደጋጋሚ እንደሚስተዋል ገልፀዋል። ከአዲስ አበባ እጅግ በጣም የራቁ ክልሎችም አዲስ አበባ ላይ የማይጠየቅ ለአንድ ካሬ ሜትር መሬት እስከ 40 ሺህ ብር እየጠየቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ከአንድ መሬት ላይ የሚገኘው ሰሊጥ ምናልባት 30 ኩንታል ከሆነ 120 ኩንታል ብለው የሚያስመዘግቡ አሉ፤ባለስልጣኑ የግብርና ቢሮዎች እና የምርምር ጣቢያዎች ድረስ በመሄድ ‹‹በአገር ደረጃ ምርቱ ምን ያህል ነው?››ብሎ ለማጣራት ሲሞከር የሚፈጀው ጊዜ እና ጉልበት፤ በአንድ ነጠላ ዋጋ ላይ ለመደራደር የሚፈጀው ጊዜ ባለስልጣኑን እና የመንገድ ልማቱን እንዲሁም መንገዱ ቢሰራ የልማቱ ተጠቃሚ ሊሆን ይችል የነበረውን ማህበረሰብ እጅግ እየጎዳው ይገኛል።
ተመኑ የሚዘጋጀው በወረዳ እና በከተማ አስተዳደሮች በሚመረጡ ኮሚቴዎች መሆኑን አስታውሰው፤ የካሳ ክፍያው ያለአግባብ መጋነን ለግለሰቦች በሚከፈል ካሳ ላይ ብቻ ሳይሆን ለክልል፣ ለወረዳዎች እና ለከተማ መስተዳድሮች ለራሳቸው ለተቋማት በሚከፈል ካሳ ላይም እንደሚስተዋል አብራርተዋል።
አቶ ደረጀ ፣ መሬት ውስጥ ለተቀበረ ንብረት እየቀረበ ያለው ግምት እጅግ በጣም የተጋነነ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የውሃ መስመር ለማስነሳት የወረዳ የውሃ ተቋማት 30 ሚሊዮን ብር መጠየቃቸውን ለአብነት ጠቅሰው፣‹‹ግምቱ ተጋኗል›› ሲባል ደግሞ ካሳው ወደ 20 ሚሊዮን ብር እንደወረደም አብራርተዋል። ክርክሩ ሲቀጥል ወደ 7 ሚሊዮን እየቀነሰ የከብት ገበያ ግብይት በሚመስል መልኩ ‹‹30 ሚሊዮን ብር ለጠየቁበት ካሳ እሺ 5 ሚሊዮን ይከፈለን።›› እንደሚሉ አብራርተዋል። ይህ የሚያሳየው ግምቱ ተጨባጭ አለመሆኑን እንደሆነም ጠቅሰው፣ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የያዙት ገንዘብ የአገር ገንዘብ ነው ብሎ ካለማሰብ እንደሚመነጭም አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ደረጃ ገለጻ፤መንገድ የሚሰራው ለአካባቢው ህዝብና ለወረዳው እንዲሁም ለከተማ አስተዳደሩ ነው። እነዚህ አካላት ይህን ተረድተው ለህዝቡ ከማስረዳት ይልቅ እነርሱም የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው በሚያሳዝን ሁኔታ ተቋሙን እየፈተኑት ናቸው።
በእንጥልጥል ያሉትን፤ ለማለቅ ጥቂት የቀራቸውን እና ገና በግንባታ ላይ የሚገኙትን 150 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 346 የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
ምህረት ሞገስ