እኤአ በመጋቢት 1980 የእግር ኳስ ሀገር በሆነችው ብራዚል እግር ኳስ ወዳድ ከሆኑ ቤተሰቦች በደቡብ ብራዚል ፖርት ኤሌግሪ ተወለደ። ስሙ እንደሚያመለክተው ጠረፍ ላይ የምትገኝ አነስተኛ መንደር ነች። ይህቺ መንደር በጣም ድሃ ሕዝቦች የሚኖሩባት ናት። ቤቶቹ የተጎሳቆሉ እንዲሁም ኑሮም ከእጅ ወደ አፍ የሆነባት መንደር፡፡ በዚህች ጎስቋላ መንደር በአንድ ወቅት ወደ ዓለም እግር ኳስ ብቅ ብሎ በአጭር ጊዜ ቆይታው ዛሬም ድረስ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ልብ ውስጥ እየኖረ የሚገኘው ሮናልዲንሆ በጣም ታታሪ ቢሆንም በጣም ድሆች ከነበሩ ቤተሰቦች ተገኘ። እናቱ ዶና ሚግዌሊና ትባላለች። የቀድሞ ሥራዋ የሽያጭ ባለሙያ ስትሆን በሂደት ነርስ ለመሆን በቅታለች፡፡
አባቱ ጃኦ ለኩርዜሮ የሚጫወት ጎበዝ ኳስ ተጫዋች ነበር። ነገር ግን ዕድሜው ሲገፋና እንደድሮው ኳስ መምታት ሲያቅተው ጫማውን ሰቀለ። የድሮ ኳስ ተጫዋቾች እንዳሁኖቹ የደላቸው አልነበሩምና ደመወዛቸውም ትንሽ ስለነበር ኳስ ሲያቆሙ ኑሮን ለማሸነፍ ሌላ ሥራ መስራት ግድ ይላቸዋል። ስለዚህ ጃኦም ኳስ እንዳቆሙ ወዲያው እዚያው ወደብ ላይ የመርከብ ሠራተኛ ሆኑ። ሁለቱም በየፊናቸው እንዲህ ቢታገሉም ኑሮን ግን ማሸነፍ አልቻሉም፣ እንዲያውም እየመራቸው መጣ። ጃኦና ዶና 3 ልጆች ያላቸው ሲሆን የመጀመሪያው ልጅ ሮቤርቶ ይባላል፣ ኳስ ተጫዋችም ነበር። ሁለተኛዋ ዴሲ ትባላለች:: ሦስተኛው ልጃቸው በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ልናስታውሰው የወደድነው ፈገግታ ከፊቱ የማይለየው መልከ ጥፉው ነገር ግን ጥበበኛው «ትንሹ ሮናልዶ» ሮናልዲንሆ ጎቾ ነው።
ሮናልዲንሆ ዕድሜው 8 ሲደርስ አባቱ ጃኦ በድንገተኛ የልብ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሌላ ከባድ ፈተና ለድሆቹ የሮናልዲንሆ ቤተሰቦች። አሁን እቤቱን የማስተዳደር ብቸኛዋ ኃላፊነት ነርሷ እናቱ ላይ ወደቀ። ሆኖም ብዙም ሳይቆዩ በዚያው ዓመት የቤቱ ትልቅ ልጅ የሮናልዲንሆ ታላቅና ብቸኛው ወንድሙ የሆነው ሮቤርቶ ግሪሚዩ ከተባለው ክለብ ጋር ኮንትራት ተፈራረመ። በሱም ጥሩ የሚባል ገንዘብ አገኘ። ቤተሰቡም ከተጎሳቆለ ቤት ወጥተው ወደ ተሻለ ቤት ገቡ። በዚህ ጊዜ ነበር ትንሹ ሮናልዶ አዕምሮ ውስጥ አንድ ጥያቄ መመላለስ የጀመረው፡፡«ኳስ ገንዘብ የሚያስገኝ ከሆነ ለምን ኳስ ተጫዋች ሆኜ ቤተሰቤን አልረዳም?» የሚል። ጥበብ ልጇን ጠራች:: ሮናልዲንሆም ወደ ተፈጠረለት እግር ኳስ ኑሮን ለማሸነፍ በሚል ምክንያት ገባ።
ትንሹ ሮናልዶ ኳስን በ8 ዓመቱ ኳስ ከሰፈሩ ልጆች ጋር በፖርት አሌግሪ የባህር ዳርቻ እንደፈለገ ያዛት ጀመር። ሜዳው ላይ በዕድሜው አነስተኛው ልጅ እሱ ነበር። ነገር ግን በችሎታው የሰውን ዓይን በቀላሉ መማረክ የሚችልና ብዙዎች ከዓይን ያውጣህ ይሉት ገቡ። እዚህም ሜዳ ላይ ነው ሮናልዲንሆ የሚለውን ስም ያገኘው። ዛሬ ላይ በመላው ዓለም መለያ መጠሪያው ይሁን እንጂ ብራዚላውያን «ሮናልዲንሆ» በሚለው ስም አያውቁትም ነበር። ትክክለኛው ሮናልዲንሆ ትልቁ ሮናልዶ ወይም «ኤልፌኖሜኖ» በሚለው ቅፅል የሚታወቀው ነው። ብራዚላውያን ስመ ረጃጅሞች ቢሆኑም አጠር አድርገው ስያሜ በመፍጠርና በማቆላመጥ ጣጣ አይወዱም። ባጭሩ መጥራት ይቀናቸዋል። የቀድሞ መሪያቸውን «ሉላ» ይሏቸዋል። ባለብዙ ጅራቱ የባህር እንሰሳ «ስኩዊድ» የሚል ትርጉም ይኑረው እንጂ ሉዊዝ ኢግናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ እያሉ ጊዜ ማባከን አይፈልጉም።
ሮናልዶ ሉዊዝ ናዛሪዮ ደ ሊማ ከማለት ይልቅ «ሮናልዶ» የሚቀላቸውም ለዚህ ነው። ግን ሁለት ድንቅ ሮናልዶች በአንድ ዘመን ተገኙና ብራዚላውያን ግራ ገባቸው። ያ ታላቅ ግብ አዳኝ ‹ሮናልዲንሆ› ተብሎ በሚጠራበት አገር ሌላ ‹ሮናልዲንሆ› የተባለ አስገራሚ ተጫዋች በእግር ኳስ ኮከቦች መፍለቂያ አገር ብቅ አለ። ትርጓሜው ‹ትንሹ ሮናልድ› እንደማለት ነው። ኤልፌኖሜኖ ‹ትንሹ› መባሉ አብቅቶ በዝናም፣ በክብርም ሲያድግ ብራዚላውያን ወደ ‹ሮናልዶነት› አሳደጉት።
ሮናልዲንሆ እስከ 13 ዓመቱ ከሰፈሩ በዘለለ ለትልልቅ ክለቦችም ሆነ ለታዳጊ መጫወት አልቻለም። ውሎው የባህርዳርቻ ነበር። በ13 ዓመቱ ግን አንድ ነገር ተከሰተ፣ የወንድሙ ክለብ የሆነው የግሪሚዩ መልማዮች ጎበዝ ተጫዋቾችን ሊመለምሉ የነ ሮናልዲንሆ ሰፈር ደረሱ። ለምልመላው ይረዳቸው ዘንድም ተጫዋቾችን ለሁለት ከፍለው ግጥሚያ እንዲያደርጉ አዘዙ። ክፍፍሉም ፍትሃዊ እንዲሆን በሰፈር አደረጉት። የላይኛው ሰፈር ልጆችና የታችኛው ሰፈር ልጆች። ጨዋታው ተጀመረ። ልክ እንደተጀመረ ሮናልዲንሆ ተከላካዮችን አተራምሶ አስደናቂ ጎል አስቆጠረ። ከደቂቃዎች በኋላም የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ሌላ ጎል ደገመ። ውጤቱም 23 ለ 0 ነበር። የሚገርመው 23ቱንም ጎሎች ያስቆጠረው አንድ ልጅ ነው። ሮናልዲንሆ ጎቾ ዲ አሲስ ሞሬራ!!
መልማዮቹ ወደ ካምፓቸው ሲመለሱ አንድ ሳቂታ ልጅ አስከትለው ተመለሱ። ሮናልዲንሆም ከወንድሙ ጋር አንድ ክለብ ውስጥ የመጫወት ዕድል አገኘ። ሮናልዲንሆ ለታዳጊዎቹ ሮቤርቶ ደግሞ ለዋናው ቡድን፡፡ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ወንድሙ ሮቤርቶ በደረሰበት ጉዳት ከኳስ ተሰናበተ። ሮናልዲንሆ ወንድሙ ባጋጠመው ነገር ቢያዝንም ኳስ ከመጫወት ግን ለደቂቃም አልቦዘነም። በግሪሚዩ የእግር ኳስ ካምፕ ውስጥ ኳስን ጓደኛው አደረጋት። ቀኑን ሙሉ ውሎው ከኳስ ጋር ሆነ። ከጓደኞቹ ቀድሞ ልምምድ ቦታ መገኘት እንዲሁም ከሁሉም በኋላ መውጣት ባህሪው ሆነ።
ይህ ታታሪነቱ ወደ ታላላቅ የዓለማችን ክለቦች አምርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በእግር ኳሱ ዓለም እስከዛሬም የማይዘነጉ ተዓምሮችን መፍጠር ቢያስችለውም ዝናና ገንዘብ ይዞት የሚመጣውን ጣጣ እንዲቋቋም አላደረገውም፡፡ ውሎና አዳሩ በየጭፈራ ቤቱ ሆነ፡፡ አብዝቶ መዝናናት ከድህነት ሕይወት ያስመለጠውን ኳስ አስረሳው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ግን ዓለምን በእግር ኳስ ጥበቡ ማስደመም ለእሱ ቀላል ነበር፡፡
በታላቁ ኤልክላሲኮ ታሪክም ከማራዶና በኋላ በተቃራኒ ደጋፊዎች ሜዳ የተጨበጨበለት ተጫዋች እስከመሆን ደረሰ፡፡ በኳሱ ተዝናንቶበታል፣ ተመልካቹንም አዝናንቶበታል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ከአምስት ዓመታት በላይ እንዲዘልቅ አብዝቶ መዝናናቱ አልፈቀደለትም፡፡ ብዙዎች ጥበቡን ሳይጠግቡ የእግር ኳስ ሕይወቱ በአጭሩ ሊቀጭ ችሏል፡፡ ያም ሆኖ በትንሽ ዓመታት የሰራው ተዓምር አሁን ላይ በመጫወት ላይ የሚገኝ የትኛውም ተጫዋች ያላሳካውን ዓለም ዋንጫን፣ ባሎንዶርንና ቻምፒየንስ ሊግን ያሸነፈ ተጫዋች አድርጎታል፡፡ አሁን ላይ ግን የጎቾ ሕይወት በሌላ የታሪክ መፅሐፍ ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ እየተገለፅ ይገኛል። በፓራጓይ ከተጭበረበረ የፓስፖርት ሰነድ ጋር በተያያዘ እስር ቤት ውስጥ ሆና 40ኛ ዓመቱን ባሳለፍነው ሳምንት እንዲያከብር አስገድዶታል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም
ቦጋለ አበበ