
– ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶች ፊርማ ተከናውኗል
አዲስ አበባ፡- በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ። ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሰባት የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶች ፊርማ ተከናውኗል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በፊርማው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ የመንግሥትና የግል አጋርነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊና ተቋማዊ ማሕቀፍ መዘርጋት ተችሏል። በዚህ ሂደት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ።
የመንግሥትና የግል አጋርነት የልማት ፋይናንስ አንድ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግሉን ዘርፍ የፋይናንስ አቅም እና የመንግሥትን አጋርነት በማቀናጀት በተለምዶ በመንግሥት ብቻ ወይም በግሉ ዘርፍ ብቻ ሲሠሩ የነበሩ የልማት ሥራዎችን በማቀናጀት የሚከናወን ነው ብለዋል።
በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚከናወኑ ሰባት ፕሮጀክቶች ልማትን ከማፋጠን ባለፈ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም እያደገ መምጣቱን ማሳያ መሆናቸውንም አቶ አሕመድ ጨምረው ገልጸዋል።
ትብብሩ በገንዘብ ሚኒስቴር አስተባባሪነትና በሌሎችም ተቋማት በጋራ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ የድርድር ሂደት ያሉ መኖራቸውን ጠቁመው፤ ተፈርመውም በተለያዩ የዝግጅትና የትግበራ ሂደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በስምምነቱ የተካተቱት ሰባት ፕሮጀክቶች ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳላቸው ጠቁመው፤ አራት የቤት ልማት ፕሮጀክቶች፣ ሁለት የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክቶችም እንዲሁም አንድ የተቀናጀ የምርመራ አገልግሎት ማዕከልን የሚያጠቃልል መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሮጀክቶቹ በየዘርፉ ያለውን አቅም በማሳደግ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ትልቅ ሚና እንዳላቸውም አብራርተዋል።
ስምምነቱን በመንግሥት እና ከኦቪድ ግሩፕ፣ ከአይ ሲ ኢ ቤት ልማትና ኮንስትራክሽን፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ከሰርባ ላንሴት አፍሪካ፣ ከኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ እና ከፓዮኒር ዲያግኖስቲክ ሴንተር እንዲሁም ከቦስተን ፓርትነር ጋር ተፈርሟል።
የመንግሥት እና የግል አጋርነት ማዕቀፍ መንግሥት ማቅረብ የነበረበትን የመሠረተ ልማት እና የሕዝብ አገልግሎት ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ በዘርፉ የተሠማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ማድረግ ሲሆን፤ በዚህም በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት፣ በጤና፣ በቤቶች፣ በሎጅስቲክስ እና በቱሪዝም ዘርፎች ለመንግሥት እና ለግል አጋርነት ተስማሚ የሆኑ 34 ፕሮጀክቶች ተለይተው በተለያዩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም