
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ያስገባት መሠረታዊ ችግር ካልተወገደ ጦርነቱን እንደማታቆም ተናግረዋል፡፡
ፑቲን ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ ሞስኮ ከኪዬቭ ጋር ወደ ጦርነት ያስገቧት መሠረታዊ ምክንያቶች ሳይወገዱ ጦርነቱ እንደማይቆም ነግረዋቸዋል። የፑቲም የውጭ ጉዳዮች ፖሊሲ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ ዝግጁ መሆናቸውንና የጦርነቱ መሠረታዊ
መነሻ እልባት ሳያገኝ ጦርነቱ እንደማይቆም ለትራምፕ ነግረዋቸዋል። ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርጋቸውን ውይይቶች ለመቀጠል ፈቃደኛ ብትሆንም፣ ማንኛውም የሰላም ድርድር መደረግ ያለበት ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው በሩሲያና ዩክሬን መካከል እንደሆነ ኡሻኮቭ ተናግረዋል።
ትራምፕ ከስልክ ውይይቱ በኋላ፣ ፑቲን ጦርነት ለማቆም ዝግጁ አለመሆናቸው እንዳሳዘናቸው እና ጦርነቱን ለማቆም ምንም አይነት መሻሻል እንደሌለ ተናግረዋል። ‹‹ዛሬ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ባደረግኩት ውይይት በጣም አዝኛለሁ። ጦርነቱን ለማቆም የሚፈልግ አይመስለኝም። ያ ደግሞ በጣም መጥፎ ነው›› ብለዋል። ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥር ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ከፑቲን ጋር የስልክ ውይይት ሲያደርጉ የሰሞኑ ስድስተኛቸው ነው።
ሩሲያ ከሦስት ዓመታት በፊት ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት የገባችው ጎረቤቷ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ልትቀላቀል ነው በሚል ምክንያት ነው። ሩሲያ፤ ዩክሬን አፍንጫዬ ስር ሆና ኔቶን ተቀላቅላ ልትወጋኝ ነው የሚል ወቀሳዋን ስታሰማ፣ ዩክሬንና ምዕራባውያን አጋሮቿ ግን ይህን የሩሲያን ክስ አይቀበሉትም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ከፈፀመችው ጥቃት ሁሉ ከፍተኛ ነው የተባለ የአየር ላይ ጥቃት ፈጽማለች። በዚህ ጥቃት ከ500 በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሊስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ተጠቅማለች።
ፑቲንና ትራምፕ በስልክ ከተነጋገሩ ከሰዓታት በኋላ ደግሞ ሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በኪዬቭ ላይ ጥቃት መፈፀሟን የዩክሬን ባለሥልጣናት ገልፀዋል። ለጥቃቱ ሩሲያ 550 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና 11 ሚሳኤሎችን መተኮሷን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ፣ በዋና ከተማዋ የተፈፀመውን ጥቃት ‹‹ከክፉዎቹ ምሽቶች መካከል አንዱ›› በማለት ጥቃቱን አውግዘዋል። ‹‹በኪዬቭ ፍጹም አሰቃቂ እና እንቅልፍ አልባ ሌሊት ነበር። እስካሁን ከነበሩት አስከፊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ነበር። ፑቲን ሆን ብለው ነው የሚያደርጉት። ለዩናይትድ ስቴትስ እና ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ ላቀረቡ ሁሉ ያላቸውን ንቀት በግልፅ ያሳያል ሞስኮ ሳይዘገይ በጣም ከባድ በሆነ ማዕቀብ መቀጣት አለባት›› ብለዋል።
በሌላ በኩል አሜሪካ ለዩክሬን ከምትሰጣቸው የጦር መሣሪያዎች መካከል አንዳንዶቹን ማቋረጧን አስታውቃለች። የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አና ኬሊ ‹‹ውሳኔው ላይ የተደረሰው የመከላከያ ሚኒስቴር አሜሪካ ለሌሎች ሀገራት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ መገምገሙን ተከትሎ የአሜሪካን ጥቅም ለማስቀደም ነው›› ብለዋል።
አንድ የፔንታጎን ከፍተኛ ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ ‹‹የመከላከያ ሚኒስቴር ለዩክሬን የሚያደርገውን ወታደራዊ ርዳታ ለመቀጠል ለፕሬዚዳንቱ ጠንካራ አማራጮች መስጠቱን ቀጥሏል። ሚኒስቴሩ ይህንን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ አካሄዱን በጥብቅ እየፈተሸ እና እያስተካከለ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአሜሪካ ኃይሎች ለሌሎች መከላከሎች ቅድሚያ ሰጥተው ዝግጁ የሚሆኑበትንም ሁኔታ በማስጠበቅ ላይ ነው›› በማለት ተናግረዋል።
ርምጃው የተወሰደው የአሜሪካ ወታደራዊ መሣሪያዎች ክምችት እየቀነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ መሆኑን ‹‹ሲቢኤስ ኒውስ›› (CBS News) ዘግቧል። ይህ ውሳኔ የተላለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ቭላድሚር ዘሌንስኪ ጋር ባለፈው ሳምንት በኔዘርላንድስ በተካሄደው የ‹ኔቶ› ጉባኤ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነው። በወቅቱ ትራምፕ አሜሪካ ተጨማሪ ፀረ ሚሳዔሎችን ለዩክሬን ትሰጥ እንደሆን ተጠይቀው ‹‹አንዳንዶቹን ማቅረብ እንችል እንደሆነ የምናየው ይሆናል›› ብለው ነበር። ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የመጣው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት ነው።
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም