
የሰኔ እና የመስከረም ወር ከትምህርት ጋር በጥብቅ ይቆራኛሉ። መስከረም የትምህርት መጀመሪያ ነው፤ ሰኔ ደግሞ መጨረሻ። በመስከረም ተማሪዎች ለመገናኘት ይነፋፈቃሉ፤ በሰኔ ደግሞ ከትምህርት እፎይ ብለው ትንሽ ዘና ለማለት የሚጓጓበት ነው። የሰኔ ወር ሀገር አቀፍ ፈተና ከሚሰጥባቸው ክፍሎች በስተቀር ደከም ያለ ተማሪ ጉዱን የሚያውቅበት ነው። አልፏል አላለፈም የሚለውን ለማወቅ ማለት ነው። ጎበዝ ተማሪም የዓመቱን የደረጃ ውጤት ለማወቅ በጉጉት የሚጠብቀው ነው። ለዚህም ነው ሰኔ ሠላሳ የተማሪ አበሳ ይባል ነበር።
በዚሁ እግረ መንገድ ስለትምህርት እናውራ። የትምህርት ጉዳይ የዘወትር አጀንዳ መሆን ቢገባውም በሰኔ እና በመስከረም ደግሞ የበለጠ ይደጋገማል። ሰኔ የልጆቹ ውጤት የሚታወቅበት ስለሆነ ማለት ነው።
በዚህ ዘመን ያለውን የተማሪዎች ሁኔታ በተመለከተ ከመምህራን ጓደኞቼ ብዙ ትዝብቶችን እሰማለሁ፤ ራሳቸውንም እታዘባቸዋለሁ። መምህር በዚህ ልክ ግዴለሽ መሆን አለበት? ብዬ እገረማለሁ፤ ጓደኞቼንም በቀልድም በቁም ነገርም መምህር እንዲህ ነው ማድረግ ያለበት እያልኩ እነግራቸዋለሁ። እነርሱ የሚነግሩኝ ግን ምን ያህል አሰልቺ እንደሆነ ነው። በተለይም አንዳንድ ተማሪዎች ተስፋ አስቆራጭ መሆናቸውን ነው።
አንድ መምህር ጓደኛዬ የሚነግረኝ ነገር የተማሪዎችን ጎበዝ አለመሆን ነበር። እኔም የቅርብ ጓደኛዬ ስለሆነ ‹‹መምህሩ ጎበዝ ሲሆን ነው ተማሪ ጎበዝ የሚሆነው›› እያልኩ በቀልድም በቁም ነገርም እነግረዋለሁ። እሱም ‹‹ስላላየኸው ነው የምትፈርድ! ምንም ማንበብና መጻፍ የማይችልን ተማሪ ከየት ጀምሮ ነው ጎበዝ ማድረግ የሚቻለው?›› እያለ ይሞግተኛል (እሱ የሚያስተምረው ሁለተኛ ደረጃ ነው)። ይሄም ከታች ክፍል ያሉ መምህራን ችግር ነው እየተባባልን እንከራከራለን። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የማያነቡ ተማሪዎች አጋጥመውታል ማለት ነው።
አንዳንዴ የሚነግረኝ ግን ከዚህም ከበድ ያለ ይሆናል። ‹‹ተማሪዎችን ‹ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?› ብትላቸው፤ እንደ ድሮው ‹ዶክተር፣ ኢንጂነር..› የሚሉ እንዳይመስልህ! ምኞታቸው፤ ሴቶች ወደ ዓረብ ሀገር፣ ወንዶችም ወደ ወርቅ ቁፋሮ ነው የሚሉህ›› አለኝ። ምኞታቸው ብር የሚያገኙበትን አጋጣሚ ማመቻቸት ነው። ትምህርት የማይማሩ ጓደኞቻቸው ሄደው የመጡበት አካባቢ መሄድ ነው ፍላጎታቸው። ወላጆችም ገንዘብ ካመጡልን በማለት ብዙም አይቆጧቸውም፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ የሚፈቅዱላቸውና ሂዱ የሚሏቸውም አሉ። በብዛት የሚማሩት ከ5ኛ ክፍል በታች ያሉት ናቸው። እነሱም ዕድሜያቸው ገና ለመሄድ ስላልደረሰ ነው። ይህ እንግዲህ በገጠሩ አካባቢ ነው።
ይሄ የመሄድ ፍላጎት ገና በልባቸው ሲጠነሰስ ለትምህርቱ ትኩረት አይሰጡም። መሄድ ሳይችሉ ቢቀሩ እንኳን ፈተና አያልፉም፤ ምክንያቱም ቀልባቸው ሌላ ነበር። እንኳን ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ የክፍል ውስጥ ፈተና እንኳን የሚያመጡት ውጤት ዝቅተኛ ነው።
ከዚህም በላይ አሳዛኙ ደግሞ የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የመምህራኑም ተስፋ መቁረጥ ነው። ‹‹ምክንያቱ ምን ይሆን›› ያልኩት ጓደኛዬ እንደሚለው የብዙ መምህራ ቅሬታ ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር፣ ከሥራ መሰላቸት ጋር የመጣ ነው። የሥራ መሰላቸቱንም ያመጣው ከኑሮ ውድነት ጋር የሚከፈለን ክፍያ አይመጣጠንም በሚል ቅሬታ ነው።
ይሄ ነገር ትውልድ ገደላ ነው። መምህራን በኑሮ ውድነት ላይ ያላቸውን ቅሬታ የሚገልጹት ተማሪ ላይ ከሆነ ይሄ የእውቀት አባትነት ሳይሆን ጨለማን ማውረስ ነው። እርግጥ ነው የሚከፈለው ክፍያ በቂ ነው ማለት አይደለም። በቂ አለመሆኑ ግን የተማሪዎችና የወላጆች ችግር አይደለም፤ ችግሩን መነጋገር ከመንግሥት ጋር ነው። እልሃቸውን ተማሪ ላይ አይደለም መወጣት ያለባቸው። የጠየቁት ጥያቄ ካልተመለሰ ወይም በውይይት መፍትሔ ላይ ካልደረሱ ሥራውን መልቀቅና የተሻለ ካለ መፈለግ ነው!
በነገራችን ላይ ይሄ ችግር የሚታየው መምህራን ላይ ብቻ አይደለም። በብዙ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቀጣሪ ሠራተኞች ላይ የሚታይ ነው። የግል ላይ ቢዝረከረክ በነገታው እንደሚባረር ስለሚያውቀው ማንም አይዝረከረክም። የመንግሥት ተቋማት ላይ ግን ይሄ ነገር ጎልቶ ይታያል። ብዙ ጊዜ የታዘብኩትን ነገር ልንገራችሁ።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሾፌር ይቀጥራሉ። ሹፌሮችም ሠራተኞችን ወደ ሥራ ቦታ ይወስዳሉ። ይህ ሲሆን ታዲያ ሾፌሮች በለቅሶና በጭቅጭቅ ነው። ከመሥሪያ ቤት ሲወጡ አለቃቸው ያዘዛቸውን ‹‹እሺ›› ብለው ይወጣሉ። ከዚያ በኋላ ከሠራተኛው ጋር ጭቅጭቅ ይፈጥራሉ። ‹‹እዚህ ቦታ አልሄድም፣ በዚህም አልሄድም፣ እዚህ አልጠብቅህም›› ይላሉ። ይባስ ብሎ በፉከራ ‹‹ማን አባቱ ነው የሚያዝዘኝ፣ እስኪ ማን እንዲህ አድርግ እንደሚለኝ አያለሁ!›› እያሉ ይፎክራሉ!
የቅሬታቸውን ምክንያት ሲናገሩም፤ ‹‹በዚህ ደመወዝ አልሠራም! አንተ ይህን ያህል እየተከፈለህ እኔ ልፈጋልህ ነው!›› እና ታዲያ ሥራውን ለቆ የተሻለ ካለ መፈለግ ነዋ!
ወደ ትምህርት ቤት እንመለስ!
የተማሪዎች ተስፋ መቁረጥ የመምህራን ችግር ብቻም አይደለም። ይሄ የወላጆችም ችግር ነው። አለፍ ሲልም የትምህርት ተገቢውን ዋጋ አለማግኘት ነው። ከእነርሱ በፊት የተማሩ ሲያማርሩ ከሰሙ ከታች ያሉት ተስፋ ይቆርጣሉ። ተምሮ ሥራ የለም፤ በደመወዝ መኖር ከባድ ነው፣ ሥርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል እውቀት ላይ ያተኮረ አይደለም… የሚሉ ቅሬታዎች ተደጋግመው የሚሰሙ ናቸው። ታዲያ ይሄን እየሰሙ ይሆን?
የትምህርት ነገር ገና ብዙ ያልተስተካከለ ነገር አለው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ዲግሪ ያለው እየሆነ ነው። ይሄ ጥሩ ነገር ነው። የመምህራን ብቃትና ቆራጥ ውሳኔም አንዱ አጠያያቂ ነገር ስለነበር ማለት ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ከ10ኛ እና ከ12ኛ ክፍል ውጤት ያልመጣለት ተማሪ ነበር መምህር የሚሆነው! ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀውም ቢሆን ብዙም የተሻለ አይደለም። ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ ትምህርት ክፍል የሚመደቡት ከ12ኛ ክፍል ዝቅተኛ ውጤት ያመጡት ናቸው። እነዚህ ወሳኝ እና ለሁሉም የትምህርት ክፍል መሠረት የሆኑት የትምህርት አይነቶች ‹‹ኮምፒቴሽናል ሳይንስ›› በሚለው ውስጥ ነበሩ። ይሄ ዘርፍ ማለፊያ ነጥቡን ብቻ ያመጡ ተማሪዎች ሳይመርጡት የሚመደቡበት ነው። እንደ ሕክምና፣ ምሕንድስና፣ ጤና፣ መሬት አስተዳደር፣ የመሳሰሉ የትምህርት ክፍሎችን መርጠው የሞሉ ተማሪዎች ያንን ካላገኙ የሚመደቡት ‹‹ኮምፒቴሽናል›› እና ‹‹አዘር ሳይንስ›› የሚባለው ውስጥ ነበር። መምህር የሚወጣው ደግሞ ከዚህ ዘርፍ ውስጥ ነው። አሁን አሁን ግን እነዚህ ነገሮች እየተስተካከሉ ነው፤ መምህር ለመሆን ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ትኩረት እየተሰጠው ነው።
ለማንኛውም የመምህራንን እና የሥርዓተ ትምህርቱን ጉዳይ ለሚመለከተው አካል እንተወውና ተማሪዎችና ወላጆች ግን ክረምቱን እረፍት ነው ብለው ሙሉ በሙሉ ከትምህርት እንዳይርቁ። ተማሪዎች የሚቀጥለውን ዓመት ክፍል በክረምት ማጥናት እንዲጀምሩ ወላጆች መንገር አለባቸው። ለምሳሌ ከ5ኛ ወደ 6ኛ ክፍል የተዛወረ ተማሪ የ6ኛ ክፍል ማንበብ እንዲጀምር ማለት ነው። ወላጆች ደግሞ ለትምህርት አጋዥ የሆኑ መጽሐፍትን ሊገዙላቸው ይገባል፤ ምክንያቱም የሚፈልጉት ደረጃ ላይ የሚደርሱት ዘመኑ የሚጠይቀውን ግብዓት ሲያገኙ ነው። ስለዚህ ክረምት የእረፍት ብቻ ሳይሆን የንባብም ወቅት ይሁን!
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም