“ኢትዮጵያ በእኛ ጊዜ ልመና ታቆማለች፤ ይሄ ጥርጥር የለውም” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈፃፀም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ያታወሳል። የምክር ቤቱ አባላት በተለይም ላነሷቸው ኢኮኖሚ ነክ ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሽ እና ማብራሪያዎች የመጀመሪያ ክፍል በዛሬው ዕትማችን ይዘን ቀርበናል።

ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ ሀገር በቀሉን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም ዘርፍ መልካም ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ። በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአኅጉር ደረጃ ምሳሌ የሚሆን እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ገንብታ ማጠናቀቅ ጀምራለች። አዳዲስ በግብርና፤ በቱሪዝም፤ በማዕድን፤ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፎች የተጀመሩ ኢንሼቲቮች ውጤት እያመጡ ይገኛሉ። ነገር ግን የኢኮኖሚ እድገቱ ላይ የተለያዩ አካላት ብዙ አሉታዊ መረጃዎች እያሰራጩ ይገኛሉ። ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ አፈፃፀም ከቁልፍ የኢኮኖሚ እድገት አመላካቾች አንጻር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ቢሰጡ?

በሀገራችን የተጀመሩ መልካም ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መላው ኢትዮጵያውያን ይመኛሉ፤ ይደግፋሉ በተለያየ መንገድም በየአካባቢያችን የድጋፍ ሰልፎችም እያደረጉ ይገኛሉና ከዚህ ጋር ተያይዞ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ማለትም ወረዳ፤ ዞን፤ ከተማ አስተዳደር እና አንዳንድ ቢሮዎች ድረስ፤ ሙስና እና ብልሹ አሠራር ሕዝቡን እያማረሩ እንደሚገኙ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይቀርባሉ። ሙስና የሰላማችን እና የልማታችን ጠር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፤ የተገኙ ውጤቶች እና በቀጣይ ትኩረት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ቢሰጥ?

ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ስኬታማ እንዲሆን የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢሰጥ ?

ኢኮኖሚያችን እድገት እያስመዘገበ ቢሆንም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በኑሮ ውድነት፤ ዋጋ ግሽበት እና ሥራ አጥነት ምክንያቶች ጫና ውስጥ ናቸው። መንግሥት በአንድ በኩል የዋጋ ግሽበት እድገት እየቀነሰ እንዳለ ይገልጻል። በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ ዘንድ ግን አሁንም ከፍተኛ ጫና እንዳለ ይነሳል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሪፖርቱ የተገለፀው እና በመሬት ላይ ያለው እውነታ እንዴት ይታረቃል? የኑሮ ውድነት፤ ዋጋ ግሽበት እና ሥራ አጥነት ችግሮችን በዘላቂነት እየቀረፍን ለመሄድ የተጀመሩ ሥራዎች እና የተያዙ አቅጣጫዎች ላይም ተጨማሪ ማብራሪያ ቢሰጥበት?

እንደ ሀገር ቀጣይነት ያለው የገቢ እድገት ከማረጋገጥ አንጻር እየተመዘገበ ያለው ሥራ በጣም የሚበረታታ ይሁን እንጂ ለጥቅል ምርት ያለው ድርሻ ወይም ታክስ ጂዲፒ ሬሾ ከሰሐራ በታች ካሉ ሀገሮች አንፃር እንዲሁም እያደገ ካለው ጥቅል ሀገራዊ ምርት አንፃር ሲመዘን ዝቅተኛ ነው። ከኢኮኖሚ ከሚመነጨው ሀብት ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢሰጥ? እንዲሁም ከኅብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎች በተለይ ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ሙስናንና እና ብልሹ አሠራርን ለማስተካከል እየተወሰዱ ያሉ ተጨባጭ ርምጃዎች ላይ ማብራሪያ ቢሰጥ? የሚሉ፤ አካባቢያዊ የልማት ጥያቄዎችን እና ቅሬታዎችን ያካተቱ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ የተከበሩ አፈ ጉባኤ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት በድጋሚ ስለተገናኘን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። ለጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠቴ በፊት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዓመት ጅማሮ እንደሚሆን መግለፄ ይታወሳል፤ ማንሰራራት ብለን ያነሳነው ሀሳብ የለውጥ መትከል፣ የለውጥ ማፅናት፣ የለውጥ መሠረት ማስያዙን ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ ዕድገት፤ የሪፎርሙን ውጤት ወደምንሰበስብበት/ሃርቨስት ወደምናደርግበት ጊዜ መሸጋገራችንን ለመግለፅ ነበር። ያንን ቋንቋ መጠቀም ያስፈለገው፤ ዘንድሮ እንደተባለውም ለኢትዮጵያ በእጅጉ የማንሰራራት ዘመን ነው። ታላላቅ ድሎች የተመዘገቡበት አመርቂ ውጤቶች የታዩበት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ ያልታወቁ ድሎች የተጎናፀፉበት ዓመት ነው።

ይህ ጉዳይ እንዲሳካ የተከበረው ምክር ቤት እና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነበራችሁ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እና ለተገኘው ድል በራሴ እና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ። የፓርላማ አባላት ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ በእያንዳንዱ ሥራ ውስጥ የሰጣችሁት አመራር ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ስለሆነ ይህ ልማድ በሚቀጥሉት ዓመታት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከወዲሁ እያሳሰብኩ፤ በመጀመሪያ ለሁላችንም ትርጉም ያለው ሚና ትርጉም ያለው ውጤት ተገኝቶበታል ተብሎ የሚታሰበውን የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርም በሚመለከት መጠነኛ መረጃ ለመስጠት እሞክራለሁ።

የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርም  የጀመርነው አጠቃላይ የመንግሥታችን መርሕ በሪቮልሽን/በአብዮት ሳይሆን በሪፎርም፤ ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን ማኅበራዊ ዘርፉን እና ተቋማትን መለወጥ ይቻላል፤ የነበረውን ሳናፈርስ በነበረው ላይ የጎደለ እየሞላን እያዘመን የተሻለች ታሪኳን ያልዘነጋች ወደፊት ያላት ተስፋ በግልፅ የሚታይ ኢትዮጵያን መሥራት ይቻላል ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው።

በዚሁ አግባብ ኢኮኖሚውን በሚመለከት ወደ ማክሮ ሪፎርም እንድንገባ ያስገደዱን ጉዳዮች አንደኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶች ናቸው። እነዚህ ስብራቶች ”በኢንፕሎይመንት” ሊገለፁ ይችላሉ፤ “በኢንፍሌሽን” ሊገለፁ ይችላል። በገቢ እና ወጪ ንግድ ክፍተት/ደፍሲት ሊገለፅ ይችላል። በጥቅሉ የማክሮ ኢኮኖሚው ስብራት ነበረበት።

ሁለተኛው ወደዚህ ሪፎርም ያስገባን የግሉ ዘርፍ መነቃቃት እንዲችል የሥራ አካባቢው ምቹ አልነበረም፤ አንድ ማሳያ ለማቅረብ የግሉ ዘርፍ በተለያዩ ባንኮች የሚያስቀምጣቸው ገንዘቦች 27 ፐርሰንቱ ቦንድ በሚል ስም ስለሚወሰድ በቂ ሀብት ፈሶለት ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል አልነበረም።

ሦስተኛው ምርታማነት ነው፤ በግብርናም በኢንዱስትሪም ምርታማ/ ፕሮዳክቲቭ የመሆን ውስንነት ነበር። ምርታማ/ፕሮዳክቲቭ ባለመሆናችን ደግሞ ቅድም ሲነሱ የነበሩት በርካታ ችግሮች በሀገራችን ውስጥ እንዲስተናገዱ ሆነዋል። አራተኛው እና ለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ያስገባን ጉዳይ ተወዳዳሪነት/ኮምፒተንት የሆነ ኢኮኖሚ፤ የሚወዳደር ኢኮኖሚ፤ በገበያ ውስጥ የሚወዳደር እና የሚያሸንፍ የኢኮኖሚ ሁኔታን መፍጠር አለመቻላችን ነው። ተወዳዳሪ አልነበርንም። ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት/ፎሬይን ዳይሬክት ኢንቨስትመንት ለመሳብም ኤክስፖርት ለማድረግም የነበረው የገንዘብ አስተዳደር “ኦቨር ቫሊዩድ” ስለነበረ ለኢትዮጵያ/ለኢኮኖሚ እድገት አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር አልነበረም።

እነዚህን ጉዳዮች ጨክነን በመፍታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ደረጃ በደረጃ ሊቀረፍ ይችላል የሚል እምነት ተይዞ ነው ሥራው የተጀመረው። ይህ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አያልቅም፤ ከዓለም ጋር ባለን ትስስር ምክንያት አንዳንድ ፍላጎታችን የዓለምን የኢኮኖሚ ሂደትና ጉዞ የማንገነዘብ የማናይ የማናነብ ከሆነ የኛ ፍላጎት ብቻውን በበቂ ደረጃ ሊሳካ አይችልም። ከዚህ አንፃር ዓለም ላይ የነበረው አጠቃላይ የኢኮኖሚክ ሂደት ከፍተኛ መዋዠቅ የታየበት ነው።

በወረርሽኝ በግጭት ምክንያት የዓለም የንግድ ሥርዓት ከምንጊዜውም በላይ መዛባት የገጠመው ጊዜ ነበር። ዘንድሮን ብቻ እንደ ማሳያ ብንወስድ እንደ አይኤምኤፍ ትንበያ መሠረት አጠቃላይ የዓለምን ዕድገት 3 ነጥብ ሦስት ፐርሰንት ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ ተንብዮ የነበረ ቢሆንም በሂደት ዓመቱ እየተጋመሰ ሲሄድ ካጋጠሙ አዳዲስ ችግሮች በመነሳት የዓለም ዕድገት ከትንበያው ዝቅ ብሎ 2 ነጥብ ስምንት ገደማ ሊሆን እንደሚችል አይኤምኤፍ አስቀምጧል።

ከሰሐራ በታች ያሉ ሀገራት እኛን ጨምሮ በጥቅልና በአቨሬጅ ሲታይ ዘንድሮ 4 ነጥብ ሁለት ፐርሰንት ዕድገት ሊያመጡ ይችላሉ የሚል አስቀድሞ ተተንብዮ የነበረ ቢሆንም፤ ሌላው ዓለም የገጠመው ችግር በቀጥታ እነዚህን ሀገራት የሚነካ በመሆኑ ዕድገቱ ከትንበያው ዝቅ ብሎ 3 ነጥብ ስምንት ገደማ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ትንበያውን አስቀምጧል።

የዓለም የንግድ ሥርዓት በዋዠቀበት ሁኔታ ውስጥ እኛ ምን ዓይነት ስልት እና በምን ዓይነት ያቀድነውን ነገር ልናሳካ እንችላለን የሚለውን ነገር ካለን ትስስር አንፃር ማየት በእጅጉ ማየት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ወደ አፍሪካ የሚፈሰውን ርዳታ ብንመለከት ዘንድሮ ሰባት ፐርሰንት ቀንሷል፤ ከዚህ ቀደም ይሰጥ ከነበረው ርዳታ 7 ፐርሰንት ቀንሷል፤ ይሄ ጉዳይ በሚቀጥለው ዓመት ይበልጥ ሊጠናከር ይችላል።

በዓለም ደረጃ “ኢንፍሌሽን” የንግድ ሥርዓቱን የሚያዛቡ በርካታ ግጭቶች እያጋጠሙ ስለሆነ ባልተለመደ ሁኔታ በዚህ ዓመት 4 ነጥብ ሦስት ፐርሰንት ይጨምራል የሚል ትንበያ ተቀምጧል፤ አጠቃላይ የዓለም ንግድ ቢበዛ አንድ ነጥብ ሰባት ፐርሰንት ገደማ ነው ከአምና ይሻሻላል ተብሎ የሚጠበቀው የንግድ ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል።

ከዚህም በመነሳት የውጭ ኢንቨስትመንት በዓለም ደረጃ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፤ ሰዎች አምነው ብራቸውን ሌላ ቦታ የማኖር ፍላጎታቸው ቀንሷል፤ ለምን ሆነ ያላችሁ እንደሆነ የዓለም መንግሥታትን ትኩረት የሚሻሙ በርካታ ከፍ ከፍ ያሉ ችግሮች ስላሉ እነዚያን ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረግ ጥረት እንደኛ ዓይነት የሌሎችን እጅ እየጠበቀ የሚኖር ሕዝብና ሀገር ከፍተኛ ፈተና እንዲያጋጥመው ሆኗል። ይህን ለመቅረፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከውጭ ባለን ትስስር ልናገኝ እና ልናጣ የምንችለውን በሀገር ውስጥ ባለን አቅም፣ ዕምቅ አቅም እነዚያን ዕምቅ አቅም በመመንዘር ልናገኝ የምንችላቸውን አሁናዊ ውጤቶች በለካ መንገድ የተቀመጠ ነው።

ከዚህም በመነሳት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በሀገርዋ ሰፋፊ ፈተናዎች ያሉባት ቢሆንም ባለፈው ዓመት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅንጅት እና ትብብር በእናንተም ከፍተኛ አመራር የ8 ነጥብ አንድ ፐርሰንት ዕድገት ማረጋገጣችን ይታወሳል። በዚህ ዓመት በዚያ ዕድገት ሳንዘናጋ 8 ነጥብ አራት ፐርሰንት አጠቃላይ ዕድገት ለማምጣት ታቅዶ ሲሠራ ቆይቷል። ምንም እንኳን በዓለም ላይ ያለው ፈተና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ይህን ዕቅድ ለማሳካት ኢትዮጵያ የሄደችበትን መንገድ የተከበረው ምክር በግልፅ መገንዘብ እንዲችል ከአጠቃላይ ጂዲፒ ዕድገት አንድ ደረጃ /ስቴፕ ዝቅ ብዬ የሴክተሮችን በማንሳት፤ እዚያ ውስጥ በሴክተር ያገኘናቸውን ድሎች እንዲሁም አልፎ አልፎ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተብለው ለሚነሱ የፕራዮሪቲ/ ጉዳዮች ምላሽ ስለሚሆን የተወሰኑትን ለማንሳት ልሞክር።

አንደኛውና እና ዋነኛው ሴክተር ግብርና ነው። ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ ነው። የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ/ኤክስፖርት እስካሁን ባለው ሁኔታ ዋልታ ነው። የምንመገበው ብቻ ሳይሆን ሸጠን የውጭ ምንዛሪ የምናገኘውም ከዚህ ዘርፍ ነው። በርከት ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሳተፍበት ሴክተር ነው። በዚህም ምክንያት ትልቅ ግምት ይሰጠዋል።

በውጭ እንደምንሰማው ትኩረቱ ኮሪዶር ሳይሆን ትኩረቱ ብዝኃ ዘርፍ ነው። በአንድ ዘርፍ ላይ ጥገኛ/ዲፔንድ የሆነ ኢኮኖሚ ዘርፍ በተለያየ ምክንያት ሲመታ ወዳቂ ስለሚሆን፤ ብዝኃ ዘርፍ እና ብዝኃ ተዋናይ ብናደርገው ብዝኃ ጥቅም እናገኝበታለን በሚል እሳቤ ነው በግልጽ መንገድ ከእናንተም ጋር ተግባብተን ሪፎርም የተጀመረው።

ግብርና በዚህ ዓመት 6 ነጥብ 1 ፐርሰንት እድገት እንዲያመጣ ነበር የታቀደው፤ ለግብርና ስድስት ፐርሰንት በጣም ከፍተኛ ቁጥር ነው። ምክንያቱም መሠረቱ/ቤዙ የሰፋ ስለሆነ ስድስት ፐርሰንት በዚያ መስክ ስኬት ማምጣት ማለት አጠቃላይ የምናስበውን ኢኮኖሚ ለማሳካት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። የግብርና ሴክተር ከሌሎች ሴክተሮች በተለየ መንገድ ትኩረት/አቴንሽን ያገኘበት ምክንያት ለእድገቱ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ አለባት፤ አምርታ መብላት የማትችል ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማሳካት ትቸገራለች፤ እነዚህ ምርቶች አርሶ፣ ዘርቶ፣ ኮትኩቶ ማምረት ብቻ ሳይሆን ብዙ ወሳኝ ግብዓቶች አሉት፤ አጠቃላይ ጥቅማዊ ትስስሩ በደንብ ታውቆና ተለይቶ ኢንቨስት በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ አለበት የሚል ጽኑ እምነት ተይዞ ሲሠራበት ቆይቷል ።

ሁለተኛው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ 27 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በሴፍቲኔት የታቀፉ ተረጂዎች ነበሩ፤ እነዚህን ተረጂዎች ደረጃ በደረጃ ከሴፍቲኔት ነፃ ማውጣት አለብን የሚል ሥራ በግብርና ንዑስ/ሰብ ሴክተር ውስጥ እንደ ዋና ቁልፍ ጉዳይ ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል። በዚሁ ዓመት ከወራት በፊት ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ እና ደቡብ ሀላባ ዞን የመሄድ ዕድል አግኝቼ ነበር። ሁለቱም ቦታ ለረዥም ዘመናት በሴፍቲኔት ይተዳደሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው አምርተው፤ ከሴፍቲኔት ነፃ መሆናቸውን ከአርሶ-አደሮች በቀጥታ ሰምቻለሁ፤ ይሄ ብዙ ቦታ የተሳካ ተግባር ነው።

ኢትዮጵያ መለመን የለባትም፤ ልጆቿ ተግተው ሠርተው ከልመና ራሳቸውን መገላገል አለባቸው የሚለው እምነት ፍሬ እያፈራ መጥቶ በቅርቡ እንደገለጽኩት ዘንድሮ 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከሴፍቲኔት ተረጂነት ነፃ ወጥተዋል። ይህ የማንሰራራት ትልቁ ማሳያ፤ የእናንተ አመራር ትልቁ ማሳያ ኢትዮጵያን ከጥገኝነት የሚገላግላት ትልቁ ማሳያ ስለሆነ ሁላችንም ኩራት ሊሰማን ይገባል። ኩራት ሲሰማን ግን ቀሪው ከአራት ሚሊዮን ያላነሰ ተረጂም በአጭር ጊዜ ውስጥ መሰል ተግባር በመፈጸም ነፃ አውጥተን ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ከምግብ ተረጂነት የተላቀቀች፤ የምግብ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ሀገር መሆኗን ማረጋገጥ ከእኔና ከእናንተ የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል።

እነዚህን አንኳር ነገሮች ለማሳካት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የታዩ ዝርዝር ጉዳዮች አሉ። አንደኛው መሬት ነው፤ ኢትዮጵያ ሊታረስ የሚችል በጣም ሰፊ መሬት ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች። ባለፈው ዓመት ብዙ ጨምረናል ብለን 26 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ነበር። በዚህኛው ዓመት ግን 31 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ተችሏል። 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ተጨማሪ ቦታ አርሰናል ማለት ነው። በዚህ ምን አገኘን ከምርት አንጻር? የተባለ እንደሆነ፤ ባለፈው ዓመት በጥቅሉ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ነው ኢትዮጵያ የሰበሰበችው።

ዓመቱን ሙሉ በሁሉም አይነት የሰብል ምርቶች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኩንታል ነበር የተሰበሰበው፤ ዘንድሮ ግን 300 ሚሊዮን ኩንታል ጨምሮ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኩንታል መሰብሰብ ተችሏል። 24 ነጥብ 7 ፐርሰንት ከአምና ዘንድሮ እድገት አለ። 24 ነጥብ 7 ፐርሰንት እድገት ያመጣነው አንደኛ በመስኖ/በእሪጌሽን ነው። መስኖን አስመልክቶ ፕሮጀክቶች ዘግይተዋል ለተባለው፤ በከፍተኛ እና በተወሰኑ መካከለኛ ፕሮጀክቶች በፌዴራል መንግሥት 20 ገደማ ግድቦች ይሠራሉ። እነዚህ 20 ገደማ ግድቦች ሲጠናቀቁ፤ ከ220ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት ይችላሉ። 220 ሺህ ሄክታር በዓመት ሁለቴ ካመረትን 440 ሺህ ሦስቴ ካመረትን 660 ሺህ ገደማ ሄክታር ይሆናል ማለት ነው። መስኖ ሲሆን ድግግሞሽ ስለሚጨምር፤ በዚህ ዓመት እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ስድስት ከፍተኛ ግድቦች፤ 84 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ፤ በተለያዩ ክልሎች ይመረቃሉ።

ቅድም የተነሳውን የደቡብ ኦሞውን እንኳን ብንወስድ 145 ኪሎ ሜትር ካናል ተሠርቷል። ከዚህ አዳማ 75፤ 76 ኪሎሜትር ይሆናል፤ 145 ኪሎ ሜትር ማለት ከአዳማ ደርሶ መልስ የሚጠጋ ያህል ካናል በደቡብ ኦሞ ተገንብቷል። ዝም ብሎ ቦይ አይደለም፤ ትላልቅ ካናሎች ናቸው፤ እንደዚህ አይነት ሥራ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ተከውነዋል፤ በዚህ ዓመት እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ስድስቱ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ። ይሄ ከፍተኛ እና መካከለኛ ነው፤ በክልል ደረጃ የሚሠሩ አነስተኛ የሚባሉ ግድቦች ከ55 በላይ ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል።

በነገራችን ላይ ስለግድብ ብዙ አውርተን አናውቅም፤ ከ100 በላይ አነስተኛ እና መካከለኛ ግድቦች ኢትዮጵያ ውስጥ ይሠራሉ። ብዙ ቢሊዮን ብር ኢንቨስት የሚደረግበት ሥራ በግድቦች እና በመስኖ ዙሪያ ይሠራል። ይህ ለምርት እድገት የራሱን የሆነ አስተዋፅዖ አድርጓል። በተጨማሪ ሜካናይዜሽን፤ በሺ የሚቆጠሩ ትራክተሮች፣ ፓንፖች፣ ኮምባይነሮች ገብተዋል፤ በዚህ ዓመት። በሺህ የሚቆጠሩ ትራክተሮች አምና ከነበረው ጨምረናል፤ በዚህ ዓመት። በዚህ ምክንያት ነው የመስኖ ሥራው ሲጨመር ምርታማነቱ የጨመረው።

አሲዳማ መሬት ብቻ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ ታክሞ ወደ እርሻ ገብቷል፤ በዚህ ዓመት። ኖራ እያመረትን ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ እርሻ ገብቷል። መሬትን ደጋግሞ የማረስ ልምምድ አድጓል፤ በዓመት ሁለቴ፤ ሦስቴ የማምረት ልምምድ አድጓል። በተለይ የበጋ ስንዴ ብለን የጀመርነው ጉዳይ ከፍተኛ እመርታ አምጥቷል።

ግብርና 5 ሚሊዮን ሄክታር፤ 300 ሚሊዮን ኩንታል፤ ጨምሮ ሳለ፤ ትኩረት ለኮሪዶር ነው ቢባል፤ አርሶ አደሮች እንዴት አድርገው ሊያምኑ ይችላሉ። ትራክተር፣ ፓንፕ የምንገዛው፤ መሬት የምናርሰው፤ ገንዘብ መድበን ነው፤ የግብርና ኤክስቴንሽን ሙያተኞች በእያንዳንዱ የአርሶ አደር ማሳ ላይ፤ ቀን ከሌሊት እየፈጉ ነው፤ ሞቅ የሚሉ አካባቢዎች ማታ በፓውዛ በትራክተር የሚያርሱባቸው አካባቢዎች አሉ። ቪዲዮዎች ይላኩልኛል። አዳዲስ ልምምዶች አሉ።

ሌማትን እንኳን እንደማሳያ ብንወስድ፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ “ፓርንትና ግራንግ ፖርንት” በመታገዝ የጀመረችው የዶሮ እርባታ በብዙ ቁጥር የእንቁላል ምርት አሳድጓል፤ የወተት ምርት አድጓል፤ በአርቴፊሻል ኢንተርሚኒሽን እየተስፋፋ ያለው የላሞች የማራባት ዘዬ በሰው 66 ሊትር የነበረውን የወተት ፍጆታ ወደ 88 ከፍ አድርጓል።

በማር፣ በዓሣ ከፍተኛ ለውጦች አሉ። እነዚህ ለውጦች እንደመልካም ጅማሮ የሚወሰዱ እንጂ ለግብርና ኢትዮጵያ ካለምንም ችግር በተሟላ መንገድ ምላሽ ሰጥታለችና እጅ እግራችንን አጣጥፈን እንቀመጥ ሳይሆን ጅማሯችን ተስፋ ሰጪ ነው። ምርታማነት እያደገ ነው። ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶችን መተካት ችለናል። ይህንን አጠናክረን ብንቀጥል በብዙ ዘርፍ ውጤታማ ልንሆን እንችላለን የሚል እምነት ነው ያለኝ።

የግብርና ሴክተር ትልቅ ትኩረት ያገኘ ትልቅ ውጤት ያመጣ ለአጠቃላይ እድገታችንም ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን እናንተ አብዛኛዎቻችሁ የአርሶ አደር ልጆች ወይም ከተለያዩ ወረዳዎች የመጣችሁ ስለሆናቸው ምንያህል እርሻው ቡናው ሻዩ፣ ሩዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እያመጣ እንዳለ ለመገንዘብ አትቸገሩም። ይሄ ውጤት ትኩረት ነበረው፤ ተመርቷል ውጤት አምጥቷል፤ ተጠናክሮ ደግሞ ይቀጥላል።

ሁለተኛው ሴክተር ለአጠቃላይ እድገታችን ከፍተኛ ትርጉም ያለው ኢንዱስትሪ ነው። ኢንዱስትሪ ዘንድሮ 12ነጥብ8 በመቶ እድገት ሊያመጣ እንደሚችል ታስቦ እየተሠራ ነው። ይሄ ሥራው እንዲሳካ የናሽናል እስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን በሴክተር፣ በንዑስ/በሰብ ሴክተርና በፋብሪካ ደረጃ በመለየት ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ በጣም ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ኢትዮጵያ ታምርት አምና 59 በመቶ ነበር የደረሰው፤ ዘንድሮ 65 በመቶ ደርሷል። ስንጀምር ታስታውሱ ከሆነ 47 ገደማ ነበር። ፋብሪካው እያለ በተለያየ ችግር ምክንያት ማምረት ከሚችለው ያነሰ ያመርት የነበረው ፋብሪካ በማሻሻል ብቻ ማለት ነው። አሁን 65 በመቶ ደርሷል። በዚህ ዓመት ኢንዱስትሪ ሴክተር የኢነርጂ ፍላጎት 40 በመቶ ጨምሯል። ቅድም ኢነርጂ ችግር አለ ብለው አንድ የምክር ቤት አባል አንስተዋል። ትክክል ነው ችግር አለ። ችግሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ማንም ሀገር “ክሌም” ማድረግ በማይችለው ልክ ጀኔሬተር ላይ ኢንቨስት እያደረገች ነው። ጀኔሬተር እና ትራንስሚሽን ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለየብቻ ናቸው፤ በዚያ ምክንያት ያረጁ ፖሎች ሊወድቁ ይቻላሉ።

ሌላው ከኢንዱስትሪ ዘንድሮ ብቻ 40 በመቶ ኢነርጂ አድጓል። በሴክተሩ የመጣው እድገት ታምር ሊባል የሚያስችል ነው። ያንን የሚያህል ኢነርጂ አምርተን ማቅረብ መቻል ቀላል ግምት የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። ሲሚንቶ 16 በመቶ አድጓል። አምና ውድ ሆነ ጠፋ ነበር የሚባለው፤ በዚህ ዓመት ደግሞ ምርቱ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ አሳይቷል። ለሚ የሲሚንቶ ፋብሪካ በማለቁ ሌሎቹም በማሻሻላቸው ምክንያት የሲሚንቶ ምርት ከፍ ብሏል።

የብረት ውጤቶች 18 በመቶ አድገዋል። ብረት ከአይረን ኦር ከአፈሩ የማምረት አቅም ኢትዮጵያ ባትገነባም በሁሉም የብረት አይነቶች ቁርጥራጭ/እስክራፕ ከተገኘ ጨፍልቆ ለመሥራት የሚያስችል አቅም ገንብቷለች። አሁን የሚቀረን ዋናው ጉዳይ አይረን ኦሩን አቅልጦ ወደ ብረት የመቀየሩ ሥራ ካልሆነ በስተቀር ከዚያ በኋላ ያለው ከሞላ ጎደል የኢትዮጵያን ፍላጎት መመለስ በሚመስል ደረጃ በርካታ ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል።

መስታወት ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የዘመናዊ የኮንስትራክሽን ሴክተር በከፍተኛ ደረጃ መስታወት ይጠቀማል። ኢትዮጵያ በቂ የመስታወት ፋብሪካ አልነበራትም። ያሉትም ሙሉ ለሙሉ ግብዓት ከውጭ የሚመጡ ነበሩ። አሁን በዓመት 600ሺ ቶን ገደማ የሚያመርት የመስታወት ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል። ይህ ፋብሪካ ሙሉ ለሙሉ አፈሩን ሮውማቴሪያሉን ከኢትዮጵያ ወሰዶ መስታወት የሚያመርትና ከመስታወት ምርት በኋላ የሚሠሩ የፊኒሽንግ ማቴሪያሎችንም እዚያ ቦታ የሚያመርት ነው። የፋብሪካ ግንባታ ሥራው በማንኛውም መስፈርት በጣም ሳቢ/ኢንፒረሲፍ ነው። ምናልባት አጠቃላይ ሥራ በመጪው “ዲሴንበር ወይም ጀነዋሪ ያልቃል” ተብሎ ይገመታል።

የተከበረው ምክር ቤት ይህንን ኢንዱስትሪያል ፓርክና የመስታወት ፋብሪካውን ሥራ እንዲጎበኝ ከወዲሁ ልጋብዝ እፈልጋለሁ። እጅግ አስደሳች ሥራ ስለሆነ ምንያህል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንን እንደሚቀየር፣ የኢትዮጵያ ፕራይቬት ሴክተር ቆርቆሮ አስቀምጠው ምርት የሚያመርቱ ሳይሆኑ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለዓለም ገበያ ለውድድር ልክ በጥራት ማምረት እንዴት እንደጀመሩ የሚያሳይ ስለሆነ በእጅጉ የምትኮሩበት ሥራ ነው። እዚሁ አቃቂ አካባቢ ነው፤ ሲመቻችሁ በማየት ለሰዎቹ ሞራል ብትሰጡ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።

አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን በሚመለከት በተለይ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከዚህ ቀደም በዕዳ የገነባናቸውና ያመጣናቸውም ኢንቨስተሮች በትክክለኛው መንገድ ሥራ ሠርተው ለኢትዮጵያ ፋይዳ ከማምጣት ይልቅ አነስተኛ አቅም ያላቸው በመሆናቸው ያን መልክ እንቀይር ብለን ትላልቅ ኢንቨስተር፣ አቅም ያለው፣ ፍላጎት ያለው፣ የመንግሥትን ድጋፍ ካገኘ ውጤት የሚያመጣ የግል ሴክተር ብናመጣ ይሻላል በሚል ሥራ ተጀምሯል።

በቅርቡ አንድ ሀገር ሄድን ያገኛናቸው ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሶላር ፓናል ምርት ጀምረዋል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ቢበዛ መስከረም ፋብሪካዎቹ ይመረቃሉ። እነዚህ ሶላር ፓናሎች በጣም ዘመናዊ በሆነ መንገድ የሶላር ፓናሎች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ናቸው። አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ናቸው። በተለያየ ዘርፍ በዚህ አግባብ ሰዎች እያመጣን ኢንዱስትሪውን ለማንቃት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

ይሄ ኢንዱስትሪ የሚባለው እድገት፣ ማኑፋክቸሪንግ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ኮንስትራክሽንም አለ። ኮንስትራክሽን ስላለ በሕንፃ ግንባታ፣ በግድቦች፣ በመንገድ ግንባታ፣ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኮሪዶር ዲቨሎፕመንት ጨምራችሁ የተነቃቃ የኮንስትራክሽን መስክ ያሳያል። ከኢንፖርትም ሲታይ ለካፒታል ጉድስ አምስት ቢሊዮን ዶላር ነው ያወጣነው። ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት ስላለው ሀብት አሎኬት ሲደረግ ቀላል የማይባል ሼር ነው የወሰደው።

ከኮንስትራክሽን ውጪ በዚህ ዘርፍ የሚታየው ማዕድን ነው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ፖቴንሻል ያላት ሀገር ናት። በአፍሪካ ውስጥ ትላልቅ የማዕድን ፖቴንሻል አላቸው ተብለው የሚጠሩ ሀገራት ካሉ አንዷ ኢትዮጵያ ናት። እስካሁን በዚያ መስክ በበቂ ደረጃ ያልተነሳበት ምክንያት ቅድም ትኩረቱ ኮሪዶር ሆነ ያላችሁት በነበሩት መንግሥታት የትኩረት ማነስ፣ የአመራር ማነስ፣ የእይታ ማነስ ችግር ስለነበረ ነው። እንጂ የማዕድን ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ማገዝ ይችል ነበር። ለምሳሌ ወርቅ ባለፈው ዓመት አራት ቶን ነው ኤክስፖርት ያደረግነው። በዚህ ዓመት 37 ቶን ኤክስፖርት አድርገናል። አራት ስንት ጊዜ ቢባዛ ነው 37 የሚሆነው። ያን የሚያህል ፖቴንሻል ተኝተንበት ከርመን ነው ስንለምን የነበረ ማለት ነው። አምና ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት አድርገን፤ ዘንድሮ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት አድርገናል። ይሄ ትኩረት ያመጣው ውጤት ነው።

ብዝኃ ዘርፍ ባንል ኖሮ በየትኛውም መስፈርት ኢትዮጵያ ውስጥ ማዕድን በዚህ መንግሥት የተሰጠውን ትኩረት አግኝቶ ተሠርቶ አያውቅም፤ ውጤቱም ይናገራል። ሁለተኛው ጋዝ ነው። ጋዝ በንጉሡ ዘመን፣ በደርግ ዘመን፣ በኢሕአዴግ ዘመን ሙከራዎች ነበሩ። ለማውጣት ሙከራዎች፣ ንግግሮች፣ ስምምነቶች/አግሪመንቶች ነበሩ። ከለውጥ በኋላም በፕራይቬት ሴክተር ጋዝ ለማምረት፣ ፋብሪካ ለመትከል መጥተው ተፈራርመው ሥራ መጀመራቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዝና አካባቢው ላይ ያሉ የፕራይቬት ሴክተር እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበራቸው አቀራረብ/አፕሮች መጥቶ ፈቃድ/ላይሰንስ መውሰድና በዛ ፈቃድ ብር መፈለግ ነው። ፈቃዱን ይይዙታል ግን ብር የላቸውም፤ በዚያ ፈቃድ ብር ይፈልጋሉ።

ይሄ መንገድ አያዋጣም ብለን በመንግሥት ደረጃ በነበረ ንግግር የነበሩትን ኩባንያዎች ሰርዘን በማውጣት አዳዲስ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ወደ ሴክተሩ እንዲገቡ በመደረጉ ምናልባት የተከበረው ምክር ቤት ለእረፍት ወጥቶ ሲመለስ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዝ ምርት ለገበያ ታውላለች። ለምን አልተነገረም እስካሁን ሳንሰማ ቆየን ለሚለው እኛ መንግሥት ነን። ሠርቶ አዳሪ ነን እንጂ አውርቶ አዳሪ አይደለንም። በሚያስፈልግ ቦታ ለሕዝብ መግለጥ ያስፈልጋል፤ ብዙ ባንዳዎች ባሉበት ቦታ ደግሞ ደብቆ መጨረስ ያስፈልጋል። እና ባንዳዎች እንዳያበላሹት ደብቀን የሠራነው የጋዝ ፕላንት ተጠናቋል በቅርቡ በሶማሌ ክልል ስንዴና ግድብ ሳስመረቅ ያያችሁኝ በዋነኛነት/ፕራይመርሊ የሄድኩት ለጋዙ ሥራ ነው። ለምን ሄደ እንዳትሉ ነው ስንዴ ሳይ የነበረው ነው።

ጋዝ የመጀመሪያው ምዕራፍ/ፌዝ አልቋል፤ በቅርቡ ይመረቃል። ሁለተኛው ምዕራፍ ይጀመራል። ጋዝ ስንጠብቅ ነበር። በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት የግብርና ሴክተር የተሟላ ውጤት የሚያስገኘው የማዳበሪያ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ካላት ብቻ ነው። በማዳበሪያ ምክንያት ምርታማነት ሊወርድ ይችላል። የማዳበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ከተለያዩ ኃይሎች ጋር ስንነጋገር ነበር። በመጨረሻ የአፍሪካን ልማት የራሱ ልማት አድርጎ የሚያስብ በኢትዮጵያም በተለያዩ አፍሪካ ሀገራትም ብዙ ኢንቨስትመንት ያለው የናይጄሪያ ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ጋር ድርድር ጨርሰን የጋዙን ምርት ለገበያ መዋል ስንጠብቅ ነበር። በቅርቡ አሊኮ ዳንጎቴም ሲመላለስ የነበረው ለዚሁ ጉዳይ ነው። ይህ ምክር ቤት ከእረፍት ሳይመለስ ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ መሥራት ትጀምራለች። የማዳበሪያ ፋብሪካ መሥራት ትጀምራለች ብቻ ሳይሆን ከ40 ወራት በኋላ ደግሞ ጨርሳ ታስመርቃለች። ለመጀመር ሳይሆን ለመጨረስ ስለምንሠራ ማለት ነው።

ስለዚህ ማዕድን አጠቃላይ በጋዝ፣ በወርቅ፣ በማዳበሪያ እየመጣ ያለው እመርታ ትኩረት አልተሰጠውም የሚያስብል ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ ውጤት ያለው ነው። ወርቅ አሁን ካመጣነው በላይ ሦስት አራት ፋብሪካዎች እየተሠሩ ነው፣ ምናልባት ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ፋብሪካዎቹ ያልቃሉ። እነሱ ካለቁ በከፍተኛ ደረጃ የወርቅ ምርት ያድጋል። ከዚህ ውጪ ታንታለም ላይ ሊቲየም ላይ ከትላልቅ ኩባንያዎች ንግግር ተጀምሯል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን አቅም አላት ትክክለኛውን ኢንቬስተር መርጠን ከመንግሥት ጋር ሴክተሮችን በጋራ ማልማት ነው፤ ለምሳሌ ጋዙን ብንወስድ የኢትዮጵያ መንግሥትና የቻይና መንግሥት የሰጡን ኩባንያ በጋራ ነው የሚያመርቱት። ሼር ሆልደር ነን እኛ። ማዳበሪያውን ብንወስድ የኢትዮጵያ መንግሥትና ዳንጎቴ በጋራ ነው የሚያመርቱት። ያ የሆነበት ምክንያት ፈቃድ/ላይሰንስ እየወሰዱ ሰዎች እንዳይጠፉ፤ ኢትዮጵያም እየወሰደች ለፕራይቬት ሴክተር ኮንፊደንስ ሰጥታ እውቀትና ካፒታል የምታገኝበትን መንገድ ለመከተል ነው።

ማዕድኑን ኮንስትራክሽኑን እና ኢንዱስትሪውን ደምራችሁ ስታዩ የዚህ ዓመት ዕድገት በአቀድነው ልክ ብቻ የሚወሰን አይመስልም። ምክንያቱም ሦስት መቶ ሚሊዮን ኩንታል ምርት በግብርና ብያችኋለሁ፤ ከ300 ሚሊዮን ዶላር፣ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ወርቅ በማዕድን ብያችኋለሁ። እነዚህ ዘርፎች ከእቅዳችን በጣም ከፍ ብለው የተፈጸሙ ናቸው።

ሦስተኛ ሴክተር ሰርቪስ ነው። ሰርቪስ ዘንድሮ የታሰበው ስምንት ነጥብ አንድ ፐርሰንት ዕድገት እንዲመጣ ነው። የተከበረው ምክር ቤት ሰርቪስ ሦስት አራት አካባቢዎች/ኤሪያዎች በውስጡ የሚካተቱ መሆናቸውን እና ምን ያክል ለግብርናው ለኢንዱስትሪውም አስፈላጊ እንደሆኑ እንዲገነዘብልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ። አንደኛው ቱሪዝም ሁለተኛው ትራንስፖርት ሦስተኛው ቴሌ ኮሙኒኬሽንና መገናኛው በጥቅሉ፣ አራተኛው እዚያ ውስጥ ያሉ ንግድና ሰርቪሶችን የሚያያይዝ ቴክኖሎጂ ሊካተትበት ይችላል።

ሰርቪስ ሲባል፤ የትኛውም ዓለም ያደገ ኢኮኖሚ መጨረሻ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ማለት ነው። ለምሳሌ የአሜሪካን ኢኮኖሚ ብንወስድ ግብርና እና ኢንዱስትሪ ተደምሮ 30 ፐርሰንት አይሆንም። አብዛኛውን ሼር የሚወስደው ሰርቪስ ነው። ይሄ መንግሥት ቱሪዝም ብቻ የቱሪዝም መዳረሻ ብቻ ብለው ለሚያስቡ ሰዎች፣  በርግጥ ይሄ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ስለሚሠራ በየትኛውም ዘርፍ ቢኬድ ስንዴ ብቻ ፤ ወርቅ ብቻ፤ ጋዝ ብቻ ሊባል ይችላል፤ በርካታ ድሎች ያሉት ስለሆነ። ነገር ግን ሰርቪስ በተቀናጀ መንገድ ብንሠራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመሸከም ያለው ጉልበት ከፍተኛ ነው።

ዘንድሮ በሀገራችን ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ተስተናግደዋል፡ አምና ከነበረው አንጻር በብዙ እጥፍ ይበልጣል። የዓለም ተቋማት ኢትዮጵያን መርጠው ለምን መጡ? ኢትዮጵያ ነበረች ድሮም ምን አዲስ ነገር መጣ፤ ኮንፍረንስ ዘንድሮ ወደዚህ ደረጃ ለመድረሱ በጣም ብዙ ምክንያቶች ላይ በመመሥረት ሊገለጽ ይችላል።

ዘንድሮ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ የውጭ ቱሪስት ኢትዮጵያን ጎብኝቷል። እስካሁን ካለው ከፍተኛ ቁጥር ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የኢሚግሬሽን ሪፎርሙ፤ ኢሚግሬሽን ላይ የሠራናቸው ሥራዎች፣ የአየር መንገድ ሥራ፣ የሆቴሎች መዳረሻ ቦታዎች፣ የኮሪዶር ልማት በጣም በርካታ ምክንያቶች/ፋክተርስ ሊነሱ ይችላሉ።

እዚች አካባቢ ዩኒቲ ፓርክ፣ ፍሬንድሺፕ አደባባይ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ ናሽናል ፓላስ ብቻ በዚህ ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰው ጎብኝቷል። ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተንበታል። አስቡት ዩኒቲ ለምን ይሠራል፣ ፍሬንድሺፕ ለምን ይሠራል ሲባል የነበረበትን ዘመን። በአንድ ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰው መሄጃ አዘጋጀንለት ማለት ነው። ያ አንድ ሚሊዮን ሰው ዩኒቲ ባይኖር ፍሬንድሺፕ ባይኖር ወይ ጫት ላይ ነው ወይ ድራፍት ላይ ነው ማለት ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእነዚህ ቦታዎች 13 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰው ጎብኝቷል። ሳይንስ ሙዚየም፣ ፍሬንድሺፕ ዩኒቲ። ይሄ የተመዘገበና ብር የሚከፍል ነው። የሚታወቅ ቁጥር ነው ማለት ነው። አዲስ አበባ ላይ ባለው ዳታ በዚህ ዓመት ያለው የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስት ዕድገት በጣም ከፍተኛ ነው። የቱሪዝም እድገት አንዱ ለሰርቪስ እድገት እንደ ፒላር ይወሰዳል

ሁለተኛው አየር መንገድ ነው። አየር መንገዳችን በዚህ ዓመት 13 ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ገዝቶ 180 አውሮፕላን ደርሷል።

ስድስት አዳዲስ መዳረሻዎች ጨምሮ እስካሁን አጠቃላይ ያለው መቶ ሰላሳ ስድስት መዳረሻዎች ደርሷል። በሀገር ውስጥ እና በውጪ ከአስራ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰው በላይ አጓጉዟል።

እኛ ስንመጣ የዚህ ግማሽ ገደማ ነው የሚያጓጉዘው። የሚታይ ነው እድገቱ ማለት ነው። በአውሮፕላን ቁጥርም በሚያጓጉዘው ሰው መጠንም በሚያገኘው ትርፍም የሚታይ ለውጥ ነው ያለው። ባቡር ከዚህ ቀደም እንዳነሳሁላችሁ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚሄደው ባቡር የመጣበት የተሠራበት መንገድ ይታወቃል። የባቡር ኮርፖሬሽን የሠራተኞቹን ደሞዝ መክፈል አይችልም ነበር። ሁለት ሶስት ፉርጎ ነው የሚጎትተው በቂ ገንዘብ አያመነጭም ደሞዝ አይከፍልም። ልክ እንደ አዲስ አበባው ላይት ሬል ዌይ ማለት ነው።

አሁን በተሠራው ሪፎርም በቁም እንስሳት ኤክስፖርት ከፍተኛ እመርታ ያመጣንበት አንዱ አሱ ነው፤ በባቡር፣ ቡና እና የቁም አንስሳት እናጓጉዛለን። በጣም በርካታ ፉርጎዎች መጎተት ጀምሯል። በኢምፖርትና ኤክስፖርታችን ላይ የሚታይ አዎንታዊ ድርሻ ተጫውቷል።

በፋይናንስ ዘርፍ፤ በዚህ ዓመት ብድር ከአምናው፤ ሰባ አምስት ፐርሰንት ጨምሯል። ለግል ሴክተር ሰማንያ ፐርሰንት ሼር አላቸው። የፋይናንስ ሴክተሩ በእጅጉ ተነቃቅቷል። ቅድም ሪፎርም የማይክሮ ሪፎርም ላይ ሊነሳ የሚገባው አንዱ በፋይናንሺያል ሴክተር ላይ ያመጣው አዎንታዊ ውጤት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት በቦንድ እና በተለያየ ፕሮጀክቶች ስም ከስምንት መቶ ሃምሳ አስከ ዘጠኝ መቶ ቢሊዮን ብር ገደማ ዕዳ ነበረበት።

ዘጠኝ መቶ ቢሊዮን እዳ የነበረበት ንግድ ባንክ፤ ይሄ የማይክሮ ሪፎርም ባይመጣ ኖሮ ንግድ ባንኩም ይወድቃል፤ የፋይናንሺያል ሴክተሩም ይከሰከሳል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ፋይናንሺያል ሴክተር ዋናው ባንከ ንግድ ባንክ ነው። ያ ዘጠኝ መቶ ቢሊዮን ብር እዳ፤ በተሠራው ሪፎርም ከንግድ ባንክ ወደ መንግሥት በመዘዋወሩ እና ለንግድ ባንክ ተጨማሪ ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ኢንጄክት ማድረግ በመቻሉ፤ ንግድ ባንክ ድኗል፤ ፋይናንሺያል ሴክተር ድኗል። ይሄ ሪፎርም ሌላው ሁሉ እንኳን ቢቀር ለረዥም ዘመን የነበረ ንግድ ባንክን ከመውደቅ ታድጓል ማለት ነው።

ፋይናንሻል ሴክተሩ ውስጥ ዲጅታል ያለው ሚና፤ ሞባይል መኒ ሃምሳ አምስት ሚሊዮን ሰው ደርሷል። ሶስት ዓመት ገና ከጀመርን ታስታውሳላችሁ። የቨርችዋል ገብይት የዘመን ገበያ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የካሽ ትራንዛክሽን በዲጂታል ትራንዛክሽን ተበልጧል። አሁን ዲጂታል ትራንዛክሽን 12 ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ደርሷል። ዲጂታሉ እየወሰደ ነው ማለት ነው። ሼሩ እየበለጠ ሄዷል። በብድር ያየን እንደሆነ 11 ሚሊዮን ገደማ አነስተኛ ጥቃቅን ተበዳሪዎች 24 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ቨርችዋሊ ተበድረዋል። 11 ሚሊዮን ወጣቶች በስክል ብቻ የ24 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ብድር አግኝተዋል። ይሄ የብድር ስርጭቱ ከጥቂት ሰዎች ወደ ብዙ ሰዎች እንዲበተን ያደርገዋል ማለት ነው።

ዲጅታል አድጓል፤ ፋይናንሺያል ሴክተር አድጓል፣ ቱሪዝም አድጓል፣ ትራንስፖርት አድጓል። የሰርቪስ ሴክተሩ ከኮሪዶር ጋር ተያይዞ ቱሪዝም ብቻ ሳይሆን መለስተኛ ጥናት፤ ተጠንቷል አዲስ አበባ ላይ፤ ሸራተንን ጨምሮ በርካታ ሆቴሎች እናንተም አረጋግጡ ይሄንን፤ በየዓመቱ ያስገቡ ከነበረው በላይ ከፍ ብሏል ገቢያቸው፤ የሚከፍሉትም ግብር ከፍ ብሏል፤ የመያዝ አቅሙም ሩም የሚያዝበት ሬትም አድጓል። ይሄ ጥናት ነው።

የሰርቪስ የኢንዱስትሪ እና የግብርና እድገት ደምራችሁ ስታዩ፤ የዘንድሮ እድገታችን ካቀድነው በላይ እንደሚሳካ ምንም ጥርጥር የለውም። ተጠቃሎ የሚመጣው መስከረም ስለሆነ አስቀድሞ አሁን መናገር ቢያስቸግርም፤ ስምንት ነጥብ አራት ብለን ያቀድነው እቅድ ከዚያ በላይ ልናሳካ እንደምንችል እያንዳንዱ የሴክተር እድገት ያመላክታል።

እግረ መንገድ አይ ኤም ኤፍ ወይም ወርልድ ባንክ የኢትዮጵያ ሪፎርም ችግር ውስጥ ነው ያለው ብሏል፤ ለተባለው ምናልባት የመረጃ ስህተት እንዳይሆን በዓለም ላይ ምሳሌ ሊወሰድበት የሚገባ፤ በመንግሥት ቁርጠኝነት የተመራ ድንቅ ሪፎርም ነው ያለው። ኖት የዛሬ ወር፤ ትናንትና። ትናንትና የአይ ኤም ኤፍ ቦርድ ተሰብስቦ ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ ሪፎርም በኢትዮጵያ ተከናውኗል ነው ያለው። ትናንትና። ሪፖርቱን ማንበብ ትችላላችሁ።

ምንም ጥርጥር የለውም የእኛ ሪፎርም በዓለም የፋይናንሺያል ተቋማት የተመሰገነ ሪፎርም ነው። በከፍተኛ ዲሲፕሊን የተመራ የተመሰገነ ሪፎርም ነው። ውጤቱም እንደምታዩት ነው። ለምሳሌ ኢምፖርትና ኤክስፖርትን እንውሰድ፤ ለተከበረው ምክር ቤት በእቅድ ያቀረብነው ኤክስፖርት በዚህ ዓመት አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ነው። ምክንያቱም አምና ስሪ ፖይንት ኤይት ገደማ ስለሆነ በአንድ ቢሊዮን ፕላስ ጨምረን አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት እናደርጋለን ነው እቅዳችን። ያሳካነው ጥቂት ቀናት ስለሚቀሩት ኤግዛክት ቁጥሩን መናገር ቢያስቸግረኝም ስምንት ነጥብ አንድ ወይም ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነው።

ይህ ማለት ካቀድነው ሶስት ቢሊዮን ተጨማሪ ማለት ነው። እቅድ አሳክታ የማታውቅ ሀገር ካቀደችው ሶስት ቢሊዮን ጭማሪ ማለት ነው። ከአምናውስ ከእጥፍ በላይ ማለት ነው። ታዲያ ሪፎርሙ ካልሠራ ኢትዮጵያ ስምንት ቢሊዮን በሁለት ሶስት ዓመታት የምታመጣውን ኤክስፖርት በአንድ ዓመት ከየት ልታሳካ ትችላለች። ይሄ የጉድስ ነው፤ ሬሜታንስ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አራት ቢሊዮን ተመዝግቧል፤ ከሰርቪስ የተገኘው ኤክስፖርት ስምንት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። ዓምና ከሁሉም የውጪ ምንዛሬ ማግኛ ምንጮቻችን ብድርና ርዳታን ጨምሮ የነበረው ግኝት 24 ቢሊዮን ዶላር ነበር፤ አጠቃላይ ያገኘነው ሀብት፤ ዘንድሮ ያገኘነው ሀብት ሰላሳ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነው። እንዴት ሪፎርሙ ሪስፖንድ አላደረገም ሊባል ይችላል። ሪፎርሙማ ከጠበቅነው ፍጥነትና ውጤት በላይ ሪስፖንድ አድርጓል። ለምን ያክል ዘመን ኢትዮጵያ ታስራ እንደቆየች ማሳያው ይህ ሪፎርም ነው።

ይሄ የዛሬ አስር አስራ አምስት ሃያ ዓመት ጀምረነው ቢሆን፤ አስቡት ዛሬ የት እንደሚደረስ። ዘንድሮ ሰላሳ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ መገኘቱ በኤክስፖርት ጂዲፒ ሬሾ፤ በኤክስፖርትና ጂዲፒ ጥመርታ አምና ሁለት ነበርን ዘንድሮ ሰባት ደርሰናል። ምን ማለት ነው፤ ኢትዮጵያ ለብድር ተጨማሪ ሀብት ለመበደር ብቃት የላትም ሲባል፤ አጠቃላይ የኢትዮጵያ አቅም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ ኤክስፖርት የምታደርገው እና የውጪ ምንዛሬ የምታመነጭበት አቅም ያንን እዳ ለመክፈል ያስችላል ወይ? በሚል ሂሳብ ነው። ካልሆነ በስተቀረ በአፍሪካ አንደኛ ሁለተኛ ሶስተኛ የሚባሉ ሀገሮች የኛን እጥፍ እጥፍ እዳ አለባቸው።

የእኛ ዕዳ በንፅፅር ከብዙዎቹ ያንሳል። ችግር የነበረው የእኛን ዕዳ ለመክፈል የሚያስችል የኤክስፖርት አቅማችን ውስን መሆኑ ነው። ዘንድሮ ወደ ሰባት አድጓል ብቻ ሳይሆን፤ የትሬድ ባላንስ ዴፊሲት በአራት ቢሊዮን ተሻሽሏል። አንዱ የማይክሮ ስብራት የትሬድ ዴፊሲት ነው። በወጪ እና ገቢ ንግድ መካከል ያለው ዴፊሲት ነው። በአራት ቢሊዮን ተሻሽሏል። ባላንስ ኦፍ ፔመንት ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ኔጌቲቭ ነበረች። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ፖዘቲቭ ታይቷል።

ለአሥራ ምናምን ዓመታት ኔጌቲቭ የነበረው ባላንስ ኦፍ ፔመንት ፖዘቲቭ ሆኗል ማለት፤ የሪፎርሙ ውጤት የሚጨበጥ ነው ማለት ነው።

የሪዘርቭ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ይነሳል፤ ከሦስት ዕጥፍ በላይ ጨምሯል። በቂ ሪዘርቭ አለን፤ ጥሩ የኤክስፖርት ጅማሮ አለን፣ ዓለም ላይ ያለው ሼክ የሚቀጥል ከሆነ እንደከዚህ ቀደሙ በአንድ ወር በሁለት ወር የምንታነቅ አንሆንም ማለት ነው። የተሻለ ዝግጅት እና ቁመና ተፈጥሯል። ኢምፖርት ኤክስፖርቱ፣ ግብርናውም፣ ሰርቪሱም፣ እንዱስትሪውም፤ በኢንዱስትሪው ውስጥ ኮንስትራክሽኑም ማይኒንጉም የሚያሳዩት ኢትዮጵያ ዘንድሮ ካቀደችው ከፍ ያለ ዕድገት ልታረጋግጥ እንደምትችል ነው። ይሄንን እኛ ብቻ ሳንሆን ሴክተሩን በትክክል በቅርበት የሚከታተሉ ዓለም አቀፍ ፋይናንሻል ተቋማትም የሚያምኑበት ጉዳይ ነው።

ትናንት የአይ ኤም ኤፍ በአንድ ድምጽ ቦርድ ያወደሰውን የእኛን ሪፎርም፤ ማጠቃሊያ ማሰሪያ ቃላቸው ይሄ ሪፎርም ወደኋላ ሳይመለስ ከቀጠለ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ ይችላል ነው። የተከበረው ምክር ቤት ይሄን ሪፎርም ደፍረን እንድንሠራ ስለፈቀደልን፤ ይሄ ሪፎርም ሲጀመር ያማል ብያለሁ። እንደ ካንሰር በሽታ ነው፤ ካንሰርን በአንቲ ፔይን ልናክመው አንችልም። ካንሰር የህክምና ሥርዓቱ በራሱ በሽታ ነው። ኬሞ ቴራፒ ማለት በራሱ በሽታ ነው። ያንን የሚያም ከባድ ነገር ሰው ተቋቁሞ ህክምናውን የሚወስደው ከዚያ አስከፊ አድካሚ ጉዳይ በኋላ ፈውስ አገኛለሁ በሚል ሒሳብ ነው። ይሄም ሪፎርም እንደዚያ ነው፤ በአንድ ጊዜ ታስሮ የቆየ ሪፎርም ስንፈታ በብዙ መልኩ ሊያውከን እንደሚችል ይታወቃል። በፈጣሪ ርዳታ፣ በሕዝባችን ቁርጠኛ ትብብር፣ በእናንተ ድጋፍ፣ ከጠበቅነው በእጅጉ የተሻለ ውጤት መጥቷል፤ ኢትዮጵያ ማንሰራራት ጀምራለች።

ኢምፖርትን በሚመለከት አጠቃላይ ያወጣነው 19 ቢሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ ካፒታል ጉድስ ቅድም እንዳነሳሁት 36 ፐርሰንቱን ይወስዳሉ። ኢንፖርት ሲባል ከረሜላና ማስቲካ ብቻ ሳይሆን፤ አብዛኛውን ሼር የወሰደው ካፒታል ጉድስ ነው። ፍጆታ 26 ፐርሰንት ገደማ ይወስዳል፤ ነዳጅ 18 ፐርሰንት ገደማ ይወስዳል። የተሰናዱ ዕቃዎች አሥራ ምናምን ፐርሰንት ይወስዳሉ። የቀረውን ጥሬ ዕቃ ጨምሮ የቀረውን ሼር ይወስዳል።

አብዛኛው ኢምፖርት ላይ እያዋልነው ያለው ገንዘብ የካፒታ ጉድስ መሆናቸው እና አስገዳጅ የሆነ ነዳጅ መሆኑ ኢኮኖሚው ጤናማ በሆነ መንገድ እየሄደ መሆኑን ያሳያል። ዕዳን በሚመለከት በዚህ ዓመት 92 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከፍለናል። ከመጣን ጀምሮ አንድ ዶላር ኮመርሻል ሎን አልወሰድንም። ኮሜርሻል ሎን ነው፤ ኢትዮጵያን የዕዳ ቀንበር እንዲያጎብጣት ያደረገው በሚል እምነት በውስጥ አቅም ከሠራናቸው ሥራዎች ውጭ ኮሜርሻል ሎን አልወሰድንም፤ ይሄ አሁንም ይቀጥላል።

የዕዳ ሽግሽጉ ትናንትና በፈረንሳይ የመጨረሻውን ስምምነት ተፈራርሟል፤ ገንዘብ ሚኒስቴር። ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግሥታት ተበድረው ዕዳው ወደ እኛ ተሸጋግሮ የነበረውን ዕዳ ወደ ልጆቻችን መሸጋገር የለበትም፤ ያለአግባብ ነው ይሄ ብድር ኮሜርሻል የሆነው ብለን ሁለት ሦስት አራት ዓመታት ስንደራደር ቆይተን ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያን ቀንበር አንስተናል፤ ይሄ ማንሰራራት ነው።

የዕዳ ቀንበር ክፉ ነገር ነው፤ ተረጂ 23 ሚሊዮን ቀንሰን፣ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ረጅም ርቀት ተጉዘን፣ የኢትዮጵያ ዕዳ ስሪ ፖይንት ፋይፍ ቢሊዮን ዶላር መቀነስ ብቻ ሳይሆን፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ቀይ የነበረው የኢትዮጵያ ሬት ካለምንም ጥርጥር ይሄ ምክር ቤት የሥራ ዘመኑን ሳይጨርስ ሌላ እንደምንሰማ ምንም ጥርጥር የለውም፤ አካሄዳችን ያንን የዕዳ ቀንበር የሚሰብር ስለሆነ።

ከዚህ በላይ ለዚህ ምክር ቤት ኩራት ሊሆን የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም፤ በእናንተ ዘመን ውስጥ ልጆቻችሁ ዕዳ እንዳይረከቡ አድርጋችሁ፤ የንግድ ሥርዓቱ ሪስፖንድ እንዲያደርግ አድርጋችሁ፤ ለዘመናት የተያዘው ሪፎርም የሚቀይር አካሄድና አመራር ሰጥታችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ኤክስፖርት 8 ቢሊዮን ደርሶ ዴፊሲት ቀንሶ፣ ከኮሜርሻል ከናሽናል ባንክ አንድ ብር ሳንበደር ዓመቱን ሙሉ ማሰለፍ መቻል ፋይናንስ ለሚገባቸው ሰዎች ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል፤ አልተበደርንም።

 ገቢን በሚመለከት በኦሮምኛ ያነሳችው እህቴ ትክክለኛ ሃሳብ ነው። ዘንድሮ 900 ቢሊዮን ነው ገቢ ያስገባነው፤ ወጪ ያወጣነው አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ነው። በገቢያችን እና ወጪያችን መካከል 300 ቢሊዮን ልዩነት አለ። በእርግጥ ገቢ ግብር ብቻ አይደለም፤ ልዩ ልዩ ገቢዎች ይኖራሉ፤ ግን ከግብር ገቢ ያገኘናቸው አጠቃላይ ሀብት ከወጪያችን አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ነው። ለምን እንደዚያ ሆነ ያላችሁ እንደሆነ ታክስ ከጂዲፒ ያለው ጥምርታ በአፍሪካ ሲታይ 14 ፐርሰንት ነው። የኬንያ 14 ፐርሰንት ነው፤ የኢትዮጵያ ግማሽ ነው። ካለን ጂዲፒ አንፃር የምንሰበስበው ታክስ ከኬንያ አንፃር ግማሽ ነው። ለምሳሌ የኬንያን ያህል ብንሰበስብ ኖሮ ፎርቲን ፐርሰንት ብንሰበስብ ኖሮ አንድ ነጥብ ስምንት ትሪሊዮን እንሰበስብ ነበር።

የወጣነው ዋን ፖይንት ቱ ነው፤ የቀረው ሲክስ ሀንድረድ ቅድም ለነበረው ለመንገድ፣ ለመብራት ልማት ይውል ነበር ማለት ነው ቢሰበሰብ። 14ቱ በዛ ካላችሁ 10 ፐርሰንት ብንሰበስብ ዋን ፖይንት ስሪ ትሪሊዮን ብር እንሰበስብ ነበር፤ ቴን ፐርሰንት ብንገባ፤ አልገባንም። ከጂዲፒ ያለው ጥምርታ ብቻ ሳይሆን ከትርፍ ገቢ እና ከካፒታል ገቢም ሲታይ የትርፍ ገቢ እና የካፒታል ገቢ አፍሪካ ላይ ስድስት ነጥብ ሁለት ፐርሰንት ነው። ኤዢያ ላይ ሰባት ነጥብ ሰባት ፐርሰንት ነው፤ የእኛ ሦስት ፐርሰንት ነው። ከአፍሪካ ከግማሽ በታች ነው የትርፍ ገቢያችን፤ የካፒታል ገቢያችን፤ የተከበረው ምክር ቤት በአንክሮ እንዲያስተውል የምጠይቀው ነገር፤ 46 ሺህ የሚጠጉ የታክስ ተመዝጋቢዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር አይከፍሉም፤ 46 ሺህ!!

እንዴት አይከፍሉም? ያላችሁ እንደሆነ፤ ከፊሉ የኪሳራ ሪፖርት ያቀርባል፤ ሰርቼ ከሰርኩ ይላል። ገቢና ወጪዬ ተመጣጣኝ ነው፤ ሳፊ ነው ትርፍ የለኝም ይላል። ያስገባሁትን አውጥቻለሁ ለመንግሥት የምከፍለው የለም ይላል። ከፊሉ ሪፖርትም አያቀርብም። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ንግድ ፈቃድ ወስደው ግብር መክፈል ከሚገባቸው ግብር የሚከፍሉ 37 ፐርሰንት ብቻ ናቸው። 50 እንኳን አልደረስንም።

ከተመዘገበው 50 አልደረስንም፤ ይሄ 37 ፐርሰንት የሚባለውም የሚከፍለው 60 ፐርሰንት ገቢያችንን ነው። 40 ፐርሰንት የሚሰበሰበው ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ነው። ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ደሞዝ መክፈል የማይችሉ፣ ለሽያጭ ቀርበው ገዢ ያላገኙ፣ በኢ አይ ኤች በተሠራው ሪፎርም ዘንድሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ልማት ድርጅቶች ሁለት ትሪሊዮን ሪቨኑ አስገብተዋል። ሁለት ትሪሊዮን!! ከዚያ ውስጥ በመቶ ቢሊዮኖች ግብር ከፍለዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ሥራ በልማት ድርጅቶችና በመንግሥት የሚሠራ ስለሆነ እንደምታውቁት፤ የኢ አይ ኤች ሪፎርም ሁለት ትሪሊዮን ያስገባው ብዙ በኪሳራ የነበሩ ተቋማት ደሞዛቸውን ከፍለው ማትረፍ በመጀመራቸው ነው። ከእነዚህ የሚሰበሰበው ግብር 40 ፐርሰንት ገደማ ሼር ይወስዳል። የሚጠበቀው ምንድ ነው አሁን ከእኛ ያላችሁ እንደሆነ፤ 37 ፐርሰንት የሆነውን ግብር ከፋይ ከተመዘገበው ውስጥ 50 እንኳን ብናደርሰው ዘንድሮ የሰበሰብነው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ማለት ነው።

በነገራችን ላይ የምታውቋቸው ሰዎች ካሉ በግል መንግሥት ግብር አስቸገረን ግብር ክፍያ በዛብን የሚሉ ሰዎች ካያችሁ፤ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ቢሯቸው መኪናቸው የሚገነቡት ቤት እና የግብሩ ጉዳይ አይመጣጠንም።

በሕንድ ሀገር አንድ ሰው ሞል ሄዶ ሱፐርማርኬት ሄዶ፤ እቃ ሲገዛ ግብይቱ ዲጂታል ስለሆነ ሰውዬው ከሚያስገባው ገቢ በላይ እቃ ሲገዛ ካየ ሲስተሙ፤ የምታወጣው ወጪ ከገቢህ ይበልጣል፤ ብሎ አለርት ያደርገዋል። እኛ ሀገር ሲ ኢም ሲ ሂዱ፤ ከኮንቬንሽን ሴንተር ፊት ለፊት ያለ ቦታዎች ሂዱ የሚገነባውን ቤት እዩ፤ እንኳን ኢትዮጵያ አፍሪካ አይደለም የሚገነባው፤ ሰው ቤት ሲገነባ መኪና ሲገዛ፤ ቢሮ ሲገነባ አይደለም፤ ግብር የሚያነሳው።

በዚያው ልክ ደግሞ ታማኞች አሉ። በዚያው ልክ ግብር የሚከፍሉ፤ ልማትን የሚያግዙ ቤታቸውን የሚያፈርሱ፤ በጣም ታማኝ ሰዎች ደግሞ አሉ። ግብርን በሚመለከት ግን አንደኛው ችግራችን የታክስ አስተዳደር ነው። አስተዳደሩ ችግር አለበት። ማሻሻያ እያደረግን ነው። ውጤት እያየን ነው ግን ማጠናከር አለብን።

ሁለተኛው የግብር ስወራ ነው። ሶስተኛው መደበኛ ያልሆነ (ኢንፎርማል) ኢኮኖሚ ነው። ሰው ገቢውና ወጪው አብዛኛው (ኢንፎርማል ኢሌጋል) ስለሆነ ለቁጥጥር አይመችም። በኮንትሮባንድ ብቻ ሳይሆን ከተማ ውስጥ፤ ባለው የግብይት ሥርዓት ነው። ሪሲትን ጨምሮ በጣም ብዙ ባላንስ የሚደረግበት መንገድ አለ። እነዚህ ጉዳዮች አሁን በጀመርነው ማሻሻያ ውጤት እያመጡ ነው መጠናከር አለባቸው። የተከበረው ምክር ቤት ማገዝ አለበት።

አንዱ ማሻሻያ ልክ እንደ ኢንዱስትሪ ናሽናናል ስትሪም ኮሚቴ አለ። እያንዳንዷን የእየዕለት ሥራ የሚመራ፤ ለገቢዎች አልተተወም ሥራው ማለት ነው። ይሄ ኮሚቴ ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ነው። በተለይ ቀረጥ ነፃ ላይ የነበሩ በጣም በርካታ ችግሮች ዜሮ ባይሆኑም በጣም ተሻሽለዋል። ለውጥ አለ፤ ግብር ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተሠራውም ውጤት እያመጣ ነው።

ለነጋዴዎች ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጥቅሟ፤ እነሱም ከመቀመጥ ለመሥራት መሞከራቸው ነው። የመጀመሪያ ጥቅሟ ራሳቸውን ቀጥረው ሌላ ሰው ቀጥረው መንቀሳቀሳቸው ትርፍ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ግን በታማኝነት ግብር መክፈል ካልቻሉ መንገድ የለም፤ መብራት የለም ውሃ የለም ወታደር የለም ፖሊስ የለም ሀገር የለም ማለት ነው።

ግብር ሰው የሚከፍለው ራሱን ለመጠበቅ ነው። ልጆቹን ለማስተማር ነው። ለጤናው ነው። ይሄንን ታሳቢ አድርጎ በንግድ ሥራው ላይ ያሉ ወገኖኝ በታማኝነት ግብር የመክፈል ልምምድ እንዲያሳድጉ፤ በዚሁ አጋጣሚ አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ቅድም ከእዳ ሽግሽጉ ጋር ተያይዞ አንድ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ያገኘነው ከተቋማት መንግሥታት ጋር የነበረውን ብድር ነው። በዩሮ ቦንድ ኢትዮጵያ የተበደረችው ገንዘብ የፕራይቬት ስለሆነ ድርድሩ እየቀጠለ ነው ያለው።

ለዩሮ ቦንድ አበዳሪዎችም በዚሁ አጋጣሚ መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው ልክ እንደመንግሥታቱ በተቀመጠው ሬት በፍጥነት ተስማምተን እዳውን ብናሸጋሽግ ብዙ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ስላለ ብዙ ፖቴንሺያል ስላለ፤ አብረን ልንሠራ ስለምንችል እነሱም በዚሁ እሳቤ ቢሠሩ ለእነሱም ለእኛም ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ጉዞ ጠቃሚ ነው የሚል መልዕክት እግረመንገድ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

የብሔራዊ ባንክ የጀመረው ሪፎርም፤ እያመጣ ያለው ውጤት አንዱ ኢንፍሌሽን ላይ ነው። ኢንፍሌሽን ላይ ከብሔራዊ ባንክ ምንም ብድር ሳንበደር ዓመቱን መጨረሳችን፤ አብዛኛው ወጪያችን የዋስትና ሰነድ ገቢ ብቻ መሆኑ፤ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ነበረው። ኢንፍሌሽን በሚመለከት ሪፎርማችን መጠነኛም ቢሆን ውጤት ካሳየባቸው ምላሽ ከሰጡ ዘርፎች (ሪስፖንድ ካደረጉ ሴክተሮች) አንዱ ነው። አምና አቻምና ታስታውሳላችሁ የዋጋ ንረት (ኢንፍሌሽን) ሞከርን አልቻልንም፤ እላችሁ ነበር። ዘንድሮ ግን እንደዛ አይደለም ከፍተኛ ውጤት መጥቷል።

የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ላይ የተወሰደው ርምጃ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ላይ የተወሰደው ርምጃ እጅ አጠር ሰዎች የምንደጉምበት በመቶ ቢሊዮኖች ገንዘብ መመደቡ (አሎኬት መደረጉ) እንዳልኩት ከብሔራዊ ባንክ ብድር አለመወሰዱ፤ ገበያ (ማርኬት) እና ምርት ላይ መሠራቱ ነው። ዋናው የኢንፍሌሽን መልስ ምርታማነትን ማሳደግ ነው፤ ዋነው ሌሎቹ አጋዥ ናቸው።

ምርታማነት አድጎ የገበያ ትስስር ደግሞ እንዲጠናከር፤ እናንተም እንዳያችሁት አዲስ አበባ ላይ ብቻ አርሶአደሮች እያመጡ የሚሸጡበት ሰፋፊ ቦታ ተገንብቷል። በሀገር ደረጃ ከ1 ሺህ 400 በላይ የእሁድ ገበያ (ሠንደይ ገበያ) ቦታዎች ተስፋፍተዋል። ይሄ አርሶአደሩን ከሸማች ጋር የሚያገናኝ የዋጋ ንረትን ለመከላከል የሚያግዝ አንዱ መንገድ ነው። በእነዚህ ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ ኢንፍሌሽን ቀንሷል። አምና ሪፖርት ሳደርግላችሁ 22 ነጥብ 8 በመቶ ነበር። ዘንድሮ 14 ነጥብ 4 በመቶ ደርሷል። የምግብ ነክ ኢንፍሌሽን 12 በመቶ ደርሶ ነበር። ይሄ ጉዳይ የሚሊኒየም መባቻ ከ2000 በፊት በኢትዮጵያ አቆጣጠር፤ የኢትዮጵያ የምግብ ነክ ኢንፍሌሽን 60 በመቶ ደርሶ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ እዳ እና ስብራት መሆኑን የተከበረው ምክር ቤት መገንዘብ አለበት። አሁን ወደ 12 ዝቅ ብሏል።

ሁለት ጉዳዮች እዚህ ጋር ግምት ሊወሰድባቸው ያስፈልጋል። አንደኛው ስንዴ ምርት አለ ካላችሁ ለምን ዋጋ አይቀንስም? የሚል ጥያቄ ሰዎች ይነሳል። ስንዴ ተመርቶ ዋጋ ከቀነሰ ለምንድነው አርሶ አደሩ የሚያመርተው የሚለው ጥያቄ ግን መልስ ይፈልጋል። አርሶ አደር የሚያመርተው ትርፍ ካለው ብቻ ነው። 23 ሚሊዮን ተረጂ ከሴፍቲኔት ድጋፍ ነፃ ወጣ ካልን፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው በመንግሥት ብቻ የግሉን ሳይጨምር፤ ሥራ ይዘው ደመወዝተኛ ከሆኑ ገንዘብ እያፈሰሱ ከገበያ ላይ ይሸምታሉ፤ ማለት ነው። ትናንትና የማይሸምት ሰው ዛሬ ሸማች ሆነ ማለት ነው። ይሄ ሁሉ ጉዳይ የጎንዮሽ ጉዳት አለው። ያም ሆኖ ግን ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የእድገት ምጣኔ ቀነሰ ነው ያልኩት እንጂ፤ የሸቀጥ ዋጋ ቀነሰ አላልኩም። የሸቀጥ ዋጋንና የዕድገት ምጣኔን ቀላቅሎ የማየት ጉዳይ አለ። ለምሳሌ 12 በመቶ ገባ ሲባል፤ እስቲ ሱቅ ጠይቁ ከዓምናው ቀንሷል ወይ ይላሉ ሰዎች። ነገር ግን ስሌቱ እንደዚያ አይደለም። የዋጋ ንረት እና የሸቀጥ ዋጋ ተመጋጋቢ ናቸው እንጂ አንድ እና ያው አይደሉም።

ኢንፍሌሽን ከሌለማ ዕድገት የለም ማለት ነው። ድፍሌሽን ከሆነማ አጠቃላይ ያለው ነገር፤ ለምሳሌ ዘንድሮ 100 ብር ኢንቨስት ያደረገ ሰው በሚቀጥለው ዓመት ምን ያክል እንደሚያተርፍ ከሚያመላክቱ ጉዳዮች አንዱ ኢንፍሌሽ ነው። ኢንፍሌሽን ዜሮ ከሆነማ ዕድገት ተቀዛቀዘ ማለት ነው። ያ ኢንፍሌሽን ግን ጤናማ መሆን አለበት። ያ ኢንፍሌሽን ግን ደብል ዲጂት መሆን የለበትም ምክንያቱም ሰው በየዓመቱ በዚያው ልክ ገቢው ስለማያድግ ኢንፍሌሽኑ ደብል ዲጂት እንደኛ ሆኖ የሰውን ኑሮ የሚያቃውስ መሆን የለበትም ነው እንጂ፤ ኢንፍሌሽንማ የግድ ነው። በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አነጋገር መሠረት እንደኢትዮጵያ ላሉ ለሚያድጉ ሀገራት እስከ 10 በመቶ ኢንፍሌሽን ተቀባይነት አለው ነው ይላሉ። እንደአሜሪካ ላለው 3 በመቶ ድረስ ተቀባይነት አለው ይላሉ። ምክንያቱም አንድ ኢንቨስተር ገንዘቡን ኢንቨስት ለማድረግ አሜሪካ ያለው ሪስክና ኢትዮጵያ ያለው ሪስክ በነሱ ሬቲንግ መሠረት እኩል ስላልሆነ ያንን ታሳቢ አድርጎ እያደጉ ያሉ ሀገራት እስከ 10 በመቶ ኢንፍሌሽናቸው ተቀባይነት አለው ይባላል። የእኛ ፈተና የሆነው ወደዛ ተቀባይነት ወዳለው መሬት ማውረድ  አለመቻላችን ነው።

አንድ ኢንቨስተር ገንዘቡን ኢንቨስት ለማድረግ አሜሪካ ያለው ሪስክ (አደጋና) ኢትዮጵያ ያለው አደጋ (ሪስክ) በእነሱ መመዘኛ መሠረት እኩል ስላልሆነ ያንን አደጋ ታሳቢ አድርገው ያደጉ ሀገራት እስከ 10 በመቶ የዋጋ ግሽበታቸው (ኢንፍሌሽናቸው) ተቀባይነት ያለው ነው ይባላል። የእኛ ፈተና የሆነው ወእደዛ ተቀባይነት ወዳለው ሬት ማውረድ አለመቻላችን ነው። እዚህ ላይ ደምወዝተኞች አልተጎዱም ወይ? እጅ አጠር ሰዎች አልተጎዱም ወይ? ለተባለው ምን ጥያቄ አለው? በጣም ነው የተጎዱት። ደሃማ በጣም ይጎዳል። ለእዛ ነው ኢትዮጵያ 900 ቢሊዮን ሰብስባ 350 ቢሊዮን ድጎማ ያለችው እኮ፤ ደሃ ይጎዳል በሚል ሂሳብ ነው እንጂ ያ ብር እኮ ለልማት ቢውል ብዙ ቀዳዳ ይሸፍናል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኞች ሃኪምም ይሁን መምህር ወታደርም ይሁን ሌላ ሙያተኛ፤ የተገኘው ውጤት የልማት ስኬት ተሸካሚ መሠረት (ፋውንዴሽን) ነው። ሃኪምን አስተማሪን ወታደርን ሌላ ሙያተኛን የዘነጋ ልማት ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰብ የለበትም። የተከበሩ የምክር ቤት አባል እንዳነሱት የሃኪሞች ጥያቄ ውድቅ የተደረገና ፖለቲካ ብቻ ነው አልተባለም። በጣም ትክክለኛ (ለጅትሜት) ጥያቄ ነው ያነሱት። የእነሱን ትክክለኛ ጥያቄ ግን ለመሳፈር የሞከሩ ሰዎች ነበሩ። ለይተን ነው ያስቀመጥነው። እውነተኛ ጥያቄ በተሳሳተ (ሮንግ) በሆነ መንገድ።

ምንም ምላሽ አላገኙም፤ ለተባለው አይመስለኝም። ተወያይተን ተስማምተን መምህራኖችና የጤና ባለሙያዎች የተግባባነው ነገር የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የእኔና የእናንተ ሥራ መሥዋትነት ከፍሎ ልጆቻችንን ከድህነት መገላገል ስለሆነ አድራሽ ስለሆን መከራውን እንቀበልና ኢትዮጵያን እናሸጋግር ተባብለን ተግባብተን ተጨባብጠን ተሳስመን ነው የተለያየነው።

ያ ደግሞ ሆኖ ሳለ መንግሥት አምና እንዳደረገው፤ አምናኮ አድርጓል። በደሞዝም በአጠቃላይ በድጎማም መቼም ድጎማውን ሰው አይቀበለውም። በቀጥታ ኪሱ ስለማይገባ እንጂ፤ ድጎማ ተደርጓል። እንደዚህ አይነት ጉዳዮች አቅም በፈቀደ መጠን ዘንድሮም ይሠራሉ። ነገር ግን የዋጋ ግሽበትን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም የሚቻለው እያንዳንዱ ግለሰብ ለፍላጎቱ የሚመጥን ገቢ ማስገባት ሲችል ብቻ ነው። ለምሳሌ አንድ ሚሊዮን ብር በወር ደሞዝ የሚበላ ሰው ማኪያቶ ሃምሳ ብር ሆነ መቶ ብር ሆነ ለሱ ትርጉም የለውም። በቂ ገቢ ነው ያለው ስለዚህ ትርጉም የለውም። ትርጉም ያለው አስር ሺህ የሚበላ ከሆነ ነው። በአንድ ማኪያቶ ብዙ ብር ስለሚወስድበት ማለት ነው።

የሰውን ገቢ ለማሳደግ ደግሞ ያለው መንገድ አጠቃላይ ዕድገቱን ማረጋገጥ ነው። ዕድገት ሲረጋገጥ የሰው ገቢ ሲያድግ የዋጋ ግሽበቱ ተቀባይነት ያለው ሲሆን፤ የእኛ ኑሮ አሁን ያለው መከራ ይቀንሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ድሃ ይቸገራል። ሠራተኛ ይቸገራል ለተባለው እውነት ነው። እዚህ ያለ የምክር ቤት አባል ለምን ህክምና ጋር መሔድ አስፈለገ፤ እዚህ ያለ የምክር ቤት አባል መቶ ሰው አሳንሼው ነው፤ መቶ የምክር ቤት አባል የሚያገኘውን ደሞዝ እዚሁ ጎረቤት አንድ ሰው ሊያገኘው ይችላል። መቶ ሰው የሚበላውን፤ በእርግጠኝነት የዚህን ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር ደመወዝ፤ እዚሁ ቅርብ ሀገር ያለ አንድ የፖሊስ ወታደር ሊበላው ይችላል።

ግልፅ ነው እኮ የኔ እና የእናንተ ነገር ማገልገል እና ኢትዮጵያን ካለችበት ነገር ማውጣት መሆኑን ተስማምተን ነው እንጂ በክፍያማ ከሆነ እናንተ እዚህ መቀመጥ የለባችሁም። ግን ‹‹ግድየለም ዕዳውን ተረክበናል ፣ ሥብራት ተረክበናል፣ እኛ ዋጋ ከፍለን ልጆቻችን እንዳይለምኑ እናድርግ›› ብለን ከወሰንን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለብን። ይሄ ጤናውንም፣ መምህሩንም፣ ወታደሩንም ሁሉንም ይመለከታል። ወታደሮች መከራ ያያሉ እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ። በነጻ እየቆሰሉ፤ እየሞቱ በዚህ ዝናብ በእግር እየተጓዙ።ምን ይከፈላቸዋል ለእነሱ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ያለበት የሚቆጠረው (ሲግኒፊካንት የሆነው) የኢትዮጵያ ሀብት የሚውለው ለኢንቨትመንት ነው። ከፍተኛ ኢንርቬሽን የሚያካሂድ መንግሥት ነው። በመንገድ፣ በልማት ሥራ። ያን ልማት ብንቀንስ፣ መንገዱን ብንተው፣ ርዳታ የሚሰበስቡበት፣ አናላይዝ የሚያደርጉበት እና ቁጥሩ ከፍ ካለ ‹‹ትክክል ናችሁ ዝቅ ካለ ትክክል አይደላችሁም›› ከተባለ ትክክለኛ ድምዳሜ አይመስለኝም።

በድምሩ የኢትዮጵያ የገንዘብ ምንዛሪ ዩኒፊኬሽን ለኢትዮጵያ ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ ሂደት ነው። ከዚህ ቀደም የነበረው ኢኮኖሚ ልክ እንደ ‹‹ባሉን›› ውሰዱት። ተኮፍሷል ግን ምንም ነገር መሸከም አይችልም። ወይ ደግሞ በሰፈር ውስጥ አይታችሁ ከሆነ፤ ሻይ የሚጠጣበት ገንዘብ የሌለው አንድ ጎረምሳ ጂንሱን፣ ጫማውን ጽድት አድርጎ በካፍቴሪያ በር ላይ በእግሩ ሲመላለስ፤ ‹‹ግባና ጠጣ›› ብትሉት የሚከፍለው የሌለው ማለት ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደ እዛ ነው። ሲታይ ያበጠ ነው ግን መክፈል አይችልም። ይሄ አርቴፊሻል ነው። ይሄን አርቴፊሻል ነገር ተጋፍጠን ወደ ዩኒፌኬሽን እንግባ ማለታችን እንደመንግሥት እኮ በጣም ደፋር ውሳኔ ነው። እኔ ስም አልጠራም። አንዳንድ ወዳጆቼ ሌላ ሀገር ያሉ ሰዎች እንደኛው አይነት የዕዳ ችግር ያለባቸው አነጋግረውኛል በዚህ ጉዳይ።

‹‹ሪፎርሙን ካላደርግን መውጫ መንገድ የለም ተባብለን እኛ አንሞክረውም ምርጫችን በሚቀጥለው ዓመት ስለሆነ በዓመት ሪስፖንድ አያደርግም ሪፎርሙ ሁለት ሶስት ዓመት ይቆያል። ቆይቶ ነው ተስፋው የሚታየውና አንሞክረውም። እና እንዴት ትዘልቃላችሁ፣ ለደሞዝ እንበደራለን፣ ተበድረን ደሞዝ እየከፈልን ምርጫውን እናልፋለን ›› ያሉኝ ሰዎች እኮ አሉ። እኛ ደግሞ የወሰነው ‹‹ሪፎርሙን እናደርግና ሸክሙን እንሸከምና ምርጫውን ሉዝ እናደርጋለን እንጂ፤ ምርጫ ከፊታችን አለ ብለን ይህን በሽታ አናሸጋግርም ነው።›› ያልነው። ሃላፊነት የሚወስድ (ሪስፖንሲብል) መንግሥት ስለሆነ ያደረገው ውሳኔ ነው እንጂ፤ አንድ ዓመት ምርጫ ሲቀረውማ እንዲህ አይነት ሥራ አይሠራም። ከባድ ነው።

ለምሳሌ ናይጄሪያን ብትወስዱ፤ ልክ ምርጫ እንዳሸነፉ ነው ያደረጉት። ቢኮዝ አምስት ዓመት ሙሉ ሠርተውበት ነው ሪስፖንድ ያደረገው። እኛ አንድ ዓመት ሲቀር ያደረግነው፤ የኢትዮጵያ ስብራት ከምርጫ ጋር መገናኘት የለበትም። የሚል ዕምነት ስላለን ጭምር መሆኑን፤ በደንብ የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘብ ያስፈልጋል። ሪፎርሙ ውጤት እንዳመጣ ለማወቅ ከፈለጋችሁ ደግሞ በተለይ ጠያቂዬን በሚመለከት፤ ወደ ምርጫ ክልሎ ሲሔዱ፤ ከፈለጉ ገዳማትን ያናግሯቸው። በጎጃም አካባቢ ያሉ ገዳማት ዘንድሮ በቡና ኤክስፖርት ትልቅ ገቢ አግኝተዋል። እነሱን ጠይቀው ይሔ ሪፎርም ምን ያክል በገዳማት እንኳን ሪስፖንድ እንዳደረገ ማወቅ ይችላሉ።

ከልቤ ነው የምናገረው። እያንዳንዱን አርሶ አደር ጠይቁ። ገዳማት ጠይቁ፤ ከዚህ ቀደም ቡና አላቸው፤ ገበያ ይወጣል እምብዛም ጥቅም አልነበረውም። ዘንድሮ ግን ከፍተኛ ጥቅም አግኝተውበታል። እና ሪፎርሙ በዓለም ዓይንም በእኛ ዓይንም በማንም መመዘኛ በጣም የተሳካ ነገር ነው። ትላልቅ ኩባንያዎች በጀመርነው መንገድ ሃንት አድርገን ኢንቨስትመንትን ካሻሻልን ደግሞ ውጤቱ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይጠበቃል።

መንገድን በተመለከተ ሁለት የተከበሩ የምክር ቤት አባላት ያነሱትን ሃሳብ በደንብ አድምጫለሁ። ኖት ወስጃለሁ፤ ግን የተቀረነው ሰዎች ልንገነዘብ የሚያስፈልገው፤ የኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን 175 ሺህ ኪሎ ሜትር ደርሷል። 300 ፕሮጀክቶች አንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ብር የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ፀድቀዋል፤ ኮንትራት ተፈራርመናል። ሥራ ጀምረናል። በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ 169 ፕሮጀክቶች ከ11 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ አሁን ዛሬ እየተገነባ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ። በዚህ ዓመት ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ይመረቃል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ። አዲስ አበባ ብቻ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ይመረቃል። የሚጠገን ጥገና 145 ፕሮጀክት አለን። እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም የነበረው መንገድ ሽሮ ፈሰስ ነው። ልክ እንደኮሜርሻል ኖል ሽሮ ፈሰስ ይቅር ብለን ወስነናል ታውቃላችሁ።

17ሺህ ኪሎ ሜትር ከባድ እና መካከለኛ ጥገናዎች እየተካሔዱ ይገኛሉ። መንገድ 28 ሺህ ኪሎ ሜትር በጥገና እና በአዲስ እየተሠራ፤ የመንገድ ሥራ እርግጠኛ ነኝ የትም አፍሪካ ሀገር በዚህ ቁጥር አይገኝም። ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው። በጣም ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው። ነገር ግን መንገድ ላይ ያለው ትልቁ ችግር አንደኛው ሰላም፤ ሁለተኛው የካሳ ክፍያ ነው።

ሦስተኛው የኮንትራት አቅም፤ አራተኛው ሥራው ሰፍቶ ኮንትራክተሩ ውስን ስለሆነ ሦስት አራት ቦታ ሥራ ይይዝና እዚህም እዚያም ሲራወጥ የሚወስደው ጊዜ ችግሮች አሉበት። በልየታ ያነሱት የፍሰሀ ገነት – ኬላ – ሰገን እስከ ግባልባኖ የሚሄደው መንገድ 171 ኪሎሜትር ነው። ሁለት ሎት ተከፍሎ ጨረታ ወጥቶ ሥራ ጀምሮ ነበር። የተወሰነ ፐርሰንት ከሄዱ በኋላ በገላና ወረዳ በነበረው የጸጥታ ችግር ኮንትራክተሩ ለቆ ወጣ ።

የጸጥታ ሥራ ሰበብ ሲባል እኮ እኛ ከፋይ ነን እንጂ ገንቢ እኮ አይደለንም የሚገነባው ሰው ችግር ገጠመው በራሱ ለቆ ወጣ ሁለተኛ ጨረታ ወጣ የሚጫረት ሰው አልተገኘም። አሁንም የጨረታ ፕሮሰስ ላይ ነው። መንገዱ ያስፈልጋል፤ ግን የቀረበት ምክንያት ከመንግሥት አለመፈለግ ጋር መያያዝ የለበትም። አሁንም በተቻለ መጠን ሰላሙ ተረጋግጦ ፤ የወሰን ጉዳይ መፍትሄ አግኝቶ መንገዱ ቢሠራ እናንተ እንዳላችሁት ጠቃሚ ነገር ነው።

በተመሳሳይ ከጉጂ ጋር፣ ከጌዲኦ ጋር ተያይዞ የተነሳው ሃሳብ፣ ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው። ጌዲኦ የምድር ለምለም ነው፤ በጣም ሰላማዊ ሕዝብ ነው፤ እየጣረ እየሠራ ያለ ሕዝብ ነው። በተቻለ መጠን በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል በፌዴራል ደረጃ በሚሠሩ ሰዎች እንደማንኛውም ዞን ልማት ይገባዋል። ልማት ያስፈልገዋል። ለኢትዮጵያም ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ባህል እና ሀብት ያለው አካባቢ ነው። ጥያቄ የለውም። ግን ሥራው ክልል የሚሠራው፣ ፌዴራል የሚሠራው ዞን የሚሠራው ከተቀላቀለ አይሆንም። አንዳንዱ ሥራ እዛው ባሉ ሰዎች የሚሠራ ነው የሚሆነው።

ከዛ ጋር ተያይዞ የስልጣን ጉዳይ የተነሳው በሁለት መንገድ ብናየው ጥሩ ነው። በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት በየትኛውም ደረጃ ሥልጣን በፌዴራልም በክልልም ደረጃ ምርጫ ባደረግንበት 100 ፐርሰንት መብት ያለው ብልፅግና ብቻ ነው። ይሄ ሊሰመርበት ይገባል። ስልጣን ለመያዝ የሚያስችል አብላጫ ወንበር ስላገኘ ማለት ነው። ከዴሞክራሲ ጋር ትስስር የለውም። ምክንያቱም ዴሞክራሲ በመወዳደር አሸንፎ ስልጣን መያዝ ስለሆነ። ያም ሆኖ ግን ብልፅግና አሳታፊ መሆን አለብኝ፤ አቃፊ መሆን አለብኝ ስላለ ከፌዴራል ጀምሮ ብዙዎች ታቅፈው እየሠሩ ነው። እናንተ ዞን ላይ የሚታይ ችግር ካለ እንፈትሻለን። አስገዳጅ አይደለም።

የጌዲኦ ዞን የብልፅግና አመራሮች ጌዲኦን ማስተዳደር ሙሉ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፤ አሸንፈዋል። ነገር ግን ብትሳተፉ አብራችሁ ብትሠሩ ለጌዲኦ ሕዝብ ጠቃሚ አለው ፤ ለምን እንደዚያ ማድረግ እንዳልተቻለ አጣራለሁ / ቼክ አደርጋለሁ። እንደ ግዴታ ግን መወሰድ የለበትም። ልናገኞት አልቻልንም ለተባለው ያው የተከበረው ምክር ቤት እንደሚያስታውሰው ወር እንኳን አልሞላኝም ከተቋዋሚዎች ጋር ስወያይ ገና ሁለት ሳምንት ቢሞላኝ ነው። እና ጠርቼ አወያይቻለሁ።

በርግጥ ሽምግልናን በሚመለከት የተሞከረ ነገር ካለ ጥሩ ሃሳብ ነው። መቀጠል አለበት። ግን ምንም ከእኔ ጋር የሚያያይዘው ጉዳይ የለውም ፤ አሠራሩ የታወቀ ነው። ለምሳሌ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሆነ ሽምግልና የሚካሄደው በኦሮሚያ ክልል እና በሸኔ መካከል ነው የሚካሄደው። እነሱን ማነጋገር ይቻላል። በአማራ ክልል ከሆነ የሚካሄደው በአማራ ክልል እና እዛ ባለው የጸጥታ ሃይል ነው የሚካሄደው። እንደዛ ማድረግ ይቻላል። ከእኔ የሚፈለግ ድጋፍ ካለ እኔ ዝግጁ ነኝ። በቀጥታ ከእኔ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ግን አይደለም።

እዛ ያሉ የታጠቁ ሃይሎች ከወረዳቸው፣ ከዞናቸው፣ ከክልላቸው ጋር ተደራድረው እየገቡ ነው ፤ መግባትም ይችላሉ። እንደዛም እያደረጉ ነው። እናንተም ሙከራ ካደረጋችሁ በቅንነት ነው የማየው። ሃሳቡን በጥሩ ነገር ነው የማየው፤ ቢቀጥል ይሻላል ብዬ ነው ማስበው። ክቡር የተከበሩ ዶክተር አሸብር ያነሱት፣ አሁንም አቋሜ እንደዛ ነው።

አሁንም ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ሰላም ነው።

አሁንም የሚያስፈልገው ብልፅግና ነው፤ አሁንም የሚያስፈልገው ተደምሮ መሥራት ነው። ወንድሞቻችን ሆይ እባካችሁን በያዛችሁት መንገድ የትም ስለማትደርሱ ኑ ነው ምክሬ ፤ የተለወጠ ሃሳብ አይደለም። ይኸው ይቀጥላል። ያን የሚሞክር ካለ በግልም በቡድን በመንግሥት በኩል በደስታ የምንቀበለው መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ ነው።

መንገድን በሚመለከት፣ ሰፊ ሥራ ነው ያለው፤ ሰፊ ችግርም አለበት። ሀብቱም ሥራውም ብዙ ስለሆነ፤ እየፈተሽን ጥያቄዎቻችሁ ምላሽ እንዲያገኙ እናደርጋለን። ጉብኝት ለተባለው ያው የእኔ ሥራ አንዱ ሕዝቤን መጎብኘት፤ ልማት ማየት ስለሆነ፤ በሚመች ጊዜ ውስጥ ያንን ነገር ለመፈጸም እሞክራለሁ። አምና ደቡብ ኦሞ ሄጃለሁ፤ ዘንድሮም የግድ መምጣት አለብህ ከተባለ ሲመች አያቸዋለሁ፤ ችግር አይደለም ማለት ነው።

ኢነርጂ በሚመለከት፣ ቅድም በመንገድ እንዳነሳሁት፤ ማንም የአፍሪካ ሀገር ማንም አንደኛ ኢኮኖሚም ሆነ አስረኛ የኢትዮጵያን ያክል በኢንቨስትመንት ሴክተር ኢንቨስት እያደረግሁ ነው ሊል አይችልም። ህዳሴ፣ ኮይሻ፣ አይሻ፣ አሰላ እና አሉቶ ቢያንስ በከፍተኛ ደረጃ እያለቁ ያሉ ሥራዎች ናቸው። ህዳሴን በሚመለከት ህዳሴ አልቋል፤ ህዳሴን እናስመርቃለን፤ ህዳሴን ከመመረቁ በፊት ብንረብሽ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፤ እናስመርቃለን። ህዳሴን እንዳይመረቅ ለማድረግ የሚያስችል ነገር አሁን የለም። የሚመረቀውም አሁን ነው። ነገ ክረምቱ ሲያልቅ። ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያለኝ መልዕክት ህዳሴ ለሱዳን ፤ ህዳሴ ለግብጽ ትልቅ በረከት ነው። በፍጹም ጉዳት አያመጣባቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልማት ልማታቸው ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኢነርጂ (በኋላም በኢነርጂ እንደምመጣበት) ለሁሉም ጎረቤቶች የሚዳረስ ነው።

የእኛ ግድብ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚጎዳ ቢሆን ኖሮ ቱርካና አጀንዳ አይሆንም ነበር። ታስታውሳላችሁ ጊቤ ሶስት ሲሠራ ቱርካና ይደርቃል የሚል ከፍተኛ ችግር ነበር። እንኳን ሊደርቅ ከግድቡ በኋላ ይኸው ሞልቶ እያስቸገረ ነው። አሁንም ግብጽ ብትሄዱ የግብጽ አስዋን ግድብ አንድ ሊትር ውሃ አልቀነሰም። ወደፊትም ኢትዮጵያ እስከበለጸገች ድረስ ፤ እስካለች ድረስ የግብጽ ወንድሞቻችንን ጉዳት እኛ አናይም። ተባብረን ከወንድሞቻችንን ጋር ማደግ እንፈልጋለን። ምንም አይነት የጥፋት ሃሳብ “ኢል ኢንቴንሽን” የለንም ግብጽ እንድትጎዳ ሱዳን እንድትጎዳ አንፈልግም። ኢነርጂውን በጋራ እንጠቀማለን፤ ውሃውንም በጋራ እንጠቀማለን፤ ልማት በጋራ ይመጣል። ንግግር ካስፈለገም እንነጋገራለን፤ ችግር የለውም።

እኛ ለረጅም ጊዜ ስናነሳ የነበረው አትሥሩ አትበሉን ነው ያልነው፤ በእኛ ገንዘብ የሚሠራውን ሥራ አታግዱ ነው ያልነው ፤ ያን እስካልከለከሉን ድረስ አሁንም ከግብጾች ጋር ለመነጋገር እና ለመሥራት ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት፤ ምንም ችግር የለብንም ግን በእርግጠኝነት የምናገረው ህዳሴ ለግብጽም ለሱዳንም ጉዳት አያመጣም። በዚሁ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ የስልጣን ባለቤት ይህ የተከበረው ምክርቤት ስለሆነ፤ ለግብጽ መንግሥት ለሱዳን መንግሥት እንዲሁም ለተፋሰሱ ሀገራት መንግሥታት በሙሉ መስከረም ዝናብ ጋብ ሲል ህዳሴን ስናስመርቅ የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ በተከበረው ምክርቤት ፊት ግብዣ አቀርብላቸዋለሁ። የጋራ ሀብታችን ነው፤ በጋራ እናስመርቃለን፤ በጋራ እናየዋለን፤ የሚታዩ ጉዳዮች ካሉም በጋራ እናየዋለን።

ከድርቅ ጋር ተያይዞ፣ በተደጋጋሚ በግብጽ የሚነሳው ነገር፤ ድርቅ በሚሆንበት ሰዓት ግብጽ ትጎዳለች ነው። ያው ሁላችሁም እንደምታውቁት ድርቅ የሚባለው ኢትዮጵያ ነው፤ ኢትዮጵያ ከደረቀች ውሃው የለም ማለት ነው። እዛ አይደለም ድርቅ የሚባለው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ እንዳትደርቅ ግሪን ሌጋሲ እየሠራን ነው። ስለዚህ እኛ አንደርቅም ማለት ነው። እኛ ዝናብ ካገኘን እኛም፣ ግብጽም፣ ሱዳንም ፣ሌሎቹም ሀገራት ይጠቀማሉ ማለት ነው። እና በቅንነት አይተን በጋራ ለልማት እንድንሠራ አደራ ማለት እፈልጋለሁ።

አይሻ የንፋስ ፕሮጀክት አለ፤ ሱማሌ ክልል። ከዚህ ቀደም በብድር ከሌላ መንግሥት ጋር የተጀመረ ነው። ብድሩ ሲቋረጥ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵ መንግሥት ነው ሥራውን እየጨረሰ ያለው። ያሰላንም እንደዚሁ። አሉቶ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ (ጂኦ ተርማል) 98 በመቶ ደርሷል። ከኮይሻ ውጭ እነዚህ ሁሉ ህዳሴን ጨምሮ በሚቀጥለው ዓመት የሚያልቁ ሥራዎች ናቸው። ኮይሻም 70 በመቶ በላይ ደርሷል። ሌሎቹም ከ85 በላይ ዘጠናም የደረሱ ስላሉ እንጨርሳቸዋለን።

የዚህ ዓመት ኤክስፖርት ኢነርጂያችን 136 በመቶ አድጓል። በሀገር ኢንዱስትሪም አቅርቦታችን አድጓል። በውጪ ገበያም አድጓል። ለምን፣ የማምረት አቅማችን ስላደገ ነው። ይሄ እንዳለ ሆኖ ግን የትራንስሚሽን (የማሰራጫ መስመሮችን) ችግር አለ ። ይህን በሚመለከት አዲስ አበባን ጨምሮ ፤ በጥያቄ የተነሳው በጌዲኦ ችግሩ አለ። ሴት እህቶቻን ላይ የሚደርሰው መከራ በዚህም በሌላም መንገድ ቢገለጽ ትክክል ባይሆንም፤ አዲስ አበባ ላይ ጭምር ከጫፍ ጫፍ ብትነዱ ታይታላችሁ። እዚህ ይበራል፤ እዚያ አይበራም፤ እዚያ ይበራል፤ እዚህ አይበራም። ያ የሆነበት ምክንያት ትራንስሚሽን ላይናችን (የማሰራጫ መስመሮቻችን) በሀገር ደረጃ በየቦታው ሥራ ይፈልጋሉ።

አሁን ህዳሴን እና ኮይሻን ከጨረስን በኋላ ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፉ (ኢነርጂ ላይ) ከ10 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ኢንቨስት ታደርጋለች። ከዚያም ወደ ትራንስሚሽን ስንመጣ በተወሰነ ደረጃ መፍትሄ ያገኛል ብዬ አስባለሁ። ችግሩን (ፔኑን) እጋራለሁ፤ መፍትሄው ግን በጀመርነው የልማት አካሄድ መቀጠል ብቻ መሆኑን እግረ መንገድ ታሳቢ መደረግ አለበት።

መኖሪያ ቤት ግንባታን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱና ትልቁ ክፍተት (ዴፍሲት) የመኖሪያ ቤት ነው። ቤት ሲባል፣ ቤት አልባ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ቤት ያላቸው የሚመስሉ፣ ግን ቤት አልቦ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከጫፍ ጫፍ ሞልተዋል። ለምሳሌ፣ እዚህ እኛ ሰፈር አዋሬ የሚኖሩ ሰዎች ብዞዎቹ ቤት አልነበራቸውም። 20 እና 30 ዓመት ሽንት ቤት አይቶ የማያውቅ ሰው ምን ቤት አለው ይባላል። ቤት እኮ አይደለም እሱ። በቤት በኩል ያለው ክፍተት ‹ዲፊሲት› ከፍተኛ ሥራ ይፈልጋል። ለዚህ ብለን በመንግሥት፣ በግል፣ በመንግሥት እና በግል ትብብር ብለን እየሠራን ነው።

ለምሳሌ፣ ጥይት ቤት የነበረው የወታደር ካምፕ በግል እና በመንግሥት ትብብር በ40/60 ሕንጻ እየተገነባ ነው። ይሄ አሠራር ድሮ አልነበረም። በመንግሥትና በግል ትብብር መንግሥት መሬቱን አቅርቦ፣ የግል ባለሀብት ገንዘቡን አቅርቦ በጋራ መገንባት አልነበረም። በዚህ ሂደት (በሦስቱም መንገድ) ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ገደማ ቤቶች ተገንብተዋል።

አሁን 265 ሺህ ገደማ ቤት እየገነባን ነው። እንደምታዩትም በየቦታው ግንባታዎች ይካሄዳሉ። ሲሚንቶ ሲያድግ፤ ብረት ሲያድግ፤ መስታወት ሲያድግ፤ የኢነርጂ አቅማችን ሲያድግ ትልቁን ኢንተርቬንሽን ልክ እንደ ህዳሴ ግድብ የሚፈልገው አንዱ ቤት ግንባታ ነው። ቤት ሲባል ግን ቤት ነው። ስለ መጠለያ እና ስለየላስቲኩም አይደለም የማወራው፤ ቤት ያስፈልገናል። እናም ተንፈስ ስንል በደንብ በተቀናጀ መንገድ ከግሉ ዘርፍ ጋር ሆነን የምንገባበት ጉዳይ ቢሆንም፤ አሁንም የተጀመረው ሥራ ግን የሚናቅ አይደለም።

በክረምት በጎ ፈቃድ ከ100 ሺህ ቤት ያላነሰ ተገነባ። አሁን በቅርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ያስጀመርነው የገጠር ኮሪዶር መስከረም አካባቢ (የእኛ ፕሮጀክት) ይመረቃል። የዛኔ ታዩታላችሁ። በዚህ በኩል ያለው ፍላጎት ሶላር ያለው፤ ሽንት ቤት ያለው፤ ባዮ ጋዝ ያለው፤ የከብቶች ማደሪያ እና የሰው ማደሪያ የለየ ቤት አርሶአደራችን ይኑረው የሚል ነው። ከተማ ላይ ገንብተን ሞክረን ውጤት አይተንበታል።

እኔኮ 20 ዓመት፤ 30 ዓመት ሽንት ቤት አይተው የማያውቁ አሮጊት የቤት ባለቤት እና የሽንት ቤት ባለቤት ሆነው እያለቀሱ ሲያመሰግኑ አይቻቸው፤ የእሳቸው ወግ ደግሞ ከአዲስ አበባ ወጥቶ አርሶ አደሩን መንካት እንዲችል ነው የገጠር ኮሪዶር ያልነው። ይሄ አርሶአደር ሶላር ካለው፣ መብራት አለው ማለት ነው። ባዮ ጋዝ ካለው እናት እንጨት አትቆርጥም ማለት ነው። ለከብቶች ሌላ ቤት ካለው በሽታ አይጋባበትም ማለት ነው። የጓሮ አትክልት አለው፤ ሌማት አለው፤ ዶሮ አለው፤ በዚያ ደግሞ ይጠቀማል።

ይሄንን ማስፋት ያስፈልጋል። ይሄንን የምናሰፋው በሥራ ብቻ ነው። ሌላ መንገድ የለውም። ኢትዮጵያ ውሃ እያላት፤ መሬት እያላት፤ ወጣት እያላት፤ ለምን ትራባለች? የሚል ንድፈ ሃሳባዊ (ቲዎረቲካል) ጥያቄ ማንም ማንሳት ይችላል። ግን ሁሉም እያለ ትራባለች። እንሥራው ሲባል፤ ለካ መሬት ሁሉ መሬት አይደለም። የሚያመርት መሬት አለ፤ የማያመርት አለ። ዘሩን ወስዶ አላየሁም የሚል መሬት አለ። ለካ ውሃ ሁሉ ውሃ አይደለም። ለምሳሌ፣ የዝናብ ውሃ እና በቦቴ የሚሰጥ ውሃ እኩል ሳር አያበቅልም። የዝናብ ውሃ ናይትሮጂን ይዞ ይወርዳል፤ ይሄኛው ግን ናይትሮጂን የለውም።

ስንገባበት ነው የምንማረው። ሥራ ላይ ስንሆን ነው የምንማረው። ካልሠራነው፤ ካላቦጫረቅነው ቁጭ ብሎ በመናገር ኢትዮጵያን መለወጥ አይቻልም። እኛ የገባን ነገር፣ ሥራ ውስጥ ስንገባ ፈተናው፣ መከራው፣ ችግሩ ብዙ ነው። አንዳንዴ ብር እያለም ጭምር ሥራውን መሥራት ከባድ ነው። እናም ሳንሠራ የምናነሳው ጥያቄ እና ሃሳባዊ ንግግር ኢትዮጵያን አይለውጣትም። እየሠራን፣ እያንቦጫረቅን ቀስ እያልን እንገፋዋለን፤ ከዛ ልጆቻችን ይቀበሉናል።

የተከበረው ምክር ቤት በሙሉ ልብ እንዲቀበል የምፈልገው ጉዳይ ግን ኢትዮጵያ በእኛ ጊዜ ልመና ታቆማለች። ይሄ ጥርጥር የለውም። በእኛ ጊዜ የጀመረቻቸውን እንደ ህዳሴ ያሉ ሥራዎች ትጨርሳለች። በእኛ ጊዜ የብልፅግናዋ መሠረት ይጣላል። ብልፅግና ግን ጫፍ የለውም (ኢንድ ለስ ነው)። ዛሬ አንድ መኪና ያለው አስር መኪና ይመኛል። ዛሬ አንድ ቤት ያለው አስር ቤት ይመኛል። እሱን ደግሞ ትውልድ ይቀጥላል። እናም መሠረታዊ ፍላጎቱ ሲመለስ የቀረው በትውልድ እየተመለሰ ይሄዳል።

ኮሪዶርን በሚመለከት ቀደም ሲል እንዳነሳሁት የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት ኮሪዶር ብቻ አይደለም። በሁሉም ሴክተር ብዙ አመርቂ ሥራዎች አሉ። የተከበረው ምክር ቤት መገንዘብ ያለበት ግን፣ ኮሪዶር የኢትዮጵያን ከተሞችን ማሳደግና መቀየር ነው። አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዓመታዊ ትቅል ምርት እድገት (ጂ.ዲ.ፒ) 60 በመቶው ከተሞች ላይ ነው። ከተማን ከዘነጋን 60 በመቶው ኢኮኖሚ ተኛ ማለት ነው። ለምሳሌ፣ ከ50 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ጂ.ዲ.ፒ አዲስ አበባ ነው ያለው። የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ ካልተሠራ 50 በመቶው ኢኮኖሚያችን ተኛ ማለት ነው። በመሆኑም ከተማ ማነቃነቅ፣ አጠቃላይ ሀብታችንን ማነቃነቅ ነው።

ይሄ እንዳለ ሆኖ አዲስ አበባ እስካሁን የተሠራው ሥራ ከፍተኛ የሀብት (ሪሶርስ) እጥረት እያጋጠመም ቢሆን፤ እስካሁን ድረስ ከፌዴራል መንግሥትም ይሁን ከየትኛውም ባንክ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ ብር አልተበደረም። በራሱ ገቢ ነው እየሠራ ያለው። ይሄንን ሥራ ባንሠራ ኖሮ ብሩ ምን ይሆን ነበር? እስካሁንስ ምን እየሆነ ነበር? የሚለው መታየት አለበት። ይሄንን ሥራ ግን ተበድረን ብንሠራው ኖሮ፣ ብድር አበዛችሁብን ሊባል ነው። በራሱ ገቢ ከተማው ራሱን ሲቀይር የኮሪዶር ሥራ ብቻ ነው የሚሉ ሰዎች፤ አንደኛ ሥራ ስለማያውቁ ነው። ሁለተኛም ከተማ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ስላልገባቸው ነው። ሦስተኛ፣ የሀብቱን ምንጭ ስለማያውቁ ነው። አራተኛ እና አምስተኛ ግን በፎቶ ነው እንጂ በአካልም ስላላዩት ነው። በአካል ቢያዩት በእርግጠኝነት እንደዛ አይሉም።

የተከበረው ምክር ቤት፣ አንድ ነገር ብቻ እንዲያስተውል እፈልጋለሁ። ከዚህ ከአራት ኪሎ እስከ እንጦጦ ያለውን የኮሪዶር ሥራ ዛሬ ከሰዓት ተመልከቱት፤ ነገም ተመልከቱት። እኔ በየቀኑ ነው የማየው። በጣም ነው የማፍረው። የሚያሳፍረኝ አሁን መሠራቱ አይደለም። እንዴት ላለፉት 100 ዓመታት እዛ ቆሻሻ ውስጥ ኖርን የሚለው ጉዳይ ነው። እንደዚህ ማማር የሚችል መንገድን ነው ያልሠራነው።

የዛሬ ዓመትና ስድስት ወር እኮ እኔ ሳላፍር እንግዳ ይዤ ኑ ጎብኙልኝ (እዩልኝ) ብያለሁ። ይሄ ድፍረትም ነው። እናም አሁን ያለውን ለውጥ እና ሥራ እዩት። እኛ መቆሸሽ አይገባንም። መቆሸሽ እንደ ትክክል መታየት የለበትም። ልጆቻችን ይሄን እያዩ ትላልቅ ነገር ማለም/ አስፓየር ማድረግ አለባቸው። አዳሜ እዛ በሞርጌጅ የራሱን ልጆች እያሳደገ እኛን አትጽዱ ቢለን መቀበል የለብንም። እነሱኮ በየሰፈሩ ፓርክ አላቸው። እያወጡ ልጆቻቸውን እያዝናኑ ነው ፓርክ አያስፈልግም የሚሉን። ይሄ ትክክል አይደለም። መቀየር የሚችል ሀገር ነው፤ መቀየር አለበት፤ የምንቀይረው ደግሞ እኛ ነን። ለሌላ ሰው የሚተው ጉዳይ አይደለም።

አዲስ አበባ ላይ የመጣው የኮሪዶር ለውጥ የእናንተን ባላውቅም ብዙዎች (ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ሰዎች) ጥያቄ የሚያነሱበት ነው። አንደኛ ገንዝቡ ከየት መጣ ይሉኛል። እንደምታውቁት እኛ አንበደርም፤ ግን እዳ እየቀነስን ነው። ሁለተኛ፣ ዲዛይን ማን ሠራላችሁ ይሉኛል። ሦስተኛ ሥራውን የሚሠራው ማን ነው ይላሉ። አራተኛ፣ የፈለገስ ቢሆን በዚህ ፍጥነት (አምና መጥቼ ዘንድሮ) እንዴት ይቀየራል ይላሉ። በእርግጥ እነሱ ከራሳቸው ሀገር ጋር እያወዳደሩ ነው የሚያነሱት። እናንተ ግን የምታወዳድሩበት ካጣችሁ የባለፈውን የአዲስ አበባ ፎቶ እያያችሁ አወዳድሩ። ለውጡኮ ይታያል። ይሄንን ሥራ መደገፍ ጥሩ ነው።

በቅርቡ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ስወያይ የአዲስ አበባ ጥሩ ነው። ግን አዲስ አበባ ብቻ ለምን ሆነ አሉ። አይ አዲስ አበባ ብቻ አይደለም ሂዱና እዩ አልኳቸው። ሄደው ካዩ በኋላ በአንዳንድ ጉዳይ እንደውም አዲስ አበባ ወደኋላ ቀርታለች አሉ። ይሄ እውነት ነው። ብንተባበር ግን መቀየር የሚያስችል አቅም አለን። ለምሳሌ፣ ጅማን ብትወስዱ፤ ጅማ እኔ በተወለድኩበት እድሜ አካባቢ እና ልጅ እያለሁ ስሟ ገናና ነበር። ከዛ በኋላ ባለው ዘመን ያው የምታውቁት ነው።

አሁን ግን ጅማ መልኳ እየተመለሰ ነው። በጣም ነው የምታምረው። የሚገባት ይሄ ነው። ጅማ የዐቢይ ሀገር ስለሆነች ግን አይደለም። የጅማ ሰዎች መሯቸዋል። አቧራ፣ ጭቃ፣ ድህነት። ጨክነው ስለወሰኑ ነው። ወስነው ስለሠሩ እየተለወጡ ነው። ጎንደር እየተለወጠ ነው። ባህርዳርም እንደዛው። ቢሾፍቱ ይቀየራል፤ ደረጃው ቢለያይም ብዙ ከተሞች እየተቀየሩ ነው። እኒህን ሥራዎች እናበረታታቸውና እንሥራ።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ነሀሴ መጨረሻ ድረስ (በጣም ቀንሼው ነው ሀምብል ለመሆን) ከሃያ ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ይመረቃሉ። አንዳንዱ ትምህርት ቤት ነው፤ አንዳንዱ ጤና ጣቢያ ነው፤ አንዳንዱ የቀበሌ ምናምን ነው፤ አንዳንዱ መንገድ ነው። ጉዳዩ የፕሮጀክቱ ማነስ መብዛት ሳይሆን፤ በየቦታው ሥራዎች አሉ የሚለው ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች በጥራት ይለያያሉ፤ በመጠን ይለያያሉ። ለምሳሌ፣ ዶክተር አሸብርን ቦንጋ ሲሄድ የጅማን እድገት በጣም ይወደዋል፣ ያደገበት ስለሆነ። ለምን ግን ቦንጋ አይደገምም ይላል። ይሄ ትክክለኛ ቅናት ነው። ከሌላው ቦታ ስትመጡ ጅማን ያያችሁ መቅናት አለባችሁ። ከቀናችሁ ግን ሥሩ። ሌላ መንገድ የለውም። እያየን መቆጨት አለብን፤ ተባብረን መሥራት አለብን፤ እንደዛ ሲሆን ሀገር ይቀየራል።

አንድ ወዳጄ አንድ የሚገርም ቁም ነገር ነገረኝ። ይሄ ወዳጄ ምን አለኝ “ፈታኝ ጊዜ፣ ቻሌንጂንግ ጊዜ፣ መከራ የበዛበት ጊዜ ጠንካራ ሰው፣ ጠንካራ ትውልድ ይፈጥራል። ምክንያቱም ችግር ጠንካራ ሰው፣ ጠንካራ ትውልድ ይፈጥራል። ያ የተፈጠረ ጠንካራ ሰው፣ ጠንካራ ትውልድ ደግሞ በርትቶ ሠርቶ በመፍጠር ምቹ ሁኔታ፣ ምቹ ሀገር ይሠራል። ያ የተሠራው ምቹ ሀገር ደግሞ መልሶ ደካማ ሰው ይፈጥራል” አለኝ። ምክንያቱም እኛ ከበሻሻ አጋሮ በእግራችን ተምረን ከሆነ አሁን አስፓልት እና ትራንስፖርት ካለ በእግር አይሞከርም ማለት ነው። ደካማ ሰው ይፈጥራል ማለት ነው።

ወዳጄ ጨምሮም፣ “አራተኛው ያ ደካማ ሰው ችግር እና መከራ ይፈጥራል። አያቴ በግመል ሄደዋል። አባቴ ላንድሮበር ነበራቸው፤ እኔ ከአባቴ የተሻለውን ገዝቻለው። ልጄ ከዛ ውድ የሆነውን መኪና ይገዛል፣ ምክንያቱም ገንዘቡ ስላለ። ከልጄ ወደ ልጅ ልጄ ዝቅ ሲባል ግን ተመልሶ ግመል ላይ ይወጣል” አለኝ። ይሄ ለምን ሆነ ከተባለ፣ ምቾት ስንፍናን ስለሚያመጣ ነው። ሲመች ሲደላ ሰው እየሰነፈ ስለሚሄድ።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ችግር አለ። መከራ አለ፣ ፈተና አለ። እውነት ነው። እንጠንክር እና ጠንካራ ሰዎች እንሁን እና ምቹ ነገር እንፍጠር። የእኛ ሃላፊነት ያንን ችግር መናገር አይደለም። የእኛ ሃላፊነት ጠንክረን ፈጣሪዎች/ኢኖቬቲቭ ሆነን፣ ዓይናችን ተገልጦ ምቹ ሀገር፣ የማይለምን ሀገር፣ የሚያንሰራራ ሀገር መፍጠር ነው። ከተባበርን ደግሞ ያን ለማድረግ እንችላለን። በዛ መንፈስ ቢታይ ጥሩ ነው።

ጤናን በሚመለከት፤ በቅርብ ስወያይ ስምታችኋል። ጤና ላይ በጣም ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ሃያ ሁለት ሺህ ገደማ ተቋማት አሉ፣ ስድስት ሺህ ገደማ ተቋማት እኛ ነን የገነባነው። በጣም ጥሩ ሥራ የሚሠሩ የግል ተቋማት አሉ። በሰሞኑ አንዳንድ ሰዎች ታመው አንዳንድ የግል ተቋማት ሄጄ አይቼ ነበር። ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፣ ችግርም ደግሞ አለ። ሊወልዱ ገብተው ሞተው የሚወጡበት በጣም ብዙ ቦታዎች አሉ። ይሄ መፈተሽ አለበት፤ በሁሉም መንገድ።

የጤና ሙያተኛ ጥያቄዎችን ማድመጥ ያስፈልጋል። አቅም በፈቀደ መጠን መመለስ ያስፈልጋል። እነሱም ያለንበትን ሁኔታ ማወቅ አለባቸው። በርትተን ሠርተን፣ የጤና መድህንን አስፋፍተን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጤና ተቋማት አገልግሎት /ሰርቪስ ማሳደግ አለብን። ጅማሮዎች አሉ። ነገር ግን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል።

ትምህርትን በሚመለከት፤ ትክክል ነው የተነሳው ጥያቄ። ግን የተከበረው ምክር ቤት አንድ ጉዳይ ብቻ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ። በዚህ ዓመት አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ህጻናት ቅድመ መደበኛ ተቀብለናል። ሃያ ዘጠኝ ሺህ ደግሞ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች፣ ህጻናት ለቅድመ መደበኛ ተቀብለናል። በእዚያ ልክ ኬጂ ተገንብቷል ማለት ነው። ከአራት ሚሊዮን ህጻናት በላይ የሚውሉበት መዋዕለ ህጻናት ተገንብቷል ማለት ነው። ለዚያ ሁሉ መምህር ተቀጥሯል ማለት ነው። ይሄ በጣም ትልቅ እምርታ ነው። ዋናው ሥራ ያለው ታች ስለሆነ። በነገራችን ላይ ልጅህን ለማስተማር፣ ልጅህን ሰው ለማድረግ ዋናው እድሜ ቢበዛ ቢበዛ እስከ አስር ነው። ከዛ በኋላ ድግግሞሽ ነው። ያንን በደንብ ከሠራንበት ጥሩ ትውልድ መፍጠር ስለሚቻል ነው “ኤርሊ ቻየልድ ሁድ” ላይ አበክረን የምንሠራው። ይሄ ትልቅ እምርታ ነው።

የመምህራንን ስልጠና በሚመለከት፣ እንደዚቀደሙ በጅምላ ሳይሆን በሚያስተምሩበት ትምህርት /ሳብጀክት እና ፔዳጎጂን በሚመለከት ባለፈው ክረምት ተጀምሯል። ወደ ስልሳ ስምንት ሺህ መምህራን ሰልጥነዋል። በዚህ ክረምትም ይሰለጥናሉ። በሰብጀክታቸው እና በማስተማር ዘዬ ስልት ላይ ። ይሄ የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል በእጅጉ ያግዛል። በጦርነት የተጎዱ ቦታዎችን ለመጠገን ሙከራ ተደርጓል ሞዴል ሀይስኩል ትምህርት ሚኒስቴር ራሱ ሰላሳ ገደማ እየሠራ ነው። ቦርዲንግ፣ ሀይስኩሎች እየሠራ ነው፣ ሥራው አይደለም የትምህርት ሚኒስቴር ይሄ ሥራው አይደለም። የክልል ሃላፊነት ነው። ግን ትምህርት ሚኒስቴር እየሠራ ነው። በተለይ ማህበረሰቡ ትምህርት ለትውልድ ብሎ ባዋጣው ገንዘብ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

መጽሀፍ አርባ ስድስት ሚሊዮን ታትሞ ለሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች /ሀይስኩሎች ለአንድ ተማሪ አንድ ደርሷል። ይሄ ትልቅ እምርታ ነው። ሥርዓተ ትምህርት/ ካርኩለም ቀይረን፣ መጽሀፍ አልነበረም፣ አርባ ስድስት ሚሊዮን ነው የታተመው። በሀይስኩል ደረጃ ተዳርሷል፣ በመጀመሪያ ደረጃ በኤለመንተሪ ደረጃ ለማገዝ ሙከራ እየተደረገ ነው። እነዚህ ጉዳዮች ሲጠናከሩ ትምህርት ላይ ውጤት እንደሚመጣ ይጠበቃል።

የሥራ እድልን በሚመለከት፤ ዘንድሮ ትልቅ እምርታ ከታየበት ሴክተር አንዱ ነው። አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ሥራ ይዘዋል። ከነዚህ ውስጥ ግብርና አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰው ወይም 49 በመቶ በግብርናው ሴክተር በተሠራው ሪፎርም ሰዎች ሥራ አግኝተዋል። በሰርቪስ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ወይም 35 ፐርሰንት ገደማ ሰዎች ሥራ ይዘዋል። በኢንዱስትሪ ወደ 680 ሺህ ገደማ ወይም 15 በመቶ ሰዎች ሥራ ይዘዋል። የውጪ ሀገር ሥራ ስምሪት ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለመላክ ተችሏል። በሪሞት ሥራ ከ60 ሺህ ሰዎች በላይ ሥራ መያዝ ችለዋል።

አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። በተለይ የውጪ ሥራ ስምሪት እና የሪሞት ሥራ ተቋሙ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የጀመረው በጣም ይበል የሚያሰኝ ነው። ግን ካለው ክፍተት አንጻር አሁንም ሥራ ያስፈልገናል። አሁንም ሰፊ ሥራ ያስፈልጋል። ሥራ መፍጠር ያስፈልጋል። አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን አራክሰን አይደለም በጣም ትልቅ ውጤት መሆኑን ተገንዝበን ማለት ነው።

ከእዛ ጋር ተያይዞ ሙስና ችግር ነው የተባለው በሁለት መንገድ ቢታይ ጥሩ ነው። አንደኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ብያለው መንግሥታዊ ኮራብሽን፣ ግራንድ ኮራብሽን የለም። እርግጠኛ ነኝ በዚህ። ለዚህ ነው እየለማን ያለነው። እያንዳንዷ ስሙኒ ተለቃቅማ ሥራ ላይ ስለምትውል ነው። እንደመንግሥት የተቀናጀ ሌብነት የለም። ነገር ግን ከሰርቪስ ጋር ተያይዞ ፒቲ ኮራፕሽን አለ። በችግሩ ዙሪያ ስልጠና ሰጥተናል ፣ አወያይተናል ዋናው መፍትሄ ግን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ነው።

ሪፎርሙን መሶብ በሚባለው ቨርቹዋል ሰርቪስ በስምንት ተቋማት በአርባ አንድ ሰርቪሶች ጀምረን ነበር። አሁን ዛሬ ላይ ያ ስምንት ተቋም ሃያ ሶስት ደርሷል። ያ አርባ አንድ ሰርቪስ መቶ ሃያ አራት ደርሷል። ከተጀመረ ሁለት ወር ሶስት ወር ገደማ ቢሆነው ነው። ሃያ ሶስት ተቋማት ተካተዋል። መቶ ሃያ አራት ሰርቪስ እየሰጠ ይገኛል። መሶብ አሁን ያለው አንድ ቦታ ብቻ ነው። መገናኛ አካባቢ። ነገር ግን ቢበዛ መስከረም መጨረሻ አስራ ሰባት፣ አስራ ስምንት ቦታ ይኖረናል። በሁሉም ክልል አዲስ አበባን ጨምሮ እየገነባን ነው። ያ እየሰፋ ሲሄድ፣ ቨርቿል ሰርቪስ ሲጠናከር፣ ተቋማት በሪሞት ማገልገል ሲጀምሩ እጅ በእጅ መቀባበሉ እየቀነሰ ይሄዳል።

ከዚያ ውጭ ለሰው እንደኮሮና ክትባት (ቫክሲን) እያንዳንዱን ሰው ወግተን፣ ከዛሬ ጀምሮ ኮራብሽን ውስጥ እንዳትገባ ፤ ከገባህ ይገልሃል ማለት አይቻልም። የግል ውሳኔ ይፈልጋል። ሰውዬው ካልወሰነ በቀር በሕግ በመመሪያ ብቻ አይሆንም። የምንከለከለው በሥርዓት/ በሲስተም ነው። ሲስተም ደግሞ እየዘረጋን ነው። ውጤትም እያየንበት ነው። ለምሳሌ፣ የመሶብ ርካታ ትናንትና ድረስ የነበረው አጠቃላይ ሪፖርት ከ90 ፐርሰንት በላይ ርካታ አላቸው። ይሄን ማስፋት አለብን ፤ ሁሉም ክልል፤ ሁሉም ከተማ ወደዛ ከሄደ ችግሩ በእጅጉ ይቀንሳል።

በጀት በሚመለከት፣ አጠቃላይ በጀታችን ለድህነት ቅነሳ ትኩረት ያደርጋል። ከእዚያ የተረፈው ለዕዳ ክፍያ (መከፈል ስላለበት የነበረው ዕዳ) እና ድጎማ ይውላል። ድጎማው ለሚያስፈልጋቸው ለሁሉም እንደባለፈው ዓይነት ድጎማ ሳይሆን ለሚያስፈልጋቸው አካላት ድጎማም ያስፈልጋል። በእዛ ምክንያት የዘንድሮው በጀታችን በንጽጽር ምንም እንኳን ያደገ ቢሆንም ሪፎርሙን ለመደገፍ አብዛኛው ገንዘባችን ድጎማ እና በጀት እንዲሁም ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ስለሚያካትት የካፒታል በጀት እድገቱ ውሱን ነው። እድገት አለው ጥያቄ የለውም ጨምሯል ግን ውሱን ነው። በአንድ በኩል ኑሮ ውድ ሆነ ደሞዝ ችግር ሆነ እያልን እሱን ሳንመልስ በውሱን ገቢ ያገኘነውን በሙሉ ልማት ላይ ካዋልን ችግሩ ስለሚባባስ ያን እያስታረቁ መሄድ ያስፈልጋል። በዚህ አግባብ ቢታይ ጥሩ ነው።

በጀት በዶላር ሲሰላ የተባለው፣ በጀት በዶላር ተሰልቶ አያውቅም። መሰላትም የለበትም። በጀት በሀገር ከረንሲ ነው የሚሰላው። እድገት በንጽጽር በዶላር ሊታይ ይችላል፤ በእድገት ደረጃ። በጀት ሲባል እምብዛም ተሰምቶ አያውቅም። የእኛን እድገት ግን የተከበረው ምክር ቤት ማየት ያለበት በኩንታል ነው። በዶላር ሳይሆን በኩንታል ነው። ስንት ኩንታል ጨመርን ብሎ ነው። የኢትዮጵያ እድገት እንደ ከዚህ ቀደሙ ቁጥር አይደለም። የጥራት እድገት (ኳሊቲ ግሮውዝ) ነው። ከዚህ ቀደም የነበረው እድገት በኮሜርሻል ብድር ካፒታል የመጣ ነው። በካፒታል ኢንፍሎ። ለምሳሌ፣ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ከሆነ የሚወስደው፤ ያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እድገት ይባላል፤ ለእኛ እዳ ቢሆንም። በካፒታል ኢንፍሎ የነበረው እድገት ወደ ኳሊቲ እድገት ነው የቀየረው፤ ወደ ምርታማነት እና ወደ ተወዳዳሪነት (ኮምፒታንሲ)።

በምንም መመዘኛ የኢትዮጵያን እድገት ለማየት የፈለገ ሰው መነጽሩን ካወለቀ ይታያል። የሚታይ እኮ ነው። በየቦታው ያለ እድገት ነው። ምንም የሚያምታታ አይደለም። ያም ሆኖ ግን በ2010 በለውጡ ዘመን ይሄ ምክር ቤት 274 ቢሊዮን ብር ነበር ዓመታዊ በጀት ያፀደቀው። 274 ቢሊዮን ብር በየትኛው ስሌት ቢሰላ ነው ከሁለት ትሪሊዮን በላይ የሚሆነው። እና የሚያምታታ ጉዳይ አይደለም። ገንዘባችን ድሮ ኦቨር ቫሊዩም ሆኖ እንደ ፊኛ ተነፍቶ ትልቅ የመምሰል ነበረው።

ያ ጠቃሚ ስላልሆነ በተጠና መንገድ ሪፎርም ሠርተናል። በሪፎሙም አመርቂ ውጤት አምጥተናል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሚቀጥለው ዓመት የበለጠ እያደገ (ሪስፖንድ እያደረገ) ይሄዳል። ይሄ የጀመርንበት ዓመት ራሱ ውጤት ላይ ያያችሁት ነው። ያ እንዲሆን እኔና እናንተ እጃችንን ጠቅልለን አፈር እየነካን በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል። ቁጭ ብሎ በመመኘት ለውጥ አይመጣም። ሥራ ብቻ ነው ለውጥ የሚያመጣው። በርትተን እንሥራ ሕዝባችንን እናስተባብር፤ ሌብነት እንቀንስ፤ በውጤት እንመን፤ ጀምረን እንጨርስ የኢትዮጵያ ማንሰራራት የሁላችን እምነት ይሁን። እንደዚያ ከሆነ ልማትና እድገት ሊመጣ ይችላል። ኢትዮጵያ እያደገች ነው። ኢትዮጵያ እያንሰራራች ነው። ኢትዮጵያ አቧራዋን ዕዳዋን እያራገፈች ነው። ኢትዮጵያ ተረጂነቷን እያራገፈች ነው። የበለፀገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናስረክባለን።

(ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ማብራሪያ በነገው ዕትም ይቀጥላል)

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You