
የሂውጂን ዳይመንድ ሊግ ዛሬ ሲካሄድ በተለያዩ ርቀቶች በርካታ ክዋክብት አትሌቶችን ያፋልማል። በሴቶች 5ሺ ሜትር የሚደረገው ፉክክር ግን ከሁሉም በላይ የርቀቱን በርካታ ክዋክብት አትሌቶች በማፋለም ይበልጥ ትኩረት አግኝቷል።
የ5ሺ ሜትሩ ፍልሚያ የርቀቱን አምስት ድንቅ ብቃት ላይ የሚገኙ ኮከቦች ያፋጠጠ ሲሆን የወቅቱ ቁጥር አንድ የርቀቱ ፈርጥ አትሌት ኬንያዊቷ ቢትሪስ ቺቤት በአራት ድንቅ ኢትዮጵያውያን ትፈተናለች።
ይህ ውድድር ከዳይመንድ ሊግ መደበኛ ፉክክር ባለፈ ለኬንያውያን አትሌቶች ለ2025 የቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና እንደማጣሪያ የሚያገለግል በመሆኑም ይበልጥ ትኩረት አግኝቷል። ለኢትዮጵያውያኑም አትሌቶች ቢሆን ፉክክሩ በርቀቱ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ለዓለም ሻምፒዮና ሀገራቸውን ለመወከል ዕድል የሚያገኙበት ይሆናል።
ድንቅ ፉክክር ያስተናግዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ይህን ፉክክር በዋናነት የርቀቱ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ቺቤት ስትመራ የአሸናፊነት ግምትም ተሰጥቷታል። የ2023 ዳይመንድ ሊግ አሸናፊ እንዲሁም የፓሪስ ኦሊምፒክ የ10 እና 5 ሺ ሜትር አሸናፊዋ ቺቤት ድንቅ ብቃት ላይ ብትገኝም ከኢትዮጵያውያኑ የርቀቱ ኮከቦች ቀላል ፈተና እንደማይጠብቃት ይጠበቃል። በተለይም የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን የጨበጠችውና የወቅቱ የ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በቀላሉ እጅ ትሰጣለች ተብሎ አይጠበቅም። ቺቤትና ጉዳፍ በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ፉክክሮች ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ኬንያዊቷ አሸናፊ ነበረች።
በኢትዮጵያዊቷ ድንቅ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ተይዞ የቆየውን የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን በ2023 ፓሪስ ላይ ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን በ14:05.20 ሰዓት መስበሯ ይታወሳል። ይህን በኬንያዊቷ አትሌት የተያዘ ክብረወሰን ብዙ ሳይቆይ በወር ልዩነት ዩጂን ላይ ጉዳፍ በድንቅ ብቃት 14:00.21 በሆነ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ችላለች።
ጉዳፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሽንፈት ያላስተናገደችውን ቺቤት አሸንፋ የርቀቱ ቁጥር አንድ ኬንያዊቷ አለመሆኗን ለማሳየት ጭምር ነው የምትፋለመው። ቺቤት ግን ከኦሊምፒኩ በኋላ በድል ላይ ሌላ ድል እያስመዘገበች ታሪክ የመሥራት ከፍተኛ ጉጉት እንዳላት ዘገባዎች ጠቁመዋል።
ቺቤት ከፓሪስ ኦሊምፒክ የጥምር የወርቅ ሜዳሊያ ስኬቷ በኋላ በውድድር ዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ፉክክሮች ላይ ከማሸነፍ የዘለለ ሕልም አላት። ይህም ከአራት ወር በኋላ በሚካሄደው የቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 እና 5 ሺ ሜትሮች ሌላ ጥምር የወርቅ ሜዳሊያ ማሳካት ሲሆን ለዚያም እየተዘጋጀች እንደምትገኝ ገልፃለች።
ኦሊምፒክ ቻናል ለተሰኘው ድረ-ገፅ ይህን እቅዷን ስትናገርም “ትኩረቴ በዓለም ሻምፒዮና ጥምር የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ነው፣ በዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፌ አላውቅም፣ ያንን ለማሳካት ግን እየተዘጋጀሁ ነው” ብላለች።
ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ያገኘው የ5ሺ ሜትር ትንቅንቅ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን በእጇ የሚገኘው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይና የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮና ኬንያዊቷ ባትረስ ቺቤት የሚያደርጉት ፉክክር ነው። ጉዳፍ 14:0021 በሆነ ሠዓት በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን ስትይዝ፣ ባትሪስ ቺቤት ደግሞ በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ በ5ሺና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ስትሆን በ2025 ሞሮኮ ራባት ላይ በ3ሺ ሜትር 8:11:56 በሆነ ሠዓት በመግባት ማሸነፏ ይታወሳል።
በዚህ ውድድር የ5ሺ ሜትር የሪከርድ ባለቤት የሆነችው ጀግናዋ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይን ጨምሮ 13 ሴት አትሌቶች ከኬንያውያን ጋር ለማሸነፍና ለዓለም ሻምፒዮና የሚያበቃ ሚኒማ ለማስመዝገብ ይፋለማሉ፤ መዲና ዒሣ (14:16:54)፣ ፅጌ ገብረሠላማ (14:18:76)፣ አይናአዲስ መብራቱ (14:22:76)፣ ብርቄ ሀዬሎም (14:23:71)፣ አለሽኝ ባወቀ (14:27:33)፣ ፎቲዬን ተስፋዬ (14:28:53)፣ ሂሩት መሸሻ (14:29:29)፣ ልክነው አምባው (14:30:54)፣ አሳየች አይቸው (14:31:88)፣ ፋንታዬ በላይነህ (14:35:27)፣ ማርታ ዓለማየሁ (14:39:61) እና የኔዋ ንብረት (14:47:56) ለቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ሚኒማ ለማሟላት የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ አሸናፊዋን ባትሪስ ቺቤትን ጨምሮ ከሰባት ኬንያውያን ጋር ይተናነቃሉ።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም