
አዲስ አበባ፦ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት መጀመር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ። የሀገራዊ ምክክር ዋና ጉባዔን ለማካሄድ የዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የሚደረገው ምክክር እንዲሳካ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከምሑራን እና ከክልሉ ተወላጆች ጋር ውይይት አድርጓል። ውይይቱ በቀጣይ በክልሉ ለሚደረገው ምክክር ግብዓት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ለመጀመር ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። በዚህም ለምክክር ሂደቱ ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በትግርኛ ቋንቋ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የፌደራል መንግሥት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በአሁን ጊዜ በትግራይ ክልል ሀገራዊ የምክክር ሂደትን በተሟላ ሁኔታ ለመጀመር አስቻይ ሁኔታዎች የሉም ያሉት አቶ ጥበቡ፤ ይህም ኮሚሽኑ በሚያከናውነው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግልጽ የሆነ ደብዳቤ በመጻፍ መልስ እየጠበቀ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ጥበቡ፤ በክልሉ የምክክር ሂደት ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች ሲገኝ በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ መጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ እንደ ሀገር ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰበውን አጀንዳ በየፈርጁ በማደራጀት አጀንዳ ወደ መቅረፅ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችለውን ሥራ እያገባደደ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ጥበቡ ገለፃ፤ የአጀንዳ ቀረጻ ለማካሄድ የአሠራር ሥርዓት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በየፈርጁ እየተደራጁ ነው። ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። አሁን ላይ ጉባዔው የሚመራበት የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ለዚህም የኮሚሽኑን አማካሪ ኮሚቴ ጨምሮ በየደረጃው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ግብዓት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፤ ለምክክር ጉባዔው አመቻቾችንና አወያዮችን ለመምረጥ መስፈርቶች ተዘጋጅተው የመለየት ተግባራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የዲያስፖራው ማኅበረሰብም በምክክሩ እንዲሳተፍ ዝግጅቶች መጀመራቸውን አንስተው፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባራት አሁንም መቀጠላቸውን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ማኅበራት በቅርቡ የምክክር አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን አስረድተዋል።
ይህ ሂደት እንዲፋጠን የምክክሩን ሂደት ይበልጥ አሳታፊ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉና በማረሚያ ቤት የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ አካላትን ጨምሮ ከምክክሩ ራሳቸውን ያገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳዎቻቸውን እንዲያስይዙና በምክክሩ እንዲሳተፉ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም