ብዙዎች «ጋንች» በሚለው ስማቸው ያውቋቸዋል።በተለይ የመርካቶ፣ የአውቶቡስ ተራ፣ የአባኮራን ሰፈር ልጆች በዚህ መጠሪያቸው ነው የሚለዩዋቸው።የዛሬውን የ79 ዓመት አዛውንቱን በቀለ አለሙ።ቁመተ ለግላጋውን በአካል ለተመለከታቸው በ60ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ይመስላሉ።ነገሩ ግን ወዲህ ነው ጋንች ወደ ሰማኒያው ጎራ እያሉ ነው። በተለይ ለእንደ እርሳቸው ዓይነት ሰው የማይመከር ከበድ ያለ ጭነትን አንስተው መኪናቸው ላይ ሲያስቀምጡ ለተመለከተ ሰው የዕድሜ ባለጸጋነታቸውን ይጠራጠራል።በዙሪያቸው ያሉት ወጣቶች «ጋሼ» እያሉ ይጠሯቸዋል። ማህበራዊ ተግባቦታቸው ከሰዎች ጋር ያላቸውን ቀረቤታ ያሳያል።በተለይ ጥንካሬያቸውንና ሥራ ወዳድነታቸውን ሳያደንቅ የሚያልፍ የለም።
ጋንች ከዚህ ሌላ የተለየ ምስጢርም አላቸው። በቦክስ ውድድር አገራቸውን ያስጠሩ ትጉህ ስፖርተኛም ነበሩ።ዛሬም በዚህ ዕድሜያቸው ፒካፕ መኪናቸውን ይዘው የጭነት ሥራ አቀላጥፈው ይሰራሉ።በስፖርቱ የሰሩትን ታታሪነት በኑሮ ግብግብም ደግመውት አሸናፊነታቸውን ካወጁ ዓመታትን አስቆጥረዋል። የሰነቁት ወኔ አስገራሚ ነው። ቀረብ ብሎ ስለ ጥንካሬያቸው ላነሳላቸው እንዲህ ይላሉ «ልብ ያለው ዛሬም ቢሆን መጥቶ ይግጠመኝ»። ካሳለፉት የሕይወት ልምድ ብዙዎች መማር ይችላሉ። ለዚህም ነው የዝግጅት ክፍላችን እኚህን ጠንከራና ታታሪ ሰው እንግዳ ሊያደርጋቸው የወደደው።ከሕይወት ልምዳቸው ትዕግስት፣ ጥንካሬ፣ ብልሃት፣ ወኔና ትጋት እንደምትቀስሙ ተስፋ እናደርጋለን። መልካም ንባብ!
ጋንች ማነው?
የመርካቶና የአውቶቡስ ተራ ልጆች ናቸው «ጋንች» የሚለውን ቅጽል ስም ያወጡላቸው።ይህ ስያሜያቸው የመጣው ደግሞ ያለምክንያት አልነበረም።ከቁልፍ ጥንካሬ ጋር ስለሚያያይዙ ነው።ስለዚህም በመርካቶዎች ትልቁ የብረት ቁልፍ ጋንች ይባላልና ከእርሱ ወስደው ስሙን ሰጧቸው።
ይህ ቁልፍ በቀላሉ የማይሰበር፣ የማይፈለቀቅና ንብረትን ለሌባ አሳልፎ የማይሰጥ ነው።እርሳቸውም በቦክስ ፍልሚያ በተወዳደሩበት ሁሉ ማሸነፍ እንጂ እጅ የማይሰጡ በመሆናቸው ከቁልፉ ስያሜ ጋር በማያያዝ ቅፅል ስም አወጡላቸው።ጋንች ሌላም ትርጓሜ አለው።በልብስ ላይ የሚተከል ጠንካራ ቁልፍ ነው።ቶሎ ተበጥሶ አይወድቅም።
ጋንች መኪናን ለመጎተት የሚረዳ የብረት ገመድም ይሆናል።እርሳቸውም ጠንካራ በመሆናቸው ከዚህ ጋር ሲያመሳስሏቸው ጋንች ብለዋቸዋል።በተመሳሳይ ጋንች የትልቅ ጋን ማስቀመጫም የሚል ትርጓሜ አለው።እናም በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ የመከላከል ተግባሩን ስለሚያከናውኑና ጎል ሳይገባ እንዲያሸንፉ በማድረጋቸው የክለቡ አለኝታ ለማለትም ቅጽል ስሙ እንደወጣላቸው ይነገራል።
ትክክለኛው መጠሪያ ስማቸው አቶ በቀለ አለሙ ነው። በ1933ዓ.ም በጉራጌ ክስታኔ ውስጥ ከሚገኙ 21 ቀበሌዎች ውስጥ አንዱ በሆነው የከዝን ቀበሌ ነው የተወለዱት።አባታቸውን ገና በልጅነታቸው አጥተዋል።እናታቸው ሌላ ትዳር በመመስረታቸው የተነሳ ከቤተሰቡ ጋር መስማማት አልቻሉም።ስለዚህም መኖሪያቸውን ከእናታቸው ወንድ አያት ጋር አደረጉ።ግን እዚህም ቢሆን ዕድል ጠሞባቸው ነበር።አሳዳጊያቸውን ሞት ነጠቃቸው።በዚህም ከእናት ሴት አያት ጋር ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ያላቸውን ሁሉ ይዘው ከቅድም አያት ጋር ወደ አዲስ አበባ በእግር ተጓዙ።
ከሁለት ቀን የድካም ጉዞ በኋላም አዲስ አበባ ደረሱ።ቅድመ አያት የመጡት ታዳጊውን አቶ በቀለን ለልጃቸው አቶ በዳሶ አደራ ለመስጠት ነበርና አስረክበው ተመለሱ። የዚያን ጊዜው ትንሹ ታዳጊ የዛሬው አዛውንት ሁለተኛ የእድገት ቦታቸውን በአዲስ አበባ አባ ኮራን ሰፈር አደረጉ።
ሰፈሩ ለጎጃም በረንዳና ለመርካቶ ቅርብ በመሆኑ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከዚህ ሰፈር ልጆች ጋር እንደነበር የሚያወሱት እንግዳችን፤ ገና በስድስት ዓመታቸው አዲስ አበባ እንደገቡ ያስታውሳሉ።የገጠሩን እንጂ የከተማውን አኗኗር አያውቁምና ቶሎ ለመላመድ ተቸግረው ነበር።ቀስ በቀስ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጥረት ጋር ተዳምሮ ከተሜነቱን እየለመዱት መጡ።
ሲጫወቱም ሆነ ሲናገሩ ቁጥብና ትግስተኛ የነበሩት አቶ በቀለ፤ በዚህ ባህሪያቸው ከብዙ ጓደኞቻቸው ጋር በፍቅር መጫወት እንጂ መጣላት እንደማይወዱ ይናገራሉ።ከአንዱ ዘመድ ወደ አንዱ በማለት ስላደጉም ብዙም የጎደለባቸው ነገር እንዳልነበርም ያነሳሉ።በዚያ ላይ ሥራ ስለሚወዱ ሁኔታውን ይበልጥ አቅልሎላቸዋል።ስለ ጉዳዩ ሲያስታውሱ «ምንም እንኳን ልጅ ብሆንም ራሴን በራሴ አኑሬ ነው እዚህ የደረስኩት» ይላሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንደነበሩ ሲገልፁ፡፡
አቶ በቀለ በእራስ እምሩ ግቢ ውስጥ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች ነበሩ።ከጥንካሬያቸው የተነሳም ብዙ ጊዜ የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ናቸው።የቦክስ ስፖርትም ቢሆን ገና በ16 ዓመታቸው ነበር የጀመሩት።እነዚህን ሁለት ስፖርቶች አብዝተው በመውደዳቸው ከሥራ መልስ ሰፊውን ጊዜ ያሳልፉ ነበር።ከዚህ ሌላ ፊልም ስለሚወዱ ይመለከታሉ።በተለይ የአሜሪካ የቦክስ ፊልሞችን ከሥራ መልስ ይኮመኩሙ ነበር።ቦክሰኛ የመሆን የልጅነት ፍላጎታቸው የተፀነሰውም በፊልም ምክንያት እንደነበር ያስታውሳሉ።
በከንዝ ምድር በጣም ታዋቂና ዝነኛ ከሆኑ ቤተሰቦች የተገኙት አቶ በቀለ፤ አባታቸው የተበደሉትን የሚያስክሱ፤ የተጣሉትን የሚያስ ታርቁና በወቅቱ ለንጉሱ የሕዝብን በደል ተናግረው መፍትሄ የሚሰጡ ባላባት ነበሩ። እርሳቸውም በባህሪያቸው አባታቸውን የተከተሉ እንደሆኑ ብዙዎች እንደሚነግሯቸው አጫውተውናል።
ትምህርት
እንግዳችን ከቀለም ትምህርት ጋር እንዲተዋወቁ ማንም አላገዛቸውም።ስለዚህም በራሳቸው ጥረት ነው የጀመሩት።ለዚያውም ቀን ሙሉ እየሰሩ ማታ ማታ ነበር የሚማሩት።የአስኳላው ስፍራ ደግሞ የቀድሞው ወሰን ሰገድ የአሁኑ የካቲት 23 ነበር።በዚያ መጻፍና ማንበብ እስኪችሉ ድረስ ትምህርታቸውን ተምረዋል።
እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ግን ብዙ ነገሮች ተደራረቡባቸውና ራሳቸውን ማስተማር አቃታቸው።እዚህ ላይ ለማቋረጥም ተገደዱ።በቀለም ትምህርቱ ባይገፉም ቅሉ ሕይወት ግን ብዙ አስተምራቸዋለች።ለአብነትም የቦክስ ስፖርት ላይ ትጉ በመሆናቸው ሳይንሱን ጠንቅቀው ያውቁታል።
ሥራን ከቤተሰብ
«በራስ ሰርቶ የመለወጥን ያህል ምንም የሚያረካ ነገር የለም» ብለው የሚያምኑት እንግዳችን፤ አንድም ቀን ከበዛው ቤተሰባቸው ገንዘብ ተቀብለው አያውቁም።የሚፈልጉትንም ግዙልኝ አይሉም።ቤተሰቦቻቸው ሲሰሩ ስለሚያዩ ላለመጠየቅ ሲሉ በቻሉት ልክ ሰርተው ገንዘብ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።ለመጀመሪያ ጊዜ ገንዘብ ያገኙበት ሥራን የጀመሩትም በጨው ንግድ ነበር።
«አባ አረጋሽ» በመባል የሚጠሩት አያታቸው ነጭ ሽልንግ (ቼንች) እየተባለ የሚጠራውን ገንዘብ በመመንዘር የሚታወቁ ናቸውና ከብዙ ነጋዴዎች ጋር የሚተዋወቁበትን መንገድ ሰጥቷቸዋል።ስለዚህም ብዙ ሥራንም መስራት የቻሉት በእነዚህ ሥራ ወዳድ ቤተሰቦቻቸው አማካኝነት እንደነበር ይናገራሉ።
መርካቶ ውስጥ መደብ ይዘው ጨው በመነገድ የጀመሩት ሥራ ብዙም አዋጪ ያልሆነላቸው እንግዳችን፤ በአጎታቸው ልጅ አማካኝነት የፒያሳው ሕብረት ማህበር ውስጥ የማያውቁትን ሥራ ለመስራት ወሰኑ።ሥራው የልብስ ዘምዛሚነት ነበር። በዚያ ተቀጥረውም ለዓመታት ሰርተዋል።ሥራው አልፊ ቢሆንም ክፍያው ግን እዚህ ግባ የማይባል ነበር።ሆኖም በራሳቸው ሰርተው በልተው ማደርን ስለነበረባቸው የተሻለ አማራጭ እስኪያገኙ በዚያው መቆየት ነበረባቸው።
በሙያው ከዘምዛሚነት ከፍ ያለው የልብስ ስፌት ደረጃ ነበር። ክፍያውም ቢሆን የተሻለ ነው።ጥቂት እንደሰሩ እድገት በማግኘታቸው እርሳቸውም ልብስ ሰፊ መሆን ቻሉ። እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ደስ ብሏቸው ነበር።ሆኖም ከልጅነታቸው ጀምሮ ልባቸውን ለሰረቃቸው የቦክስ ስፖርት ጊዜ መስጠት ነበረባቸውና ወደዚያ ሲያደሉ ደመወዛቸው ይቀነስባቸው ነበር።
የቦክስ ስልጠናን እየወሰዱ በተጨማሪነት የተለያዩ ሥራዎችን ይሰሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ በቀለ፤ ከቦክስና እግር ኳስ ተወዳዳሪነታቸው ገንዘብ ባያገኙም እንደ አንድ የሥራ መስክ ይቆጥሩት ነበር።
በአሽከርካሪነት ለ50 ዓመታት
ቀጣዩ የሥራ ጉዟቸው የሚወስደን ደግሞ 50 ዓመታትን ያሳለፉበት አሽከርካሪነት ነው።በዚህ ሥራ ዛሬ ድረስ ቤታቸውን እየደጎሙበት እንደሚገኙ ይናገራሉ።ልብስ በመስፋት ብቻ የሚገኘው ገቢ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እጅግ አዳጋች ሆነባቸው። ለቦክስ ስልጠና የሚከፍሉት ስላልነበራቸው ነው ወደዚህ ሥራ ለመግባት መንጃ ፈቃድ ያወጡት።ከዚያ ግን የሚወዱት ሥራ ሆነላቸው።በተለይ በከተማዋ የታክሲ አገልግሎት ብዙም ያልተስፋፋ በመሆኑ ከስፌቱ የተሻለ ገንዘብ ያስገኝላቸው ስለነበርና የሚሰጣቸውም ክብር ከፍ ያለ በመሆኑ ወደውት ይሰሩ ነበር።ለሦስት ዓመታት ያህልም ተቀጣሪ ሆነው ሰርተዋል።
‹‹ቅጥረኛ ሆኖ መስራት ብዙ ነገርን ይቀንሳል። በመሆኑም የራሴን ታክሲ ለመግዛት ወሰንኩ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ይህን በማድረጋቸው የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ አግዟቸዋል።ተግተው መስራታቸውም ተጨማሪ ሁለተኛ ታክሲ ለመግዛት ዕድል ከፍቶላቸዋል።
ከ1968 ዓ.ም በኋላም የቦክስ ውድድራቸውን ያቆሙ በመሆናቸው ትኩረታቸውን ታክሲ ሥራ ላይ እንዳደረጉ የሚናገሩት አቶ በቀለ፤ በ1990ዎቹ የታክሲ ሥራቸውን ትተው ወደ ደረቅ ጭነት ሥራ ተሸጋገሩ።ገቢያቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ በመምጣቱ ዘመናዊ የተባለ ሞዴል መኪና ሲመጣ እርሳቸው ሳይነኩት አያልፍም ነበር።አቶ በቀለ እነ ኤር፣ ዲ፣ ቼንቶትሬ፣ ፎር ኦ ፎር የመሳሰሉትን መኪኖች በእጃቸው አስገብተው ነበር።ይህ ደግሞ ከመኪና ቴክኖሎጂው ጋር በሚገባ እንዲተዋወቁ ረድቷቸዋል።
«በሹፍርና ሥራ ከብዙዎች ጋር መጋጨትና አላስፈላጊ ንግግር ያጋጥማል።እኔ ግን ከዚያ በላይ ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፍኩ ስለሆንኩና በስፖርትም በስነምግባር ታንጬ ስላደኩ በትግዕስት አሳልፍ ነበር» የሚሉት እንግዳችን፤ በሥራቸው ውስጥ ሁለት ትልልቅ ችግሮች ገጥሟቸው እንደነበር ያነሳሉ።
የመጀመሪያው የበኩር ልጃቸውን ሲድሩ የተከሰተ ነው። ድግሱ በሚሰናዳበት ዕለት በሹፍርና ቀንም ሌሊትም ሲሰሩ በመቆየታቸው ድካም በእጅጉ ተጭኗቸው ነበር። የልጃቸው ሠርግ በመሆኑ የግዴታ ቡራዩ ሄደው ስጋ ማምጣት ነበረባቸው። እንቅልፍ በጣም አስቸግሯቸው ስለነበር ከመኪና ጋር ከምጋጭ በሚል ወደ አንድ ጫካ ውስጥ ለደቂቃዎች ለማረፍ ገቡ።ሆኖም ሲነቁ ለ10 ሰዓት ያህል በእንቅል ተረትተዋል።ይሄ አጋጣሚ ለቤተሰባቸው ትልቅ ጭንቀት የፈጠረ እንደነበር ይናገራሉ።
ሁለተኛው በሥራ ጉዳይ ያጋጠማቸው ነበር። ተሳፋሪ መስለው ለመዝረፍ ሦስት ሌቦች መኪናቸው ውስጥ ገቡ።ያላቸውን እንዲሰጧቸው ያስገድዷቸው ጀመር።ቢለምኗቸው ሊሰሟቸው አልቻሉም።ስለዚህ የነበራቸው አማራጭ የቦክስ ልምዳቸውን በመጠቀም እራሳቸውን ከጥቃት መከላከል ነው።ፖሊስ በጊዜው ደርሶ ነበርና እርሳቸውን ጨምሮ ሦስቱንም ዘራፊዎች ወደ ጣቢያ ወሰዷቸው።
ሌቦቹ አፈ ቀላጤ በመሆናቸው ተደበደብን ሲሉ ከሰሷቸው።እርሳቸው ደግሞ ሊዘርፉኝ ነው ብለው ክሳቸውን አቀረቡ።ነገር ግን የሚሰማቸው አልነበረም።ከአንድ ሰው ሦስት ሰው ተሰሚነት አለውና እርሳቸው ታስረው ሌቦቹ ነፃ ወጡ።ሆኖም ግን እርሳቸው በአካባቢው የሚወደዱ፣የሚታመኑና ከበሬታ ያላቸው ስለነበሩ ምስክር ቀርቦላቸው ተለቀቁ፡፡
የቦክስ ሀሁ
የቦክስ ስፖርት የጀመሩት በ16 ዓመታቸው ነው። ከዚያ ቀደም ብሎ ግን በቤት ውስጥ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር።ከዚያ ባሻገር እግር ኳስ ተጫዋች በመሆናቸው ጥንካሬያቸውንና ስፖርታዊ አቋማቸውን ይጠብቃሉ።አንድ ዕለት የተከሰተው ነገር ደግሞ ከዚህ ልቀው እንዲወጡና ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ ዕድል ሰቷቸዋል።ይህም በ50 ሳንቲም ከጓደኞቻቸው ጋር ፊልም ቤት ገብተው ያዩት
የአሜሪካ የቦክስ ውድድር ነበር።
ወዲያው ደግሞ አቶ እስጢፋኖስ የሚባሉ ኤርትራዊ አሰልጣኝ ደጃች ውቤ ቅጥር ግቢ ውስጥ «አዲስ አበባ ወጣቶች» በሚል ክለብ አደራጅተው የቦክስ ስፖርት ማሰልጠን መጀመራቸው ይበልጥ ዕድላቸውን አሰፋው።ጊዜ ሳያጠፉ ተመዘገቡ። ልብስ ስፌቱን ጎን ለጎን በመስራትም ጉጉታቸውን እውን እንዲሆን አደረጉ።
በቆይታቸው ችሎታቸውን ለማጎልበት በሚጥሩበት አጋጣሚ አሰልጣኙ ልጆች ማለማመድ አትችልም ተብለው በመታገዳቸው የተነሳ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን አቁመውት ነበር። በአጋጣሚ ሌላ ዕድል ቀንቷቸው በታዋቂው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ አማካኝነት በተቋቋመው ‹‹ዘርአይ ድረስ›› ክለብ ውስጥ ገቡ።አጋጣሚውም የውድድር ዕድል ከፍቶላቸው ነበር።ከዚህ በኋላ በ1959 ዓ.ም ያመሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ነበር፡፡
ዛሬም የቦክስ ፍቅር ያላቸው አቶ በቀለ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብን የተቀላቀሉት ጥቅም አግኝተው ሳይሆን በስሙ ለመወዳደር ነበር።ስለዚህም ክለቡ ትጥቅ ከመስጠት በቀር ምንም ነገር አድርጎላቸው እንደማያውቅ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ሕጋዊ ሰውነት ሲሰጠው ደግሞ በአገር ደረጃ ተመርጠው በዓለም ደረጃ እንዲወዳደሩ የሆኑት የክለቡ አባል በመሆናቸው ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሪንግ ውስጥ የገጠሙት ቦክሰኛ ሰለሞን ዓለም የተባለ ሲሆን፤ ሰውነቱ ጠንካራና ግዙፍ ነበር።በጊዜው ደረቱ ላይ ድንጋይ ቢፈልጡበት የማይሰማ ቦክሰኛ እየተባለ ይሞካሽ ነበር።ሆኖም ዕድልና ትጋት ወደ ጋንች አምርታ ድል ወደ እርሳቸው ሆነ።የመጀመሪያው ውድድራቸውን በማሸነፍ አሃዱ አሉ።
አገር ወክለው ለውድድር ውጪ ለመሄድ ዝግጅት ጀመሩ። በጊዜው ኢትዮጵያን ለመወከል ሸዋ፣ ከፋና አስመራ የመሳሰሉት ክፍለ አገራት ላይ በመወዳደር በነጥብ ማሸነፍ የግድ ይል ነበር። የጋንች ዕጣ ፈንታም ከዚህ የተለየ አልነበረም። አብዛኛውን ውድድሮች በዝረራ በማሸነፍ ነበር ቀዳሚ ተመራጭ የሆኑት፡፡
በሚሊተሪና በግል ከሚሰለጥኑ ቦክሰኞች ጋር ለውድድር እየቀረቡ አንድም ቀን ተረትተው የማያውቁት ባለታሪኩ፤ በ1952 ዓ.ም ኢትዮጵያ ወደ ሮም ኦሎምፒክ ቡድን ሲጓዝ እርሳቸው ግን ተመራጭ አልነበሩም።ዋናው ምክንያት ደግሞ የበጀት እጥረት ነበር። እርሳቸውን ጨምሮ 15 ሌሎች የቡድኑ አባላት ተቀናሽ ተደርገዋል።በዚህ ምክንያት ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ከስፖርቱ ዓለም መገለላቸውን ያስታውሳሉ።እርሳቸው ግን እጅ አልሰጡም። ነገም ሌላ ቀን ነው በማለት ወደፊት መመልከት ጀመሩ።
ከሮም ክስተት በኋላ በግል በመሰልጠን የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ለመወከል ተመረጡ።ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያን ወክለው ለመወዳደር ያላቸው ህልም ተሳክቶ ወደ ጃፓን ቶኪዮ ኦሎምፒክ ተጓዙ።በውድድር ተሳትፏቸውም የመጀመሪያ ዙር ላይ ብቃታቸውን ማሳየትም ችለው ነበር።ይሁንና ዕድል አልቀናቸውም ነበር።በሁለተኛው ዙር ደጋፊዎቹ ነጮች በመሆናቸው ፊላንዳዊውን ለማንቃት ብለው እየጮሁ ተፅዕኖ ፈጠሩባቸው፡፡
የተሳሳቱና የተሸነፉም መሰላቸው።ስለዚህም ሕጉ የሚያዘውን ለመተግበር አልቻሉምና ተሸነፉ።ሆኖም ነጭና ጥቁር ሲፈታተሸ የታየበት ጨዋታ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አድናቆታቸውን ቸሯቸው ።ቀጣዩ ጉዟቸው ወደ ሌጎስ የሚወስድ ሲሆን፤ ከሱዳናዊ ጋር ነበር የገጠሙት።ውድድሩ ጥሩ እንደነበር ጋንች ያስታውሳሉ።ግን የታዘዙትን ባለመፈጸማቸውና ግራ እጃቸው ላይ ጉዳት በመድረሱ የተነሳ ሊያሸንፉት አልቻሉም።በጊዜው ግን የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ መሳብ ችለው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሦስተኛው የውድድር ቦታቸው ሜክሲኮ ሲሆን፤ ተስፋ የቆረጡበት ወቅት እንደነበር ይናገራሉ።ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የዘር መድሎ ነበር። በተለያየ ውዝግብ ውስጥም ያለፉበት ጊዜም እንደነበርም አይዘነጉትም።ይህ ፈተና ውድድሩን ከመሳተፍ ግን ሊያግዳቸው አልቻለም።በዚህ ኦሎምፒክ ላይ ተሳታፊ በመሆናቸውም ከሜክሲኮ መንግሥት ሜዳሊያዎች ተቀብለዋል።ውጤት የማጣታቸው ዋናው ምስጢር ግን የዘር መድሎው አንደነበር ይናገራሉ።
ከውጭ አገር የውድድር ተሳትፎ በተቃራኒው በአገር ውስጥም ቢሆን የተሻለ ብቃት ያሳዩባቸው ቦታዎች በርከት ይላሉ።ከእነዚህ መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት ሲኒማ ቤቶች ሲሆኑ፤ የድሮው ማዘጋጃ ቤት፣ ሞስኮብ ሲኒማ፣ አገር ፍቅር ቴአትር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ ፣አደዋ ሲኒማ፣ ራስ ቴአትር፣ ሲኒማ አዲስ ከተማ፣ አምባሳደር ቴአትር፣ ብሔራዊ ቴአትር የመሳሰሉት በአብይነት ይነሳሉ።
በእነዚህ የውድድር ቦታዎች በርካታ ተጋጣሚዎችን አሸንፈዋል። በተለየ ሁኔታ ግን በሲኒማ አዲስ ከተማ ከካሜሮናዊው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ቶማስ ፍራንሲስ ጋር ያደረጉት ውድድር መቼም አይረሳቸውም።ቶማስ በአገረ ካሜሮን ለአራት ዓመታት የከባድ ሚዛን ሻምፒዮና ቦክሰኛ ነበር።ግን «ከአቶ በቀለ ጋር መግጠም እፈልጋለሁ» ባለው መሠረት በ1956 ዓ.ም በጋንች ጠንካራ ቡጢዎች አቅም አጥቶ ድል ተደርጓል።
በወቅቱ «አዲስ ድምጽ» የተሰኘው ጋዜጣ ባሳተመው ጽሑፉ «በቀለ የካሜሮኑን ቡጢኛ በቃኝ አስባለው» በሚል ርዕስ እንደሰፈረላቸው የታሪክ መጽሐፉ ያስረዳል።በቦክስ ዓለም ከ1949 እስከ 1953 ዓ.ም «በአዲስ አበባ ወጣቶች» ክለብ ሲሰለጥኑና ሲወዳደሩ የቆዩት ባለታሪኩ፤ ከክለቡ ምንም ዓይነት ክፍያ አያገኙም ነበር።ለእርሳቸው ክፍያቸው የነበረው እውቅናና ክህሎት ማዳበራቸው ነበር።ባደረጉት የግል ጥረትም ከኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት ታሪክ ጋር ስማቸውን ተያይዞ መጠራቱ ከክፍያ በላይ እንደሚያኮራቸው ይናገራሉ።
የስፖርት ውለታ
«ብዙ ለፍተው ብዙ ካልተጠቀሙት የምመደብ ነኝ።ምክንያቱም በግል ጥረቴ ለአገሬ ውጪ ድረስ ሄጄ ተደብድቤያለሁ።ግን አንድም አካል ጥሩ አድርገሃል ብሎ ያገዘኝና በምወደው ሥራ ተስፋ እንዳልቆርጥ ያበረታኝ የለም» የሚሉት ባለታሪኩ፤ ይህ ለምን አልሆነም ብለው እንደማይቆጩ ይናገራሉ።ምክንያቱም ስፖርቱ ለእርሳቸው የሕይወታቸው አንድ አካል ሆኗልና፡፡
ጤናማና ጠንካራ መሆን የቻሉት በእርሱ ነው።መልካም ዝናን ያገኙትም በስፖርቱ ነው።ስፖርቱ አካላዊ ሰውነታቸውን ጠብቆ ተጧሪ ሳይሆን ቤተሰብ ደጋፊ አድርጓቸዋል።ስለዚህም ስፖርት ለእርሳቸው የሞራል ድጋፍ በመሆኑም ዛሬም ድረስ ይኖሩበታል። «አንድም ቀን ሐኪም ቤት ሳልሄድ የቀረሁት በስፖርት ወዳድነቴ ነውና ስፖርትን ባለውለታችሁ አድርጉ» በማለት ለወጣቱ መልዕክት ያስተላልፋሉ።
50 ዓመት በትዳር
ትውውቃቸው የጀመረው በዘመድ ሠርግ ላይ በነበረ መተያየት ነው።በወቅቱ ሴት ልጅ በጣም አይናፋር በመሆኗ የዛሬ ባለቤታቸው ወይዘሮ ባቱ ሊያናግሯቸው አልወደዱም።ግን እርሳቸው ገፍተው በመምጣት ንግግሯን ለመረዳትና የውስጧን በጥቂቱም ለማወቅ ችለዋል።ከዚያም በዓይን የወደዷትን ከልባቸው አስገቡና ባለቤታቸው ሊያደርጓት በአካባቢው ተፈሪነት ያላቸው እናት ዘንድ ሽማግሌ ላኩ።
ቤተሰቡ ጉርብትና ብቻ ሳይሆን በአበልጅነት የተሳሰረም ነበር። ከዚህ ሌላ የወጣት ዓይን ያረፈባትን እንስት ከክፉ ይጠብቅልኛል ሲሉ እናት ለእርሳቸው ፈቅደው ሰጧቸው።ግን ወጣቷና ውቢቷ የዚያን ጊዜዋ ባቱ ፈላጊዋ ጥቂት አልነበረምና ታጭታ እንኳን ሽማግሌ አልቆመም።እንዲያውም ከእርሳቸው ጋር ጦር የተማዘዘም እንደነበር ያስታውሳሉ።«የሆነው ሆኖ የቦክስ ስፖርተኛው በቀለ በብዙ ፈተናም ቢሆን በእጁ አስገብቷል» ይላሉ በኩራት ስለ ትዳር ሕይወታቸው ሲናገሩ።
በዚህ መልኩ የተጠነሰሰው ትዳር ዛሬ 11 ልጆችን አፍርተዋል። ከ20 በላይ የልጅ ልጆችንም እንዲያዩ አድርጓቸዋል።በተለይ ባለቤታቸው የቤታቸው ምሰሶ በመሆናቸው አንድም ቀን ግጭት በቤት ውስጥ ተከስቶ እንደማያውቅም ይናገራሉ።50 ዓመታትም ያለፉት በቤት ውስጥ በነበረ ፍቅር ጭምር መሆኑንም አውግተውናል።
ቀጣይ ምኞት
በስፖርተኛነት ባለፉበት ጊዜ ብዙዎችን ማሰልጠንና ተተኪ ማፍራትን ይሹ ነበር።በዚህም በግል ጥረታቸው የተለያዩ ክለቦች ውስጥ በመግባት አሰልጥነዋል።ከእነዚህ መካከል ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በዋናነት የሚጠቀስ ነው።ግን ብዙ ፈተና ነበረባቸው።በተለይም የበጀት ጉዳይ ናላቸውን አዙሮት እንደነበር አይረሱትም።
ባላቸው ነገር ለአገራቸው መቆምን የሚወዱት እንግዳችን፤ ከዚህ ቀደም በርካቶችን በቦክስና እግር ኳስ ማሰልጠናቸውን ይናገራሉ። የገንዘብ ችግሩ ሲገጥማቸው በቀጥታ ወደ ፌዴራል መስሪያ ቤቶች በመግባት ስልጠና ለመስጠት ቢጠይቁም በጄ የሚላቸው ባለመኖሩ እገዛቸው ተቋርጧል።
አሁንም ቢሆን እጅ የሚሰጡ አይመስሉም። ዕድሉ ቢመቻችላቸው ማሰልጠንና ለብዙዎች እውቀታቸውን ማካፈል ይፈልጋሉ።
መልዕክት
‹‹ሁሉም ሰው በተሰጠው ጸጋ ቢሰራ የራሱ ንጉስ ነው።ለሌሎችም አርአያ ሆኖ ተከታዮችን ያፈራና ለአገሩ መልካም ዘርን ይዘራል።እናም ሰውን ክፉም ደግም የሚያደርገው የራሱ ምግባርና ተግባሩ በመሆኑ ይህንን ሁልጊዜ ለበጎ ብሎ ቢያደርገው መልካም ነው›› በማለት መልዕክታቸውን ለወጣቱ ትውልድ ያስተላልፋሉ።
እያንዳንዱ ሰው እንደመልኩ ባህሪዬውም የተለያየ ነውና እየተረዳዱና እየተቻቻሉ መኖርን መልመድ መንገድን ቀና ያደርጋል ይላሉ።ከራሳቸው ይልቅ የአገራቸውን ስም ለማስጠራት የሚጥሩትንም ማበርታት ያስፈልጋል የሚል ፅኑ እምነት አላቸው።
«በግል ጥረታቸው ብዙ ለፍተው ዋጋ ቢስ ነህ መባል ምን ያህል እንደሚያም ከእኔ የበለጠ የሚያውቅ የለምና ይህ በሌሎች ላይ እንዳይደገም መንግሥትም ሆነ ግለሰቦች መስራት አለባቸው» በማለትም በጠንካራ መልዕክት ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም
ጽጌረዳ ጫንያለው